Tuesday, February 27, 2024

መዋሀድ የከበዳቸው የመድረክ አባል ፓርቲዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

አወዛጋቢው ምርጫ 97 በፖለቲከኞች፣ በሲቪክ ማኅበራት አመራሮች፣ እንዲሁም በጋዜጠኞች እስር መቋጨቱን ተከትሎ የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ጭርታና ድብታ ወሮት ነበር፡፡ ይህንን ድብታ ለመስበር በሚመስል ሁኔታ የፖለቲካ ምኅዳሩን የተቀላቀለው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ)፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ በመሆን ለመሥራት እንቅስቃሴውን በ2000 ዓ.ም. ጀመረ፡፡

በዚህም መሠረት ‹‹መድረክ ለዴሞክራሲያዊ ምክክር በኢትዮጵያ›› (መድረክ) በሚል ስያሜ በስድስት ፖለቲካ ፓርቲዎችና በሁለት ታዋቂ የፖለቲካ ግለሰቦች፣ ማለትም የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ስዬ አብርሃና የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ገብሩ አሥራት አማካይነት ምሥረታውን በ2001 ዓ.ም. በይፋ አውጆ ነበር፡፡

‹‹በኢትዮጵያ ተንሰራፍተው ያሉትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ለማስወገድና በተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ያለውን ተባብሮ ለመሥራት ያለመቻል ድክመት ለመቅረፍ›› በሚል ዓላማ መቋቋሙን፣ ሰኔ 2001 ዓ.ም. አሳትሞ ባሠራጨው መለስተኛ ፕሮግራሙ ይፋ አድርጓል፡፡

በስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎችና በሁለት ታዋቂ ፖለቲከኛ ግለሰቦች አማካይነት የተመሠረተው መድረክ፣ መለስተኛ ፕሮግራሙን ይፋ በሚያደርግበት ወቅት አብረው የሚሠሩ ፓርቲዎችን ቁጥር ወደ ስምንት ለማሳደግ ችሎ ነበር፡፡

መለስተኛ ፕሮግራሙ በስምንት ፓርቲዎችና በሁለት ታዋቂ ግለሰቦች ትብብር የተዘጋጀ ቢሆንም፣ ‹‹በአገራችን መቻቻልና መተባበር ይኖር ዘንድ ሌሎች ፓርቲዎችም የመድረኩ ዓላማ የሚኖረውን ሚና ተመልክታችሁ በጋራ የምናሠራበት ሁኔታ እንዲኖር ጥሪያችንን እናቀርባለን፤›› የሚል መልዕክት በወቅቱ በአገሪቱ ለሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ አቅርቦ ነበር፡፡

ሆኖም ከዓመታት በኋላም በመድረክ ውስጥ የነበሩ ታዋቂ ግለሰቦችም ሆኑ ግማሽ ያህል ፓርቲዎች አብረው መጓዝ አልቻሉም፡፡ በዚህም ምክንያት ሌሎችን በጋራ ለመሥራትና ለመተባበር ሲጋብዝ የነበረው መድረክ፣ በውስጡ ያሉትን ፓርቲዎችና ግለሰቦች እንኳን በአንድነት ሰብስቦ ማቆየት እንዴት ተሳነው? የሚለው የብዙዎቹ ጥያቄ ነው፡፡

በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር የሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች በፖለቲካዊ ውድድር አሸንፎ የሚወጣ አማራጭ ሆነው ለመቅረብ አለመቻላቸውን ‹‹መፍትሔ የሚሻ ድክመት›› መሆኑን በቂ ግንዛቤ ያገኘበት መሆኑን የገለጸው መድረክ፣ አሁንም ከምሥረታው አሥራ አንድ ዓመታት በኋላም ሁሉም የተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎች አንድ ላይ ሆነው መሥራት የሚችሉበት መንገድ እንዲመቻችና ፓርቲዎች እንዲሰባሰቡ መወትወቱን ቀጥሎበታል፡፡

በእነዚህና መሰል የፖለቲካ አተያዮች እየተጓዘ የሚገኘው መድረክ ታኅሳስ 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔውን አካሂዷል፡፡ በጠቅላላ ጉባዔውም ከመላው አገሪቱ የተውጣጡ አባል ፓርቲ ተወካዮች ተገኝተው በአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች፣ እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ እስከ ምሽቱ 1፡30 ሰዓት የደረሰ ውይይትና ክርክር አድርገዋል፡፡

