Wednesday, February 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ኢንዶኔዥያ ውስጥ ተገዶ አረፈ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ኢንዶኔዥያ ውስጥ ተገዶ አረፈ

ቀን:

የኢንዶኔዥያና የሲንጋፖር አለመግባባት አየር መንገዱን ችግር ውስጥ ከቶታል

ሰኞ ጥር 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ወደ ሲንጋፖር ሲበር የነበረ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ ቦይንግ 777 ዕቃ ጫኝ አውሮፕላን፣ የኢንዶኔዥያ የአየር ክልል ያለ በረራ ፈቃድ በመግባቱ በኢንዶኔዥያ አየር ኃይል ተገዶ እንዲያርፍ ተደረገ፡፡

የኢንዶኔዥያ አየር ኃይል ባወጣው መግለጫ አውሮፕላኑ ያለ በረራ ፈቃድ ወደ ኢንዶኔዥያ አየር ክልል በመግባቱ፣ በሁለት ኤፍ 16 ተዋጊ ጀቶች ታጅቦ ባታም በተባለ ደሴት በሚገኝ ኤርፖርት እንዲያርፍ ተደርጓል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ በረራውን ያደረገው ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ሕግ ተከትሎ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ አየር መንገዱ ባወጣው መግለጫ፣ የበረራ ቁጥር ኢቲ 3728 ሰኞ ጥር 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ወደ ሲንጋፖር ሲበር በኢንዶኔዥያ ባለሥልጣናት በባታም ኤርፖርት እንዲያርፍ መደረጉን አስታውቋል፡፡ አውሮፕላኑ የሌላ አውሮፕላን ሞተር በአስቸኳይ ለማድረስ ወደ ሲንጋፖር ሲበር እንደነበር ገልጾ፣ በዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የቺካጎ ስምምነት መሠረት በወዳጅ አገሮች የአየር ክልል ሳያስፈቅድ መብረር ይቻላል በሚለው ሕግ መሠረት የአየር ክልሉን ባለማስፈቀዱ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስለበረራው ዝርዝር መረጃ ለኢንዶኔዥያ ባለሥልጣናት ማብራሪያ መስጠቱን ገልጾ፣ የአውሮፕላኑ ሠራተኞች በአንድ ሆቴል ውስጥ እረፍት በመውሰድ ላይ እንደሆኑ ጠቁሟል፡፡ የበረራ ፈቃድ ከኢንዶኔዥያ ባለሥልጣናት እንደተገኘ አውሮፕላኑ በረራውን እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደተናገሩት፣ ቦይንግ 777 ዕቃ ጫኝ አውሮፕላን ከሆንግ ኮንግ በመደበኛ የካርጎ በረራ ጭነት ለማምጣት ይጓዝ የነበረ ቢሆንም፣ እግረ መንገዱን ለጥገና ወደ ሲንጋፖር መላክ የነበረበትን የአውሮፕላን ሞተር ይዞ እንዲሄድ ተደርጓል፡፡ ይህም በአየር መንገዱ የተለመደ አሠራር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የተጫነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ 787 ሮልስ ሮይስ ትሬንት 1000 ሞተር ሲሆን፣ ሲንጋፖር በሚገኘው የሮልስ ሮይስ የጥገና ማዕከል ለጥገና መሄድ የነበረበት እንደሆነ ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 777 አውሮፕላን በሲንጋፖር ለማረፍ የሚያስፈልገውን ፈቃድ ያገኘ ቢሆንም፣ ወደ ሲንጋፖር ለመድረስ የኢንዶኔዥያን የአየር ክልል ማቋረጥ ነበረበት፡፡ ለዚህም የሚያስፈልገውን የበረራ ፈቃድ ሳያገኝ ወደ አየር ክልላቸው መግባቱ ያስቆጣቸው የኢንዶኔዥያ ባለሥልጣናት አውሮፕላኑ ተገዶ እንዲያርፍ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበርካታ የእስያ አገሮች መደበኛ የመንገደኛና የካርጎ በረራዎች እንዳሉት ያስታወሱት ምንጮች፣ ወዳጅ በሆነ አገር ያለ በረራ ፈቃድ መብረር እንግዳ ድርጊት እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹አንድ የአየር ክልል ስታቋርጥ በውጭ ምንዛሪ ትከፍላለህ ይህም ለአገር ገቢ ነው፡፡ ነገር ግን የኢንዶኔዥያ ባለሥልጣናትን ያስቆጣቸው ከሲንጋፖር ጋር የፖለቲካ ቅራኔ ስላላቸው ነው፤›› ያሉት ምንጮች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሁለቱ አገሮች መካከል ባለ ቅራኔ ምክንያት ጉዳዩ ተጋኖ ተጎጂ ሊሆን እንደቻለ አስረድተዋል፡፡ ‹‹በሲንጋፖርና ኢንዶኔዥያ መካከል ያለው የፖለቲካ  ትኩሳት  ዳፋው ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ተርፏል፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም ችግሩ ከኢንዶኔዥያ ባለሥልጣናት ጋር በውይይት ተፈትቶ፣ አውሮፕላኑ በረራውን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ጥቁር የመልበስ ውዝግብና የእምነት ነፃነት በኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር ወር ላይ በፓርላማ...

የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚቆጠጠር ገለልተኛ ተቋም ለመመሥረት እንቅስቃሴ ተጀመረ

ከ70 በላይ አዳዲስ የፋይናንስ ተቋማት ዘርፉን ሊቀላቀሉ ነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...

እስቲ አንገፋፋ!

እነሆ መንገድ። ጊዜና ሥፍራ ተጋግዘው በውስንነት ይዘውናል። መፍጠን ያቃተው...