Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየበጎ አድራጎት ማኅበራት አዋጅ የዜጎችን መብት የነፈገና አገሪቱንም ያልጠቀመ መሆኑን መንግሥት አስታወቀ

የበጎ አድራጎት ማኅበራት አዋጅ የዜጎችን መብት የነፈገና አገሪቱንም ያልጠቀመ መሆኑን መንግሥት አስታወቀ

ቀን:

ሕጉ ያጎደለውን የሚያርም አዲስ ረቂቅ ሕግ ለፓርላማ አቅርቧል

ከአሥር ዓመት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀውና እስካሁን ድረስ በሥራ ላይ የሚገኘው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ የዜጎችን መብት የነፈገ፣ የሕዝብ ቅሬታ እንዲጨምርና ተቃውሞ እንዲነሳ አስተዋፅኦ ያደረገ፣ በአጠቃላይ አገርን ያልጠቀመ የሕግ ማዕቀፍ መሆኑን መንግሥት አስታወቀ፡፡ ይኼንን ሕግ የሚቀይርና ችግሮቹንም ይቀርፋል የተባለ ረቂቅ አዋጅ እንዲፀድቅለትም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰሞኑን አቅርቧል፡፡

በሥራ ላይ የሚገኘውን አዋጅ ለመተካት የተረቀቀው አዋጅ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላከ ሲሆን፣ ረቂቁ ሐሙስ ጥር 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመጀመርያ ውይይት ቀርቧል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት አፅድቆ የላከው ይህ ረቂቅ አዋጅ ነባሩን ሕግ ለመቀየር ያስፈለገበትን ምክንያቶች የሚተነትንና የረቂቅ አዋጁን ይዘቶች በጥቅሉ የሚያስቀምጥ የማብራሪያ ሰነድ በአባሪነት አካቷል፡፡

በሥራ ላይ የሚገኘው አዋጅ ቁጥር 621/2001 የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እጅግ የነፈገና አገርንም ያልጠቀመ መሆኑን ይገልጻል፡፡

የመደራጀት መብት በራሱ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት ከመሆን አልፎ ዜጎች ሌሎች መብቶቻቸውን ጭምር የሚያስከብሩበት ሁነኛ መሣሪያ፣ እንዲሁም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ቁልፍ ሚና ያለው ሕገ መንግሥታዊና ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ሕጎች ሳይቀር የተከበረ ዕውቅና እንዳለው በማብራሪያ ሰነድ ተጠቅሷል፡፡

ሕገወጥ እስካልሆነ ድረስ ዜጎች ለማናቸውም ዓላማ የመደራጀት መብታቸው ሳይሸራረፍ ሊጠበቅላቸው ሲገባ፣ በሥራ ላይ የሚገኘው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ ግን በተቃራኒው ዜጎች መንግሥት በወሰነላቸው ዓላማዎች ዙሪያ ብቻ እንዲደራጁ በመወሰን መብቱን በከፍተኛ ደረጃ ገድቦ መቆየቱን ገልጿል፡፡

መብት ተኮር ልማት ላይ ይሠሩ የነበሩ ድርጅቶች ሕዝብን ስለመብትና ተጠያቂነት ከማስተማርና ከማወያየት ታቅበው በአገልግሎት አቅርቦት ላይ ብቻ ላለፉት አሥር ዓመታት እንዲሠሩ ማድረጉን፣ ይህም ሙስና እንዲንሰራፋ፣ የሕዝብ ቅሬታ እንዲጨምርና አማራጭ የመወያያ መድረክ እንዳይኖር ማድረጉን ያትታል፡፡

‹‹ይኼንን በማድረጉም ባለፉት ዓመታት ለመልካም አስተዳደር ዕጦትና ለሕዝባዊ ተቃውሞ አስተዋፅኦ አድርጓል፤›› በማለት ተችቷል፡፡

በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች፣ በሴቶች፣ በሕፃናትና በአካል ጉዳተኞች መብቶች፣ እንዲሁም በሃይማኖትና በብሔር መቻቻልን የማበረታታት ሥራ ለማከናወን የሚደራጁ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት በኢትዮጵያውያን ሊመሠረቱና 90 በመቶ የሚሆነውን በጀታቸውንም ከኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ማግኘት እንዳለባቸው በመደንገጉ፣ በርካታ ድርጅቶች መዘጋታቸውን ይገልጻል፡፡ በሴቶች መብት ላይ ድጋፍ ለማድረግ ከዚህ አዋጅ በፊት የተቋቋመው የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ከአዋጁ በፊት ለ18 ሺሕ ያህል ሴቶች የሕግ ማማከርና ድጋፍ አገልግሎት ያደርግ እንደነበር፣ አዋጁ ከወጣ በኋላ በነበሩት ዓመታት ግን ይህ ቁጥር ወደ አምስት ሺሕ ማሽቆልቆሉን ለአብነት ይጠቅሳል፡፡

አገሪቱ ውስጥ የከፋ ድህነት፣ እንዲሁም ለመብትና ለዴሞክራሲ ጉዳዮች የበጎ ፈቃድ ድጋፍ የማድረግ ባህል ባለማደጉ፣ እንዲሁም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችን መርዳት በተቃዋሚነት ያስፈርጃል በሚል ሥጋት በግል ባለሀብት ዘንድ በመኖሩ፣ በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች ሥራቸውን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንሱና እንዲቀጭጩ በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ምክንያት እንደሆነ ይገልጻል፡፡

በአጠቃላይ በሥራ ላይ የሚገኘው አዋጅ ከሕገ መንግሥቱ መንፈስ  በመጣረስና ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በመጣስ፣ ‹‹የዜጎችን መብት የገደበ፣ አገርንም ያልጠቀመ ሆኖ ተገኝቷል፤›› በማለት አዋጁ መቀየር እንዳለበት የማብራርያ ሰነዱ ይገልጻል፡፡

አዲስ የተረቀቀው አዋጅ ‹‹የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ ይህ የሆነበት ምክንያትም፣ ‹‹የበጎ አድራጎት›› የሚለው በሥራ ላይ የሚገኘው አዋጅ ስያሜ ዘርፉ የደረሰበትን ደረጃ የማይገልጽና የመፅዋችና ተመፅዋች ዓይነት ግንኙነት የሚያመላክት በመሆኑ ነው፡፡

በዚህ መሠረት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በኢትዮጵያ የሚኖርና በውጭ አገር ሕግ ተመዝግቦ በኢትዮጵያ ፈቃድ ያገኘ ማንኛውም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት፣ የሚሠራው ሥራ ሕጋዊ እስከሆነና በጀቱን የሚያገኘው ከሕጋዊ ምንጭ (በወንጀል ድርጊት ያልተገኘ) ብቻ መሆኑን በማረጋገጥ በመረጠው ዘርፍ ተደራጅቶ መሥራት እንደሚችሉ በረቂቁ ተደንግጓል፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀቶች ማንኛውንም ሕጋዊ ሥራ የመሥራትና በመረጡት የሥራ ዘርፍ የመሰማራት፣ የገቢ ምንጫቸውን ከማንኛውም ሕጋዊ ምንጭ የማግኘት፣ አንድ ጊዜ ከተመዘገቡ በኋላ ዓመታዊ ሪፖርት ከማቅረብ ባለፈ ፈቃዳቸውን እንዲያድሱ እንዳይገደቡ የሚያስችሉ ድንጋጌዎች በረቂቁ ተካተዋል፡፡

በስማቸው ንብረት የማፍራትና ንብረቱን የማስተላለፍ፣ ኅብረት የመመሥረት መብት፣ በመንግሥት ወይም በተቆጣጣሪው ኤጀንሲ የሚወሰንባቸውን በተመለከተ በመደበኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለት ፍትሕ የማግኘት መብት፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት፣ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት፣ ራስን የመክፈል ወይም ወደ ሌላ የመቀላቀል መብትና ሌሎች ድንጋጌዎችን ረቂቁ አካቷል፡፡

ረቂቁ ሕጉ የቀረበለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተጨማሪ ዕይታ ለሕግ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...