Friday, March 31, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አገር ግንባታና የለውጥ አመራሩ ቀጣይ ፈተናዎች

በመኮንን ዛጋ

የአንድ አገር አጠቃላይ ህልውና በዋናነት የሚመሠረተው አገሪቱ በምታራምደው ሶሺዮ ኢኮኖሚ ሥርዓትና ብልፅግና ነው፡፡ የበለፀገ አገር እንኳን የራሱ ዜጎች ይቅርና ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ ያሉ ዜጎች ለመኖርና ለመሥራት የሚያልሙት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የተጠናከረ ኢንቨስትመንትና የሥራ ዕድል ፈጠራ ወሳኝ ነው፡፡

ሁሉም የኢንቨስትመንት ተቋማት መዋዕለ ንዋያቸውን የሚያፈሱበትን አገር፣ ፖለቲካዊ ዳራና መዋቅር በሚገባ በመዳሰስና በመተንተን አስቀድመው በማቀድ ሊፈጠር የሚችለውን ሥጋታቸውን ለመቀነስ ይሞክራሉ፡፡ ስለሆነም ለአንድ አገር ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና የዜጎች ብልፅግና ወሳኙ ነጥብ የፖለቲካዊ ሥርዓት መረጋጋት ይህን ተከትሎም የሚፈጠር የጋራ አስተሳሳሪ ማንነት በመሆኑ የሉዓላዊ አገሮች መንግሥታትና ዜጎች ለአገር ግንባታ ጉልህ ትኩረት መስጠት አለባቸው፡፡   

በዚህ ጽሑፌ ለማሳየት የምፈልገው አንደኛው ጉዳይ አገሮች በተመረጡ ዜጎችና ቁርጠኛ የአገር መሪዎች ራዕይ አማካኝነት በጊዜ ሒደት ተገንብተው፣ መልካም አስተዳደርና ፍትሐዊነትን በሚያሰፍኑ ልዩ ልዩ ተቋማት ዘላቂነታቸውን በማረጋግጥ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን እንደሚደግፉ፣ ሁለተኛው የጽሑፌ መነሻ ሁሉም መንግሥታዊ ተቋማት የሚጠናከሩበትን መንገድ በመጠቆም በአሁኑ ወቅት በአገራችን እየታየ ላለው የለውጥ እንቅስቃሴ ጅማሮ የበኩሌን ጠጠር በመጣል፣

የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ዓላማዎች ከላይ የተጠቀሱት ይሁኑ እንጂ በጣም አስፈላጊው ምክንያት በጠንካራ አገር ግንባታ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና በዘርፉ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ተቋማትና ኢትዮጵያዊያን ግለሰቦች ሐሳባቸውን እንዲያዋጡ የውይይት መክፈቻ እንዲሆን ለማድረግ ነው፡፡

ይህ ጽሑፌ ያለፈውን ታሪካችንን በጥንቃቄና በጥልቀት እንድንመረምር የሚጠይቅ ሲሆን፣ የረዥም ዘመን የነፃነት ታሪክ ያላት አገራችን ኢትዮጵያ አሁንም ከመጠፋፋትና መለያየት አረንቋ ውስጥ ያለመውጣቷ እጅግ ግራ ስለሚያጋባ ነው፡፡ ዓለም ወደ አንድ ማዕቀፍ ለመምጣት በምትታትርበት፣ የሉላዊነት አስተሳሰብ በሰፈነበት በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያዊያን ለመበታተን ቋፍ ላይ በመሆን ቀን ቆጣሪ የምንሆንበት የታሪክ ቡራኬ ለሁላችንም እንደ ዓብይ ጉዳይ ሊያሳስበን ይገባል፡፡

ስለሆነም እስካሁን ድረስ የመጣንበትን በጎም ክፉም የታሪክ ዳና፣ በአብሮነት የወጣን የወረድንበትን የችግር አቀበት ቁልቁለት መንገድ በማሰላሰል፣ በመመርመርና በመሰነድ ከዚህ ልምድ በመውሰድ አገራችንን የተሻለች በማድረግ ለቀጣይ ትውልድ የበለፀገችውን አገር ማውረስ እንችላለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለዚህም የሆነ ቦታ ላይ ተንገራግጮ የቆመውን የአገር ግንባታ ሒደት ማስቀጠል ይገባል፡፡

አገር ግንባታ (Building a Nation)

ከሰው ልጅ የዘመናዊ ሕይወት ጅማሮ አንስቶ ምንም እንኳ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ለረዥም ጊዜ በስፋት ጥቅም ላይ ቢውልም ‹‹አገር ግንባታ›› የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በአግባቡ ሳይገለጽና በተለያዩ አካላት ሲያከራክር ቆይቷል፡፡ በአብዛኞቹ አገሮች የፖሊሲ ሰነዶች ላይም ትርጓሜም ፍቺም ከሚሰጥበት ይልቅ ማብራሪያ እየተሰጠበት ይታለፋል፡፡ በአብዛኛውም ርዕዮተ ዓለም ትንታኔዎች ‹‹አገር  ግንባታ›› (Nation Building) የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ‹‹መንግሥት ግንባታ›› (State Building) ከሚለው ቃል ጋር በተለዋጭነት የመጠቀም ዝንባሌ ይታያል፡፡ ምንም እንኳ ሁለቱ ጽንሰ ሐሳቦች ለበርካታ አካላት ተመሳሳይና በቅርብ የተሳሰሩ ቢመስሉም ሒደታቸውና ቅርፃቸው ለየቅል ናቸው፡፡

