Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊከ30 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት የመሠረታዊ አገልግሎት ተጠቃሚ አይደሉም ተባሉ

ከ30 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት የመሠረታዊ አገልግሎት ተጠቃሚ አይደሉም ተባሉ

ቀን:

በኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች ከሆኑ 41 ሚሊዮን ሕፃናት መካከል 36 ሚሊዮን ያህሉ ወይም 18 ዓመት በታች ከሚገኙ ሕፃናት መካከል 88 በመቶዎቹ ለኑሮ መሠረታዊ የሆኑ አገልግሎቶችን ማግኘት እንደማይችሉ ተገለጸ፡፡ ሕፃናቱ  ካላገኙት መሠረታዊ አገልግሎቶች መካከል የተመጣጠነ ሥርዓተ ምግብ፣ ጤና፣ ውኃ፣ ትምህርት፣ ከጤና ጋር የተያያዘ ዕውቀት፣ መረጃና አሳታፊነት ይገኙበታል፡፡ ሰነዱን ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ከተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ጋር በመተባበር ያወጣው መልቲ ዳይሜንሽናል ቻይልድ ዲፕሪቬሽን ሪፖርት ነው፡፡

ጥር 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ይፋ የሆነው ሪፖርት እንዳመለከተው፣ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ከሚያገኙ 36 ሚሊዮን ሕፃናት መካከል 13 ሚሊዮን የሚሆኑት ከደሃ ቤተሰብ የወጡ ሲሆን፣ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡

ሪፖርቱ የመሠረታዊ አገልግሎት ዕጦት በስፋት የሚታየው ከከተሞች ይልቅ በገጠር እንደሆነም ያሳያል፡፡ የችግሩ ስፋትና ጥልቀትም ከክልል ክልል የተለያየ መሆኑም ተካቷል፡፡ 94 በመቶ የሚሆኑት በገጠር የሚኖሩ ሕፃናት፣ በከተማ ደግሞ 42 በመቶ ሕፃናት ከላይ ለተጠቀሱት አገልግሎት ተደራሽነት የላቸውም፡፡ በኦሮሚያ ክልል 16.7 ሚሊዮን፣ በደቡብ ክልል 8.8 ሚሊዮን፣ በአማራ ክልል 8.5 ሚሊዮን ሕፃናት ሲሆኑ፣ በሐረር 90,000፣ በድሬዳዋ 156,000፣ በጋምቤላ ደግሞ 170,000 ደሃ ሕፃናት መሠረታዊ ፍላጎታቸው ሳይሟላ እንደሚኖሩ አመልክቷል፡፡

- Advertisement -

በአዲስ አበባ 18 በመቶ፣ በአፋር፣ በአማራ፣ በደቡብ ክልሎች 91 በመቶ፣ በኦሮሚያ 90 በመቶ፣ እንዲሁም በሶማሌ ክልል 90 በመቶና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 89 በመቶ ሕፃናት በድህነት ውስጥ እንደሚኖሩ ሪፖርቱ ያትታል፡፡

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የልማት አጀንዳ የሆነውን ዘላቂ የልማት ግብ ከ2007 ዓ.ም. እንደተቀበለች፣ በዚህም አጀንዳ በድህነት አረንቋ ውስጥ የሚገኙ ሕፃናትን፣ ሴቶችንና ወንዶችን ቁጥር እስከ 2042 ዓ.ም. ድረስ በግማሽ ለመቀነስ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኗም አመላክቷል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሕፃናት ከአዋቂዎች በተለየ በሰው ልጆች ላይ የዕድሜ ልክ ተፅዕኖ መፍጠር ለሚችሉና በቀላሉ ሊቀለበሱ ለማይቻሉ ችግሮች የተጋለጡ ናቸው፤›› ያሉት የዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ተወካይ ሚስ ጊሊያን ሚልሰን ናቸው፡፡ ሚስ ጊሊያን በኢትዮጵያ ለመፍጠር የሚሞከረው ጠንካራ ኢኮኖሚ ልማት፣ በአጠቃላይ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመግባት የሚደረገው ሩጫ በልጆች አካላዊ ዕድገት፣ የማገናዘብ አቅም፣ ማኅበራዊ ልማት ላይ ከሚደረገው ኢንቨስትመንት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ሚስ ጊሊያን ከድህነት ለማላቀቅ የበኩሉን ዕገዛ ያደርጋል ተብሎ የታመነበትን ዘላቂ የልማት ግቦችን ኢትዮጵያ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ፕላን ውስጥ በማካተት እንደሌሎች አገሮች ሁሉ አሁን ያለውን የድህነት መጠን በግማሽ ለመቀነስ ያነገበችውን ራዕይ ለማሳካት ጊዜና ትዕግሥት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የዩኒሴፍ ራዕይም ከሕፃን ድህነት ነፃ የሆኑች ኢትዮጵያን ማየትና የፆታ፣ የመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና የማኅበራዊ ኢኮኖሚ ሁኔታ ልዩነት የሌለበት ሁሉም ሕፃናት የሥርዓተ ምግብ፣ የንፁህ ውኃና ሳኒቴሽን፣ ቤትና ፍትሐዊ ትምህርት የማግኘት ዋስትናቸው የተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ መሆኑን ተወካይዋ አስረድተዋል፡፡

የሕፃናት ድህነት በፍጥነት ለመቀነስ እንዲቻል ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች መከናወን እንዳለባቸው ሚስዝ ጊሊያን ገልጸዋል፡፡፡ ከጉዳዩም መካከል አንደኛው የሕፃናትን ድህነት ለመቀነስ ብሎም ለማጥፋት የሚያስችል ብሔራዊ አቅጣጫ መቀየስ፣ የድህነቱን መጠን ደረጃ እንደደረሰ የሚከታተል ተቋም መመሥረትና የሕፃናት ድህነት ቅነሳ ጉዳይን የተመለከተ ነገር በሦስተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ፕላን ውስጥ በግልጽ መቀመጥ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ፣ ‹‹ኢትዮጵያ የሕፃናትን ድህነት በግማሽ በመቀነስ የዘላቂ ልማት ግብን ውጤታማ ማድረግ የምትችለው የሕፃናትን የድህነት መጠን በየዓመቱ አራት በመቶ መቀነስ ከቻለች ነው፤›› ብለዋል፡፡

የሕፃናትን የድህነት መጠንን ለመቆጣጠርና ለመቀነስ መንግሥት ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አቶ ቢራቱ ጠቁመው፣ ለዚህም ከመንግሥት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች፣ አካዴሚክ ተቋማት ፖሊሲዎችን በመቅረፅና በሌላም ተግባራት ሊተባበሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...