Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

‹‹እጠየቃለሁ››ን ጠበቅ!

የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከደንበኞቻቸው ወይም ከባለጉዳዮች ጋር ሊኖራቸው በሚገባው ግንኙነት ውስጥ ተጠያቂነትን ያካተተ አሠራር ይከተሉ ነበር ለማለት ይቸግራል፡፡ ጤናማ ግንኙነት አላሰፈኑም ለማለት የሚቻልባቸው በርካታ መገለጫዎች አሉ፡፡ ተቋማቱ ደንበኞቻቸውን በአግባቡ አያገለግሉም፡፡ አያስተናግዱም፡፡

አገልግሎት አሰጣጣቸው ቢጓደል ወዲያውኑ የሚጠየቁበትና ችግሮች የሚስተካከሉበት አሠራር ባለመለመዱ፣ ችግሮች ሲያባባሱ፣ ደንበኞች ሲበደሉ ኖረዋል፡፡ የአንድ ደንበኛ ወይም ባለጉዳይ መበደል ተደማምሮ የአገር ጉዳት፣ የኢኮኖሚዊ መደቆስ እንደሆነ የሚያሳስብ ግብረ ገብነት ተንጠፍጥፎ ጠፍቷል፡፡

በአገልግሎት አሰጣጥ ችግር፣ በተገልጋይ መጉላላት አቤቱታ ከሚቀርብባቸው ተቋማት አንዱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ነው፡፡ ትልቅ የአገር ሀብት የሚያንቀሳቅሰው ይህ መሥሪያ ቤት፣ በሚያደርሰው የአገልግሎት መጓደል ደንበኞች ምሬታቸውን ሲገልጹ ኖረዋል፡፡ አንድ ለእናቱ በመሆኑ፣ ተፎካካሪም ስለሌለበት ምርጫ በማጣት ፀጉር የሚያስነጩ ችግሮቹን እያማረሩ መኖር ግድ ሆነና ለዘመናት በዚህ አልፈናል፡፡

ተቋሙ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረት እንዳለበት ቢታመንም፣ እንዲያሠራጭ የተሰጠውንም በአግባቡ አላደረሰም፡፡ ለዓመታት አታካች ምክንያቶቹን ስንሰማ ኖረናል፡፡ ከዚሁ ሳንወጣም ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ ችግሩ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጡ ብቻም ሳይሆን፣ ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀሙ ተቋማትም ተገቢውን የኃያል ሥርጭት በማጣትና በተቋሙ ስህተት ምክንያት ሲጎዱ መክረማቸው ነው፡፡ ከኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ በርካታ ጥያቄዎች ቢኖሩም፣ ያለችውንም በአግባቡ ማዳረሱ ላይ ከፍተኛ ችግሮች ይታያሉ፡፡ የአገሪቱ አምራች ተቋማት፣ ላኪዎችና በርካታ የንግድ ድርጅቶች በአቅማቸው ልክ ለምን አያመርቱም ሲባል፣ በዋናነት የሚጠቀሰው ሰበብ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ የሚል ነው፡፡

ይህ ችግር ብዙ ቢመከርበትም ዛሬም ድረስ ተገቢውን ምላሽ ማግኘት አልቻለም፡፡ የግል ተጠቃሚዎችም ቢሆኑ በፍላጎታቸው ልክ አገልግሎቱን ባለማግኘታቸው በኃይል መዋዠቅ ሳቢያም ንብረታቸው ሲበላሽ እንኳ ለችግራቸው ሰሚ እያጡ ተቋሙን በተደጋጋሚ ሲወቅሱና ሲያስወቅሱት ኖረዋል፡፡ እርግጥ ነው ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት ችግሮች አሉ፡፡ ዋናውም ችግር እዚህ ላይ ነው፡፡ ጥቂት ያለው ያንኑ በአግባቡ መጠቀም ካልቻለ እንዴት ተብሎ ለተትረፈረፈው ጉዳይ ኃላፊነት ይሰጠዋል?፡፡ ‹‹ችግር ብልኃትን ያስተምራል›› የሚለው አባባል ግን የአሌክትሪክ ኃይል ሥርጭትን ጨምሮ በሌላውም የመንግሥት ተቋማት ዘንድ ጉዳዬ የማይባል ሰንኮፍ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ችግርን ችግር እየወለደ ብዙ ጉዳት ደርሷል፡፡ 

ከሰሞኑ እንደሰማነው ተቋሙ በደንበኞች የሚቀርቡበትን ቅሬታዎች ለመፍታት መነሳቱ እንደ መልካም ጅምር የሚወሰድለት ተግባር ነው፡፡ ከከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ተቋማት ጋር ውይይት ሲካሄድ፣ ከዚህ ቀደም ከተለመዱት የቃላት ጋጋታ ይልቅ ለተግባር ተስፋ የሚሰጡ ጅምሮች የታየበት አካሄድ ታዝቤያለሁ፡፡

በእስከዛሬው የተቋሙ ጉዞ እንደ አገልጋይነቱ ደንበኞቹን በአግባቡ የሚያስተናግድበት ወይም ደንበኛው ሊከበርለት የሚገባውን መብት በመንፈግ እንዳሻው መብራት እንዳሻው ሲያበራና ሲያጨልም የኖረ ከመሆኑ አንፃር፣ ከሰሞኑ ያስደመጠን ሐሳብ የመልካምነት መንደርደርያ ነው፡፡

እስከዛሬም ማድረግ የነበረበትና አሠራሩም እያለ እንደሌለ የሚቆጠር ዓይነት ቢሆንም ተጠያቂነትን ለማጉላት ይዤው መጣሁ ያለው ሐሳብ በአግባቡ ከተተገበረ፣ በተቋሙ ጥፋት ሳቢያ የሚፈጠሩ ጉዳቶችን ለማስቀረት አጥፍቶ ሲገኝም በይፋ ተጠያቂ ያደርገዋል፡፡ ተገቢውን የጉዳት ካሳ እስከመክፈል የሚደርስ አካሄድ ይከተላል፡፡ እርግጥ ከዚህ ቀደም የጉዳት ካሳ እንዲከፍል ቢታወቅም፣ ካሳ ከምጠይቅ ጥንቅር ብሎ ይቅር እያለ የሚቀረው፣ የባሰበት በየፍርድ ቤቱ ሲጉላላ የኖረው ስንቱ ነው፡፡

 በአገልግሎት ሰጪና በተቀባይ መካከል ሊኖር የሚገባውን መልካም ግንኙነት ለመተግበር የሚያስችል ስምምነት በአዲሱ አሠራር ይዘረጋል መባሉ ሸጋ ነው፡፡ ይህ ስምምነት ሁለቱንም ወገኖች በእኩል የሚያይ በመሆኑ፣ በአገልግሎት ሰጪና በተቀባይ መካከል በሽምምነት የሚፈጸም መሆኑም እሰየሁ ነው፡፡ በደንበኛውና በአገልግሎት ሰጪ መካከል በሕግ የሚታወቅ ስምምነት ካለ፣ ያለመግባባት ቢፈጠር እንኳ ጉዳዩን ወደ ሕግ  ወስዶ ዳኝነት ማግኘት ይቻላል፡፡

ከተቋሙ ገለጻ መረዳት እንደተቻለው፣ በተለይ በኃይል መቆራረጥና ተያያዥ ጉዳዮች ሳቢያ የሚፈጠረው ውድመት ቀላል ባለመሆኑ፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎትም ሆነ በኤሌክትሪክ ኃይል በኩል ለሚፈጠረው ችግር በይፋ ተጠያቂ አካል የሚጠየቅበት አሠራር ይኖራል ማለት ነው፡፡

የአገልግሎት አሰጣጡን በጥንቃቄ ላይ የተመሠረተ ባለመሆኑ ሳቢያ ኃይል እንዳሻው እየጨመረና እየቀነሰ፣ ሲከፋም ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ ለቀናት ኃይል በማቋረጥ ለሚፈጠረው ችግር ተቋሙ ጠያቂ አልነበረበትም፡፡ ቢጠየቅም ሰሚ አልነበረም፡፡ በራሱ ስህተት ለተፈጠሩ ችግሮች መልስ አይሰጥም፡፡

ስለዚህ አሁን እጀምራለሁ ያለው ነገር በተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ችግር ቢፈጠር ተጠያቂ እንደሚሆንና ለደረሰው ጉዳትም ለተጎጂው ካሳ የሚከፈል ጭምር መሆኑ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ የመድን ሽፋን በመስጠት ጭምር የሚተባበር መሆኑን አገልግሎቱን ለማሻሻል ጥሩ ጅምር ነው፡፡ ኃይል በሚቋረጥበት ጊዜ አስቀድሞ እናገራለሁ ብሎ ከመረጃ ውጪ ከኃይል አቅርቦት ጋር ሊፈጠር ለሚችልም ችግር ተጠያቂ እሆናለሁ ማለቱ መልካም ነው፡፡ በአገራዊ ለውጥ ከምንጠብቃቸው ተግባራት መካከል አንድን የመንግሥት ተቋም በሚሰጠው አገልግሎት ተጎጂ የሆነ የኅብረተሰብ ክፍል ተጠያቂ ሊያደርግ የሚችልበት ዕድል እንዲመቻች ነው፡፡

ምክንያቱም የበርካታ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጣቸውን ሲያጓድ የሚከሰሱበትና ካሳ የሚከፍሉበት፣ ተጎጂው ይቅርታ የሚጠየቅበት አሠራር ባለመኖሩ፣  ችግር ሲፈጠር ቆይቷል፡፡ ተቋሙ እተገብራለሁ ያለውን በአግባቡ መፈጸም ከቻለ ችግሩን ለማቃለል ይረዳዋል፡፡ እርሱም ከተጠያቂነት ለመዳን ኃይል በአግባቡ እንዲያሠራጭ፣ ችግር ካለበትም ይህንኑ ገልጾ ደንበኞች እንዲጠነቀቁ በማድረግ የተሻለ አሠራር ይፈጥርለታል፡፡ ከአቅሙ በላይ የሆነ ችግር ተፈጥሮ ተገልጋይ ሲጎዳም በይፋ ይቅርታ እየጠየቀና ሕዝቡ እንዲረዳለት እያደረገ ቢጓዝ ዘመናዊነት ነው፡፡ ስለዚህ እንደ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ያሉ ተቋማት ደንበኛን ማክበር ባህል እንዲኖራቸውና በጥንቃቄ እንዲሠሩ እንዲህ በውል የታሰረ የአገልግሎት አሰጣጥ ጠቃሚ ነው፡፡

ሳይገለጽ የማይታለፈው ሌላው ጉዳይ ከታኅሳስ ወር ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ የተጋነነ ነው የሚል ስሞታ ሲቀርብበት የመቆየቱ ጉዳይ ነው፡፡  ተቋሙ ይህንን ጉዳይ ቢፈትሸው ተገቢ ነው፡፡ የአገራችን የኤሌክትሪክ ፍጆታ ታሪፍ እጅግ አነስተኛ እንደሆነ ቢታወቅም፣ ዋጋውን ለማስተካከል የተወሰደው ዕርምጃ ኢኮኖሚው ላይ ጫና እንዳያሳድር ነገሩን በአግባቡ ማየቱ ክፋት የለውም፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት