Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየውጭ ስደተኞችን የሚመለከተው ረቂቅ አዋጅ የኢትዮጵያን ጥቅም እንዲያስከብር ተጠየቀ

የውጭ ስደተኞችን የሚመለከተው ረቂቅ አዋጅ የኢትዮጵያን ጥቅም እንዲያስከብር ተጠየቀ

ቀን:

በኢትዮጵያ የሚገኙ የውጭ ስደተኞችን አስተዳደር በተመለከተ የተረቀቀው አዋጅ ከመፅደቁ በፊት፣ በጥልቀት ሊታይና የኢትዮጵያን ጥቅም የበለጠ እንዲያስከብር ማሻሻያዎች ሊደረግበት እንደሚገባ ተገለጸ።

ረቂቅ አዋጁ በሰኔ 2010 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ነበር፡፡ ምክር ቤቱም ረቂቁ ላይ ዝርዝር ፍተሻ እንዲደረግ ለሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዋናነት፣ እንዲሁም ለውጭ ግንኙነትና ለሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተባባሪነት መርቶት ነበር።

ሁለቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ሰኞ ጥር 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ሕዝባዊ የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርገዋል።

በዚህ ውይይት ላይ ስደተኞች በኢትዮጵያ ላይ ስለሚፈጥሩት የማኅበራዊ አገልግሎት ጫና፣ የአገሪቱን ሀብትና ለዜጎች የሚፈጥረውን የሥራ ዕድል በመሻማት የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተፅዕኖን የተመለከቱ ጥያቄዎች በውይይቱ ተሳታፊዎች በሥጋት ተነስተዋል፡፡

ለተነሱት ጥያቄዎችና የረቂቅ ሕጉን ይዘቶች በተመለከተ የስደተኞችና ከስደት ተመላሽ ጉዳዮች ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ጫኔ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ በማስጠለል በኩል ረጅም ታሪክ ያላት ቢሆንም፣ ሕጉ የተሟላ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ በማድረግ በኩል ክፍተት እንደነበረበት አቶ ከበደ ተናግረዋል። ስደተኞች እየተረዱ ከመቀመጥ ውጪ በልማት የሚሳተፉበትና ንብረት የሚያፈሩበት ዕድል ተነፍጓቸው መቆየታቸውንም ገልጸዋል።

 በመሆኑም የሕግ ማሻሻያ በማድረግ ስደተኞች ጥገኝነት ባገኙበት አገር ከዜጎች እኩል የትምህርትና የሥራ ዕድል የማግኘት፣ እንዲሁም ተደራጅተው የመሥራት መብታቸው እንዲከበር ለማድረግ መታቀዱን፣ ይህም የአገርን ገጽታ ከመገንባት ባሻገር ከአጎራባችም ሆነ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር የሚኖረውን የወዳጅነት ግንኙነት እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።

ረቂቅ ሕጉ በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች የሥራ ዕድል እንደሚመቻችላቸው፣ ከካምፕ ወጥተው መኖር እንዲችሉ፣ ንብረት የማፍራት፣ የመሸጥና የመለወጥ መብት እንደሚኖራቸው ይገልጻል። ስደተኞች በኢትዮጵያ ለሚያገኙት ማንኛውም አገልግሎት ወጪው የሚሸፈነው ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሚገኝ ብድርና ዕርዳታ ስለሆነ፣ በኢትዮጵያ ላይ ምንም ዓይነት የበጀት ጫና እንደማይኖረው አቶ ከበደ በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል።

ለስደተኞች ተብሎ በሚፈጠረው የሥራ ዕድልም ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ፣ ስደተኞቹም በሚያገኙት አገልግሎት እንደማንኛውም የአገሪቱ ዜጋ ታክስ እንደሚከፍሉ አስታውቀዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው አዋጁ ቀደም ሲል የነበረ ቢሆንም፣ የተሟላ ባለመሆኑ የኢትዮጵያ ዜጎችን መብትና ጥቅም በማይጎዳ መንገድ እዲሻሻል መደረጉን በጥንካሬ አውስተው፣ አሁንም ሕጉ ከመፅደቁ በፊት መታየት ያለባቸው ነገሮች በጥልቀት እንዲታዩና ኢትዮጵያም ስደተኞችን መቀበል ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ የደረሰባትን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ሊፈታ የሚችል ሕግ ሊሆን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ከ900 ሺሕ በላይ የጎረቤት አገሮች ስደተኞች ተጠልለው ይገኛሉ።

ረቂቅ ሰነዱ በሥራ ላይ የሚገኘውን የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ አሻሽሎ እንደ አዲስ የሚደነግግ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች ከመጠለያ ካምፖች ውጪ ለመኖር እንዲችሉ፣ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመዘዋወር ነፃነትን የሚያጎናፅፍ ድንጋጌ ይዟል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የባንክ ሒሳብ የመክፈት፣ መንጃ ፈቃድና መታወቂያ ማውጣት እንዲችሉ መብት የሚሰጥ ድንጋጌ የያዘ ሲሆን፣ ከ20 ዓመት በላይ በኢትዮጵያ የኖሩ ስደተኞች አግባብ ባለው ሕግ የኢትዮጵያ ዜግነትን እንዲያገኙም በሰነዱ ተካቷል፡፡

 የሥራ ዕድልን በተመለከተም ለውጭ አገር ዜጎች ከተሰጡ መብቶች እጅግ የተሻለውን ያህል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መብት የሚሰጥ ድንጋጌ በረቂቁ ተካቷል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተለየ ሁኔታ ለስደተኞች የሚፈቀዱ የሥራ ዘርፎች ተለይተዋል፡፡ እርሻ፣ ኢንዱስትሪ፣ አነስተኛና ጥቃቅን የዕደ ጥበባትና የንግድ ዘርፎች ተዘርዝረዋል፡፡

ንብረት የማፍራትና የማስተላለፍ፣ የአዕምሮ ውጤቶች ጥበቃ እንዲያገኙ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያውያንና በስደተኞች መካከል መድልኦ እንደማይደረግ የሕግ ሰነዱ ይዘረዝራል፡፡

መንግሥት ይኼንን የሚፈቅድ ከሆነ ለኢትዮጵያውያን ሥራ አጦች የጋራ ተጠቃሚነትን የሚውል የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ዕርዳታ እንደሚገኝ የሰነዱ ማብራርያ ይገልጻል፡፡

 ከእነዚህም መካከል ለ100 ሺሕ ሰዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በተመሳሳይ 100 ሺሕ ሰዎችን በመስኖ የታገዘ የእርሻ ልማት እንዲያለሙ እንደሚያስችል እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ለዚህም ሲባል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የዓለም ባንክ፣ የአውሮፓ ኅብረትና ሌሎች አገሮች የኢንቨስትመንት ካፒታል በዕርዳታ ለመስጠት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት ማድረጋቸውን ያስረዳል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ሲጠናቀቁ ከሚፈጠረው ለ100 ሺሕ ሰዎች የሚሆን የሥራ ዕድል ውስጥ 70 በመቶ (70 ሺሕ) ለኢትዮጵያውያን የሚደለደል ሲሆን፣ ቀሪው 30 በመቶ (30 ሺሕ) ለስደተኞች እንደሚሆን ማብራርያው ይገልጻል፡፡

በተመሳሳይ በእርሻ ልማት የሥራ ዕድል ለመፍጠር 10 ሺሕ ሔክታር መሬት የተዘጋጀ መሆኑን፣ በዚህም ከሚፈጠረው 100 ሺሕ የሥራ ዕድል 70 በመቶ ለኢትዮጵያውያን ቀሪውን 30 በመቶ ደግሞ ለስደተኞች እንደሚደለድል ይገልጻል፡፡

በመሆኑም በሁለቱ የሥራ ዘርፍች ከሚፈጠረው የሥራ ዕድል ውስጥ 60 ሺሕ ስደተኞች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

በረቂቅ ሕጉ ላይ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ሁለቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን፣ ይኼንን ተከትሎም ረቂቁ በቅርቡ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...