መንግሥት  ግንባታ (State Building) ስንል የዘመናዊ መንግሥትን መሠረታዊ ባህርያት ማሟላት የሚያስችል ቁመና ያላቸው ጠንካራ አስተዳደራዊ ተቋማትን የመገንባት ተግባር ሲሆን ‹‹አገር  ግንባታ›› (Nation Building) የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የሚያመለከተው ደግሞ በአንድ አገር ውስጥ በሚኖሩ የተለያዩ ቡድኖች መካከል የጋራ የማንነት ስሜትና አንድ ማኅበረሰብ የሚገነባበት ረቂቅ ሒደት ነው፡፡ የአገር ግንባታ ዋናው ዓላማ በአንድ ሥርዓተ መንግሥት ውስጥ ባሉ ሕዝቦች መካከል አንድነት እንዲኖር በማድረግ የፖለቲካ መረጋጋትና ዘላቂ ህልውና እንዲኖር ማስቻል ነው፡፡ በአጭሩ ስናስቀምጠው መንግሥት ግንባታ ማለት መንግሥታዊ የአስተዳደራዊ አገልግሎት ተቋማትን መገንባት፣ መልሶ መጠገን ወይም የማጠናከር ተግባር ሲሆን፣ አገር ግንባታ ይበልጥ የሚያተኩረው ደግሞ የመንግሥት ሥርዓትን በመጠቀም በዜጎችና በአገሮች መካከል መተማመን መፍጠር የሚያስችል የጋራ የግንኙነት ድልድይ በመገንባትና አብሮነት ሸማና ድር መፍተል ላይ ነው፡፡

የሁለቱ ጽንሰ ሐሳቦች ብያኔ ከላይ በተገለጸው መልኩ ቢሆንም፣ በአብዛኛው የዓለም አቀፍ ተቋማት ዕርዳታዎችና ድጋፎችን የሚሰጡትና የሚውሉት ለመንግሥት  ሥርዓት ግንባታ ሲሆን፣ የአገር ግንባታ ግን የዜጎችና የአገሮች መንግሥት ብቻ የጋራ ስሙር የሥራ ውጤት ነው፡፡ ባለፉት ሥርዓቶች በተለይም የ27 ዓመቱ የኢሕአዴግ ሥርዓት  የሥርዓቱን ህልውና ለማስቀጠል የአገር ግንባታን ወደ ጎን በመተው በዋናነት ያተኮረው መንግሥታዊ አቅም ግንባታ ላይ ማለትም መንግሥት ግንባታ (State Building) ላይ ነው፡፡ ሆኖም የመንግሥት ግንባታው በራሱ፣ በየተቋማቱ ውስጥ በተሰገሰጉ የተደራጁ ሙሰኞችና ነፍሰ ገዳዮች የተጠለፈ ነበር፡፡ በዚህም የመንግሥት  ተቋማት ለጥቂት ግለሰቦች መጠቀሚያ ሆነዋል፡፡ ተቋማቱ ሕዝባዊና አገራዊ ተልዕኳቸውን ስተዋል፡፡ ገለልተኛ መሆን የነበረባቸው የመንግሥት መዋቅሮች በፓርቲ መዋቅሮች ተጠልፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ አገራዊ፣ ማኅበራዊ እሴቶችም ፈራርሰዋል፡፡ በዚህም አሁን ላለንበት የብተና ፉከራ ዋዜማ በቅተናል፡፡

በዘመናዊው ማኅበረሰብ ውስጥ አገራት መሠረታዊ የፖለቲካ መዋቅር አካል ሲሆኑ ወደ ሰው ልጅ የኋልዮሽ ታሪክ ስንመለስ ዓለም በግዛተ አፄዎችና በጎሳ ሥርወ መንግሥታት የተከፋፈለች እንደነበር እናያለን፡፡ ይሁን እንጂ በዘመናችን እነዚህ አፄያዊ መዋቅሮች በሉዓላዊ አገራት ወይም ዴሞክራሲያዊ መራሄ መንግሥታት እንደ አንድ የፖለቲካ አኃድ ተደርገው መዋቀር ጀመሩ፡፡ አገራችን ኢትዮጵያም የዘመናዊው ዓለም አካል እንደመሆኗ መጠን ለአገር ግንባታ ውጣ ውረድ ውስጥ ማለፋችን የማይካድ የታሪካችን አንድ አካል ነው፡፡ ስለሆነም ዜጎቿ ስለአገረ ኢትዮጵያ ግንባታና ውቅር አብዝተን መጨነቅ አለብን፡፡ ሆኖም ግን አገሮች በድንገት የሚበቅሉ ይልቁንም በረዥም ጊዜ የተሰነቀ የዜጎች የራዕይና የድርጊት መስተጋብር ድምር ውጤቶች ናቸው፡፡

በቀደመው ዘመን አገሮች የተመሠረቱት ‹‹በደምና በብረት›› ጫና እንደነበር በርካታ የዓለም የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው ውጤታማ የአገር  ግንባታ ተግባር ለማከናወን ወታደራዊ ግፊትን እንዳስፈላጊነቱ መጠቀም የተገባ መሆኑን ነው፡፡

በዘመናዊ የዓለም ፖለቲካ ውስጥ እንደ አዲስ ዕውቅና እያገኘ ቢሆንም እንኳ የአገር ግንባታ ተግባር የረዥም ዘመን ታሪክ ያለው ነው፡፡ ላለፉት ክፍለ ዘመናት የዓለም ፖለቲካ ካርታ እንዴት በፍጥነት እንደተለዋወጠ ስንቃኝ የምንገነዘበው አንዱ ጉዳይ አገር ግንባታ በርግጥም የዘመናት ክስተት ሆኖ መቆየቱ ነው፡፡

እንደ ዘመናዊ የአገር ግንባታ ጽንሰ ሐሳቦች ትንታኔ ከሆነ ዋና ዋናዎቹ የአገር ግንባታ መርሐ ግብሮች በአገሪቱ ውስጥ አብዛኛውን ማኅበረሰብ የሚያካትት የጋራ ማንነት፣ የተቀናጀ የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ ሁሉን አቀፍ የሲቪል ማኅበረሰብ አቅምን ማጎልበት፣ ባህላዊና ዘመናዊ የግጭት አፈታት ሥልቶች መንደፍና መተግበር፣ እንዲሁም የጋራ የኢኮኖሚ ዕቅዶችን በመንደፍ የአገሮች ነባራዊ የማስተዳደር አቋምን በመደገፍ የአብሮነት መሠረት ማኖር ነው፡፡ በዚህም አገር መገንባት ቅጽበታዊ ግኝት ሳይሆን አዝጋሚ የለውጥ ሒደት ሲሆን፣ ይህም ረዥም ጊዜ የሚወስድና እንዲሁ ከመሬት ተነስቶ ከውጭ መጀመር የማይችል ማኅበራዊ ሒደት ነው፡፡

በዚህም ህንፀተ አገር (Nation Building) ማለት ሆን ተብሎና ታቅዶበት በባለራዕይ መሪዎች፣ በአገሮች አስተዳደራዊ መዋቅር ሥሪት ማዕቀፍ ውስጥ በሚተገበር ተከታታይ ሥራ የሚገኝ ውጤት እንጂ የዕድል ክስተት ውጤት አይደለም፡፡ አገር ግንባታ ሁለት ፈርጆች ያሉት ሲሆን፣ በመጀመርያ ደረጃ በአጠቃላይ ማኅበረሰቡ ተቀባይነት ባላቸው ሕግጋት፣ ደንቦችና መርሆዎች፣ እንዲሁም የዜጎች የጋራ የአመለካከትና ማንነት ላይ በመመሥረት ከግዛት ዳር ድንበር ጋር የተያያዘ አንድ የፖለቲካ ተቋም መገንባት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የፖለቲካ ተቋሙን የሚወክሉ ተቋማትን እንደ የመንግሥት  ቢሮክራሲ፣ ኢኮኖሚ፣ የፍትሕ አካላት፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሲቪል ሰርቪስና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የመሳሰሉትን የሚያመለክቱ ተቋማትን መገንባት ነው፡፡

ከሁሉ በላይ ግን አገር መገንባት ማለት የዜጎችን የጋራ ዓላማዎች፣ የጋራ ዕጣ ፈንታ ስሜት፣ የጋርዮሽ ኅብረትና የእኔነት ስሜት መገንባት ነው፡፡ ስለሆነም አገር ግንባታ ስንል የፖለቲካ ተቋሙን (አገር) በአንድ አስተሳስረው የሚይዙና ተጨባጭ የአብሮነት ስሜት የሚያጎለብቱ የሚታዩና የማይታዩ የአብሮነት ማሰሪያ ድሮችን መፍተልና መሸመን ነው፡፡

የ19ኛው እና 20ኛውን ክፍለ ዘመንን መለስ ብለን ስንቃኝ በጉልህ የሚያመለክተን ነገር ቢኖር በዘመናዊው ዓለም ዓይነተኛ ተጠቃሽ አገር ግንባታ በመከወን ዘላቂነት ያለው አገር ለመመሥረት ብሔርተኛነትና ቅኝ ግዛት ወሳኝ መሠረት ሆነዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶች መሬት የነካና አሳማኝ ክርክር ለማቅረብ ባይደፍሩም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጀርመንና ጃፓን ዳግም የተገነቡበትን በውጭ ኃይል የታገዘ የአገር ግንባታ እንደ ትርክት ያቀርባሉ፡፡

በዚህ ዓለም አቀፋዊነት በተንሰራፋበትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን የሰዎች ዝውውር፣ እንዲሁም የሐሳቦች ቅጽበታዊ እንቅስቃሴ በሚታይበት ክስተት የጋራ ዕጣ ፈንታ የሚጋሩ፣ የጋራ ማንነት ያላቸው በአንድ አገር ውስጥ የታቀፈ ማኅበረሰብ (One Nation State) መኖር የብልፅግና መገለጫ ከመሆኑም በላይ በራሱ ዘመናዊነት ነው፡፡ በተጨማሪም አገር መገንባት ማለት በዚህ ዘመናዊ ዓለምና የቴክኖሎጂ ዕድገት ወቅት የጋራ ማኅበረሰብን ህልውናና አብሮነት የሚደግፉ ተቋማትንና እሴቶችን ማቋቋም ነው፡፡

ይሁን እንጂ አገራችን ኢትዮጵያ በዓለምና በአፍሪካ አኅጉር ውስጥ ያላትን ብሔራዊ ጠቀሜታ ለመግለጽ ‘የአፍሪካ ታላቅ’ በማለት በመጥራት የአገራችንን ጂኦ ፖለቲካዊ አስፈላጊነት የሚገልጹ አንዳንድ አካላት ቢኖሩም፣ ይህ አገራችን በአሁኑ ወቅት ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር በግልጽ የተጋነነ መገለጫ ነው፡፡ በእነዚህ አካላት ዘንድ እንደ ታላቅ የተባበረና ግዙፍ አገር የምንታየው በአገራዊ ተቋማቶቻችን ዘመን ተሻጋሪነት፣ ጥንካሬና ተዓማኒነት፣ በምጣኔ ሀብታችን ብልፅግና፣ እንዲሁም በጋራ አገራዊ እሴቶቻችን ጥራት ወይም በፅኑ መሠረት ላይ በተዋቀረ በአገር ግንባታ ምክንያት ሳይሆን ባለን ቀደምት የነፃነት ታሪክ፣ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ቁጥርና ጥቅም ላይ ባልዋለው የተፈጥሮ ሀብታችን ምክንያት ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የአንድ አገር ታላቅነት የሚገኘውና የሚወሰነው በአገሪቱ የቆዳ ስፋት፣ የሕዝብ ቁጥር ወይም በተፈጥሮ ሀብቷ ብዛት ምክንያት አይደለም፡፡

ቻይናና ህንድ በዓለም ላይ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ቢኖሯቸውም እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ በዓለም አቀፍ መድረክ ከባድ ሚዛን ወይም ጉልህ ተወዳዳሪ መሆን አልቻሉም በሌላ በኩል ጃፓን ያሏት የተፈጥሮ ሀብቶች ጥቂት ቢሆኑም፣ ቅሉ ዓለም አቀፋዊ ከባድ ሚዛን የኢኮኖሚ አቅም ለመገንባት ችላለች፡፡

በአሁኑ ወቅት ባለው ዘመናዊው ዓለም ውስጥ ከብሔር ማንነት ይልቅ ክህሎቶች፣ ታታሪነት፣ ምርታማነትና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት አገራዊ ታላቅነትን የሚወስኑት ነጥቦች ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ የኑክሌር ቦምብ ባለቤትነት እንኳ የዜጎችን ታታሪነትና የፈጠራ ችሎታ፣ እንዲሁም በተጣምሮ ሥራን ሳያካትት አንድን አገር ወደ ታላቅነት ለማራመድ በቂ አይደለም፡፡ ከአዳም ስሚዝ ዘመን ጀምሮ እያንዳንዱ አክራሪ ብሔርተኛና ፖለቲከኛ የአንድን አገር ብልፅግናና ምርጫ የሚለካው አገሮች ባላቸው ሀብትና ግዙፍነት ላይ ተመሥርቶ ሳይሆን፣ በዜጎች ምርታማነትና ታታሪነት መሆኑን ተረድቷል፡፡

በምሁራን ሊቀርብ ከሚገባው ትክክለኛው ጥያቄ አንዱ ምንም እንኳ አገራችን ኢትዮጵያ በውስጧ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሰውና የተፈጥሮ ሀብቶች እያላት የአገር ግንባታ ሥራ ለምን እንዲህ ከባድና አዳጋች ሆነ? ትሩፋቱንስ ለመልቀም ምነው አልተቻለም? ፍሬዎቹስ ምነው ተበታተኑ? ዜጎቿስ የተቸገሩት ለምንድን ነው? የሚለው ነው፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች ሁነኛ መልሶች ለማግኘት በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ አተኩረን ምላሽ መፈለግ እንዳለብን ሐሳብ አቀርባለሁ፡፡

  1. በአገር አቀፍ ደረጃ ለአገር ግንባታ ሒደት እንቅፋት በሚሆኑ የፖለቲካ ከባቢ (የሐሳብና የብሔር ማንነት) ውስጥ የሚፈጥሩ ሥጋቶችና ተግዳሮቶች፣
  2. እነዚህ ተግዳሮቶች ያጋጠሙት የአገሪቱ (የፖለቲካና መንግሥታዊ) አመራር ጥራትና አመራሩ የሚጠቀማቸው የችግር አፈታት ሥነ ዘዴዎችና
  3. በአገራችን ያሉ የፖለቲካ እና የልማት ተቋማት ደካማ ቁመናና ብልሹ አሰራሮች ናቸው፡፡

ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ በኢትዮጵያ ውስጥ ለጠንካራ አገር ግንባታ ሒደት ያለንን ከባቢያዊ ነባራዊ ሁኔታ በጥልቅ በመገምገም ጥንካሬያችንን፣ ድክመቶቻችንን፣ ዕድሎቻችንንና ቁልፍ ተግዳሮቶቻችንን በግልጽ ለይተን ማወቅ ይገባናል፡፡

በተጨማሪም ለጠንካራ አገር ግንባታ ጠቃሚ በሆነ መልኩ የአካባቢን ተፈታታኝ ሁኔታ በመቋቋም ለሚራመዱ የፖለቲካ መሪዎች ጥርጊያ መንገድ የሚያመቻች የአመራር ልማት ምርጫና የተጠያቂነት ሥርዓት መዘርጋት አለብን፡፡

በመጀመርያ ላይ እንዳስቀመጥኩት አገሮች የዜጎች ሰብዓዊ ፈቃድና አርቆ አሳቢነት እንዲሁም የእነርሱን ጥረቶች ለማጠናከር የሚያስችሉ አጋዥ ተቋማት ውጤት ናቸው፡፡ ስለዚህ አገራችንን በመገንባት ረገድ ስኬታማ ለመሆን እነዚህን ሀብቶች በውስጣችን ፈልጎ ማግኘት አለብን፡፡

የአገረ ኢትዮጵያ ግንባታ ተግዳሮቶች (Challenges for Ethiopian Nation Building)

በአሁኑ ወቅት ያለው የለውጥ አመራር እውነተኛ የአገር ግንባታን ከቆመበት አስቀጥላለሁ የሚል ከሆነ በኢትዮጵያ የአገር ግንባታ ፕሮጀክት ሒደት በቀዳሚነት ሊፈቱ የሚገቡ አምስት ዋና ዋና ተግዳሮቶች እንደሚገጥሙት ይታመናል፡፡ እነዚህም፣

  1. ከቀደመ ታሪካችን የሚመጣ ፈታኝ ሁኔታ፣
  2. የማኅበረ ኢኮኖሚያዊ፣ ኢፍትሐዊነት ፈተና፣
  3. በሕግና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ የተፈጠረ የተዓማኒነትና ቅቡልነት ተግዳሮት፣
  4. የዴሞክራሲ ሥርዓት  ግንባታ፣ የሰብዓዊ መብትና የልማት ተቋማት ጥንካሬ ተግዳሮቶችና
  5. የአመራር ቁርጠኝነት፣ ራዕይና የአመለካከት ጥራት ተግዳሮት ናቸው፡፡

እስካሁን ባለን ረዥም የታሪክ ሒደት ለአገር ግንባታ ባደረግነው አስጨራሽ ውጣ ውረድ በርካታ ፈተናዎችን በማለፍ ከሞላ ጎደል አገራችንን በአንድ የማቆየት አንዳንድ መለስተኛ ስኬቶችን አስመዝግበናል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ተጠቃሽ ተግዳሮቶች በአገር ግንባታ ንቁ ተሳታፊ የሆኑ ዜጎቻችንን ችሎታ ሙሉ ለሙሉ እንዳንጠቀም አቅም እያሳጡን ይገኛሉ፡፡

በቀደመ ታሪካችን ካለመግባባት የሚመጣ ተፈታታኝ ሁኔታ

የቀደሙ የኢትዮጵያ ገዥዎች፣ ሥርወ መንግሥታት፣ የአስተዳደር ሥርዓቶችና ታሪካዊ ቅርሶች ባለባቸው ዓድሏዊነት አገራችን ኢትዮጵያን እንደ አገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የተወሰኑ ተግዳሮቶችን ይፈጥራሉ፡፡ በእነዚህ የታሪክ ሁኔታዎች መነሻነት ጭፍን የብሔር ጥላቻ፣ የተበዳይነት ስሜትና የእርስ በርስ ፍርኃትንና አለመተማመንን ለማስፋፋት እጅግ ቀላል ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በሚደረገው ፖለቲካዊ ትግል ውስጥ እንኳ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ያሉ የብሔር መብት ተሟጋቾች፣ ተፎካካሪ ፖለቲከኞችና የብሔር ፓርቲዎች ጨቋኝና ዘረኛ ነው ከሚባለው ከገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ጋር ከሚያደረጉት እልህ አስጨራሽ ትግል በማይተናነስ ደረጃ እርስ በእርስ ይጋጫሉ፣ አንዳንዴም ጦር ሰብቀው ይዋጉ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ታሪክ ይህንን ዓይነቱን ብሔርተኝነት ለማቀንቀን ምቹ መደላድል የመሆኑን ያህል የተግዳሮቱም ምንጭ ነው፡፡ ዳሩ ግን ከሌላው እምነትም ሆነ ባህላዊ አምልኮ ተከታይ ይልቅ ለክርስቲያኑ፣ ከቀሪው የኢትዮጵያ ዜጋ አብልጦ ለነገሥታቱ የሚያደላው የኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ የተጻፈው ለዚህ ዘመን ተስማሚ ሊሆን አይችልም፡፡ የኢትዮጵያ የአገር ሥሪት ታሪክ የማይወጣው ፈተና ውስጥ የገባበት አንዱ ጊዜ በ1950ዎቹ መግቢያ በተነሳው የተማሪዎች ንቅናቄ ነው፡፡ የንቅናቄው ክፋት ፍፁም ከመጽነፉ የተነሳ የየሠውን ልብ በአብዮተኛነት መንፈስ ሞላው፡፡ ማፍረስ ብቻ፣ መንቀል ብቻ ግቡ ሆነ፡፡ ነፍስ ያላወቀው ትውልድ፣ በነቀለው የጋራ እሴትና የአብሮነት ትርክት ፋንታ አዲስ አልተከለም፡፡ ባፈረሰው ታሪክ ምትክ ሌላ አላበጀም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ዛሬ ከገጠሙን ሰብዓዊ ድቀቶች፣ የባህልና የመንፈስ ንቅዘቶች፣ የጋራ ማንነት ዕጦት፣ የብሔር ግጭቶች በርካቶቹ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ከዚህ የቀደመ ታሪክ ጋር የሚዛመዱ ናቸው፡፡

በግልጽ እንደሚታወቀው የአገር ግንባታ ጥብቅ መሠረትን ይጠይቃል፡፡ ይህ ዓይነቱ መሠረት የሚጣለው ደግሞ በጥልቅ ጊዜ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ‹‹ጥልቅ ጊዜ›› ሁለቱን የጊዜ ጽንፎች ‹‹ሩቁን ትናንት ታሪክ››፣ እንዲሁም ‹‹ሩቁን ነገን ራዕይ›› አስተቃቅፎ የሚይዝ ነው፡፡

የቀድሞው የመኢሶን አባል የነበሩት፣ የአሁኑ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበርና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ መረራ ጉዲና (ዶ/ር) ‹‹በኢትዮጵያ ታሪክ የተቃርኖ ትንታኔዎች፣ የአዲስ ስምምነት አስፈላጊነት›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት ጥናታዊ ጽሑፍ በዝርዝር እንደገለጹት በኢትዮጵያ የሚገኙ የብሔር ወይም የዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኞች የመከራከሪያ ሐሳብ የሚመሠረተው በኢትዮጵያ የአገረ መንግሥት  ግንባታ ሒደት ላይ ባላቸው ጽንፍ የረገጠ የታሪክ አረዳድ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

በሌላ መልኩ ታሪክ በታዳሚው ዘንድ ቅቡል የሚሆነው ላቀረበው ትርክት እንደማስረጃ የሚያቀርበው አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ ሲኖረው ነው፡፡ ከእውነታ ተነስቶ፣ ምንጭ ኖሮት በመረጃ የተደገፈ ታሪክ ተቀባይነቱ ከፍ ይላል፡፡ ሆኖም በአብዛኛው የኢትዮጵያ ታሪክ አመዘጋገብና ትርክት መሠረቱ ዜና መዋዕሎች፣ አፈ ታሪክና የመሳሰሉት ሁለተኛ ደረጃ ምንጮች ናቸው፡፡ እነዚህ የታሪክ ማጣቀሻዎች ግን ታሪክ ከሚፈልገው ከአስተማማኝ መረጃ፣ ከተዓማኒነትና ግልጽ እውነታ መሠረት አንፃር የተዛባ ምልከታ ሲፈጥሩ ይስተዋላል፡፡

