ቡናን ጨምሮ ከቅመማ ቅመምና ከሻይ 340 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል
በመንፈቅ ዓመቱ 132 ሺሕ ቶን ገደማ ቡና ወደ ውጭ በመላክ ከ475 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደሚገኝ ቢታቀድም፣ በውጤቱ ግን 103 ሺሕ ቶን በመላክ 334 ሚሊዮን ዶላር ገደማ መገኘቱ ታውቋል፡፡
የቡናው የወጪ ንግድ አፈጻጸም ይላካል ተብሎ ከታቀደው አኳያ በመጠን ሲታይ የ78.44 በመቶ እንዲሁም በገቢ በኩል ከታቀደው አንፃር የ70.29 በመቶ መመዝገቡን ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም በመጠን የ4200 ቶን ወይም የአራት በመቶ እንዲሁም በገቢ አንፃር የ47.9 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ12.54 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ በዚህም ሳቢያ የቡና የወጪ ንግድ ገቢ ዕድገትም ሆነ የሚላከው የቡና መጠን ዕድገት ዝቅ ማለቱ ታውቋል፡፡
የቡና የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከ2010 ዓ.ም. የመጀመርያ ስድስት ወራት አኳያ በሚታይበት ወቅት በገቢ ደረጃ ከ12.5 በመቶ በላይ ዕድገቱ ሲቀንስ፣ በመጠንም አራት በመቶ ገደማ ዝቅ ብሏል፡፡ ባለፈው ዓመት የመጀመርያዎቹ ስድስት ወራት ወደ ውጭ ከተላከው 107.3 ሺሕ ቶን ቡና የተገኘው 382 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ነበር፡፡
ባለሥልጣኑ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ማዘጋጀት በጀመረው የተብራራ አኃዛዊ መረጃ መሠረት፣ የየወራቱን አፈጻጸም ከዕቅዱና ካለፈው ጊዜ አኳያ በማመሳከር ተንትኖ እያቀረበ ይገኛል፡፡ በዚህ መነሻነት ለአብነት በታኅሳስ ወር የነበረውን የቡና እንቅስቃሴ ብንመለከት፣ 18.6 ሺሕ ቶን ቡና በመላክ 66.82 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እንደነበር ያሳየናል፡፡ ይሁንና 12,991.83 ቶን ቡና ተልኮ የዕቅዱን 69.93 በመቶ ማከናወን እንደተቻለና 37.42 ሚሊዮን ዶላር ወይም የዕቅዱን 56 በመቶ ገቢ ማስገኘት እንደቻለ አስፍሯል፡፡ የዚህ ዓመት የታኅሳስ ወር አፈጻጸም ከ2010 ታኅሳስ አኳያም በመጠን 2,175 ቶን ወይም 14.34 በመቶ፤ በገቢም የ20.8 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡
በሪፖርቱ የቡናን ጨምሮ የሻይና የቅመማ ቅመም የወጪ ንግድ አፈጻጸም በውጤት ተተንትኖ ይቅረብ እንጂ በተለይ ቅናሽ በሚታይበት ወቅት ከምን አኳያ እንደታየ አመላካች ምክንያቶች ቢካተቱም፣ በግልጽ ተብራርተው አለመቅረባቸው የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ሪፖርት ክፍተት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት የነበረውን የዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ ሁኔታ በተለይም በኒው ዮርክ ገበያ የታየውን የዋጋ መዋዠቅ የባለሥልጣኑ ሪፖርት አጣቅሷል፡፡
ከዚህ ባሻገር የኢትዮጵያን ቡና በሚገዙ አገሮች የታየው የዋጋ መውረድም ለቡና የወጪ ንግድ አፈጻጸም መቀዛቀዝ ድርሻው የጎላ ነበር፡፡ ከሐምሌ 2010 ዓ.ም. እስከ ታኅሳስ 2011 በጀት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የተላከው ቡና ዋና መዳረሻ ከነበሩት አገሮች መካከል በሳዑዲ ዓረቢያ ቀዳሚው አገር ነበር፡፡ ወደ ሳዑዲ ያቀናው ቡና በመጠን 21,817.17 ቶን ወይም የ21 በመቶ ድርሻ እንዲሁም በገቢ ረገድም የ60.16 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ18 በመቶ ድርሻ በመያዝ ለሳዑዲ ቅድሚያውን አስገኝቷል፡፡ ለጀርመን ከተላከው 16,270.41 ቶን ወይም 16 በመቶ ቡና 45.79 ሚሊዮን ዶላር በማስገኘት የ14 በመቶ ድርሻ ነበረው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠው ወደ ጃፓን የተላከው ሲሆን 13,868.77 ቶን ወይም 13 በመቶ ድርሻ ያለው ቡና ተልኮ የ40.72 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ12 በመቶ ድርሻ ያለው አፈጻጸም በማስመዝገብ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸው ተመልክቷል፡፡
ከእነዚህ አገሮች በተጨማሪ ቡናው ባስገኘው የገቢ መጠን በቅደም ተከተል ሲቀመጡ አሜሪካ አራተኛ፣ ቤልጅየም አምስተኛ፣ ደቡብ ኮሪያ ስድስተኛ፣ ጣሊያን ሰባተኛ፣ ሱዳን ስምንተኛ፣ አውስትራሊያ ዘጠነኛ እንዲሁም ፈረንሳይ 10ኛው ደረጃ ይዘዋል፡፡ እነዚህ አገሮች በጠቅላላው በመጠን 84 በመቶ፣ በገቢም 81 በመቶ በማስመዝገብ ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ ይሁንና ወደ ተዘረዘሩት አገሮች ከ2010 መጀመሪያ መንፈቅ ዓመት የተላከው ቡና ከ2011 ጋር ሲወዳደር፣ በመጠን የአራት በመቶና በገቢ የ14 በመቶ ቅናሽ በዚህ ዓመት ተመዝግቧል፡፡ እንደ አሜሪካ ያሉ አገሮች በመጠን የ31 በመቶ፣ በገቢ ረገድም የ29 በመቶ ቅናሽ የተመዘገበባቸው መዳረሻዎች ሲሆኑ፣ ወደ ሳዑዲ ይላክ ከነበረውም የ22 በመቶ የቡና መጠን ቅናሽ ተመዝግቧል፡፡ ወደ ጀርመን ይላክ ከነበረው የ25 በመቶ የመጠን ቅናሽ ሲመዘገብ ወደ ሱዳን ይላክ ከነበረውም የ24 በመቶ ቅናሽ በመጠን ቅናሽ መመዝገቡ ለቡናው አፈጻጸም መቀዛቀዝ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡
በባለሥልጣኑ ሪፖርት በይፋ የተጠቀሱ ላኪዎችም አፈጻጸማቸው ተካቶ ቀርቧል፡፡ በዚህም መሠረት፣ ቀርጫንሼ ኩባንያ፣ ትራኮን ትሬድንግ እንዲሁም አደም ከድር ሐጂ የተሰኙት ላኪዎች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ በከፍተኛ ገቢ አስገኝነት ተጠቅሰዋል፡፡ ሙለጌ፣ አባሐዋ ትሬድንግ፣ ኦሮሚያ ቡና አምራቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር፣ ሲዳማ ቡና አምራቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር፣ አርፋሳ ትሬድንግ፣ ኤስ.ኤ ባገርሽና ኢትዮጵያን ትሬድንግ ቢዝነስ ኮርፖሬት ከአራተኛ እስከ 10ኛ ደረጃ በማግኘት ትልቁን የውጭ ምንዛሪ ገቢ በማስገኘት ተካተዋል፡፡ በስድስት ወራት ውስጥ በቡና ላኪነት ከተሳተፉት ከከፍተኞቹ ባሻገር 278 ላኪዎች በዘርፉ ተሳትፎ እንዳደረጉም ተመልክቷል፡፡
እንደ ቡናው ሁሉ በቅመማ ቅመምና በሻይ ምርቶች የወጪ ንግድ መስክም ከታቀደው አኳያ ቅናሽ መመዝገቡን ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ያጠናቀራቸው መረጃዎች አመላክተዋል፡፡ በመንፈቁ 4368.6 ቶን ቅመማ ቅመም ወደ ውጭ ተልኮ አምስት ሚሊዮን ዶላር ገደማ ተገኝቷል፡፡ ከታቀደው በመጠን የ39 በመቶ፣ በገቢ ረገድም የ50 በመቶ ቅናሽ ተመዝግቧል፡፡ በሻይ ምርትም እንዲሁ 1.65 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኘ የ984 ቶን ምርት ለውጭ ገበያ ቀርቧል፡፡ ይሁንና የየ54 በመቶ የገቢ ቅናሽ ሲመዘገብ፣ በመጠን ረገድም ከታቀደው አኳያ የ65 በመቶ ቅናሽ ተመዝግቧል፡፡
በጠቅላላው በስድስት ወራት ውስጥ ከቡና፣ ከሻይና ከቅመማ ቅመም ምርቶች 340 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