ይህንን ውይይትና ክርክር ተከትሎ ፓርቲው ሊቀመንበር፣ ምክትል ሊቀመንበርና ዋና ጸሐፊ መርጧል፡፡ በዚህም መሠረት መረራ ጉዲና (ዶ/ር) በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር)፣ እንዲሁም አቶ ደስታ ዲንቃን እንደ ቅደም ተከተላቸው ሊቀመንበር፣ ምክትል ሊቀመንበር እንዲሁም ዋና ጸሐፊ በማድረግ መርጧል፡፡፡

ጠቅላላ ጉባዔው ስብሰባውን አጠናቆ ባለ 13 ነጥብ የአቋም መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ በአቋም መግለጫውም የብሔራዊ አንድነት መንግሥት እንዲቋቋም፣ በአገሪቱ በመካሄድ ላይ ያለው የለውጥ ሒደት ዓላማውን ሳይስት መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦችንና የፖለቲካ አማራጭ ኃይሎችን ያሳተፈ እንዲሆን፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ተማሪዎችን ደኅንነት በተገቢው ሁኔታ እንዲያስጠብቅ፣ እንዲሁም ፍፁም ነፃ የሆነ የምርጫ ቦርድ እንዲቋቋምና ገለልተኛ የቦርድ አባላትና ምርጫ አስፈጻሚዎች እንዲሰየሙ መንግሥትን ጠይቋል፡፡

የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ጉዳይ

በ2001 ዓ.ም. መድረክ ባሳተመው መለስተኛ ፕሮግራም፣ ‹‹የአገራችን ኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግሮች በኢሕአዴግ ርዕዮተ ዓለምና መስመር፣ እንዲሁም በኢሕአዴግ አቅም ብቻ ሊፈቱ እንደማይችሉ በመገንዘብ፣ ችግሮቹ ሁሉንም ባለድርሻዎች በማሳተፍ እንዲፈቱ በተደጋጋሚ ቢጠይቅም በሥልጣን ላይ ካለው የኢሕአዴግ መንግሥት ገንቢ ምላሽ ባለመገኘቱ፣ ችግሮቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ መሄዳቸው ግልጽ ነው፤›› በማለት ገልጾ ነበር፡፡

አሁንም ቢሆን ይህን ጥያቄ ለመጠየቅ ተስፋ ያልቆረጠው መድረክ በታኅሳስ 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ጉባዔው ማጠናቀቂያ ላይም፣ ‹‹ኢሕአዴግ ባለፉት 28 ዓመታት የአገዛዝ ዘመኑ የፖለቲካ ምኅዳሩን ዘግቶ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት በአገሪቱ ውስጥ እንዳያብ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢሕአዴግ ብቻውን የአገሪቱን የፖለቲካ ቀውስ መፍታት ስለማይችል፣ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት እንዲቋቋም በማድረግ የፖለቲካ ምኅዳሩ ለሁሉም ዜጎች በሚመች ሁኔታ እንዲዋቀር ቁርጠኝነቱን እንዲያሳይ›› ሲል ለመንግሥት ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡

ከዚህ አንፃር የመድረክ አዲስ ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ዶ/ር) ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት ይቋቋም ማለት፣ ‹‹አሁን ያለው መንግሥት መሠረቱ ይስፋ›› ከሚል ትንታኔ የመጣ እንደሆነ በመግለጽ ሲያብራሩ፣ ባለፈው ዓመት ከመንግሥት ጋር ለመደራደር 17 ነጥቦች ያሉት የመደራደርያ ሐሳብ ማቅረባቸውን በማስታወስ ነው፡፡

ከመንግሥት ጋር ለመደራደር መድረክ ካቀረባቸው 17 ነጥቦች መካከል ሁለቱ ምላሽ ማግኘታቸውን የገለጹት ሊቀመንበሩ፣ እነዚህም አምና ታውጆ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ እንዲሁም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ የሚሉት መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ‹‹አሁንም ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት ይመሥረት ስንል ሌሎች ጥያቄዎቻችንን መልስ ለመስጠት እንዲቻል በማሰብ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የሽግግር መንግሥት እየጠየቅን አይደለም፤›› የሚሉት ሊቀመንበሩ፣ ‹‹እያልን ያለነው የካድሬ መገላበጥ ብቻ ያለውን ሁኔታ አይፈታውም፡፡ ሁሉም የአገሪቱ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ኃይሎች ለመፍትሔው የድርሻቸውን ያዋጡ፡፡ ይህንን አስተዋጽኦ ይዞ የተጠናከረ ለሕዝቦች ጥያቄ በተሳካና በተጠናከረ መንገድ መልስ የሚሰጥ መንግሥት መመሥረቱ፣ አገሪቱ አሁን ካለችበት ችግር ያወጣታል፣ አስፈላጊም ነው ከሚል ትንተና የመነጨ ነው፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

በተመሳሳይ የመድረክ አባል የሆነው የአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉዓላዊነት ፓርቲ አመራር አባል የሆኑት አቶ ጎይቶም ፀጋዬ፣ ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት የሚለው ሐሳብ የደኅንነቱ፣ የፖሊስንና የመከላከያን ጉዳይ ለኢሕአዴግ በመተው በሌሎች ሲቪል ጉዳዮች ላይ ግን ያገባናል የሚሉ ኃይሎች ሁሉ በውሳኔው የሚሳተፉበት እንዲሆን የተሰጠ ሐሳብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹ኢሕአዴግ ሥልጣን ይዞ ገለልተኛ ምርጫ ይደረጋል እምነት የሌለን በመሆኑ፣ እንዲሁም ያልተመረጠ መንግሥት ስለሆነ ሁሉም ኃይሎች በውሳኔ አሰጣጥ ላይ ይሳተፉ ከሚል እሳቤ የመጣ ነው፤›› ሲሉ ጨምረው አስረድተዋል፡፡

የውህደት ነገር

መድረክ በምሥረታው ወቅት እንደ ስትራቴጂ ከያዘው አንደኛው መንገድ በሒደት አንድ ጠንካራ ፓርቲ የመመሥረት አጀንዳ ይጠቀሳል፡፡ በዚህም መሠረት ፓርቲዎቹ በሒደት ይዋሀዳሉ የሚል ስትራቴጂ እንደሚከተል ይገልጻል፡፡ ከዚህ ባለፈም በአገሪቱ የሚገኙ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች መድረኩን ተቀላቅለው በጋራ እንዲሠሩም በተደጋጋሚ በሚያወጧቸው መግለጫዎች ሲወተወት ነበር፡፡

ምንም እንኳን የመድረክ ስትራቴጂ ይህን ቢልም የመድረኩ አባላት ግን ለመዋሀድ አሁንም ሌላ ቀን እየጠበቁ ነው፡፡ ከምሥረታው አሥራ አንድ ዓመት በኋላ እንኳ የመድረኩ አባላት ከሌሎች መድረኩ ውስጥ ከሌሉ ፓርቲዎች ጋር  አብሮ ለመሥራት፣ እንዲሁም እስከ መዋሀድ ለሚያደርስ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ድርድር እንዳደረጉ ቢገልጹም በመድረኩ አባል ፓርቲዎች መካከል ግን አሁንም ግንባር ሆኖ የመቀጠል ፍላጎት ነው ያለው፡፡

በጠቅላላ ጉባዔውም ከአረና አባላት ስትራቴጂውን መሠረት በማድረግ ‹ወደ ውህደት የሚወስደን ስትራቴጂ ቀርቷል ወይ? ወዴት ነው እየሄድን ያለነው? ለምንድነው የማንዋሀደው?› የሚል ጥያቄ ቀርቦ እንደነበር አቶ ጎይቶም ገልጸዋል፡፡ ‹‹ዞሮ ዞሮ ሐሳቡ የሁሉም ፍላጎት ሆኖ ስላልተገኘ ውሳኔ ላይ አልተደረሰም፤›› ሲሉ የመድረክ አባላት ድርጅቶች አሁንም ለመዋሀድ እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ የመድረክ ሊቀመንበርም፣ ‹‹የውህደት ጥያቄ ያነሱ አባላት ነበሩ፡፡ ነገር ግን መድረክን ወደ አንድ ወጥ ፓርቲ ለመለወጥ ሙሉ በሙሉ ስምምነት ላይ አልደረስንም፤›› በማለት፣ የውህደት ጉዞው ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት አለማግኘቱን አረጋግጠዋል፡፡

ኦነግና ኦፌኮ

ነሐሴ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. በአስመራ ከተማ ከመንግሥት ጋር የዕርቅ ስምምነት ተፈራርሞ ወደ አገር ቤት የገባው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ ከኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ጋር አብሮ መሥራት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ መወያየታቸውን በመስከረም ወር ይፋ አድርገው ነበር፡፡

ኦነግ ወደ አገር ቤት ከገባ ወዲህ የተለያዩ የፖለቲካ ሥራዎችን መሥራቱን እየገለጸ የሚገኝ ሲሆን፣ በተለየ ሁኔታ ከመንግሥት ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ መግባቱ የመገናኛ ብዙኃንን ቀልብ ስቧል፡፡

የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ መሣሪያ ከመፍታት ጋር ሰጡት የተባለው አስተያየትና በምዕራብ ወለጋ እየደረሱ ያሉ የፀጥታ መደፍረስ ችግሮች ከድርጅቱ ጋር የሚያያዙ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ከዚህ አንፃር የኦፌኮና የኦነግ አብሮ የመሥራት አጀንዳ ምን ያህል ይዘልቃል? የሚኖረው የፖለቲካ እንደምታስ ምንድነው? የሚሉ ጥያቄዎች ከበርካቶች ዘንድ ይነሳሉ፡፡

ሆኖም የኦፌኮና የመድረክ ሊቀመንበር መራራ ጉዲና (ዶ/ር) ፓርቲያቸው ኦፌኮ እየሠራ የሚገኘው ከኦነግ ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ከሁሉም ከውጭ የመጡ የኦሮሞ ፓርቲዎች ጋር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በኦነግና በመንግሥት መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ አስመልክቶም፣ ‹‹በኦዴፓና በእነሱ (ኦነግ) የሚደረገውን ነገር በሰላም እንዲፈቱ እየመከርን ነው፤›› ሲሉ በኦዴፓና በኦነግ መካከል ያለው አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ምክር እየለገሱ መሆናቸውን በመግለጽ፣ በኦነግና በኦፌኮ መካከል ያለው ግንኙነትም አቅጣጫ ተቀምጦለት ወደ ሰፊ ድርድር ለመግባት እየተዘጋጁ እንደሆነ ይፋ አድርገዋል፡፡

አዲስ የአመራር ፊት?

ሐምሌ 2009 ዓ.ም. በተደረገ 13ኛ ጠቅላላ ጉባዔ የመድረክ ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ሚሊዮን ቱማቶ (ዶ/ር) ታኅሳስ 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ደግሞ፣ ለአዲሱ ተመራጭ ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ዶ/ር) ኃላፊነታቸውን አስረክበዋል፡፡

በዚህ መሀል በርካቶች መድረክ አዲስ የአመራር ፊት ለምን እያመጣም? በማለት ይጠይቃሉ፡፡ ታኅሳስ 28 ቀን 2011 ዓ.ም. በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ አረና ለሊቀመንበርነት ሥፍራ ተወዳዳሪ ያላቀረበ ሲሆን፣ ሦስቱ የመድረክ ፓርቲዎች በጠቆሙት መሠረት መረራ (ዶ/ር) በድጋሚ ተመርጠዋል፡፡

የአዲስ የአመራር ፊትን በተመለከተ፣ ‹‹ዞሮ ዞሮ መድረክ አመራር የሚያወጣው ከራሱ ምንጭ (Pool) ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በመድረክ በኩል ብዙ ችግሮችን አላየንም፡፡ አንዳንድ ሰዎች የተወሰኑ ግለሰቦች አመራሮች መሆናቸው ላይ የራሳቸው የሆነ አሉታዊ አተያይ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን ከአሉታዊ አስተያየቶች ይልቅ ማበረታታቱ ይሻላል፤›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር በድፍረት የምንሳተፍ ምሁራን ጥቂት ነን፡፡ ከዚህ አንፃር ሌሎች ምሁራንንም እንዲወጡ ማበረታታት እንጂ፣ አሉታዊ አስተያየቶችን መስጠት የአገሪቱን ምሁራን የበይ ተመልካች ከመሆን አይታደግም፤›› ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

መድረክ በአሁኑ ጊዜ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን)፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ እንዲሁም አረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት (አረና) የተሰኙ በብሔር ደረጃ የተደራጁ ፓርቲዎችን አባልነት የያዘ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) የተሰኘ አገር አቀፍ ፓርቲም በስብስቡ ውስጥ ይገኛል፡፡ በኅብረ ብሔራዊነትና በብሔር ተኮር ርዕዮተ ዓለማዊ ቅኝቶች የተዋቀሩ ፓርቲዎችን በአባልነት ያቀፈው መድረክ ልዩነቶችን አጥብቦና አንድ ወጥ ፓርቲ ሆኖ የሚወጣበት ጊዜ መቼ እንደሆነ ከአመራሩ ባይገለጽም፣ ስትራቴጂው ግን አንድ ወጥ ፓርቲ የመፍጠር ህልም እንዳለው አስፍሯል፡፡

ይህ ስትራቴጂ ተፈጻሚ ሆኖ መድረኩ አንድ ፓርቲ ይሆናል ወይስ እንዲሁ ያዘግማል የሚለው ግን አሁንም የበርካቶች ጥያቄ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -