Wednesday, October 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሪል ስቴት ኩባንያዎች ላይ የተጣለው ዕግድ እንዲነሳ መመርያ ተሰጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመሬት ቢሮ ያቆመውን አገልግሎት በድጋሚ መስጠት ጀመረ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ለሪል ስቴት ኩባንያዎች መስጠት አቁሞ የነበረውን አገልግሎት በድጋሚ መስጠት እንዲጀምር መመርያ ሰጡ፡፡ ፍርድ ቤት እንጂ የፌዴራል ፖሊስ የማገድ ሥልጣን ስለሌለው፣ የሪል ስቴት ኩባንያዎች ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ምክትል ከንቲባው ጨምረው መመርያ ሰጥተዋል፡፡

በሪል ስቴት ልማት ዘርፍ የተከሰተውን ችግር ለመፍታት ረቡዕ ጥር 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ምክትል ከንቲባው ከሪል ስቴት ኩባንያዎች ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት ሁለት ጉዳዮች ነጥረው የወጡ ሲሆን፣ የመጀመርያው በከተማው አስተዳደር መሟላት የነበረባቸው ግን ደግሞ ያልተሟሉ አገልግሎቶች ለዘርፉ ዕድገት ማነቆ መሆናቸው ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ዋነኛ የሪል ስቴት ተዋናዮች በገቡት ውል መሠረት ግንባታቸውን አካሂደው ለደንበኞቻቸው ያለማስረከባቸው ነው፡፡

ከእነዚህ ነጥቦች በተጨማሪ ከአንድ ወር በፊት የፌዴራል ፖሊስ፣ በወንጀል የጠራጠራቸውን 28 የሪል ስቴት ኩባንያዎች እንዲታገዱ ለክፍላተ ከተሞች ደብዳቤ መጻፉ የተፈጠረው ችግር ነው፡፡ ከተዘረዘሩት 28 ሪል ስቴት ኩባንያዎች መካከል፣ በሪል ስቴት ልማት ምንም ተሳትፎ እንደሌላቸው የገለጹና በዝርዝሩ ውስጥ በመካተታቸው ብቻ ሌሎች ሥራዎቻቸው ላይ ተፅዕኖ በመፍጠሩ እንዲስተካከል የጠየቁም አሉ፡፡ 

ምክትል ከንቲባው በሰጡት መመርያ በሪል ስቴት ልማት ዘርፍ በአስተዳደሩና በግል ተዋናዮች በኩል ያሉ ችግሮችን ለይቶ፣ በግንባታ ቦታ ላይ ተገኝቶ ችግሩን የመፍታት ሥልጣን የተሰጠው ግብረ ኃይል ተቋቁሟል፡፡

ግብረ ኃይሉ በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የሚመራ ነው፡፡ ከፕላን ኮሚሽን፣ ከኮንስትራክሽን ቢሮ፣ ከገቢዎች ቢሮ፣ ከግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣንና ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት የተውጣጡ አባላት ይኖሩታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከሪል ስቴት ኩባንያዎች በተለይም ፀሐይ ሪል ስቴትና ሰንሻይን ሪል ስቴት የተካተቱ ሲሆን፣ ግብረ ኃይሉ የሚያካሂደውን ሥራ ምክትል ከንቲባው በቀጥታ እንደሚከታተሉ ታውቋል፡፡

ግብረ ኃይሉ ይፈታዋል ተብሎ የሚጠበቀው የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የሚሰጠው አገልግሎት የተሟላ ስለመሆኑ በተለይም በካርታ አሰጣጥ፣ በስም ዝውውር፣ እንዲሁም በውሉ መሠረት የመሠረተ ልማት ዝርጋታ በተለይ መንገድ፣ ኤሌክትሪክ፣ ቴሌኮም፣ የውኃና የፍሳሽ መስመሮች ዝርጋታን ያካትታል፡፡

