Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርዓብይ አስቸገሩን!

ዓብይ አስቸገሩን!

ቀን:

በሰሎሞን ዳኞ

አቤት ጊዜው እንዴት ይከንፋል? ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከነገሡ አንድ ዓመት ሊሞላቸው ሦስት ወራት ብቻ ቀሯቸው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ቅቤ ማጠጣት ከጀመሩ ዘጠኝ ወራት ሞሉዋቸው ማለት ነው፡፡ ሕዝባችን 44 ዓመት ሙሉ በመብራት ፈልጎ ያላገኘውን ቅቤ ዘጠኝ ወራት ሙሉ አንቆረቆረው፡፡ የወደፊቱን አንዱ ጌታ ያውቅለታል፡፡

ጃንሆይ ራሳቸውን ሥዩመ እግዚአብሔርበማለታቸው ሲሳለቁ የነበሩት ዕድሜ ጠገብ ሸበቶ ፕሮፌሰሮቻችን ሳይቀሩ ከእግዚአብሔር የተላከነውሲሉ የመሰከሩላቸው ዶ/ር ዓብይ እኔን ግን አስቸግረውኛል፡፡ ትዝታ እየቀሰቀሱብኝ፣ የሞተውን እያስነሱብኝ፣ ነገረ ሥራቸው ጃንሆይን እየመሰለኝ ተቸግሬአለሁ፡፡

ለጊዜው መልከ መልካምነታቸውን፣ ሸንቃጣነታቸውንና ቁመታቸውን ልተወው፡፡ ትኩረቴ ድርጊታቸው ላይ ነው፡፡ ራስታዎች እንዳይሰሙኝ እንጂ ዓብይ የሚያደርጉትን ስመለከት ጃንሆይ በእሳቸው ተመስለው ዳግም ወደ ዓለም መጥተው ይሆን? እላለሁ፡፡ ዓብይ የተወለዱት ጃንሆይ በተገደሉ በዓመቱ መሆኑ ደግሞ ይበልጥ እንድጠራጠር ያደርገኛል፡፡ ዓብይ ሞኛቸውን ይፈልጉ! ነቅተንባቸዋል! ለካ ስለዚህ ኖሯል ጃንሆይን ከአፋቸው የማይለዩአቸው፣ እንደ ሌሎቹ የማያንቋሽሿቸው፣ ቤተ መንግሥታቸውን የሕዝብ መናፈሻና ሙዚየም ሊያደርጉት ማሰባቸው!

ጃንሆይ ሞገስ ነበራቸው፡፡ ዶ/ር ዓብይም ግርማ ሞገስ የሞላባቸው ናቸው፡፡ ጃንሆይ ጉቦ አይበሉም ነበር፡፡ ዶ/ር ዓብይም ሌብነትን የሚፀየፉ ናቸው፡፡ ጃንሆይ በሽተኛ ጠያቂ ነበሩ፡፡ ዶ/ር ዓብይም ያልረገጡት ሆስፒታል የለም፡፡ ጃንሆይ ወታደራዊ ዩኒፎርም መልበስ ይወዱ ነበር፡፡ ዶ/ር ዓብይም ይለብሳሉ፡፡

ጃንሆይ ለቅሶ ይደርሱ ነበር፡፡ ያዘኑትንም ያፅናኑ ነበር፡፡ ዶ/ር ዓብይም ይህንኑ ያደርጋሉ፡፡ ጃንሆይ ተስፋ አይቆርጡም ነበር፡፡ ዶ/ር ዓብይም ያዝልቅላቸው እንጂ የሚበገሩ አይመስሉም፡፡ በጃንሆይ ጊዜ ኢትዮጵያ የባህር ኃይል ነበራት፡፡ ዶ/ር ዓብይም የባሕር ኃይል ለማቋቋም አቅደዋል፡፡ ጃንሆይ ይሰገድላቸው ነበር፡፡ ለዶ/ር ዓብይም አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በእንባ እየተነጠፉላቸው ነው፡፡ ጃንሆይ አርቲስቶችን ያቀርቡና ያበረታቱ ነበር፡፡ ዶ/ር ዓብይም ያልተወዳጁት አርቲስት ያለ አይመስልም፡፡ ጃንሆይ ለታራሚዎች ምሕረት ያደርጉ ነበር፡፡ ዶ/ር ዓብይም እስረኞችን በመፍታት የዓለምን ሪከርድ ሰብረዋል፡፡ ጃንሆይአገር የጋራ ነው ሃይማኖት የግል ነውየሚል አቋም ነበራቸው፡፡ ዶ/ር ዓብይም የሁሉንም ሰው እምነት ያከብራሉ፡፡

ጃንሆይ እግዚአብሔርን የሚያምኑና የሚፈሩ ነበሩ፡፡ የሃይማኖት አባቶችንም ያከብሩ ነበር፡፡ ዶ/ር ዓብይም እንዲሁ ናቸው፡፡ ጃንሆይ የተጣሉትን በማስታረቅ ይታወቁ ነበር፡፡ ዶ/ር ዓብይም ያልፈቱት ቋጠሮ የለም፡፡ በዚህም ትልቅ ዝናና ከበሬታ አግኝተዋል፡፡ የልጅ አዋቂተብለዋል፡፡

ጃንሆይ ፈረስ ይወዱ ነበር፡፡ ጠቅል የሚባል ፈረስ ነበራቸው፡፡ በፈረሰኛ ይታጀቡ ነበር፡፡ ዶ/ር ዓብይ ዕድሜና ጤና ይስጣቸውና በ44 ዓመታችን ፈረስ አሳዩን፡፡

ጃንሆይ የባለቤታቸውን የእቴጌ መነንን መልካምነት ከአብርሃም ሚስት ከሣራ ጋር አመሳስለዋል፡፡ ዶ/ር ዓብይም ሚስታቸውን ሲያሞካሹ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል፡፡

ጃንሆይ ድሆችን፣ አረጋውያንንና አካለ ስንኩላንን ይወዱና ይደግፉ ነበር፡፡ ዶ/ር ዓብይም የእኔ ቢጤዎችን ቤት እስከ መጠገን ደርሰዋል፡፡ መቄዶንያን ጎብኝተዋል፣ ድጋፍም አድርገዋል፡፡

አይጠቀሙበትም ነበር እንጂ ለጃንሆይ ዶክትሬት ዲግሪ ያልሰጠ ዩኒቨርሲቲ የለም፡፡ ዶ/ር ዓብይም ዶክተር የእሳቸው ዓብይ ደግሞ የአባታቸው ስም እየመሰለ አስቸገረ እንጂ ዶክተር ናቸው፡፡

ጃንሆይ የአገር መሪ ለመሆን የቻሉት በሥርዓቱ መኳንንትና መሣፍንት ተመርጠው ነው፡፡ ዶ/ር ዓብይም ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የበቁት የኢሕአዴግን መኳንንት አብላጫ ድምፅ አግኝተው ነው፡፡

ጃንሆይ ሕዝቡን እጅግ ይወዱ ነበር፡፡ ዶ/ር ዓብይም እንዲሁ ናቸው፡፡ ከግድያ ባመለጡ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ተጎጅዎችን መጎብኘታቸውና ማበረታታቸው የፍቅራቸውን ትልቅነት የሚያሳይ ነው፡፡

ጃንሆይ ወንዞችን ለመገደብና ጥቅም ላይ ለማዋል ትልቅ እንቅስቃሴ ጀምረው ነበር፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ቦታ የተጠናው በእሳቸው ጊዜ ነው፡፡ ዶ/ር ዓብይም የመስኖ እርሻን ለማስፋፋት ቃል ገብተዋል፡፡

ጃንሆይ ሕዝቡን ሲሳደቡ ተሰምተው አይታወቁም፡፡ ዶ/ር ዓብይም በአመለ ሸጋነታቸው የተመሠገኑ ናቸው፡፡ ድንገት እንደ መንጌ ታክቷቸውወርቅ ሲያነጥፉለት ፋንድያ ነው የሚል ሕዝብብለው እንደማይወርፉን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

በአምስቱ ዘመን ጊዜ ቤተክህነት ጃንሆይን ባትገዝታቸው ኖሮ ጣሊያንን ማይጨው ላይ እስከ መጨረሻው ተዋግተው ለመሰዋት ቆርጠው ነበር ይባላል፡፡ ዶ/ር ዓብይም ለዚህ ድንቅ ሕዝብ እያገለገሉ ቢሰው ክብራቸው እንደሆነ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

ጃንሆይ ወደ አንድ አካባቢ ለጉብኝት ሲሄዱ ምድርና ሰማይ በደስታ ይዘሉ ነበር፡፡ ፈረንጆች ሳይቀሩ በአጥር ላይ እየተንጠለጠሉ በአግራሞት ይመለከቷቸው ነበር፡፡ ዶ/ር ዓብይም በሚሄዱበት ቦታ ሁሉ በደስታ ሊቀበላቸው የሚወጣውን ሕዝብ ብዛት በቃላት መግለጽ ይከብዳል፡፡

ጃንሆይ በሕዝብ መካከል በግልጽ ይመላለሱ ነበር፡፡ ዶ/ር ዓብይም ከሰኔ 16ቱ የመስቀል አደባባይ የቦምብ ፍንዳታ ወዲህ እነዚያ ምቀኛ ሴኩሪቲ ምናምን የሚባሉት ከለከሏቸው አሉ እንጂ ተውኝ፣ ልቀቁኝ፣ እሄዳለሁ እያሉ ያስቸግሩ ነበር ይባላል፡፡ ራሳቸው እየሾፈሩ እንግዳ ማስጎብኘትም ጀምረው ነበር፡፡

ጃንሆይ ኃይልዬ፣ ኃይሌ፣ አባ ጠቅል፣ ጠቅልዬ፣ ድል አድራጊው ንጉሣችን፣ አባ ጠቅል ኃይሌ፣ መኩሪያችን . . . ተብለው ተቆለማምጠዋል፡፡ ዶ/ር ዓብይም ዓብያችን፣ ዓብይዬ፣ የእኛ ንጉሥ፣ የእኛ ጌታ፣ ደጉ ንጉሣችን፣ የእኛ መልዓክ፣ የእኛ ማር፣ የእኛ ፍቅር፣ የእኛ ወለላ፣ ነቢያችን፣ ሳሳንልህ፣ የእኛ ማንዴላ፣ ከሰማይ የወረደ ፀጋ፣ ከእግዚአብሔር የተላከልን ስጦታ . . . ምን ያልተባሉት አለ?

ጃንሆይ አንባቢም ደራሲም ነበሩ፡፡ሕይወቴና የኢትዮጵያ ዕርምጃየሚባለውን መጽሐፍ ትተውልን አልፈዋል፡፡ ዶ/ር ዓብይም ፖለቲካውን፣ ኮምፒዩተሩን፣ ወታደራዊ ሳይንሱን፣ ሕክምናውን፣ ግብርናውን፣ ሥነ ልቦናውን፣ ኢኮኖሚክሱን፣ ማኔጅሜንቱን፣ ታሪኩን፣ ፍልስፍናውን፣ ኬሚስትሪውን፣ ሥነ ጽሑፉን፣ መጽሐፍ ቅዱሱን፣ ቅዱስ ቁርዓኑን . . . ይተረትሩታል፡፡ በብዕር ስም መጽሐፍ ጽፈዋልም ይባላል፡፡

ጃንሆይ የብሔር ጉዳይ ምንም ስሜት አይሰጣቸውም ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ሌላ አያውቁም ነበር (የአቶ ቡልቻ ደመቅሳን ቃል ነው የወሰድኩት)፡፡ ዶ/ር ዓብይምኢትዮጵያዊነት በደማችን የተዋሀደ፣ ከአጥንታችን ጋር የፀና፣ በልባችን የታተመ ማኅተምነው ብለዋል፡፡ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያያሉትም እሳቸው ናቸው፡፡ እስካሁን የዶ/ር ዓብይን ስም ከዘር ጋር በተያያዘ በክፉ የሚያነሳሰው ተሰምቶ አይታወቅም፡፡

ጃንሆይ ተማሪዎችን ይወዱና ያቀርቡ ነበር፡፡ ትምህርት ቤቶችን ይጎበኙ ነበር፡፡ ወደ አሜሪካና እንግሊዝ ተማሪዎችን በብዛት ይልኩ ነበር፡፡ ዶ/ር ዓብይም ትምህርት ቤቶችን ሲጎበኙ፣ ተማሪዎችን ሲያቀርቡና ለትምህርት ወደ ቻይናና አቡዳቢ ሲልኩ እየተመለከትን ነው፡፡ ልዩነቱ የዓብይ ዘመን ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በብሔር እየተቧደነ ሲከሳከስ የሚውል መሆኑ ነው፡፡ ትንሽ ፋታ ሲያገኝ ደግሞ ጫትና ፌስቡክ ጨምድዶ ይይዘዋል፡፡ ኮሌጆች ከሚከፈቱበት ይልቅ የሚዘጉበት ጊዜ እየበለጠ ነው፡፡ ለጥናትና ለምርምር ጊዜ የሌለው ተሜ ለኩረጃ እንዲመቸው ስሙን በፍርድ ቤት እስከመቀየር መድረሱም እየተነገረ ነው፡፡

እነ ማርክስ የድሮ ተማሪዎቻችንን ከማሳሳታቸው በፊት ጃንሆይ በሕዝብ ዘንድ እጅግ የተወደዱ ነበሩ፡፡ ይፎከርላቸው፣ ይዘፈንላቸው፣ ይዘመርላቸው፣ ይሸበሸብላቸው ነበር፡፡ ኃይለ ሥላሴ ይሙትእየተባለ በስማቸው ይማል ነበር፡፡ ቋቅ እስኪላቸውሺሕ ዓመት ይንገሡይባሉ ነበር፡፡ ሐውልት ካላቆምንልዎ ብሎ ሕዝቡ ለምኗቸው ነበር፡፡ ፈጥኖ እንደገነባ ፈጥኖ ይንድዋል ብለው ጠርጥረው ነበር መሰል አሻፈረኝ አሉ፡፡ ወደ ፊት ነገሮች ሲረጋጉ የሚሆነው አይታወቅም እንጂ ዶ/ር ዓብይም ምሥጋናና አድናቆት እየጎረፈላቸው ነው፡፡ በሙገሳ ብዛት ሰው የሚሞት ቢሆን ኖሮ ዶ/ር ዓብይን የሚቀድማቸው አይኖርም ነበር፡፡ የሕዝብ ልብ የሰረቁእስከ መባል ደርሰዋል፡፡ ዕልልልልል . . . ተብሎላቸዋል፡፡ የገጠር እረኞች ምን እንዳሉ ባላውቅም ፖለቲከኛ አርቲስቶቻችን አንጎራጉረውላቸዋል፣ ወግ ደርሰውላቸዋል፣ ስንኝ ቋጥረውላቸዋል፣ ቅኔ ተቀኝተውላቸዋል፡፡ ሕዝቡ አስተባባሪ ቢያገኝ አገሪቱ ሐውልት በሐውልት ትሆን ነበር፡፡ ፍቅሩ በዚሁ ከቀጠለና ምቀኛ ካልመጣዓብይ ይሙትእየተባለ የሚማልበት ጊዜ ሩቅ አይመስልም፡፡

ጃንሆይ የዋህና ሰውን አማኝ ነበሩ፡፡ ደርጎች ገና መዶለት ሲጀምሩይህች ባቄላ ካደረች አትቆረጠምምቢባሉልጆቼ ናቸው፣ ተዋቸው፣ አትንኳቸውይሉ ነበር ይባላል፡፡ በመጨረሻ ተበሉ፡፡ ዶ/ር ዓብይም ሰውን ያምናሉ፡፡ ውሸት መናገር ምን ያደርጋል እዚህ ላይ ዓብይ ይበልጣሉ፡፡ እንደ እሳቸው የዋህና ሰውን ሁሉ የሚያምን በምድር ላይ ያለ አይመስልም፡፡ ከልክ ያለፈው የዋህነታቸው የሚሳሱላቸውን ደጋፊዎቻቸውን እስከማስጨነቅ ደርሷል፡፡ የየዋህነታቸውን ደረጃ አንዳንዴ ሳስበው ክርስቶስ ሰምራን ያስታውሱኛል፡፡ ኢትዮጵያዊቷ መነኩሴ ክርስቶስ ሰምራ የሚገርም ታሪክ አላት፡፡ እንደሚባለው ከሆነ ከአንድ ጉዳይ በቀር እሷ ፀልያና ለምና ያልተመለሰ ጥያቄ የለም፡፡ ለሰው ልጅ መከራና ሥቃይ ምክንያቱ ሰይጣንና እግዚአብሔር ጠበኛ መሆናቸው መሆኑ ተገልጦልኛል ትላለች፡፡ እናም ሁለቱን ለማስታረቅ ቆርጣ ተነሳች፡፡ ይህ የዘወትር ጸሎታቸው እንዲሆን ተከታዮቿን አሳሰበች፡፡ አንዴ መንግሥተ ሰማይ አንዴ ሲኦል መመላለስ ሆነ ሥራዋ፡፡ ሲታክታት ተወችው፡፡

እንዲያውም መላኩ ሚካኤል ባይደርስላት ኖሮ ሰይጣን እዚያው ሲኦል ሊያስቀራት ነበር ይባላል፡፡

ጃንሆይ ከወታደሩ ጋር ችግር ነበረባቸው፡፡ እንደ ወታደሩ ክፉኛ የተፈታተናቸው የለም፡፡ መንግሥት በኃይል ለመገልበጥ ያሴሩ እነሱ፡፡ ሌላው መሬት ላራሹእያለ ሲጮህ ደመወዝ ካልተጨመረልን ብለው የተሰለፉ እነሱ፡፡ ደመወዝ ሲጨመርላቸው ደግሞ መንገሥ ይገባናል ያሉ እነሱ፡፡ ይኼ የወታደር ፈተና ዓብይንም ጀምሯቸዋል፡፡ ዓብይ ሥልጣን በያዙ ገና በስድስተኛ ወራቸው እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ወታደሮች ቤተ መንግሥቱን ድንገት እንደ ንብ ወረሩት፡፡ ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ ዓብይን ደመወዝ ጨምርልንአሏቸው፡፡ በዓብይ ዕይታ ግን መንግሥት ግልበጣ ነው፡፡ ደግነቱ ዓብይ ለተቆጣ ወታደር ምን እንደሚመለስ ያውቃሉ፡፡ በፑሽ አፕ ላብ በላብ አድርገው ለቀቋቸው፡፡ ዳኛም ወህኒ ወረወራቸው፡፡ ወታደሮቻችን ጠመንጃ መያዝና አገር ማስተዳደር ለየቅል መሆኑ ዛሬም የገባቸው አይመስሉም፡፡ የደርግን ታሪክ የዘነጉት ይመስላሉ፡፡ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም 17 ዓመታችን ነው፣ ተኝተን አናውቅም፣ ተደስተን አናውቅም፣ ስቀን አናውቅም፣ ዕረፍት የሚባል ነገር አናውቅምሲሉ አልሰሟቸውም ይሆን? ሳይመረጡ ሥልጣን ላይ ወጥተው ሕዝብ ከሚፈጁና ሲሸነፉ ደግሞ መንገድ ላይ መለዮአቸውን አንጥፈው ከሚለምኑ ወህኒ መጣላቸው ይሻላል፡፡ ቶርቸር እንደሆነ ድሮ ቀረ፡፡ ማዕከላዊ ተዘግቷል፡፡ በዓብይ ዘመን ግርፋት የለም፡፡ አሸባሪ ብሎ ነገር የለም፡፡ ጨለማ ክፍል ውስጥ መጣል የለም፡፡ ጥፍር መነቀል የለም፡፡ ወፌ ላላ የለም፡፡ ሳይቤሪያ ውስጥ መወርወር የለም፣ መደፈር የለም፣ ግብረ ሰዶም የለም፡፡ በአደገኛ አውሬ ማስፈራራት የለም፡፡ ስውር እስር ቤት የለም . . .፡፡ በዚያ ላይ የዓብይ አንጀት አይችልም፡፡ መፍትሔው ፍቅር ነው ይሉና እንደ ሌሎቹ ሊለቋቸው ይችላሉ፡፡

/ር ዓብይ ጃንሆይ እየተባሉ በስፋት ይጠሩ የነበሩትን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን በዚህ ዓይነት ሲተርኩልን ከረሙ፡፡ ዓብይ የቀራቸው ቢኖር ድንክ ውሻ ማበጀትና መንገድ ላይ እየወጡ ደሃ ላይ ብር መነስነስ ነው፡፡ ቸር ያሰማን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