Thursday, September 21, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ጥራዝ ነጠቅነት የአገር ጠንቅ እየሆነ ነው!

የ19ኛው ክፍለ ዘመን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሊቅ ጀርመናዊው ካርል ማርክስ ከተናገራቸው መሠረታዊ ነጥቦች መካከል አንዱ፣ ‹‹ፈላስፎች ዓለምን በተለያዩ መንገዶች ተርጉመዋል፣ ዋናው ቁም ነገር ግን ዓለምን መለወጥ ነው፤›› የሚለው ይገኝበታል፡፡ ይህ ጥልቅ እሳቤ የሰው ልጅ ከአካባቢው ጀምሮ ሰፊው ዓለም ድረስ፣ ይህ ነው የሚባል ለውጥ እንዲያመጣ ትምህርት መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ ትምህርት ደግሞ ዓለምን ለመለወጥ የሚያስችል ብርቱ ኃይል ያለው መሣሪያ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ትምህርት ቤት የሚኬደው ደግሞ ከራስ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ ዕውቀት ለማግኘት ነው፡፡ በትምህርት ዓለም፣ ‹‹አንድ መጽሐፍ፣ አንድ ብዕር፣ አንድ ተማሪና አንድ መምህር ዓለምን ይለውጣሉ፤›› የሚለው አባባል በስፋት ይታወቃል፡፡ የላቀ ሐሳብ የሚገኘውም በዚህ ሒደት ነው፡፡ የተማረ ሰው በዚህ ደረጃ ሳይገኝ ሲቀር ግን በኢትዮጵያ አንድ የተለመደ አባባል አለ፡፡ ‹‹የጋን ውስጥ መብራት›› ይባላል፡፡ በዚህ ዘመን ዕውቀት ይዘው የጋን ውስጥ መብራት የሆኑ ብዙ ናቸው፡፡ በጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት አገር የሚያምሱም እየበዙ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ዘለቄታዊ የሆነ ለውጥ ማምጣት የሚቻለው፣ በትምህርት ላይ የተመሠረተ ዕውቀትና ልምድ ከትውልድ ወደ ትውልድ መሸጋገር ሲችል ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ግን ጥራዝ ነጠቅነት አገር ያጠፋል፡፡

የ19ኛው ክፍለ ዘመን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተንታኙ ኢትዮጵያዊው ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፣ በወቅቱ በኢትዮጵያ በነበረው ሥርዓት ላይ ጠንካራና አስገራሚ ትችትና ትንተና ያቀረቡ ዝነኛ ምሁር ነበሩ፡፡ እሳቸው በዚያን ዘመን እንኳን ኢትዮጵያውያን የአውሮፓ የኢኮኖሚ ምሁራን ያልደረሱበትን ትንተና በማቅረብ፣ የሕዝብ አስተዳርና የአገር ኢኮኖሚ እንዴት መመራት እንዳለበት ምክረ ሐሳቦች አቅርበዋል፡፡ በተለይ ‹‹መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር›› በሚባለው ታዋቂ ጽሑፋቸው ቀድመው ያነሱዋቸውን ሐሳቦች፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በአሜሪካና በአውሮፓ ሳይንቲስቶች እንደተፈጠሩ በዚህ ዘመን ብዙ ተመራማሪዎች እንደሚያውቁ የኢኮኖሚ ምሁሩ ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር) በጥናታቸው አስታውቀዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ ነጋድራስ የዛሬ መቶ ዓመት ገደማ የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግሮች ብለው ምሁራዊ ትንታኔና የፖሊሲ አቅጣጫ ያሳዩባቸው ጉዳዮች፣ በሚያሳዝንና በሚያሳፍር ሁኔታ ዛሬም ያሉና በምክራቸው መጠቀም አለመቻሉን በቁጭት አውስተዋል፡፡ እኝህን የመሰሉ የረቀቁና የመጠቁ ሊቅ ያፈራች አገር ውስጥ ዕውቀትን ከማዳረስ በላይ ለጥራት ትኩረት በመነፈጉ፣ አገር የጥራዝ ነጠቆች መጫወቻ ሆናለች፡፡ በኢኮኖሚ ትንታኔው ዓለምን የመራ አርቆ አሳቢ የፈጠረች አገር የዓለም ጭራ መሆኗም ያንገበግባል፡፡ ጥራዝ ነጠቅነት አገር ያጠፋል፡፡

ጥራዝ ነጠቅነት ከሚገለጽባቸው መሠረታዊ ነገሮች መካከል ዋናዎቹ አርቆ አለማሰብ፣ ስግብግብነት፣ ክፋት፣ ሴረኝነትና ለአገር አለማሰብ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በዚህ ዘመን ብሔርተኝነትን ሙጭጭ ብለው የያዙ ወገኖች አገርን የምታህል የጋራ ቤት ዘንግተው ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ተጥደዋል፡፡ ከእነሱ አመለካከት ውጪ ምንም ነገር ማዳመጥ ስለማይሹ፣ ተቃራኒ የሚሉትን በሙሉ በጠላትነት ይፈርጃሉ፡፡ የእነሱ ድርጊት በዚህ አያበቃም፡፡ ብሔርን በጎሳና በጎጥ እየከፋፈሉ ስለሚሻኮቱ እርስ በርስም አይግባቡም፡፡ ከዘመነ መሣፍንት ጋር ተቀራራቢ በሆነ አስተሳሰብ ላይ ተጥደው፣ ሐሳብን በሐሳብ ከመሞገት ይልቅ ልዩነትን በነፍጥ ለመፍታት ይጋበዛሉ፡፡ በሌላ በኩል ከዴሞክራሲያዊ መሠረታዊ ሕጎች በማፈንገጥ፣ ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ደንታ የላቸውም፡፡ ለቢጤዎቻቸው እንጂ ለሰብዓዊ ፍጡራን ነፃነት፣ ፍትሕና እኩልነት ግድ ስለሌላቸው፣ የዘወትር ነጠላ ዜማቸው ‹‹እኛ›› እና ‹‹እነሱ›› የሚል ዲስኩር ነው፡፡ ከዕውቀት ነፃ ስለሆኑ የሚቀናቸው ዘለፋና ስድብ ሲሆን፣ ለውይይትና ለድርድር በራፋቸው ዝግ ነው፡፡ በሕዝብ ስም ቢምሉም ዋናው ትኩረታቸው ዝና፣ ሥልጣንና ጥቅም ላይ ነው፡፡ በሕዝብ ስም እየነገዱ ዓላማቸውን ካሳኩ በኋላ የሚንደረደሩት አምባገነን ለመሆን ነው፡፡ የጥራዝ ነጠቅነት ግቡ ይኼ ነው፡፡

አርቆ ባለማሰብና በስግብግብነት የተለከፉት ደግሞ ዋና መለያቸው ጥላቻ ነው፡፡ የገዛ ወገናቸውን ያሰቃያሉ፣ ይገድላሉ፣ ያፈናቅላሉ፡፡ ለሰብዓዊነት ክብር ስለሌላቸው በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ሸሽተው የተጠለሉ የጎረቤት አገር ስደተኞችን ከመጥላት አልፈው አደጋ ያደርሱባቸዋል፡፡ ለእነሱ ሕዝብና አገር ከጥቅሞቻቸው በታች ናቸው፡፡ የአገር ክብርና ሉዓላዊነት አይገባቸውም፡፡ ታሪክን እያዛቡ ስለሚረዱ የአገር ባለውለታዎችን ማንቋሸሽ፣ ታላላቅ አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን የጋራ እሴቶች መናድ፣ የአገር ተቆርቋሪዎችን መዝለፍ፣ ሞራላዊና ሥነ ምግባር የጎደላቸው ድርጊቶችን ማስፋፋት፣ ሥርዓተ አልበኝነትን ማንገሥ፣ በአሉባልታ አገር ማሸበር፣ የንፁኃንን ደም ማፍሰስ፣ ወዘተ. መገለጫዎቻቸው ናቸው፡፡ በሴራ ፖለቲካ የተካኑ በመሆናቸው ለሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ባዕድ ናቸው፡፡ አስተሳሰባቸው የሚቀዳው ከጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት በመሆኑ ስም ማጥፋት ዋናው ሥራቸው ነው፡፡ የሚሠሩትን አላሠራም ማለት ብቻ ሳይሆን፣ የሥራ ባህል ጠፍቶ አገር የስንፍና መጫወቻ እንድትሆን ያመቻቻሉ፡፡ ጥራዝ ነጠቆች የበላይነት ከያዙ የትውልዱ ዕጣ ፈንታ ያሳስባል፡፡

ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ናት፡፡ ታላላቅ ገድሎች የተከናወኑባት ታሪካዊት አገር ናት፡፡ በተለያዩ መስኮች አገራቸውን በታላቅ ትጋትና የኃላፊነት ስሜት ያገለገሉ፣ ለትውልድ አርዓያ የሆኑና የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ብርቅዬ ኢትዮጵያውያን እናትም ናት፡፡ የእነዚህን ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ገድል እያስተማሩ ትውልድን በዕውቀት መቅረፅ ሲገባ፣ ሕዝብን በብሔር እየከፋፈሉ ለማፋጀት መነሳት ጥራዝ ነጠቅነት ነው፡፡ የፖለቲካ ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ በመፍታት ለአገር በአንድነት መቆም ሲገባ፣ ግጭት እየቀሰቀሱ ንፁኃንን መግደልና ማፈናቀል ጥራዝ ነጠቅነት ነው፡፡ ለዴሞክራሲዊያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚረዱ አስተዋጽኦዎችን ማበርከት ሲቻል፣ በተቃራኒው መሣሪያ ታጥቆ መፎከር ጥራዝ ነጠቅነት ነው፡፡ ኢትዮጵያን የነፃነት፣ የፍትሕና የእኩልነት አምባ ማድረግ እየተቻለ በሕዝብ ላይ መቆመር ጥራዝ ነጠቅነት ነው፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንደ ዘመነ መሣፍንት ኬላ እየፈጠሩ መንገድ መዝጋት፣ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ማቋረጥ፣ የመዘዋወር መብትን ማገድና በአጠቃላይ የአገር ኢኮኖሚን ማሽመድመድ ጥራዝ ነጠቅነት ነው፡፡ በዕውቀት ላይ በተመሠረተ ሥልጣኔ ወደፊት መራመድ ሲገባ ወደ ኋላ እየተንሸራተቱ አገርን አዘቅት ውስጥ መክተት ጥራዝ ነጠቅነት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አሳፋሪና አሳዛኝ ድርጊት ውስጥ ተዘፍቆ መኩራራትና አገር የሚያጠፋ ጥራዝ ነጠቅነት የአገር ጠንቅ ነው መባል አለበት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...

በሰጥቶ መቀበል መርህ መደራደርና ሰላም ማስፈን ለምን ያቅታል?

በያሲን ባህሩ አገር ግንባታ የትውልድን ትልቅና ታሪካዊ ኃላፊነት የሚጠይቅ ተግባር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...

ለሕዝብና ለአገር ክብር የማይመጥኑ ድርጊቶች ገለል ይደረጉ!

የአዲሱ ዓመት ጉዞ በቀናት ዕርምጃ ሲጀመር የሕዝብና የአገር ጉዳይን በየቀኑ ማስታወስ ግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ልማትና ዕድገት ያስፈልጋሉ ከሚባሉ ግብዓቶች...