በግሉ ዘርፍ በኩል ደግሞ መሬት አስፋፍቶ መያዝ፣ በተሰጠው የፕላን ስምምነት ግንባታ አለማካሄድ፣ የሊዝ ክፍያ በአግባቡ አለመክፈልና በውል መሠረት ለደንበኞች ቤት አለማስረከብ ተለይተው ውሳኔ ከሚሰጥባቸው ተርታ ተመድበዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከ700 በላይ ቤት ገዥዎች የተለያዩ ችግሮች እየደረሰባቸው መሆኑን ለአስተዳደሩ ቅሬታ አቅርበው፣ መፍትሔ እንዲሰጣቸው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

ምክትል ከንቲባው እንደተናገሩት፣ ግብረ ኃይሉ በሁለት ሳምንታት ውስጥ ሥራውን ያጠናቅቃል፡፡

ወቅታዊ ችግር ሆኖ የቀረበው ሌላው ጉዳይ ፌዴራል ፖሊስ ታኅሳስ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. 28 የሪል ስቴት ኩባንያዎችን አግዶ እያጣራ መሆኑ ከተገለጸ በኋላ፣ የተከሰተው የገበያ ችግር ይገኝበታል፡፡

ይህ ጉዳይ በወቅቱ የተሰበሰቡ የሪል ስቴት ኩባንያዎች ከፍተኛ ችግር እየደረሰባቸው መሆኑን ከገለጹ በኋላ፣ ምክትል ከንቲባው አስተያየት ሰጥተውበታል፡፡

‹‹አገሪቱ በሕግ ነው የምትመራው፡፡ ፍርድ ቤት እስካላገደ ድረስ የማንም ሰው ቢዝነስ አይታገድም፡፡ ፖሊስ አጣራለሁ ካለ ያጣራ፣ አጣርቶ ሲያበቃ አትሽጥ ማለት አይችልም፡፡ ንብረት አትሽጥ የሚለው ፍርድ ቤት ነው፡፡ ፍርድ ቤት እስካላገደ ድረስ ቢዝነስ ይቀጥላል፤›› ሲሉ ምክትል ከንቲባው የዕግዱ ጉዳይ ተቀባይነት እንደሌለው ለተሰብሳቢዎቹ ገልጸዋል፡፡

በዚህ መሠረትም የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ያቆመው አገልግሎትና በፖሊስ ዕግድ ምክንያት የተደነቃቀፈው የሪል ስቴት ገበያ፣ በምክትል ከንቲባው መመርያ በመነሳቱ ጭምር የሪል ስቴት ገበያ ወደ ቀድሞ መረጋጋቱ እንደሚመለስ ይጠበቃል፡፡

በወቅቱ የተካሄደው ውይይት በመግባባት የተጠናቀቀ በመሆኑ፣ የነበሩ ችግሮችን ከመሠረቱ እንደሚፈታ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሪል ስቴት ኩባንያዎች ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ 139 ሪል ስቴት ኩባንያዎች፣ በአጠቃላይ ከአሥር ሔክታር እስከ 50 ሔክታር የሚደርስ መሬት ወስደዋል፡፡

ኩባንያዎቹ በአጠቃላይ 560 ሔክታር መሬት የተረከቡ ሲሆን፣ እስካሁን 9,963 ቤቶችን ለደንበኞቻቸው አስረክበዋል፡፡ በ2003 ዓ.ም. በተደረገ ማጣራት 19 ኩባንያዎች ችግር እንዳለባቸው በመረጋገጡ የሊዝ ውላቸው የመከነ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ በከተማው 120 ሪል ስቴት ኩባንያዎች በሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ሥር የሚገኘው የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ጥላሁን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሪል ስቴት አልሚዎች እስካሁን ማስተላለፍ የነበረባቸው 27 ሺሕ ቤቶችን ነበር፡፡ ነገር ግን እስካሁን ያስተላለፉት አሥር ሺሕ የማይሞሉ ቤቶችን ብቻ መሆኑን ጠቁመው፣ በአሁኑ ወቅት 16 ሺሕ የሪል ስቴት ቤቶች በግንባታ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡        

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች