በኢትዮጵያ የሚገኙ የማሠልጠኛ ማዕከላትና አካዴሚዎች ከፌዴሬሽኖችና ከክለቦች ያላቸው ግንኙነት ክፍተት እንዳለው ተገለጸ፡፡
በስፖርት ኮሚሽን በስፖርት ትምህርቶችና ሥልጠና የዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት በአዳማ ከተማ ጥር 7 ቀን 2011 ዓ.ም. በተሰናዳው መድረክ ላይ የስፖርት አካዴሚዎቹ ሥልጠና መስጠት ቢችሉም ከፌዴሬሽኖች ጋር ክፍተት በመኖሩ ስፖርተኞችን በአግባቡ ማብቃት እንዳልተቻለ ተገልጿል፡፡
በአትሌቲክስ በመካከለኛ ርቀት፣ በረዥም ርቀት እንዲሁም በሜዳ ተግባር ላይ ትኩረታቸውን በማድረግ ሥልጠናቸው እያከናወኑ ያሉት አካዴሚዎቹ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ስላፈሯቸው ታዳጊዎችና ውጤቶች እንዲሁም ችግሮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኘውን የወጣቶች ስፖርት አካዴሚ፣ በአሰላ የሚገኘው የጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት አካዴሚ፣ እንዲሁም በቆጂ፣ ማይጨው፣ ሀገረ ሰላም፣ ደብረ ብርሃንና የአምቦ ጎል ማሰልጠኛ ማዕከሎች የሦስት ዓመት ሪፖርታቸውን አቅርበዋል:: በሪፖርታቸውም በሦስት ዓመታት ውስጥ በአገሪቷ ለሚገኙት ክለቦች፣ የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ለብሔራዊ ቡድን በርካታ አትሌቶችን ማበርካታቸውን በየደረጃው አብራርተዋል:: ከሥልጠናው ባሻገርም በዘርፉ በቂ የሥልጠና ቁሳቁሶች፣ ባለሙያዎች፣ የውድድር ሥፍራዎች፣ አትሌቶች ከክለቦች ጋር የሚያደርጉት ሕገወጥ ግንኙነትና የቀን የምግብ ወጪ እንዲሁም የኪስ ገንዘብ በቂ ያለመሆንና በቂ የማዘውተሪያ ቦታ አለመኖር በሥልጠና ተቋማቱ ከፍተኛ እንቅፋቶች መሆናቸው ተጠቅሰዋል::
በአገሪቱ የሚገኙ የስፖርት የሥልጠና ማዕከላትና አካዴሚዎች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የልምድና ተሞክሮ ልውውጥ ማድረግ እንደሚገባቸው የስፖርት ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጌታቸው ባልቻ አሳስበዋል:: የልምድ ልውውጡ በዋናነት መሠረት የሚያደርገው በማዕከላትና በአካዴሚዎች የሚሰጡ ሥልጠናዎች ቅንጅታዊ አሠራርና ውጤታማነትን መሠረት ያደረገ መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡
በተለይ አትሌቲክሱ ዘርፍ ከፍተኛ ወጤት ማምጣት መቻሉ አህጉርና አገር አቀፍ ወጤቶች ተጠቅሰዋል:: በተለይ በእግር ኳስና በአትሌቲክስ ሥልጠና ሒደት ከፍተኛ ውይይት እየተደረገ ሲሆን፣ በመድረኩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስና የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ቢጋበዙም አለመገኘታቸውን ስፖርት ኮሚሽኑ አስታውቋል:: የሥልጠና ማዕከላትና የአፈፃፀም ሪፖርቱን ተከትሎም አዲስ ማሻሻያዎች እንደሚኖሩ ይጠበቃል::