Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየዓድዋ መንገደኞች

የዓድዋ መንገደኞች

ቀን:

‹‹ያልሠለጠነ፣ ኋላቀር፣ ጨካኝ፣ ሃይማኖት የሌለው›› ተደርጎ ይታሰብ የነበረውን ጥቁር ሕዝብ ለመውረር የጣልያን ጄኔራሎች በዘመኑ የነበሩ ልዩ ልዩ የጦር መሣሪያዎችን ወደ አፍሪካ ቀንድ አጋዙ፡፡ ቀሪውን የአፍሪካ ክፍል ቅኝ ግዛታቸው አድርገው የነበሩ ምዕራባውያን ኢትዮጵያን የጣልያን ድርሻ ብለው ትተዋል፡፡

በወቅቱ ኢትዮጵያ እንኳንስ ድንበር ተሻግሮ የመጣን ወራሪ ለመመከት እንደ አገር በሁለት እግሯ መቆም ጋራ የመውጣት ያህል የሚከብዳት ጊዜ ነበር፡፡ በ1886 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ውስጥ ንጉሠ ነገሥቱ ከአካባቢ ገዥዎች ጋር ውጊያ አካሂደዋል፡፡ ከወላይታው ገዥ ካዎ ጦና ጋር የማዕከላዊ መንግሥትን የሚመራው የዳግማዊ ምኒልክ ሠራዊት ውጊያ ገጥሟል፡፡ ሌሎችም መሰል የጦር ውሎዎች ዜና ከየአቅጣጫው የሚሰማበት፣ አንዲት ጠንካራ አገርን ለመገንባት የሞት ሽረት ትግል የሚጠይቅ ወሳኝ ወቅት ነበር፡፡ ተጠሪነታቸውን ለንጉሠ ነገሥቱ አድርገው ማዕከላዊ የአገዛዝ ሥርዓትን ለመገንባት ወገቤን የሚሉ ገዥዎች ጋር የሚካሄደው ድርድርና የጦር ውሎ ፀሐፌ ትዕዛዝን ፋታ ሳይሰጥ በጎን ሌላ ጠላት ብቅ የማለቱ ጉዳይ አስደንጋጭ ነበር፡፡ ለዚያውም የተደራጀ የጦር ሠራዊት ከሙሉ ትጥቅ ጋር ነበርና በወራሪውና በተወራሪው መካከል ያለው የአቅም ጉዳይ ወደ አንዱ ሚዛን የደፋ ስለነበር ‹‹ወየውላት ኢትዮጵያ›› ተብሎም ነበር፡፡

አገሬን አሳልፌ ከምሰጥ ሞቴን እመርጣለሁ ያሉ የንጉሠ ነገሥቱን ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የጦር ክተት ጥሪ ተቀብለው ለዘመቻ ይጣደፉ ገቡ፡፡ ከገብር አልገብርም ጋር በተያያዘ ቁርሾ የነበራቸው ገዥዎች ሳይቀሩ ከንጉሠ ነገሥቱ ጎን በመቆም ዳር ድንበራቸውን ለማስከበር ኢትዮጵያዊነት አንድነታችን አሉ፡፡ የሃይማኖት አባቶች፣ እናቶች፣ ወጣቶች፣ የአሥራ አንድ ዓመት ታዳጊዎች ሳይቀሩ እንደየድርሻቸው ለውጊያ ዘመቱ፡፡ ለንጉሠ ነገሥቱን የክተት ጥሪ ፈጥኖ ምላሽ ከሰጡት አንዱ በራስ መኮንን የሚመራው የምሥራቅ ጦር ቀድሞ አዲስ አበባ በመግባት ደጀን ነኝ አለ፡፡ አፄ ምኒልክ መናገሻ ከተማቸውን አዲስ አበባን ለጅማው ንጉሥ አባጅፋር፣ ለከፋው ቃዎ ጦና እና ለራስ ዳርጌ አደራ ሰጥተው ወደ ጦርነት ዘመቱ፡፡

- Advertisement -

ወራሪን ጦር ለመመከት በ1888 ዓ.ም. መላው ኢትዮጵያዊ የዘመተው በአገራዊ ፍቅር በአንድነት መንፈስ በዚህ መልኩ ነበር፡፡ ‹‹የዓድዋ ድል የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ብቻ ሳይሆን የአንድነት መንፈስ ያበረታው የጥንካሬ ውጤት ነው፡፡ ተምሳሌትነቱም ለጥቁር ብቻ ሳይሆን ለመላው የዓለም ሕዝብ ለወራሪውም ጭምር ነው፤›› የሚለው ከጉዞ ዓድዋ መሥራቾች መካከል አንዱ መሐመድ ካሳ ‹‹ዓድዋ ከጦርነትም በላይ የአንድነት መንፈስ ነው›› ይላል፡፡ የግል ቁርሾውን ወደ ጎን ብሎ አገሩን ከጣልያን ወረራ ለመከላከል የተመመው ሠራዊት ጠላትን አምባላጌ፣ እንዳየሱስ ላይ ድል ነሳ፡፡ ቀጥሎም የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ዓድዋ ላይ በጠላት ላይ ዳግመኛ ድል ተቀዳጀ፡፡

‹‹ሊወጉን የመጡ ጣልያኖች ሞተው ፀሎት አድርገን ቀብረናቸዋል፡፡ የተማረኩ ወታደሮችንም ሳናጉላላ አጋሠሥ ተከራይተን ወደመጡበት ሸኝተናል፡፡ ከጣልያን ጋር የተጋጠምንባቸው ሦስቱ ጦርነቶች ኢትዮጵያውያን ሰብአዊ ክብር ያለን፣ ሃይማኖተኞች፣ እንዳሰቡን ጨካኞች አለመሆናችን የታየበት ነው፤›› በማለት መሀመድ የዓድዋ ድል ተዋግቶ የማሸነፍ ጀብዱ ብቻ ሳይሆን ሚዛን የሚደፋ ተምሳሌታዊነት ያለው አኩሪ ገድል መሆኑን ይናገራል፡፡

የዓድዋ ድል የነፃነት ቀንዲል፣ የኢትዮጵያውያን ኩራት፣ ጀግንነት፣ ጊዜ የማይሽረው ታሪካዊ ክስተት ነው፡፡ የዓድዋ ድል ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየዓመቱ የካቲት 23 ቀን ተከብሮ ይውላል፡፡ ጦርነቱ በተካሄደ በሰባተኛው ዓመት ማለትም 1895 ዓ.ም. ላይ በተለየ ሁኔታ ተከብሮም ነበር፡፡ ይህ የሕዝብ በዓል በድምቀት የመከበሩ ነገር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዘ መጥቶ እንደምንም መቆጠር ጀምሮም ነበር፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ዓድዋ በአዲስ መንፈስ እንዲከበር የተለያዩ አካላት ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህም እንደ ያሬድ ሹመቴ ያሉ የፊልም ባለሙያዎች ተነሳሽነቱን ወስደው እየሠሩበት ይገኛሉ፡፡

‹‹ጉዞ ዓድዋ›› የዓድዋ ጀግኖች የሚወሱበት፣ የክተት ዘመቻው ምን ዓይነት መልክ እንደነበረው የሚያንፀባርቅ፣ የአገር ፍቅር የሚታይበት፣ ኢትዮጵያዊ እሴቶች ጎልተው የሚወጡበት የጉዞ ፕሮግራም ነው፡፡ ጉዞ ዓድዋ ከስድስት ዓመታት በፊት የተጀመረ ሲሆን፣ ተጓዦች ከ1000 በላይ ኪሎ ሜትሮችን በእግር ያዘግማሉ፡፡ በዚህ ፕሮግራም ለመሳተፍ ፍላጎቱ ያላቸው ወጣቶች ከወር በላይ ለሚፈጀው የእግር ጉዞ ብቁ መሆናቸውን የሚያሳይ የሕክምና ማስረጃ ማቅረብ ግድ ይላቸዋል፡፡ እንጓዛለን ብለው ከሚመዘገቡት ውስጥ ብርቱ ሆነው የተገኙት ሜዳውን አዝግመው፣ ተራራውን ወጥተው፣ ቁልቁለቱን ተንደርድረው ጢሻ በጥሰው ያለመኪና ከአዲስ አበባ እስከ ዓድዋ ድረስ በእግራቸው ይጓዛሉ፡፡

‹‹በዚያ  ዘመን መኪና አልነበረም፡፡ አዝማቾቹ መኳንንቱ በበቅሎና በፈረስ ሌላው ደግሞ በእግሩ ነው እስከ ዓድዋ ድረስ የተጓዘው፡፡ ስለዚህ በዚህ ጉዞ ወቅት መኪና የነካ ይመለሳል፤›› የሚለው ያሬድ ነው፡፡ የዓድዋ ተጓዦች በየዓመቱ ተመሳሳይ የጉዞ መስመር የሚከተሉ ሲሆን፣ ቀጥሎ የተዘረዘሩት 28 ቦታዎች በእግር የሚያቆራርጧቸው ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ የደብረ ብርሃንን አቅጣጫ ይዘው በመውጣት ደሴ፣ ሐይቅ፣ ውጫሌ፣ መርሳ፣ ወልዲያ፣ ቆቦ፣ አላማጣ፣ ኮረም፣ ሐሸንገ፣ ማይጨው፣ አምባላጌ፣ ሂዋነ፣ ማይነብሪ፣ ኵሀ፣ እንዳየሱስ፣ መቐለ፣ ውቅሮ፣ ነጋሽ፣ ፍሬወይኒ፣ ሐውዜን፣ ነበለት፣ እዳጋ ዓርቢ፣ እንትጮ፣ ይሓ፣ አባ ገሪማ፣ ሰሎዳ የተባሉትን ቦታዎች አቆራርጠው በመጨረሻ ዓድዋ ከተማ ይደርሳሉ፡፡ ከአንድ ወር ጊዜ በላይ የሚፈጀውን ታሪካዊ የእግር መንገድ የሚያዘግሙ ተጓዦች በጉዞ ወቅት የሚያስፈልጋቸውን ወጪ የሚሸፍነው ወይም ስንቅና አዳራቸውን የሚያመቻቸው ጉዞ ዓድዋ ነው፡፡

በመጀመርያው የጉዞ ዓድዋ ፕሮግራም ላይ ከተሳተፉ አምስት ተጓዦች መካከል እንደነበር የሚናገረው መሀመድ በጉዞ ወቅት ሜዳ፣ ጫካ፣ ሐይቅ ላይ አድረው እንደሚያውቁ ያስታውሳል፡፡ እንደ የሕክምና መስጫ ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የወታደር ካምፖች፣ መስጊዶች፣ አብያተ ክርስቲያናትም በማደሪያነት እንደሚመርጡም ገልጿል፡፡ አንዳንድ የገጠር ነዋሪዎችም አልጋቸውን ለቀውላቸው ያሳድሯቸዋል፡፡ በአገር ወግ እግራቸውን አጥበው፣ ጠቦት አርደው የሚያስተናግዷቸውም ያጋጥማሉ፡፡ በአድካሚ የእግር ጉዞ የዛለ እግራቸው መሬት መቆንጠጥ እስኪችል ድረስ የሚንከባከቧቸውም እንዲሁ፡፡

‹‹ከአዲስ አበባ ወጥተን ጣርማ በርን አቋርጠን ደብረ ሲና እስክንደርስ ያለው ከባድ ቀዝቃዛ አየር ተጓዦቹን ጉንፋንና ብርድ ያስይዛቸዋል፡፡ እንዲህ ባለ አጋጣሚ አስፈላጊውን የሕክምና ዕርዳታ ማግኘት እንዲችሉ በአቅራቢያ ወደሚገኙ የሕክምና ተቋማት እንወስዳቸዋለን፡፡ የተዘጋ ክሊኒክ ሁሉ አስከፍተን አሳክመናቸው እናውቃለን፤›› ይላል ያሬድ፡፡ በመንገዳቸው ላይ በጉዞ ወቅት ካጋጠማቸው መካከል የማይረሳውንም እንደሚከተለው አስታውሷል፡፡

በተለያዩ የጉዞ ዓመቶች ተመሳሳይ ቦታ ላይ ያጋጠማቸው ነው፡፡ በአንደኛው የጉዞ ዓመት በመርሳ ከተማ አንድ ወጣት የእግር ውልቃት አጋጥሞት የሚያደርጉትን አጥተው ሳለ እግር የጣላቸውን አንድ ሰው ያገኛሉ፡፡ እሳቸውም ወጣቱን በፈረሳቸው ይሸኙታል፡፡ ይህ በተፈጠረ በዓመቱ እንደገና አንዲት ወጣት ተመሳሳይ ቦታ ላይ የቋንጃ መሸማቀቅ ያጋጥማትና እግሯ አልላወስ ይላታል፡፡ ልጅቱን በፈረሳቸው የሸኙት እኚሁ ከዓመት በፊት ወጣቱን የሸኙ ግለሰብ ናቸው፡፡ የሚገርመው ደግሞ ፈረሱም ያልተቀየረ መሆኑ ነው፡፡ ‹‹እነዚህን ልጆች ድጋሚ አግኝቼ በሸኘኋቸው ብዬ ለአላህ ስፀልይ ነበር›› እንዳሏቸው ያሬድ ያስታውሳል፡፡

45 ቀናት በሚፈጀው ጉዞ ዓድዋ በመጀመርያው ዓመት አምስት፣ በሁለተኛው ስድስት፣ በሦስተኛው አሥራ ሁለት፣ በአራተኛው አምስት፣ በአምስተኛው ሃያ አምስት ተጓዦች ከአዲስ አበባ ተነስተው እስከ ዓድዋ በእግር ተጉዘዋል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ 48 ሰዎች የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ አባላት፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች በተገኙበት ጥር 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ሽኝት ተደርጎላቸው ከረፋዱ አራት ሰዓት ከሩብ ላይ ጉዞ ጀምረዋል፡፡

በዚህ ጉዞ ዓድዋ፣ አራት የድሬዳዋ ወጣቶች ተሳታፊ ናቸው፡፡ ወጣቶቹ ለዓድዋ ጦርነት ቀድሞ አዲስ አበባ እንደደረሰው የምሥራቅ ኢትዮጵያ ጦር ሁሉ ቀድመው ጥር 5 ቀን አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፣ ከሐረር 510 ኪሎ ሜትሮችን በእግር ተጉዘው አዲስ አበባ የደረሱ ናቸው፡፡ ከሰቆጣ ላሊበላ ዙሪያ ዋግ ሹሞችን ወክለው፣ ከተምቤን የራስ አሉላን ሠራዊት ወክለው ተጓዦቹን የሚቀላቀሉ እንዳሉም ታውቋል፡፡ ከሽረም እንዲሁ አምስት ወጣቶች ተጓዦችን እንቀላቀላለን ማለታቸውን ያብራራው ያሬድ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...