በእስካሁኑ የኢትዮጵያ ታሪክ አጠናንና አደረጃጀት ታሪካችንን በዘመናዊ መልኩ ለማዘጋጀት የተደረገ እምብዛም ጥረት የለም፡፡ በአብዛኛው እንደ ዘመናዊ የታሪክ ማጣቀሻ ሰነዶቻችን የምንጠቀማቸው ምንጮች በአውሮፓውያን አገር አሳሽ ዜጎች የተጻፉ ሲሆኑ፣ እነዚህ የግል ዜና መዋዕል መጽሐፍት ከተጻፉባቸው ዓላማና ትርክት አንፃር ከፍተኛ የሚዛናዊነት ችግር አለባቸው፡፡ እንዲሁም ሚዛናዊና ዘመናዊ በሆነ መንገድ የተጠኑትና የተሰነዱት የታሪክ መዛግብት ለሕዝቡ በትክክል መድረስ አለመቻላቸው ዜጎች ለተዛባ የታሪክ ትርክት ተጋላጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ በመሆኑም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በአፈ ታሪክ፣ በዜና መዋዕሎችና በወግ መልክ የተመሠረቱ የአንድ ወገን ታሪኮችን እንዲያምን ተደርጓል፡፡

ከእነዚህ የመረጃ ቋቶች የሚቀዱ የታሪክ ድርሳናት አብዛኛውን ሕዝብ ለተሳሳተ የታሪክ ንባብ ከማጋለጣቸውም በላይ፣ ለአገረ ኢትዮጵያ ግንባታ ሥሪት አብዛኛው የታሪክ መንገራገጭ ክፍተት የተፈጠረው ታሪካችን ከባለሙያዎችና ከምሁራን እጅ በኃይል ተፈልቅቆ ወጥቶ ባለ ጊዜና አላዋቂ ፖለቲከኞች እጅ ወድቆ ታሪክ የተወሰኑ ቡድኖች የፖለቲካ ፍላጎት ማሟያና ወገንተኝነት የተጫነው እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ሌላው ወቅታዊ ችግር ደግሞ የኢሕአዴግ መንግሥት ለአገር ግንባታ አንዱ ተግዳሮት የሆነውን ይኼንን የተንሸዋረረ የታሪክ ትርክት በኢትዮጵያ ውስጥ መኖር አምኖ በመቀበል የብሔር ቅራኔ ለመፍታት ዓይነተኛው ምርጫ የ‹‹ብሔር ፌዴራሊዝም›› ነው ብሎ ማመኑ ዋነኛው ሥረ ምክንያት ነው፡፡

ስለሆነም ታሪክና ፖለቲካ በየራሳቸው ዓውዳዊ ፍቺ ተነጣጥለው መታየትም መተርጎምም ይኖርባቸዋል፡፡ ስለሆነም በዚህ የተንሸዋረረ የታሪክ አደረጃጀትና ትርክት የተነሳ ሁላችንንም ሊወክል የሚችል ‹‹የጋራ ታሪካችን›› የምንለው እውነታን መሠረት ያደረገ ታሪክ እንዳይኖረን ሆነናል፡፡ ኢትዮጵያን በአንድ አስተሳስሮ የሚያሻግራት በሁሉም ዜጎች ዘንድ ቅቡልነት ያለው እንደ እስራኤሉ ሙሴ፣ እንደ ደቡብ አፍሪካው ኔልሰን ማንዴላ፣ እንደ ጋናው ክዋሜ ንክሩማህ ያለ በአንድ ማዕከላዊነት አገር ግንባታ ትግሉን የሚያቀጣጥል መሪ እንዳይኖረን ተደርገናል ይልቁንም እያንዳንዱ ክልል የራሱን ጀግና እየፈለገ ይገኛል፡፡

ከዚህ የቀደመ ታሪካዊ ሁነት የተዛባ ትርክት የተነሳ ብሔርተኛነት (አንዳንዴም ጎሰኝነት) በአገረ ኢትዮጵያ ግንባታ ፕሮጀክት ሒደት ላይ ጉልህ ጫና እያሳደረ ዋነኛው የአገር ግንባታ ተግዳሮት ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ የአገራችን መሥራች ነገሥታትና አባቶች ይህንን ፈታኝ ሁኔታ ለመቋቋም ሲሉ የባህላዊ ፌዴራሊዝም ሥርዓትን (ሁሉም ባላባት በሚኖርበት አካባቢ እንዲያስተዳድር በመፍቀድ) የመረጡበት አንዱ ምክንያት በልዩነት ውስጥ ያለን የአንድነት ፖሊሲን ለመደገፍ ነበር፡፡ እንዳለመታደል መንቀል እንጂ ማሳደግ የማያውቀው ሾተላዩ ባህላችን ተንከባክቦ ሳያበቅለው ቀረ እንጂ!!!!

እንደ አለመታደል ሆኖ በብሉዩ የኢትዮጵያ ባህላዊ ፌዴራሊዝም ሥር ዜጎች የሚጋሯቸው ቋሚና የተለመዱ የጋራ እሴቶችና የማንነት ከፍታዎች ላይ በሚታየው ዙሪያ መለስ የአካታችነት ጉድለት የተነሳ በታሪካዊ ሒደት ላይ ተመሥርቶ የተፈጠረው የሐሳብና ትርክት ክፍፍል በአገር ግንባታ ላይ የሚደረገውን ጥረት እጅግ የሚያዳክም ሆኗል፡፡

የዚህ የቀዳሚ ታሪክ ውርስ መገለጫ አንዱ ክስተት በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በገጠርና በዋናነት ደግሞ በከተማ አካባቢዎች በሰፋሪ ዜጎችና በነባር ነዋሪ ተብዬዎች መካከል ያለው ክፍፍልና ተደጋጋሚ ግጭት፣ እንዲሁም ከቦታችን ውጡልን ንትርክ ነው፡፡

ይህ ክፍፍል የየአካባቢያዊ ውጥረት ምንጭ በመሆን ፖለቲካዊ ቀውስ የሚፈጥር፣ እንዲሁም የተባበረ ሕዝብና የጋራ አገር ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያዳክም ብሎም የሚያጠፋ ነው፡፡

የቀደሙ ስህተቶቻችንን ላለመድገም ከታሪካችን በፅኑ መማር ያለብን ቢሆንም፣ የቀደሙ ዘመናት ታሪክ ሰለባ እንደሆንን አድርገን ራሳችንን ማየት የለብንም፡፡ በታሪካችን የተነሳ ያጋጠሙንንና የሚገጥሙንን አስቸጋሪ ፈተናዎች ማሸነፍ የእኛ ኃላፊነት ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያን ታሪክ ከመንግሥታት ሥልጣን አምልኮ፣ ከሃይማኖታዊ ዳራዎች ጥጋት፣ ከአፏዊ ቅብብሎሽ፣ ካላዋቂ ፖለቲከኞች የውግንና ተረክ፣ ከታሪክ ጎዶሎ አቀራረብ፣ እንዲሁም ከቅደም ተከተል አሰዳደር ግድፈት ማፅዳት ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ ከጨቋኝ ተጨቋኝ ብሔሮች ትርክት (The Opperesser Oppressed Dichotomy)፣ ከሰፋሪ ዜጋና ከነባር ነዋሪ የአባራሪ ተባራሪ ንትርክ በአግባቡ ቃኝቶ ማረቅ ያስፈልጋል፡፡

ስለሆነም የታሪክ ድርሳናት፣ አፈ ታሪኮችንና ሌሎች የታሪክ መነሻ ሰነዶችን በአግባቡ የሚተነትኑ ባለሙያዎችን በማስተባበር ለክፉም ሆነ ለደግ ታሪካችን ትርጓሜ በማሰጠት በአንድ አገር ለምንኖር ዜጎች የጋራ ታሪክ እንዲኖረን በማድረግ የጋራ አገር ግንባታ ሒደትን ማፋጠን ይገባል፡፡

የማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ኢእኩልነት (ኢፍትሐዊነት)

የአገር ግንባታ ዋነኛውና አስፈላጊው ፈርጅ በዜጎች መካከል የሚያስማሙ የጋራ ማንነቶችና የጋራ ራዕይ መገንባት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአንድ የአገሪቱ አካባቢ ውስጥ የሚኖረው ሰው በሌላ ቦታ ካለው ሰው ጋር ሲተያይ ፍፁም የተለየ አኗኗር ካለው? ወይም በአንድ የአገራችን ክፍል ውስጥ ያለች አንድ ሴት ልጅ ከሌላ አካባቢ ከምትኖር ሴት ልጅ ይልቅ በወሊድ ወቅት የምትሞትበት ዕድሏ ከፍተኛ ከሆነ? የጋራ ዜግነት ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው? ብሎ አበክሮ መጠየቅ ይገባል፡፡

ፈጣንና ድሃ ተኮር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያለማምጣት፣ እንዲሁም ለሁሉም ዜጎች እኩል የተጠቃሚነት ዕድል ያለማስገኘትም ዋነኛው ተፈታታኝ ችግር ነው፡፡ አንዳንድ በማደግ ላይ ያሉ የዓለም አገሮች የሁሉም ማኅበረሰቦቻቸውንና ዜጎቻቸውን የማኅበረ ኢኮኖሚያዊ የመጠቀም መብት መሠረቶችን በማኅበራዊ ደኅንነት ጥበቃ መረብ አማካኝነት ለማቋቋም ይጥራሉ፡፡

የአገሪቱን ሁሉን ዜጎች በእነዚህ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ መብቶች ላይ ያለማሳተፍ ማለት በጥቅም ተጋሪነት ያልተሳተፉ ጥቂት ሰዎች እንኳ ከአጠቃላይ ብሔራዊ ሕይወት ይገለላሉ ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው በርካታ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ካለማሳተፍ የሚመጣ “ማኅበራዊ ማግለልን” በመከላከል ላይ ያተኮረ ፖሊሲ የተከተሉት፡፡

ነገር ግን በአገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ በርካታ ዜጎች የትምህርትና የጤና አገልግሎቶችን የመሳሰሉ መሠረታዊ መብቶችን ከመጠቀም በአንድም ወይም በሌላ መልኩ ይታገዳሉ፡፡ በተጨማሪም በአገሪቷ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች በእነዚህ መብቶች ተጠቃሚነት ላይ ከፍተኛ ልዩነት አለ፡፡ በውጤቱም ዜጎች ስለመንግሥት ያላቸው አመለካከት የተዛባና በመንግሥታዊ ሥርዓቱ ተጠቃሚ ሆኗል ብለው የሚያስቡትን የኅብረተሰብ ክፍል ያገላሉ፣ እንዲሁም የጥላቻ ስሜት ያጎለብታሉ፡፡ የጥላቻቸው ዋነኛው ምክንያትም አብዛኛው ማኅበረሰብም ሆነ መንግሥት ስለደኅንነታቸው በቂ ትኩረት እንደማያደርግላቸው ስለሚያስቡ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በመላ አገሪቱ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ የሚታየው አለመረጋጋትና ኢእኩልነት በዜጎች ዘንድ በመንግሥት የመረሳት ፍርኃትን በማስፋፋት በጥርጣሬ የተሞሉ ሕዝቦችን አብዝቷል በሒደትም የተከፋፈለና ነውጠኛ ማኅበረሰብ ፈጥሯል፡፡

እነዚህ የኑሮ ልዩነቶች (ኢእኩልነቶች) በአገር ግንባታ ረገድ በሚደረግ እንቅስቃሴ ውስጥ ሁለት እርስ- በርስ የተሳሰሩ ተግዳሮቶችን ይፈጥራሉ፡፡

በመጀመርያ ደረጃ ከፍተኛ የሆነ የማኅበረ ኢኮኖሚያዊ አለመመጣጠን ማለት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የተለያየ ሕይወት ይኖራሉ እንደማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ጤነኛ ልጅ የመውለድ፣ የሕፃናት ያለ ዕድሜ መቀጨት፣ የትምህርትና የክህሎት ሥልጠናዎችን የማግኘት ዕድል ሁሉ ነገር በአገሪቱ ውስጥ ባሉ አካባቢዎች ሁሉ ይለያያል ማለት ነው፡፡ እነዚህ የተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተለያዩ አገሮች  ቢሆኑ ኖሮ አንዳንዶቹ ክፍሎች መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ሲሆኑ፣ ሌሎቹ ደግሞ ከዓለም ደሃ አገሮች የበለጠ ደሆች ይሆናሉ፡፡ ዜጎች በዚህ ዓይነት የተመሳቀለና ኢፍትሐዊ የኑሮ ደረጃ ውስጥ እየኖሩ ባሉበት ሁኔታ ውስጥ ስለአንድ ሉዓላዊ አገር ግንባታ ማውራትም ሆነ የጋራ ዜግነትና የጋራ ማንነት በፍፁም ሊፈጠር አይችልም፡፡ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ኢእኩልነት የአገር ግንባታ መሠረት፣ መሠረት ለሆነው ለጋራ ዜግነትና ማንነት ከፍተኛ የሥጋት ምንጭ ነው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ በአገሪቱ ውስጥ በተሻለ የኑሮ ሁኔታ ይኖራሉ የሚባሉ ዜጎች ባሉበት አካባቢ እንኳን ማኅበራዊ አቅርቦትና የደኅንነት ጥበቃ አሁንም ከዓለም አገሮች  መለኪያ ደረጃዎች አንፃር በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡

ለአብነት በደቡብ ክልል ኦሞ ዞን የኛንጋቶም፣ ዳሰነችና አንዳንድ አካባቢዎች ውስጥ ያሉ የሥራ ዕድል ያልተፈጠረላቸው ዜጎች እንኳ ከጋራ የዜግነት ጥቅም የተገለሉ ናቸው፡፡ ስለሆነም እኛ ዜጎች በአንድ ወገን፣ እንዲሁም መንግሥት፣ አገርና ክልሎች በሌላ ወገን ሆነን ብሔራዊ የማኅበረሰብ ስምምነት ውል (National Social Contract) በመካከላችን መፈራረም ያስፈልገናል፡፡ በአገሪቱና በመንግሥት የሚቀረፁ የሕዝብ ፖሊሲ ቁልፍ ዓላማዎች የተጎጂና የተገለሉ ዜጎችን ፍላጎት ማሟላት መሆን አለባቸው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የፖሊሲ አቀራረብ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች የጋራ አገርና ማንነት፣ እንዲሁም ተመሳሳይ ኑሮ እንዳላቸው እንዲገነዘቡ በማድረግ ለአገራቸው ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያጎለብቱበት የጋራ ልምድ እንዲኖራቸው ያስችላል፡፡ እንዲሁም ነባርና መጤ ሠፋሪ በሚል የነተበ ከፋፋይ የታሪክ ቀመር ላይ ተመሥርቶ በሚደረግ የሀብት ክፍፍል ልዩነት ላይ ከመመርኮዝ ይልቅ በማኅበራዊ የጋራ ዜግነት ላይ መመሠረት የዜጎችን አጠቃላይ ቃል ኪዳን በማጠናከር በጋራ መብቶችና ግቦች ዙሪያ ሰዎችን የሚያስተባብር ሕዝባዊ አወቃቀር ይፈጥራል፡፡

በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ የደሃ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛም ሆነ አነስተኛ ድህነትና አገር ግንባታ በአንድ ሜዳ የማይውሉ ሁለት ተፃራሪ የሆኑ ጓዶች ናቸው፡፡ በአብዛኛው ከሌላው የማኅበረሰብ ክፍል የተነጠሉ ዜጎች በድህነትና መሠረታዊ ፍላጎቶች አለመሟላት የሚጠቁ በመሆኑ፣ በአገሪቱ ልማት ውስጥ በፈቃደኝነት ተገቢውን ሚና እንዲጫወቱ መጠበቅ አይገባም፡፡ ምክንያቱም አገሮች የሚገነቡት በጤናማና ተግባቢ ዜጎች ነው፡፡  

በኢትዮጵያ የአብዛኛውን ሕዝብ የመሠረታዊ ትምህርት፣ የጤናና የመኖሪያ ቤት ተደራሽነትን በእኩልነትና ውጤታማነት ላይ በመመሥረት ማሳደግ ያስፈልገናል፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ ለአገር ግንባታ ሥራ ከዜጐቿ ጋር ለመተባበርና ማኅበራዊ ውህደትን እና ድጋፍን ለማግኘት ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ፍትሐዊነት ለማስፈን ያለመ ጠንካራ የማኅበረሰብ ውል (Social Contract) መመሥረት ያስፈልጋታል፡፡

ይቀጥላል

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles