በተበጀ ሞላ (ዶ/ር)
በአገራችን የዘውጌ ፖለቲካ ያለ ልክ ጦዟል። በየማዕዘኑ ዘውጌ ተኮር አፍራሽ ፉከራና ዲስኩር እየሰማን ነው። በደቡብ ማቆሚያ የሌለው የክልልነት ጥያቄ፣ በሰሜን የምናየው እልህና ፍጥጫ፣ በምሥራቅ በኩል ሕይወት የቀጠፈው የወሰን ግፍያ፣ በምዕራብ የሚርመሰመሰው ደም አፍሳሽ አማፂ፣ በመሀል የሚራገበው ፅንፈኛ ዘውጌነት ወዘተ . . . ከዕለት ወደ ዕለት የለውጥ ተስፋችን በሥጋት እንዲደበዝዝ አድርጎታል። ፖለቲከኞቻችንም ሐሳብ ከመሸጥ ይልቅ ስሜት መግዛት ላይ አተኩረዋል። በጊዜ ዕልባት ካላገኘ ይኼ አካሄድ አገር አልባ እንዳያስቀረን ያሠጋል። ለመሆኑ የዘውጌ ፖለቲካ ታሪካዊ መሠረቱ ምንድነው? ከእኛ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃርስ አክራሪ ዘውጌነት ምን አደጋ አለው? አሳታፊ የሆነ የዜግነት ፖለቲካ ዕውን እንዲሆን ምን የተሻለ መንገድ አለ? ይህ አጭር መጣጥፍ እነዚህን ነጥቦች በጨረፍታ ይዳስሳል። በጽሑፉ ውስጥ ዘውጌ፣ ዘውግና ብሔር የሚሉት ቃላት እንደ ቅደም ተከተላቸው ‹‹Ethnic››፣ ‹‹Ethnicity›› እና ‹‹Nation›› የሚሉትን የእንግሊዝኛ ቃላት ይተካሉ። ሐሳቤን ማንነትን በማብራራት እጀምራለሁ።
ማንነት ምንድነው?
ማንነት ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት በቡድንም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ራሳችንን የምንገልጽበት መለያችን ነው። በዋናነት ማንነት ለራስ በሚሰጥ ዕይታ ይገለጻል። ማንነት ዘርፈ ብዙ ነው። ነጠላ ማንነት ያለው ሰው የለም። አንድ ግለሰብ በፆታው፣ በሃይማኖቱ፣ በቋንቋው፣ በዘውጉ፣ በሙያው፣ በፖለቲካ እምነቱና አሠላለፉ፣ ወዘተ . . . ማንነቱን ሊገልጽ ይችላል። ከሁለንተናዊው ሰውነቷ ባሻገር ሶፊያ በአንድ ጊዜ ሙስሊም፣ መምህር፣ ስልጤ፣ ኢትዮጵያዊት፣ የአፍሪካ ሴት ልትሆን ትችላለች። በመሆኑም ‘ይህ ቡድን ወይም ያ ግለሰብ የተለየ ማንነት አለው’ ሲባል የግድ ስለዘውግ እያወራን ላይሆን ይችላል። በሌላ አነጋገር ማንነት እንደ ቀይ ሽንኩርት ተደራራቢ ነው። አንዱን ንብር ልጦ ጥሎ (ረስቶ) ሌላውን መብላት (ማስጮህ) የባለቤቱ ምርጫ ነው። ሰው ነንና ኑሯችን ከሌሎች ጋር የተቆራኘ ነው። ሥውር በሆነው የግል ማንነታችንና ሁለንተናዊ (Universal) በሆነው ሰዋዊ ተፈጥሯችን መካከል ራሳችንን በበርካታ የጋርዮሽ እርከን እናገኘዋለን። ከቤተሰብ ጀምረን ከፍ ስንል በዘመድ አዝማድ ከዚያም ሲያልፍ በጎሳ (Clan)፣ በዘውግ (Ethnicity)፣ በነገድ (Tribe)፣ በብሔር (Nation) እና በዘር (Race) ማንነታችንን እንገልጻለን። አንዳንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ደግሞ የውጭ ሰዎች በብሔራዊ ማንነታችንን (National Identity) ይለዩናል።
በሊብራል ዴሞክራቲክ አገሮች እንደ አዲስ ያቆጠቆጠውን አክራሪ ብሔርተኝነት ተከትሎ ስለማንነት ፖለቲካ ብዙ ትንታኔ እየተሰጠ ነው። ዕውቁ የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪ ፍራንሲስ ፍኩያማና አፍሪካዊው ፈላስፋ ክዋሜ አፕያህ በቅርቡ በማንነት ላይ ያሳተሟቸው መጻሕፍት ተጠቃሽ ናቸው። እንደ ፍኩያማ እምነት የሰው ልጅ ለዕውቅና (Recognition) የተለየ ቦታ አለው። ለማንነት የሚሰጥ ዕውቅና ከክብር ጋር ይያያዛል። ማንነቴ ተገቢውን ዕውቅና ዋጋ አላገኘም ብሎ ያመነ ግለሰብም ሆነ ቡድን ይደራጃል፣ ይታገላል። አፕያህ በበኩሉ ማንነት እንደ ዘረመል (Gene) የሚወረስ ሳይሆን፣ እንደ ፀጉር በቅጥ ተሠርቶ ማድመቂያ የሚሆን ሥሪት ነው ሲል ይከራከራል ። የዘውጌ ማንነት በዋናነት ተወራሽ መለያዎችን (Primordial Characteristics) መሠረት ያደረገ ነው። አባላቱ ‘እኛና እነሱ’ ብለው የሚለዩባቸው ቋንቋ፣ ወግና ልማድ እንዲሁም ግዛት (Ancestral Territory) ይጋራሉ። ሆኖም ማንነት ተፈጥሯዊ አይደለም ሰው ሠራሽ ነው። አዲስ ግዛት በመውረር፣ ባህልን በማሻሻልና ታሪክን ለራስ በሚመች መንገድ በመከለስ የዘውጌ ማንነት ይፈጠራል። ለዚህ ደግሞ የፖለቲካ ኃይል፣ ትውፊትና ዲስኩር ዋና መሣሪያዎች ናቸው። ካለፉት 30 ዓመታት ጀምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር እየሆነ ያለውን ያስተዋለ ይኼን እውነታ አይስተውም።
የብሔር ፖለቲካ አመጣጥ በጨረፍታ
ብሔርና የብሔር ፖለቲካ መነሻ አውሮፓ ነው። በዘርፉ ጥልቅ ምርምር ያደረገው ሊህ ግርንፈልድ እንደሚለው ብሔር የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ምንጩ ‹‹Nation›› የሚለው የላቲን ቃል ሲሆን፣ ትርጉሙም ‘የተወለደ’ ማለት ነው። የጥንት ሮማውያን ቃሉን ከአንድ አካባቢ የመጡ የውጭ አገር ሰዎችን ለመግለጽ ይጠቀሙበት እንደነበር ተዘግቧል። በዋናነት መጤነትን ስለሚገልጽ ትርጓሜው የክብረ ነክነት ባህሪ ነበረው። በኋላ በመካከለኛው የአውሮፓውያን ታሪክ ብሔር የሚለው ስያሜ በቋንቋ ወይም በትውልድ ቦታ ከሚመሳሰሉ አካባቢዎች የመጡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለመግለጽ ይውል ነበር። ተማሪዎቹም የትውልድ ቀዬአቸውን መሠረት አድርገው መተጋገዝና በክርክርም ወቅት አንድ ላይ መቆም መለያቸው ስለነበር፣ ብሔር የሚለው ስያሜ የአንድ አካባቢ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ሐሳብና ዓላማ ለሚጋሩ ማኅበረሰቦች (Communities) መጠሪያ ሊሆን በቃ። ቆይቶም ሐሳቡ ወደ ቤተክህነት ጉባዔ ዘልቆ ገባና ሌላ ትርጉሙ አገኘ፡፡ ልሂቃንን ለመግለጽ ዋለ። በ16ኛው ዘመን እንግሊዞች ብሔርንና ‘ሕዝብ’ን በእብረታ (አንድ ላይ) መጠቀም እንደጀመሩ ይነገራል። ይህ ለውጥ አገራዊ ብሔርተኝነት (Civic Nationalism) የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም እንዲሆን መሠረት የጣለ ነበር።
ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ግን ብሔር የሚለው ቃል ‘ልዩ ሕዝብ’ የሚል ትርጉም ያዘ። በፈረንሣይ፣ በጀርመንና በሩሲያ ቃሉ ዘውግን፣ ግዛትንና የፖለቲካ ታማኝነትን አጣምሮ የያዘ ማኅበረሰብ የሚገልጽ ሆነ። በተለይ ደግሞ በፈረንሣይ አብዮት ማግሥት የተቀነቀነው ‘የብሔር ጥያቄ’ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ጀምሮ በግራ ዘመም ፖለቲከኞች ቁልፍ አጀንዳ ለመሆን በቅቷል። ብሔርና ብሔረሰብን ዋና የፖለቲካ ጉዳይ አድርጎ ለመጀመርያ ያቀረበው የሶቪየቱ መሪ ጆሴፍ ስታሊን ‹‹ማርክሲዝምና የብሔር ጥያቄ›› በሚለው ጽሑፉ (እ.ኤ.አ. 1913) ብሔር መሠረቱ የግድ ዘር፣ ነገድ ወይም ዘውግ ላይሆን ይችላል ይላል። በዋነኛነት የኦቶ ባወርን በወቅቱ ስመ ጥር የነበረ ኦስትርያዊ ፖለቲከኛ ሥራ መሠረት አድርጎ፣ ስታሊን ብሔር ማለት ታሪካዊ ሒደት፣ ቋንቋ፣ አሰፋፈርና ሥነ ልቦና የሚጋራና የምጣኔ ሀብት ትስስር ያለው ማኅበረሰብ ነው ሲል አብራርቷል።
በዚህ መንገድ ቅርፅ የያዘው የብሔር ፖለቲካ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግሥት ጀምሮ ከአውሮፓ ወደ ሌሎች ክፍለ ዓለማት በሰፊው ተዛመተ። የአፍሪካ ልሂቃን በሌላ ዓውድ ስለብሔር የተጻፈውንና የተነገረውን ሁሉ ገልብጠው ለዘውግ ፖለቲካ አዋሉት። የእኛዎቹ ዋለልኝ መኮንንና መለስ ዜናዊም ይኼንኑ ነበር ያደረጉት። ሐሳቡን ሲዋሱ አግባበ ነገሩን ግን አላገናዘቡም። ከላይ እንደተባለው ብሔር (Nation) የሚለው ቃል በታሪክ ሒደት ብዙ ጊዜ ትርጉሙ ተለውጧል፡፡፡ ለሮማውያን የመጤ ሰዎች መጠሪያ ነበር። ቆይቶ ሐሳብና ዓላማ የሚጋሩ ስብስቦችን ለመግለጽ ዋለ። ኋላ ደግሞ የሃይማኖትና ማኅበራዊ ልሂቃን ስያሜ ተደረገ። ከዚያም እንግሊዞች ‘ሉዓላዊ ሕዝብ’ የሚለውን ፖለቲካዊ ትርጉም አስያዙት። በዘመነ አብዮት ደግሞ ብሔር ማለት ‘ልዩ ሕዝብ’ ማለት ሆነ። የ ‘ያ ትውልድ’ ዘውጌዎችና የዛሬዎቹ ደቀ መዝሙሮቻቸው ‘ብሔር’ ነን ሲሉ “ከሌሎች ጋር ምንም የማንጋራ ‘ልዩ’ ሕዝብ ነን” ማለታቸው ነው። ኢትዮጵያን በቅጡ ለሚያውቅ እሳቤው የተዛባ ነው። ከአገራዊ ብሔርተኝነት (Civic Nationalism) ዕድገትና ታሪክ አንፃር ሲታይ ብሔር ማለት ዕጣ ፈንታው አንድ የሆነ፣ ከሚያለያዩት የዘውጌና ሌሎች ማንነቶች ባለፈ ጠንካራ የጋራ እሴቶች ያሉት ሕዝብ ማለት ነው። ስለዚህ ፖለቲካችን በብሔር ደረጃ ከሆነ የምናወራው ስለአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ፣ ስለዘውጌ ማንነት ሊሆን አይችልም።
የኢትዮጵያ “ብሔር” እና “ብሔረሰብ” እነማን ናቸው?
እንደ ማንኛውም መድበለ ዘውጌ ማኅበረሰብ (Multi Ethnic Society) በኢትዮጵያ ከዘውዳዊው ሥርዓት ግርሰሳ ጀምሮ፣ በተለይ ደግሞ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከወጣ ወዲህ ‘የብሔር ጥያቄ’ ዋና የፖለቲካ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። የሶቭየትን (1936 – 1977 እ.ኤ.አ.) እና ዩጎዝላቪያን (እ.ኤ.አ.1946 – 1974) ሕገ መንግሥቶች ፈለግ ተከትሎ ወታደራዊው ሥርዓት በሕገ መንግሥቱ (አንቀጽ ሁለት) ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች አገር መሆኗን አስቀምጦ ነበር። በተመሳሳይ አራተኛው (አሁን በሥራ ላይ ያለው) ሕገ መንግሥት በአገሪቱ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤቶች ‘ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች’ ናቸው ይላል። ነገር ግን በሕገ መንግሥቱ የሠፈሩት አንዳንዶቹ የፖለቲካ ቃላት አስማሚና ግልጽ ብያኔ የላቸውም። ለምሳሌ ስታሊን ለብሔር የሰጠውን ብያኔ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ‘ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን’ የሚለውን ፈርጅ (Category) ለመግለጽ ተጠቅሞበታል። አንቀጽ 39 (5) ‘ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ’ ማለት “ሰፋ ያለ የጋራ ፀባይ የማንፀባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው፣ ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ህልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ ናቸው” ብሎ ይፈታዋል። ጽንሰ ሐሳቡ በቀጥታ ከስታሊን ፍቺ አሊያም ከመሰል ምንጭ የተቀዳ በመሆኑ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ማን ብሔር፣ ማን ብሔረሰብ፣ ማን ሕዝብ እንደሆነ በግልጽ አልተቀመጠም። በ1984 ዓ.ም. ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳደሮችን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ (ቁጥር 7/1984) ደግሞ ብሔርና ብሔረሰብ ተተካኪ እንደሆኑ አድርጎ አስቀምጧቸዋል። አንቀጽ 2(7) ‘ብሔር’ ወይም ‘ብሔረሰብ’ ማለት በአንድ ኩታ ገጠም መልክዓ ምድር የሚኖር አንድ የመግባብያ ቋንቋና የአንድነት ሥነ ልቦና ያለው ሕዝብ ነው‘ ይላል። በተመሳሳይ የሚዲያ ባለሙያዎችና ፖለቲከኞች ብሔርና ብሔረሰብ የሚሉትን ቃላት የዘውጌ ቡድኖችን (Ethnic Groups) ለመግለጽ ይጠቀሙባቸዋል።
የዘውጌ ማንነትን የተረዳንበትና ፖለቲካዊ ጥያቄውን ምላሽ ለመስጠት የሄድንበት መንገድ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ያልተዛመደ በመሆኑ አሁን ላለንበት ችግር ደርሰናል። የክልል መንግሥታት ምሥረታና ስያሜ ጥሩ ማሳያ ነው። ከላይ በተጠቀሰው አዋጅ መሠረት በትግራይ ክልል ትግራዋይ፣ ኩናማና ሳሆ የሚባሉ የዘውጌ ቡድኖች ይኖራሉ። በደቡብ ትግራይ ያሉ ራያዎችም አማርኛ፣ ኦሮሚኛና አገውኛ ይናገራሉ። በአማራ ክልልም እንዲሁ የአማራ፣ የአገው፣ የኦሮሞ፣ የአርጎባና ሌሎች ማኅበረሰቦች ይኖራሉ። ኦሮሚያም በውስጡ በርካታ የዘውጌ ማንነት ያላቸው ሕዝቦች ይዟል። የጋምቤላና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችም የተለያዩ የዘውጌ ቡድኖች መኖርያ ናቸው። ነገር ግን የክልላዊ መንግሥታት ስያሜና ክለላ ይኼን የብዝኃነት እውነታ አያንፀባርቅም። የትግራይን ክልላዊ መንግሥት “ብሔራዊ” በሚል ከፍታ አስቀምጦ ጋምቤላን “የብሔረሰቦችና ሕዝቦች” ክልል ብሎ መሰየም የምስቅልቅሉ ሁነኛ ማሳያ ነው። ከፊት ለፊት ሲታይ ችግሩ የጽንሰ ሐሳብ ግልጽነት (Conceptual Clarity) ሳይኖር ሕገ መንግሥቱ በመተርጎሙ የመጣ ይመስላል። ሸፍጥ የለበትም ብሎ መደምደም ግን አይቻልም።
በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ዊል ኪምሊካ የተባለ የዘርፉ ተመራማሪ በመድበለ ዘውጌ ማኅበረሰብ ውስጥ በቁጥርና ንቃተ ህሊና ከፍ ያሉ የዘውጌ ቡድኖች ብሔር ሲባሉ ቀሪዎቹ ብሔረሰብ (Nationality) ተብለው ሊሰየሙ ይቻላል ይላል። ነገር ግን ፍረጃው ሳይንሳዊ አይደለም፣ አያሳምንም። አንድ ዘውግ አናሳ የሚባለው መቼ ነው? ሰያሚውስ ማነው? ፖለቲካዊ ንቃተ ህሊናስ በምን ይለካል? ኢትዮጵያ ውስጥ ኦሮሞና አማራን ብሔር፣ ጋሞና ስልጤን ደግሞ ብሔረሰብ ብሎ ለመለየት አሳማኝ ቀመር የለም።
አክራሪው የዘውጌ ፖለቲካችን የሳታቸው አምስት ቁምነገሮች
በሰው ልጅ ታሪክ ለረጅም ጊዜ ፖለቲካዊ ቅቡልነት (Legitimacy) ምንጩ እግዚአብሔር ወይም ሥርወ መንግሥት ነበር። በአንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች አሁንም የሥልጣን ምንጭ ደም ወይም ፈጣሪ ቢሆንም፣ በአብዛኛው ዘመናዊ ፖለቲካ መሠረቱ በማንነት ዙሪያ የተሰባሰበ ሕዝብ ነው። የሙያ ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ጥቁሮች፣ ወግ አጥባቂዎች ወዘተ . . . በፖለቲካው ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩት በማንነት ስም በሚሰበስቡት ድምፅ ነው። በኢትዮጵያም የሥልጣን ምንጭ እግዜር ነበር። ቆይቶ ርዕዮተ ዓለም ሆነ። አሁን የሁሉም ነገር ምንጩ ዘውግ ሆኗል። መጀመርያ የስታሊንን የብሔር ፖለቲካ የሸመደዱ የ1960ዎቹ ተማሪዎች የዘውዱን ሥርዓት በብሔርና በመደብ ጭቆና ስም ታገሉት። የመደብ ጭቆናው በወታደራዊ መንግሥት ሲመለስ ዘውጌዎቹ የብሔር ጥያቄ አንጠልጥለው በረሃ ገቡ፣ አሸነፉበትም። አሸናፊዎቹ በተራቸው ፍላጎታቸውን በሌሎቻችን ላይ ጫኑ። ተጨቋኞቹ ሌላ ዙር ትግል አድርገው ዛሬ ላይ ደርሰናል። አሁንም የፖለቲካ ችግራችን እንደተወሳሰበ ነው። በእኔ ዕይታ ያልተገራና መሬት ያልያዘ የዘውጌ ፖለቲካ ለችግራችን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። አምስት መከራከሪያ ነጥቦችን ላንሳ።
አንደኛው ማንነት ሰው ሠራሽ እንደ መሆኑ ቋሚ አይደለም። የታሪካዊ ግስጋሴ (Historical Progress) በሕዝቦች ውህደትና የባህል ውርስ ይገለጻል። ለምሳሌ ብሔር የአዝጋሚ ዕድገት (Evolution) ውጤት ነው። ለረጅም ጊዜ በሚዘልቅ ጥልቅ የሕዝቦች መስተጋብር ምክንያት ቤተሰብ ወደ ጎሳ፣ ጎሳም ወደ ዘውግ፣ ዘውግም ወደ ብሔር ያድጋል። ቁሳዊ ልማትና የባህል ሽግግርም እንዲሁ ወሳኝ ነው። በነዲክት አንደርሰን ‘ብሔር ምናባዊ ማኅበረሰብ’ ነው ሲል ሥሪትነቱን ለመጠቆም ነው። ዛሬ ጥቁር፣ ነጭ፣ ምሥራቃዊ (Oriental)፣ ወዘተ . . . የምንላቸው የሰው ዘር ፈርጆች እንኳ ከሁለት ሚሊኒየም በፊት አልነበሩም። በምዕራብ አውሮፓም ጎሳ፣ ዘውግና ነገድ ታሪካዊ ሒደቱን ተከትሎ ወደ ብሔር አድጓል ። ፈረንሣይ፣ ጀርመንና ጣሊያን የመሳሰሉት አገሮች የግዛት ወሰናቸውን ከብሔር ክልል ጋር በማጣጣም ወጥ መንግሥታዊ አስተዳደር ወይም ብሔረ መንግሥት (Nation State) መሥርተዋል።
የፈረንሣይ ብሔር ጉዓል፣ ሮማን፣ ብርቶን፣ ተኦቶን የመሳሰሉ ነገዶችንና ጎሳዎችን በሒደት አዋህዶ የተፈጠረ ነው። የጣሊያን ብሔርም እንዲሁ ሮማን፣ ኢትራስካን፣ ተኦቶን፣ ግሪክና ዓረብ ዘር ያላቸውን ሕዝቦች ያዋሀደ ነው። በሌላ በኩል የሕዝቦች መስተጋብር ውስን በሆነባቸው፣ ለረጅም ግዜ ጎልቶ የወጣ ጠንካራ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ባልተፈጠረባቸውና በቁሳዊ ልማት ወደ ኋላ በቀሩ የእስያና የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ለቁጥር የሚያታክቱ ጎሳዎችና ዘውጌ ማኅበረሰቦች መኖራቸው ማኅበረሰባዊ አዝጋሚ ለውጥ ከቦታ ቦታ እንደሚለያይ ይጠቁማል። ለምሳሌ በኢንዶኔዥያ ከ700 የሚበልጡ፣ እንዲሁም በናይጄሪያ ከ500 የሚልቁ የዘውጌ ቡድኖች ይገኛሉ። የእነዚህ ሕዝቦች መስተጋብር ፍጥነትና ውጤት የሚወሰነው በትምህርት፣ በባህልና በፖለቲካው ዘርፍ በሚሠሩ የጋራ እሴት ግንባታ ሥራዎች ይሆናል። የአገራችንም ዕጣ ፈንታ ከዚህ የተለየ አይደለም።
ሁለተኛ ለአክራሪ ዘውጌዎች የመገንጠል መብት (አንቀጽ 39) ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ነው፣ ጊዜውን ጠብቆ እንደሚበትነን አልታያቸውም፣ አሊያም ብንበተን ግድ አይላቸውም። ‘ጎርፍ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው’ እንዲሉ፣ ከእኛ ቀድመው በሐሳቡ ላይ ሙከራ (Experiment) ያደረጉ ከስህተታቸው ለመማር እንኳ ዕድል ሳያገኙ ጠፍተዋል። ፕሬዚዳንት ጆሲፕ ቲቶ እ.ኤ.አ. በ1974 የብሔሮችና ብሔረሰቦች የመገንጠል መብት በሕገ መንግሥት እንዲረጋገጥ ሲያደርግ አገሩ ዩጎዝላቪያ ከ17 ዓመታት በኋላ እንደምትበተን አልጠራጠርም። የሶቭየት መሪዎችም እ.ኤ.አ. በ1977 ባሻሻሉት ሕገ መንግሥት የኅብረቱ አባላት ባሻቸው ጊዜ የመገንጠል መብት እንዳላቸው ሲያውጁ፣ ከ14 ዓመታት በኋላ ግዛታቸው ከ15 ቦታ እንደሚፈረካከስ አልታያቸውም። ሐሳቡ እነሱን እንዳጠፋቸው እያወቅን ራሳችንን ለማዳን ሌላ አማራጭ መንገድ አለመከተላችን ግራ ያጋባል (የእኛ ሕገ መንግሥት ሲፀድቅ ከዩጎዝላቪያና ሶቭየት ኅብረት ፍርስራሽ አዳዲስ አገሮች እየተመሠረቱ እንደነበር ልብ ይሏል)። ሌላው አስገራሚውና ከንካኙ ነገር ደግሞ ከ80 በላይ የዘውጌ ቡድኖች በሚኖሩባት አገር የመገንጠል ሕገ መንግሥታዊ መብት የተረቀቀው፣ ሁለት ቡድኖች ብቻ በሚወክሉት ሕወሓትና ኦነግ ነበር። ብዙኃኑ ድምፅ አልነበረውም። ዳግም ዕድል ሊሰጠው ይገባል። በኢትዮጵያ ጉዳይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድርሻ እንዳለው በተግባር መገለጽ አለበት።
ሦስተኛ አክራሪ የዘውጌ ፖለቲካ ለውህድ፣ ለንዑስና ለተደራቢ ማንነት ቦታ የለውም፡፡ ትኩረቱ ነጠላ፣ ጠባብና ‘ንፁህ’ ማንነት ላይ ነው። ከዘውግ ባሻገር ህልውና ያላቸውን እንደ አዲስ አበባውያን ያሉ ‘ኮስሞፖሊታን’ ማኅበረሰቦችና የትውልድ ሐረጋቸውን ከተለያዩ የዘውጌ ቡድኖች የሚስቡ ግለሰቦችን ፍላጎትና ምርጫ አያስተናግድም። አንድ ተጨባጭ ምሳሌ ላንሳ፡፡ በሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚኖር ራያ የሚባል ማኅበረሰብ አለ። በታሪክ አጋጣሚ በትግራይና አማራ ክልሎች ለሁለት ተከፍሎ ይኖራል። በቅርቡ የራያን ሕዝብ ወደ አንድ አስተዳደራዊ መዋቅር ለማምጣት የተጀመረውን እንቅስቃሴ ተከትሎ ሁለት ኃይሎች ፅንፍ ይዘው ቆመዋል። ሕወሓት “ራያ የሚባል ማንነት የለም፣ ራያ ትግሬ ነው” ሲል፣ አብን (አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ) ደግሞ “ራያ የሚባል ማንነት የለም፣ ራያ አማራ ነው” ብሎ ሌላ ጫፍ ይዟል። የራያን ኦሮሞነትም የበለጠ ለማጉላት የሚጥሩ የዘውጌ ፖለቲከኞች አሉ። እውነታው ግን ራያ ከአማራ፣ ከትግሬ፣ ከኦሮሞ፣ ከአፋርና ከአገው የሚወለድ ኅብራዊ ውህድ ማንነት ያለው ሕዝብ ነው። ከማኅበረሰቡ ባህላዊና ታሪካዊ መስተጋብር አንፃር ለራያ የሚስማማው ዜግነትን መሠረት ያደረገ ብሔርተኝነት ነው። የማንነት ሁሉ መለኪያ የግድ ዘውግ ብቻ መሆን ስለሌለበት፣ የራያ ሕዝብ ከኢትዮጵያዊነት ባነሰ ማንነት ራሱን ይግለጽ ከተባለ ራያ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም። ከዚህ ውጪ በአንድ ዘውግ ወይም ‘በብሔር’ ስም ይጠራ ቢባል የዘውግ ሐረጋቸውን ከሌላ አቅጣጫ የሚስቡ የማኅበረሰቡን ክፍሎች ማግለል ይሆናል። የዚህ ክትለት (Implication) ግልጽ ነው፡፡ ራያን የመሰሉ ውህድ ኢትዮጵያውያን በማንነት ፖለቲካ በአግባቡ አይስተናገዱም፣ ይጠባቸዋል።
አራተኛ አክራሪ የዘውጌ ፖለቲካ አገራዊ ብሔርተኝነትን እንደ መዳረሻ ዓያይም። ይባስ ብሎም የትግል ዒላማው ለአንድነት የሚሠሩ የፖለቲካ ኃይሎች ላይ ያነጣጠረ ነው። የኦሮሞ፣ የትግራይና የአማራ ዘውጌዎች ኢትዮጵያዊነትን ማዕከል አድርገው በተነሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ የሚያደርጉት አፍራሽ ቅስቀሳ የዚሁ ችግር ማሳያ ነው። በመሠረቱ አገራዊ ብሔርተኝነትና የዘውጌ (Ethnic) ማንነት አይቃረኑም። በብልኃት ከተያዙ ተመጋጋቢ ሆነው መኖር ይችላሉ። ዮሩባው ናይጄሪያዊነቱን፣ ፑንጃቢው ህንዳዊነቱን እንዳልጣለ ሁሉ ኦሮሞውም ሆነ አማራው ኢትዮጵያዊነቱንና ንዑስ ማንነቱን አስማምቶ መኖር ይቻለዋል። መሬት ላይ ያለው እውነታም ይኼንኑ እንድናደርግ ያስገድደናል። ከፖለቲካው ዲስኩር ባሻገር በተግባር ህልውናችን የተሳሰረ ነው።
በመጨረሻም የማንነት ፖለቲካ ‘የእኔ’ ከሚለው ቡድን ያልተገደበ እሽታ ይጠብቃል። ልዩነትንና የሐሳብ ፍጭትን አያስተናግድም። ይህ አጉል ተስፋ ከሰዋዊና ማኅበረሰባዊ ተፈጥሯችን ጋር አይገጥምም። የሰው ልጅ ከራሱ ጋር እንኳ ፍፁም አንድነት መፍጠር አይችልም። የአሥር ደቂቃ ጥሞና (Meditation) ለማድረግ የተቀመጥን ይኼን እውነታ በተግባር እናውቀዋለን።
እንደ ንፋስ የሚበተነውን ሐሳባችንን ሰብስበን ማቆም ፈታኝ ነው። ይህ እንግዲህ ከራስ ጋር ለመግባባት የሚደረግ ትግል ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ ጃቆስ ላካን (The Mirror Stage) በሚለው የሰውን ልጅ ዕድገት ባብራራበት ንድፈ ሐሳቡ ውስጣዊ ስሜትና ውጫዊ ሥሌት ብዙውን ጊዜ አይጣጣሙም፡፡ እንዲያ ሲሆን ጭንቀት ይፈጥራል ይላል። ለምሳሌ ዘውጌ ተኮር የፖለቲካ እንቅስቃሴ ግለሰቡ ራሱን የሚያይበት ማኅበራዊ መስታወት ነው። እንደ አባል ተስፋውንና ምኞቱን ይገልጽበታል፣ ያነብበታል። እንደ ግለሰብ ደግሞ መስታወቱ የማያሳይለት ውስጣዊ ፍላጎትና ትግል ይኖረዋል። የውስጡንና የውጪውን ሙሉ ለሙሉ ማገጣጠም የሚቻል አይደለም። ፖለቲካዊ አንድምታው በግለሰብም ሆነ በቡድን ደረጃ ከሌሎች ፍፁም አንድነትን መጠበቅ እንደሌለብን ነው። ዘውጌዎች ይኼን እውነታ አይቀበሉም። የእነሱን ቋንቋ የሚናገር ሁሉ እንደ እነሱ እንዲያስብ፣ እንዲሰማውና እንዲያደርግ ይጠብቃሉ።
ከዚህ ወዴት?
ዘግይቶም ቢሆን ኢሕአዴግ አገራዊ ማንነትን ችላ ማለት የሚያስከትለው አደጋ ተገልጾለት ነበር። በሥልጣን ላይ የነበሩት ኃይሎች ከሁለት ዓመት በፊት አዲስ ራዕይ በምትባል የንድፈ ሐሳብ መጽሔታቸው በኢትዮጵያዊነት ተኮትኩቶ ያላደገ ወጣት የዘውጌ ወጀብ ቀስቅሶ ሊያጠፋቸው እንደደረሰ ተናዘዋል። የፈሩት አልቀረም፣ ድምፅ አልባው አብዮት ገፍቶ ዳር ጥሏቸዋል። ውጤቱም ተስፋና ሥጋት ወልዷል። በጊዜ ካልተገራ በየአቅጣጫው የጦዘው ግለኝነት አገር ሊያፈርስ ይችላል። ከዚህ ሥጋት በመነሳት ይጠቅሙ ይሆናል ያልኳቸውን ሦስት ነጥቦች አንስቼ ሐሳቤን ላጠቃል። አንደኛ በእኔ ዕይታ ለእኛ የሚሻለን በመድበለ ዘውጌ ዴሞክራሲ (Multi Ethnic Democracy) ማዕቀፍ አገራዊ ብሔርተኝነትን ኮትኩቶ ማሳደግ ነው። በህንድና መሰል አገሮች ተተግብሮ እንዳየነው መድበለ ዘውጌ ዴሞክራሲ አገራዊና የዘውጌ ማንነቶችን ሚዛን ጠብቆ የመያዝ ብቃት አለው። የግለሰብና የቡድን መብቶችን አጣጥሞ ያስተናግዳል። መርሆው ተጓዳኝና ተደራቢ ማንነት ያላቸውን የተለያዩ የማኅበረሰቡ አባላት በእኩል ዜግነት የሚያስተናግድ የፖለቲካ ሥርዓት ዕውን ማድረግ ነው። አካታችነቱ እንዳለ ሆኖ ስኬታማ መድበለ ዘውጌ ዴሞክራሲ ለጋራ እሴቶች ግንባታና ጥበቃ ልዩ ትኩረት ይሰጣል። በስምምነት የሚፈጠር የጋራ እሴት ማዕከላዊ ይሆንና የዳርቻውን ማንነት በአዝጋሚ ስበት ያስገባል። በሒደቱም በማንነት ላይ ሳይሆን መርህ ላይ የቆመ፣ የግለሰብና የቡድን መብቶችን አመዝኖ የሚያስተናግድ የዜግነት ፖለቲካ ዕውን ይሆናል።
ሁለተኛ በዜግነት ፖለቲካ የተቃኘ መድበለ ዘውጌ ዴሞክራሲ ለመገንባት ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ቁርጠኝነት የሚጠይቅ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ነው። ከማሻሻያው ሥራ በፊት ግን ሕዝባዊ ምክክር ያስፈልጋል። ልሂቃኑ የሐሳብ መሪነቱን ድርሻ ይዘው አወዛጋቢ የሆኑ ጉዳዮች በስፋት ውይይት ቢደረግባቸው ሕዝቡ በዕውቀት ተመሥርቶ፣ ለማሻሻያው ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ ማድረግ ይችላል። ሁሉም ባለድርሻ አካላት (ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ምሁራን፣ ወዘተ) ቁልፍ በሆኑ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ በአደባባይ ሲሟገቱ አስተፃምሮው (The Synthesis) ለውሳኔ የሚጠቅም አሳማኝና አስተማማኝ ዕውቀት ይፈጥራል። የአገርን ዘላቂ ጥቅም ለማስጠበቅ በዕውቀት ላይ ተመርኩዞ የሚሠራ ፖለቲካ አማራጭ የለውም።
በመጨረሻም በፖለቲካ መግለጫችን፣ ትንታኔዎችንና ዲስኩራችን የምንጠቀማቸው ቃላትና ጽንሰ ሐሳቦች ግልጽና አግባቢ መሆን ይኖርባቸዋል። ዓለም በቃል ይፈጠራል ነውና በትርጉም ካልተግባባን በተግባር መተላለፋችን የግድ ነው። ለምሳሌ ከላይ እንደጠቀስኩት ሕገ መንግሥቱ ‘ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ’ ብሎ የሚጠራቸው ስብስቦች በተጨባጭ እነማን እንደሆኑ ግልጽ አይደሉም። ጽንሰ ሐሳቡ ከእነ ፍቺው ከውጭ ተቀድቶ የገባ በመሆኑ ከእኛ እውነታ ጋር አልገጠመም። ሌላም የተለመደና ችግር ያለበት አባባል አለ። ከተለያየ የዘውጌ ቡድኖች (Ethnic Groups) ብንወለድም ኢትዮጵያውያን ዘራችን አንድ ነው፣ ጥቁሮች ነን። ስለዚህ በተለምዶ እንደሚባለው በሽታችን ዘረኝነት ሳይሆን፣ አክራሪ ዘውጌነት (Ethnic Extremism) ነው። ችግራችንን በትክክለኛ ስሙ መጥራት አንድ ዕርምጃ ወደ መፍትሔው ስለሚያቀርበን፣ የፖለቲካና የፖሊሲ ውይይታችን ለጠራ ሐሳብና አመንክዮ ትኩረት መስጠት አለበት።
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በአውስትራሊያ ሜልቦርን ዲኪን ዩኒቨርሲቲ መምህር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