አዲስ አበባ ውስጥ 78 የመንግሥትና የግል አሽከርካሪ ማሠልጠኛ ተቋማት ይገኛሉ፡፡ ሕጋዊ ፈቃድ አግኝተው ከሚንቀሳቀሱት ተቋማት መካከል 62ቱ በአዲስ አበባ አሽከርካሪዎች ማሠልጠኛ ተቋማት ማኅበር ታቅፈዋል፡፡ የቀሩትም በአባልነት ለመታቀፍ ጥያቄ በማቅረብና በሒደት ላይ ይገኛሉ፡፡ የማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ ንጉሤን በተቋማቱ እንቅስቃሴ ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የማሠልጠኛ ተቋማትን አደረጃጀት ቢያብራሩልን፡፡
አቶ ተስፋዬ፡- አንድ የተሽከርካሪ ማሠልጠኛ ተቋም እንደ ተቋቋመ የሚደራጀው ቀደም ሲል በወጣው አዋጅ 600/2000 እና አሁን ደግሞ ተሻሽሎ በወጣውና በመተግበር ላይ ያለውን አዋጅ 1074/2010ን መሠረት ባደረገ መልኩ፣ የወጣውን መመርያና የቢሮ አደረጃጀትን አስመልክቶ የተዘጋጀውን መሥፈርት ካሟላ በኋላ ነው፡፡ በመሥፈርቱ መሠረት ተቋሙ ራሱን የቻለ የእንግዳ መቀበያ፣ የመምህራን ማረፊያ፣ የፈተና መለማመጃ ኮምፒዩተር፣ የመማሪያና የመፀዳጃ ክፍሎች፣ እንዲሁም የሥራ አስኪያጅ ወይም ዳይሬክተር ጽሕፈት ቤት፣ ለመማር ማስተማሩ ዕገዛ የሚያደርግ የተግባር ቤተ ሙከራ (ወርክሾፕ) ሊኖሩት ይገባል፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን ለሥልጠና የሚያስፈልጉ ግብዓቶች፣ የትራፊክ ላይቶች፣ በፊልም ለማስተማር የሚረዱ ፕሮጀክተሮች፣ ቴሌቪዥንና የመገናኛ መሣሪያዎች መሟላት ከሚገባቸው መሣሪያዎች ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡ ተቋሙ ሥልጠና የሚሰጠውም የመንጃ ፈቃድ በጠየቀበት ካታጎሪ (መደብ) መሠረት ነው፡፡ ለምሳሌ የሞተር ሳይክል ሥልጠና ለመስጠት የፈለገ ተቋም በመመርያው መሠረት የተፈቀደለት ሲሲና ዓመተ ምሕረቱን ያሟላ የማሠልጠኛ ሞተር ሳይክል ሊኖረው ይገባል፡፡ ሥልጠናውንም የሚሰጠው በተቋሙ ስም በተመዘገበ ተሽከርካሪ እንጂ ተከራይቶ ማሠልጠን የለበትም፡፡
ሪፖርተር፡- ተቋማቱ ለሥልጠና የሚመርጧቸው መደቦች ምንድናቸው?
አቶ ተስፋዬ፡- ሞተር ሳይክል፣ አውቶሞቢል፣ ቀደም ሲል በነበረው አዋጅ ታክሲ፣ በአሁኑ አዋጅ ግን ታክሲ በሕዝብ አንድ ውስጥ ተካቷል፣ ሕዝብ ሁለት፣ ሕዝብ ሦስት፣ ጭነት አንድ ሁለትና ሦስት፣ ፈሳሽ አንድና ሁለት ተብለው በተከፋፈሉ መደቦች ነው፡፡ ከእነዚህም ምድቦች መካከል ተቋሙ በመረጠው መደብ ተሽከርካሪ ይገዛል፡፡ የቴክኒክ ምርመራ ያደርግና መቆጣጠሪያ ፔዳል ያስገጥማል፡፡ ተሽከርካሪ ለሥልጠና ብቁ መሆኑን ይፈትሻል፡፡ እነዚህን ካሟላ ቀጣዩ የሚመጣው የፈቃድ ጥያቄ ነው፡፡ ፈቃድ ሰጪው አካል ደግሞ ግምገማ ያካሂድና ብቁ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ የብቃት ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡
ሪፖርተር፡- ፈቃድ ሰጪዎቹ አካላት እነማን ናቸው?
አቶ ተስፋዬ፡- ዘጠኙ የክልል ከተሞች ከፌዴራል ትራንስፖርትና ባለሥልጣን በተሰጣቸው ውክልና መሠረት ፈቃድ ይሰጣሉ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ኦሮሚያ ክልል ግን የየራሳቸው ፈቃድ ይሰጣሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ሁሉም ማሠልጠኛ ተቋማት ከፍ ብሎ በተጠቀሰው መልኩ የተደራጁ ናቸው ማለት ይቻላል?
አቶ ተስፋዬ፡- አዲስ አበባ ላይ ያሉት ተቋማት ሁሉም ማለት ይቻላል ከፍ ብሎ በተጠቀሰው ቁመና ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ለዚህም ማኅበሩና ፈቃድ ሰጪው አካል በየሦስት ወሩ ክትትል ይደረጋሉ፡፡
ሪፖርተር፡- በተቋማቱ ዘንድ እንደ ችግር የሚታየው ምንድነው?
አቶ ተስፋዬ፡- ችግሮቹ በርካታ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ብቃት ያለው አሽከርካሪ ለማፍራት ብቃት ያለው አሠልጣኝ፣ ተሽከርካሪን ጨምሮ የሥልጠና ግብዓቶችና የሥልጠና ቦታ አለመኖር ዋነኞቹ ችግሮች ናቸው፡፡ በተለይ ከአሠልጣኝ ብቃት አኳያ ሲታይ ክፍተት ይስተዋላል፡፡ አሠልጣኞችን አሠልጥኖ ለተቋማቱ የሚሰጠው ፈቃድ ሰጪ አካል የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ አንድ አሠልጣኝ የሚመለመልበት መሥፈርት ውስንነት እንዳለበት ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ባለሥልጣኑ ለአሠልጣኞች የሚጠቀምበት መሥፈርት አንድ ሰው በአውቶሞቲቭ ዲፕሎማ ወይም አሥር ሲደመር ሦስት ሊኖረው ይገባል፡፡ ቀጥሎ የሚመጣው ለደረጃው የሚመጥን ብቃት ወይም ለማሠልጠን ፈቃድ የሚወስድበትን ደረጃ የሚያሟላ መንጃ ፈቃድ ሊኖረው ይገባል፡፡ ከዚያም ቃሊቲ ትራፊክ ኮምፕሌክስ ውስጥ ተቀባይነት የሚያገኝበትን ሥልጠና ይወሰዳል፡፡ ይህንን የአፕሮቫል ሥልጠና ወይም የአሠልጣኞች ሥልጠና ከወሰደ በኋላ ተመርቆ አስተማሪ ሊሆን ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- በዚህ ዓይነቱ ሒደት ምን ክፍተት ነው ታይቷል የሚባለው?
አቶ ተስፋዬ፡- የሰውየው የማስተማር ወይም የማሽከርከር ልምዱ እንዲሁም ባህርይውና ሰብዕናው ትልቅ ክፍተት ነው፡፡ መንጃ ፈቃድና ዲፕሎማው ነው የታየው እንጂ ከዚህ መለስ ለሌላው አሽከርካሪ ወይም ለሠልጣኞቹ ምሳሌ ወይም ሮል ሞዴል መሆኑ፣ ግብረ ገብነት ያለው፣ ሞገደኛና ክልፍልፍ አለመሆኑና ኃላፊነት የሚሸከም መሆኑ አይታወቅም፡፡ ስለዚህ መንጃ ፈቃድ ያለው ማንኛውም ሰው ሁሉ ያለችግር ወደዚህ ሥራ ይገባል፡፡ ይህም ሆኖ ግን በቂ አሠልጣኞች ሥራው ላይ የሉም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ሌላ ችግር የተሽከርካሪ ማሠልጠኛ ቦታ ነው፡፡ አንድን አሽከርካሪ ብቁ ለማድረግ ብቃት ባለው ቦታ ላይ ማሠልጠን ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር የአዲስ አበባንም ሆነ የክልሎች ተሞክሮ ስንመለከት በመንግሥት በኩል ለጉዳዩ ትኩረት የተሰጠው አይመስልም፡፡ ለዚህ ማረጋገጫው በሰሚትና ዓለም ባንክ አካባቢ የሚያስተምሩት የባቡር አካፋይ መንገዶች ላይ ነው፡፡ የአካባቢ ማኅበረሰብ በማንኛውም ሰዓት ቅሬታ ካነሳ ለምሳሌ ለልጆቻችን አደጋ አለው እዚህ አካባቢ ለማጅ መኖሩ፣ ስለዚህ ከአካባቢያችን ይነሱልን ብሎ ደብዳቤ ከጻፈ ፖሊስ በአንድ ደብዳቤ ነው ከአካባቢው ተነሱ ብሎ ተቋማትን የሚያባርረው፡፡ አብዛኛው የማሠልኛ ተቋማት የሚያሠለጥኑት ከገበያ ላይ ያሉትን ተሽከርካሪዎች ገዝተው ነው፡፡ ተሽከርካሪዎቹን ሲገዙ ደግሞ የቴክኒክ ብቃታቸውንና ሞዴላቸው ዘመናዊ የሆኑትን ነው፡፡ እንደ እነዚህ ዓይነት አዳዲስ ተሽከርካሪዎችን ገዝቶ ለማስገባት የአቅም ውስንነት ያጋጥማቸዋል፡፡ መንግሥትም ምንም ዓይነት የማበረታቻና የብድር አማራጮችን፣ ከቀረጥ ነፃ ለሥልጠና ግብዓት የሆኑ ሴሙሌተር፣ (የማስተማሪያ ምሥል ተሽከርካሪ)፣ የማስተማሪያ መረጃና ድጎማ አይደርግም፡፡ ይህ እንዲሆን ላለፉት አሥር ዓመታት በየመድረኩ ስናነሳ፣ ስንጠይቅና ለሚመለከተው አካል ስናቀርብ ብንቆይም ምንም ዓይነት ግብረ መልስ አልተገኘም፡፡ ይህም በሥልጠናው ላይ የጥራት ጉድለት ወይም ተፅዕኖ ያመጣል፡፡ ሠልጣኙ የሚማርበት ተሽከርካሪና ከተመረቀ በኋላ በሚነዳው ተሽከርካሪ መካከል ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ክፍተት አለ፡፡
ሪፖርተር፡- አሠልጣኞችን አሠልጥኖ ለተቋማቱ የሚያስተላልፈው የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ነው?
አቶ ተስፋዬ፡- አዎ!
ሪፖርተር፡- ተቋሞቹ ገጥሟቸዋል ብለው በዝርዝር ያቀረቡዋቸውን ችግሮች መፍትሔ እንዲፈለግላቸው ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል ለማሳወቅ ተደርጓል ያሉትን ጥረት ዘርዘር አድርገው ቢያብራሩልን?
አቶ ተስፋዬ፡- የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን በየዓመቱ ዕቅዱን በሚያዘጋጅበት ጊዜ አገር አቀፍ የምክክር መድረክ ያዘገጃል፡፡ የተጠቀሱትን ችግሮች የያዙ ጥያቄዎችን ማኅበሩ ከማቅረቡም በላይ ክልሎቹም ጭምር በተደጋጋሚ እነዚህን ጥያቄዎች ያነሳሉ፡፡ በተለይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትራንስፖርት ቋሚ ኮሚቴ በጠራው አገር አቀፍ ምክር ላይ ጥያቄዎቻችንን ነጥብ በነጥብ አስመዝግበናል፡፡ ትራንስፖርት ሚኒስቴር በሚያዘገጃቸው የውይይት መድረኮች ላይም በተደጋጋሚ ጊዜ አሳውቀናል፡፡ ይህም ሆኖ እምብዛም ያመጣው ውጤት የለም፡፡ ከዚህ አንፃር በእኛ ዕይታ እንደ አገር ለማሽከርከር የሰጠን ግምት በጣም ዝቅተኛ ከመሆን ጋር ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ የተለያዩ ነገሮችን ማነፃፀር ይቻላል፡፡ አንድ የሕክምና ባለሙያ የሰው ሕይወት ነው የሚያድነው፡፡ አንድ አሽከርካሪ ደግሞ የሰው ሕይወት ይዞ ነው ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሰው፡፡ አንድ የሕክምና ተቋም ክሊኒክ ሲከፍት፣ ሆስፒታል ሲያቋቁም በጣም ብዙ ነገር ከቀረጥ ነፃ ያስገባል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ለግንባታ የሚሆን ቦታ ይመቻችለታል፡፡ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችም ይዘጋጁለታል፡፡ ከዚህም ሌላ ታክስ ነፃ ናቸው፡፡ ወደ አሽከርካሪ ማሠልጠኛ ተቋም ስንመጣ ግን ምንም ዓይነት የማበረታቻ ድጋፍ አይደረግለትም፡፡ ዘርፉ ታክስ እንዲከፍል ይደረጋል፡፡ ከእያንዳንዱ ሥልጠና 15 በመቶ ታክስ አንቆርጣለን፡፡ ይህ ደግሞ ሠልጣኞች ላይ የክፍያ ጫና ፈጥሯል፡፡ እንደ ትምህርት ወይም እንደ ሙያ ዘርፉን ያለማየት ችግር አለ፡፡ ምንም ዓይነት ዕገዛና ድጋፍ ሳይደረግለት ከዘርፉ ግን ውጤት መጠበቅ፣ ምንም ዓይነት ሥራ ሳንሠራ በምኞት ብቻ ከአደጋ የፀዳች አገር ለማየት መሞከር ትክክል አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- ለተጠቀሱት ጉዳዮች ትኩረት አለመስጠቱን እንደማሳያ የሚያቀርቡት ነገር አለ?
አቶ ተስፋዬ፡- አሁን የወጣው 1074/2010 የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ አዋጅ ለጉዳዩ የበለጠ ትኩረት አለመስጠቱን ማሳያ ነው፡፡ አዋጁም የአውቶሞቢል ሥልጠና የሚፈልጉ አሽከርሪዎች በቅርብ ቤተሰቡ፣ ወይም የሥጋ ወይም የጋብቻ ዝምድና ባለው ሰው ተለማምደው ፈተና ተፈትነው መንጃ ፈቃድ ማግኘት ይችላሉ ይላል፡፡ ይህም የሚያሳየው ነገር ቢኖር ሙያውን የሚያራክስ፣ አደጋን የሚያባብስ፣ ለአገርና ለዜጎች የማይጠቅም አዋጅ እስከ ማውጣት ድረስ መሄዱን ነው፡፡ ይህ አዋጅ ፓርላማ ውስጥ ከ90 በላይ የድምፅ ተዓቅቦና ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ አዋጁ የካቲት 2010 ዓ.ም. ላይ ፀድቆ ቢወጣም የማስፈጸሚያ መመርያን ማውጣት በጣም አስቸጋሪ ስለሆነባቸው እስካሁን መመርያ አልወጣለትም፡፡
ሪፖርተር፡- አዋጁ ከመፅደቁና ከመውጣቱ በፊት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አልተካሄደበትም?
አቶ ተስፋዬ፡- ውይይት ተደርጓል፡፡ እዚህ ላይ ያለው ትልቁ ተግዳሮትና ችግር የሚሰጠው ግብዓትና ሐሳቦችን አለመቀበል ነው፡፡ በተረፈ በቤተሰብ ይሠልጥን የተባለው ቤተሰቡ መኪና ሲኖረው ነው፡፡ መኪና የሌለው ብዙ ኅብረተሰብ አለ፡፡ የደሃ ልጆች ማሠልጠኛ ተቋማት ገብቶ፣ ሀብታም ልጅ ግን በቤተሰቡ መኪና ይማር ማለት ነው፡፡ ይህም አደጋን ከማባባሱ ባሻገር በሀብታምና በደሃ መካከል ልዩነትንና ማኅበራዊ ቀውስን ያስከትላል፡፡ ይህንም አቋማችንን ፓርላማው ጭምር በደብዳቤ አሳውቀናል፡፡
ሪፖርተር፡- በየማሠልጠኛ ተቋማቱ እየሠለጠኑ የሚወጡት ሰዎች በሚገባ ሠልጥነዋል፣ ጥሩ ዕውቀትና ብቃት ጨብጠዋል ማለት ይቻላል?
አቶ ተስፋዬ፡- እንዲህ ለማለት ያስቸግራል፣ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም አንደኛ ከአዋጁ ጀምሮ የግንዛቤ ክፍተት አለ፡፡ ሠልጣኙ ላይ የግንዛቤ፣ ሕጉን ተቀብለው በሚያስፈጽሙ የማሠልጠኛ ተቋማት ዘንድ የአረዳድና መረጃ አሰጣጥ ችግሮች አሉ፡፡ ሠልጣኙ የሚመለከተውን መንጃ ፈቃድ መማር ሲገባው የማይመለከተውን በግንዛቤ ዕጦት እየተማረ ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ ሠልጣኝ የንድፈ ሐሳብ ትምህርት ሲሰጠው በሥርዓተ ትምህርቱ መሠረት የሚወስደው ካሪኩለም አለ፡፡ ይህንን ካጠናቀቀ በኋላ የተግባር ልምምድ ያደርጋል፡፡ ከዚያም ወደ ገበያ ይገባል፡፡ ከአሽከርካሪ ሙያ ጋር ተያይዞ መታሰብ ያለበት የተመረቀ ወይም መንጃ ፈቃድ የያዘ አሽከርካሪ ሁሉ በማግሥቱ አሽከርካሪ መባሉ ነው፡፡ ወይም አሽከርካሪ ከተመረቀበት ዕለት ጀምሮ ረዳት ሾፌር የሚል ደረጃ ሳያገኝ ዋና ሾፌር ነው የሚባለው፡፡ በዚህም የተነሳ መንጃ ፈቃዱን ይዞ መኪና ይነዳል፣ አደጋ ያደርሳል፡፡ መንጃ ፈቃዱን ከያዘ በኋላ የከተማ ውስጥ ልምምድ ላይ ዋና አሽከርካሪ (ሲኒየር ድራይቨር) አጠገቡ ተቀምጦ የማብቃት ሥራ መከናወን አለበት፡፡ በዚህ ላይ ትኩረት ያደረገ ሕግ የለም፡፡ በሠለጠነው ዓለም ግን አንድ ሰው የመንጃ ፈቃድ ከተሰጠው በኋላ ለአንድ ዓመት ያህል አጠገቡ ሲኒየር ድራይቨር ወይም ዋና አሽከርካሪ ይቀመጣል፡፡
ሪፖርተር፡- ከማሠልጠኛ ተቋማት ሠልጥኖ መውጣቱ ወይም መመረቁ ብቻ አደጋን ከማድረስ ያድናል?
አቶ ተስፋዬ፡- የትራፊክ አደጋ በአንድ ጀምበር ወይም በመፈክር የሚቀየር አይደለም፡፡ አደጋ አለ፡፡ ነገር ግን ልንከላከል ምንችለው ወይም በአሽከርካሪ ስህተትና ቸልተኛነት የሚመጣውን አደጋ ግን ማቆም ይጠበቅብናል፡፡ ለአደጋ መንስዔ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ እነሱም ከሕግና ከፖሊሲ አወጣጥ ጀምሮ የማሠልጠኛ ተቋማትን ከመደገፍ አንፃር ሊሠሩ የሚገባቸው ናቸው፡፡ አደጋን ለመከላከል ዋና ዋና የተባሉ ስድስት ኢ-ዎች አሉ፡፡ የመጀመርያው ኢጁኬሽን (ትምህርት) እና ሥልጠና ሲሆን፣ ይኼም በስፋት ሊስፋፋ ይገባል፡፡ ሁለተኛው ኢንፎርስመንት (ቁጥጥር) ሦስተኛው ኢንጂነሪንግ ነው፡፡ ይህም ማለት ሮድ ኢንጂነሪንግ ላይ የእግረኛ መንገዶቹ፣ መሻገሪያ መሳለጫዎቹ በጣም ብዙ ችግሮች አሉባቸው፡፡ አራተኛው ኢንከሬጅመንት (ማበረታቻ) ሲሆን፣ 30 እና 40 ዓመት ነድተው ምንም ዓይነት አደጋ ያላደረሱ ሊበረታቱና ዕወቅና ሊቸራቸው ይገባል፡፡ አምስተኛው ኢመርጀንሲ ኤንድ ሜዲካል ሰርቪስ ነው፡፡ አብዛኛው ሰው ወይም 80 ከመቶው ያህሉ ሰው አደጋ ከደረሰበት በኋላ የሚሞተው የመጀመርያ ሕክምና ዕርዳታ በማጣት ነው፡፡ ስለዚህ አሽከርካሪዎች የመንጃ ፈቃድ ከመቀበላቸው በመጀመርያ ሕክምና ዕርዳታ አሰጣጥ እንዲሠለጥኑና ከዚህም በኋላ የመንጃ ፈቃድ ቢሰጣቸው ችግሩን በመጠኑ እንኳን ለመቀነስ ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በተሽከርካሪ አደጋ ሳቢያ ብዙ ጊዜ ለሞት የሚዳረጉት ከሾፌሮች ይልቅ ተሳፋሪዎች ናቸው፡፡ በዚህ ጊዜ በተጠቀሰው ዘርፍ ሾፌሩ ከሠለጠነ ወዲያውኑ የመጀመርያ ሕክምና ዕርዳታ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ስድስተኛው ኢንጌጅመንት (ቅንጅታዊ) አሠራር ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሁሉ እንደፈለገው ነው ሕግ እያወጣ ያለው፣ ኦሮሚያ የራሱን፣ አዲስ አበባም የራሱን ሕግ ያወጣል፡፡ ቅንጅታዊ አካሄድ የለም፡፡ በዚህም የተነሳ አገር አቋራጭ አውቶብሶች ተቸግረዋል፡፡ ይህንን ችግር ሁሉ ፍተሾ አንድ አገራዊ የሆነ የኢትዮጵያ መንጃ ፈቃድ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም መንጃ ፈቃዱ በአንድ የመረጃ ቋትና በአንድ ማዕከላዊ ቢሮ መመራት ይኖርበታል፡፡
ሪፖርተር፡- ተቋማት ለስንት ጊዜ ነው የሚያሠለጥኑት?
አቶ ተስፋዬ፡- ዝቅተኛው የሞተር ሳይክል ሲሆን ሥልጠናው አንድ ወር ነው፡፡ የአውቶሞቢል ሥልጠና ከ35 እስከ 40 ቀን ይወሰዳል፡፡ ሕዝብ ወይም ደረቅ አንድ ሁለት ወር ይወስዳል፡፡ ከፍተኛው የሦስት ወር ሥልጠና ነው፡፡ በሌላ ዘርፍ ሲታይ ደግሞ መከላከያ ሚኒስቴርና ፖሊስ ኮሚሽን ከስድስት ወራት በላይ ያሠለጥናሉ፡፡ ጨለማ፣ ብርሃን፣ ዳገትና ቁልቁለት እያደረጉ በብቃት አሠልጥነው ያስመርቃሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ጥራት ያለው ፈተና ካለ ጥራት ያለው ሥልጠና ይኖራል የሚል አመለካከት አለ፡፡ የማሠልጠኛ ተቋማት በዚህ አመለካከት ላይ ያላቸውን አስተያየት እንዴት ይገልጹታል? ምክንያቱም ለትራፊክ አደጋ ከመንስዔዎቹ አንዱ የተቋማት አሠለጣጠንና ፈተና አሰጣጥ ዘዴ ላይ ጥራት መጓደል ነው ይባላል?
አቶ ተስፋዬ፡- ማሠልጠኛ ተቋማት የተሰጣቸው ሥልጣን ማሠልጠን ብቻ ነው፡፡ መፈተን አይችሉም፡፡ የሚፈትነው የመንግሥት አካል ነው፡፡ ፈትኖ ብቁ ነው የሚል መረጃ የሚሰጠው ይኼው አካል ነው፡፡ ስለዚህ ማሠልጠኛ ተቋሙ አንድን አሽከርካሪ በብቃት ካላሠለጠነ ፈታኙ አካል ለምን ፈተናው ላይ አይጥለውም? ለምን ያሳልፈዋል? በተረፈ አሳልፎ መንጃ ፈቃድ ከሰጠ በኋላ ተቋሙን የመውቀስ መብት የለውም፡፡ አራት ዓይነት አሽከርካሪዎች አሉ፡፡ አንደኛው ተምሮና ሠልጥኖ በአግባቡ መንጃ ፈቃድ ያወጣ፣ ሁለተኛው ቤቱ ድረስ መንጃ ፈቃድ የመጣለት፣ ሦስተኛ ሕገወጥ መንጃ ፈቃድ የያዘ፣ አራተኛው ያለ መንጃ ፈቃድ የሚያሽከረክር ነው፡፡ በእነዚህ ሁሉ ተቋማት ያለሥራቸው ሲወቀሱ ይስተዋላል፡፡ የሚፈትነውና መንጃ ፈቃድ የሚሰጠው የመንግሥት አካል መሆኑ የታወቀ ነው፡፡