ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በኢትዮጵያ ታሪክ በዋናነት የሚያስጠቅሳቸው ለዘጠኝ አሠርታት ግድም የቆየውን ዘመነ መሳፍንትን ያስፈጸሙና የአሐዳዊት ኢትዮጵያ ጅማሬ መሆናቸው እንደሆነ ይወሳል፡፡
ጥር 6 ቀን 1811 ዓ.ም. (በአንዳንድ ጽሑፎች 1810 ዓ.ም. ይላሉ) የተወለዱት ዳግማዊ ቴዎድሮስ ከየካቲት 3 ቀን 1847 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞታቸው ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም. ድረስ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነበሩ። በትውልድ ስማቸው ደጃዝማች ካሳ ኃይሉ ሲባሉ፣ በፈረስ ስማቸው አባ ታጠቅ፣ እንዲሁም መይሳው ካሳ ይባሉ ነበር፡፡
በታሪክ ፕሮፌሰሩ ባህሩ ዘውዴ አስተያየት የአፄ ቴዎድሮስ ሕይወት በሦስት ቦታዎች ይጠቃለላል፡፡ ቋራ፣ ጋፋትና መቅደላ። የመጀመሪያው የፖለቲካና ወታደራዊ መሠረትን ሲወክል፣ ሁለተኛው የዘመናዊነትን ፍላጎት ይወክላል፣ ሦስተኛው ደግሞ መጠለያንና፣ የሞት ቦታን ይወክላል። አጠቃላዩ የቴዎድሮስ ውጤት ቅይጥ ነው፡፡
‹‹አባ ታጠቅ ካሳ›› ተብለው የሚታወቁት አፄ ቴዎድሮስ በተለያዩ የጥበባት ዘርፎች ለባለሙያዎች ርዕሰ ጉዳይ በመሆን ይወሳሉ፡፡ በልብ ወለድ «የቴዎድሮስ እንባ» እና «የታንጉት ምስጢር» ድርሰቶችን በተለያዩ ዘመኖች የጻፈው ብርሃኑ ዘሪሁን ይጠቀሳሉ፡፡ ደራሲ ብርሃኑ በ1958 ዓ.ም የቴዎድሮስ እንባን፣ ካሳተሙ በኋላ እንደገና ልብ ወለዱን ከልሰውና አስፋፍተው በመጻፍ በ1979 ዓ.ም የታንጉት ምስጢርን አውጥተዋል፡፡ ቴዎድሮስ ለታሪካዊ ልብ ወለድ መነሻ ከሆኗቸው ደራስያን አንዱ ሣህለ ሥላሴ ብርሃነ ማርያም በ«አፍሪካን ራይቲንግ ሲርየስ» ውስጥ የተመዘገበላቸው «ዘ ዋርየር ኪንግ» ይታወቃል፡፡ በተውኔት ረገድ ደጃዝማች ግርማቸው ተክለሐዋርያት የደረሱት «ቴዎድሮስ»፣ የጸሐፌ ተውኔትና ባለቅኔ ጸጋዬ ገብረመድኅን «ቴዎድሮስ» ተውኔትና «የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ» ግጥም ይጠቀሳሉ፡፡
«ታጠቅ ብሎ ፈረስ ካሳ ብሎ ስም፣
ዓርብ ዓርብ ይሸበራል ኢየሩሳሌም» የሚለው የበገና መዝሙር ንጉሠ ነገሥቱ ‹‹ኢየሩሳሌምን ከቱርክ ቀንበር ነፃ አወጣለሁ›› ይሉ ነበር የሚለውን አስተሳሰብ በበገና ደርዳሪዎች እስካሁን ድረስ የሚቀነቀን ነው፡፡
አማርኛ ከግእዝ ይልቅ የሥነ ጽሑፍ ቋንቋ እንዲሆን ይጥሩ እንደነበር ታሪካቸው ከግእዝ ይልቅ በአማርኛ እንዲጻፍ ያስደረጉ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ የአማርኛ ትርጉም ለኅብረተሰቡ እንዲሰራጭ በማድረግም ይጠቀሳሉ፡፡
የቴዎድሮስ ጀግንነት በሳይንስና ጥበብ ውስጥ ልዩ ስፍራ እንደሚይዝ የሰባስቶፖል መድፍ ሥራ ውጥን አንዱ መሆኑና በዘመናችን «ጋፋት ኢንጂነሪንግ» ለሚለው ስያሜ ንቡር ተጠቃሽ ቴዎድሮስ ናቸው፡፡
የሥነ ጥበብ ሐያሲ የነበሩት ሥዩም ወልዴ ቴዎድሮስን ‹‹ባህላዊ ጀግና›› የሚል መጠርያ ሰጥተውታል፡፡ የቴዎድሮስ ባህላዊ ጀግንነት ሰፋ ባለ መልኩ የሚታይና በሕዝባዊ ግጥሞች፣ በዘፈኖች፣ በተውኔቶች፣ በልብ ወለዶች፣ በግጥሞች፣ በቅርጻ ቅርጾች በሥዕሎችና በጥበባተ ዕድ ሥራዎች ውስጥ ጎልቶ ገጽታው ይታያል፡፡
በቴዎድሮስ ዙሪያ በርካታ ትውፊታዊና ዘመናዊ ሥዕሎች በተለያዩ ጥበባውያን ተሥለዋል፡፡ የቴዎድሮስ ምስል ከእውነታው ተገልብጦ መሣሉ ይነገራል፡፡ አንድ እንግሊዛዊ መኰንን በሠራቸው በርካታ ንድፎች በአንዳንዶቹ የቴዎድሮስ ገጽታ የሚታይባቸው ሲሆኑ በሌሎቹ የመቅደላ ተራራና የሴባስቶፖል መድፍ በብዙ ሕዝብ ሲጎተት የሚታይባቸው ናቸው፡፡
ሐያሲው ሥዩም እንደሚተነትኑት በጊዮም ለዣን ከታተመው ጉርድ ምስል ሌላ ሁለተኛ ጉርድ ምስል ይገኛል፡፡ በተለይ ደራሲው ግርማቸው ተክለሐዋርያት «ቴዎድሮስ» የተሰኘው ተውኔት በመጽሐፍነት ታትሞ በወጣ ጊዜ የመጽሐፉ ሽፋን በመሆኑ በአገር ውስጥ ሊታወቅ ቻለ እንጂ ከዚያ በፊት የሚታወቅ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡
ሁለቱ ጉርድ ምስሎች በኤትኖግራፊያዊ ይዘቶቻችው፣ በፀጉር አሠራር ፈሊጥና በአለባበሳቸው የተለያዩ ናቸው፡፡ በጊዮም የታተመው ጉርድ ምስል ለአብዛኞቻችን የቴዎድሮስና የዮሐንስ መታወቂያ የሆነው የፀጉር አሠራር ፈሊጥ (ባለሹሩባው) ሲሆን ሁለተኛው ጉርድ ምስል ግን ወደ ኋላ የተሰበሰበ ጎፈሬ የሚታይበት ምስል ነው፡፡ ከቅርብ ዘመን ኪነ ቅቦች አንዱ የሠዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ‹‹መይሳው ካሳ›› ይጠቀሳል፡፡
ከሌሎች ታላላቅ መሪዎች ይልቅ የአፄ ቴዎድሮስ አሟሟት በኢትዮጵያን ዘንድ የማይረሳ ነው። በጀግንነት፣ እጅ አልሰጥም ብለው ማለፋቸው ለሕዝቡ ‹‹ቅቤ ያጠጣ›› ተግባር እንደነበር የታሪክ ምሁሩ ዶ/ር ብርሃኑ አበበ ይገልጻሉ። ስለሆነም ንጉሡ በሞቱ ጊዜ የተገጠሙት ግጥሞች እስካሁን ድረስ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ይታወቃሉ።
«መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ
የሴቱን አናውቅም አንድ ሰው ሞተ»
በወርሀ ሚያዝያ 1860 ዓ.ም. ታላቁ ንጉሠ ነገሥት አፄ ቴዎድሮስ የተሰዉበት ዕለት «ሽጉጣቸውን አጉርሰው ራሳቸው የጎረሱበት ክስተት፡፡ የዘመኑን ትንሣኤ በዓል አክብረው በማግሥቱ የማዕዶት ዕለት ያለፉበት፡፡»
ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በእሮጌ ጦርነት ተሸንፈው የጄኔራል ናፒየር ጦር የመቅደላን ምሽግ ሲደበድብ ሕልፈታቸውን በመረዳት ካሠፈሩት መልዕክት መካከል፣ ‹‹… ያረመኔ አገር ነውና ያገሬ ሰው ገብር፣ ሥራት ግባ ብዬ ብለው እንቢ ብሎኝ ተጣላኝ፡፡ እናንተ ግን በሥራት በተገዛ ሰው አቸነፋችሁኝ…›› ማለታቸው ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡
«ጥይት ስለ ውሃ ማነው የሚጠጣ?
ቴዎድሮስ ብቻ ነው ጥሙን የሚወጣ፤»
የመጨረሻው የመቅደላ ግብግብ ሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም. ወደ ማቆሙ ተቃረበ፡፡ በጄኔራል ናፒር የሚመራው የእንግሊዝ ጦር ሠራዊት ቴዎድሮስን አድኖ ለመያዝ በየአቅጣጫው መሯሯጥ ጀመረ፡፡ ግርማ ኪዳኔ እንዳተቱት የቴዎድሮስን ሁኔታ አስመልክቶ የኒውዮርክ ታይምስ ሪፖርተር እስታንሊ ሲናገር ሰኞ ከቀኑ አሥር ሰዓት አካባቢ እንግሊዝ በመቅደላ ላይ ካሰማራቻቸው ወታደሮች መካከል ሁለት የአየርላንድ ወታደሮች የተኩስ ድምፅ ወደሰሙበት አቅጣጫ እየተክለፈለፉ እንደደረሱ አንድ ያልታወቀ ኢትዮጵያዊ ከመሬት ላይ ተዘርሮ ለመሞት በማጣጣር ላይ እንዳለ ያገኙታል፡፡
እነሱ ወዲያው አላወቁትም እንጂ ግለሰቡ ተራ አይደለም፡፡ ንጉሠ ነገሥት ቴዎድሮስ ዳግማዊ ናቸው፡፡ አፄ ቴዎድሮስን በሕይወት ሳሉ የሚያውቃቸው ራሳም መጥቶ እሳቸው ስለመሆናቸው እንዲያረጋግጥ ተደረገ፡፡ እየሮጠ መጥቶ ሲያያቸው አፄው ሆነው አገኛቸው፡፡ በእርሱና በንጉሡ መካከል አልፎ አልፎ አለመግባባት ቢፈጠርም ቆራጥ መሪ መሆናቸውን ጠንቅቆ ያውቅ ስለነበር ሁኔታውን እንደተመለከተ መንፈሱ ተረበሸ፡፡ በተለይም ከመሞታቸው በፊት የተናገሩት ቃል ትዝ አለው፡፡
ይኸውም «አንድ ቀን እኔ ስሞት ታየኝ ይሆናል፤ ከዚያም በሬሳዬ ላይ ቆመህ ይህን ደካማ ሰው በመቅበር ፋንታ ከሜዳው ላይ እንደ ወደቀ በስብሶ መቅረት አለበት በማለት ትረግመኝ ይሆናል» ብለው የተናገሩት ትዝ እያለው በሐዘን ተውጦ ይታይ ነበር፡፡ በወቅቱ የዓይን ምስክር በመሆን ያረጋገጠው አሜሪካዊ ሪፖርተር ሕይወታቸው ስላለፈችው የመቅደላ ጀግና ሲያብራራ «የተለየ ክብር ሳይደረግላቸው፣ ጠባቂ ዘብ በአጠገባቸው ሳይቆም፣ በቃሬዛ ላይ ለብዙ ሰዓት ያህል ከመሬት ተዘርረው ፀጉራቸው ተሸልቶ፣ ልብሳቸው ተገፍፎና ተቀዳዶ ከፊል እርቃነ ሥጋቸው በማየቴ የቀድሞው ቴዎድሮስ መሆናቸው አጠራጠረኝ» ይልና፣ «ራቅ ብዬ ስመለከት ብዙ መኰንኖች በደም የተበከለውን የቴዎድሮስን ሸሚዝ ለእኔ ይገባኛል በማለት ሲጓተቱና ሲጣሉ ተመልክቼ ነበር» ብሏል፡፡
እንደ ግርማ ኪዳኔ ማብራሪያ ቴዎድሮስ ሲነግሱ ለብሰውት የነበረው የክብር ልብስና በአንፃሩ ደግሞ ከሞቱ በኋላ የተወሰደባቸው በደም የተበከለችው ሸሚዝ በእንግሊዝ ሰሜናዊ ክፍል ባንክ ፊልድ ሙዚየም ሀሊፋክስ ዩክሼር ተብሎ በሚጠራው መዘክር፣ የተሸለተው ጸጉራቸው ግን በለንደን ከተማ ናሽናል ዎር ሙዚየም ውስጥ እንግሊዞች አስቀምጠውታል፡፡
የቴዎድሮስ ራሳቸውን ማጥፋት በጊዜው ለነበሩና አሁን ድረስ ላሉ ሠዓሊያን ሥዕሎች ጥሩ ርዕስ ሆነ። የንጉሡ ሞት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓ ሳይቀር ለቴዎድሮስ ከፍተኛ ሐዘንና አድናቆትን አተረፈ። «ማርከው ሊወስዷቸው አቅደው የመጡትን እንግሊዞች ግብ በማኮላሸት »ቴዎድሮስም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ቦታን አገኙ። ብዙ የልቦለድ ጸሐፊያን እና ቴአትር አዘጋጆች ለቴዎድሮስ እስካሁን ድረስ ይደርሳሉ ይጽፋሉ፣ ምሁራንም ቢሆን አሁን ድረስ ልጆቻቸውን በንጉሡ ስም ይሰይማሉ። የኢትዮጵያ ዘፋኞች፣ ዘመናዊ ዘፋኞች ሳይቀሩ የንጉሡን ስም ይጠቅሳሉ። እንደ ዶ/ር ብርሃኑ አበበ አስተሳስብ ‹‹የምርኮን ውርደት አሻፈረኝ በማለት በመሞታቸው›› በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ግምትን ንጉሡ እንዲያገኙ አድርጓል።
ሌላው የመቅደላው ጦርነት የሚታወስበት ግጥም ደግሞ የሚከተለው ነው፡፡
‹‹ገደልን እንዳይሉ ሞተው አገኟቸው፣
ማረክን እንዳይሉ ሰው የለ ከጃቸው፣
ምናሉ እንግሊዞች ሲገቡ አገራቸው፣
ለወሬ አይመቹም ተንኮለኛ ናቸው፡፡›