Thursday, June 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ790 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያስወጣ የስድስት የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች ግንባታ ጨረታ ሊወጣ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለ13 የኃይል ማመንጫዎች ግንባታ ከ5.2 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል  

በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት (መግአ) ቦርድ አማካይነት እየታዩ ከሚገኙ 16 ሜጋ ፕሮጀክቶች ውስጥ ስድስት የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች ግንባታ በ795 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ሊካሄድ፣ የአዋጭነት ጥናቶችና የጨረታ ሥራዎች ዝግጅት መጀመሩን ገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ 250 ሜጋ ዋት የሚያመነጩ የሁለት ፕሮጀክቶች ጨረታ በቅርቡ ይጀመራል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ተሾመ ታፈሰ (ዶ/ር) ሐሙስ ጥር 9 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ስድስት የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ለኢንቨስትመንት ዝግጁ በመሆናቸው፣ ለዓለም አቀፍ ጨረታ የሚቀርቡበት መንገድ እየተመቻቸ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ከስድስቱ መካከል በአፋርና በሶማሌ ክልሎች እንደሚገነቡ የሚጠበቁትና እያንዳንዳቸው 125 ሜጋ ዋት ኃይል እንደሚያመነጩ የሚጠበቁትን ፕሮጀክቶች ለመገንባት፣ ፍላጎቱ ላላቸው ተጫራቾች የጨረታ ሰነድ እንዲያቀርቡ ለማድረግ ዝግጅት ተጠናቋል፡፡ ለተቀሩት አራት የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎችም ኩባንያዎች ያላቸውን አቅምና ብቃት የሚያሳዩ ሰነዶችን እንዲያቀርቡ የሚደረግበት ሒደት ይጀመራል ተብሏል፡፡

 በአፋር ክልል ‹‹ስኬሊንግ ሶላር ዲቼቶ››፣ እንዲሁም ‹‹ስኬሊንግ ሶላር ጋድ›› በሚል የፕሮጀክት ስያሜ በሶማሌ ክልል የሚገነቡት እነዚህ ፕሮጀክቶች፣ በዓለም ባንክ ዕገዛ በተለይም በዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን የቴክኒክ ዕገዛ፣ የግሉና የመንግሥት ዘርፍ አጋርነት ከመመሥረቱም ቀድሞ የአዋጭነት ጥናት ተደርጎባቸው መገንባት እንደሚችሉ መረጋገጡን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በመሆኑም ተጨማሪ ጥናት ሳያስፈልጋቸው ወደ ጨረታ ሒደት እንዲገቡ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ ለሁለቱ ፕሮጀክቶች በምዕራፍ አንድ ግንባታቸው ወቅት ለእያንዳንዳቸው 150 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ሁለቱን የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በሁለት ምዕራፍ እስከ 500 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ሥራ ለማከናወን የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ ኃላፊዎች ለሪፖርተር አስታውቀው ነበር፡፡ በሒደቱ የግል ኩባንያዎች የኤሌክትሪክ ኃይል በራሳቸው አመንጭተው ለመንግሥት በሽያጭ የሚያቀርቡበት ስምምነት (ኢንዲፔንደንት ፓወር ፐርቼዝ) መሠረት እንደሚገነቡም ይጠበቃል፡፡

ከጋድና ከዲቼቶ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በመቐለ፣ በሑመራ፣ በወለንጪቲ፣ በወራንሶ (አፋር)፣ በመተማና በሁርሶ (ድሬዳዋ) እንደሚገነቡ የሚጠበቁት ስምንት የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች በጠቅላላው አንድ ሺሕ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያስገኙ ሲጠበቅ፣ የግንባታ ወጪያቸውም ከ1.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚገመት፣ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ይፋ አድርጎ ነበር፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር የተቋቋመው ዳይሬክቶሬት ጄኔራሉ በቦርድ እየተመራ ከፀሐይ ኃይል በተጨማሪ አምስት ከውኃ ኃይል የሚያመነጩ ግድቦችን፣ እንዲሁም ሦስት የፍጥነት መንገዶችን ጨምሮ በጠቅላላው 16 ፕሮጀክቶችን በግልና በመንግሥት ተቋማት ትብብር እንዲለሙ የማድረግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ የገናሌ ዳዋ አምስት፣ የገናሌ ዳዋ ስድስት፣ የጨሞጋ የዳ አንድና ሁለት፣ የዳቡስ፣ እንዲሁም የሀሌሌ ወራቤሳ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ሲገነቡ 2000 ሜጋ ዋት ኃይል እንደሚያስገኙ ይጠበቃል፡፡ ለእነዚህ ፕሮጀክቶችም ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ይገመታል፡፡ ከአዳማ አዋሽ፣ ከአዋሽ ሜኤሶ፣ እንዲሁም ከሜኤሶ ድሬዳዋ ድረስ 357 ኪሎ ሜትር ለሚገነቡ ሦስት የፍጥነት መንገዶችም ከ1.12 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ሲታወቅ፣ ለ16ቱም ፕሮጀክቶች የሚያስፈልገው ገንዘብ በጠቅላላው ከ6.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ይገመታል፡፡ ከዚህ ቀደም ለጋድና ለዲቼቶ ፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች ግንባታ ወጥቶ በነበረው ጨረታ 140 የውጭ ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን መግለጻቸውንና ሰነድ ማስገባታቸውን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ከእነዚህ ውስጥ 28 ያህሉ ብቁ ሆነው በመገኘታቸው በአሁኑ ሒደት ውስጥ እንዲሳተፉ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ፕሮጀክቶች በግሉ ዘርፍ ፋይናንስ የሚገነቡ ሲሆን፣ መንግሥት በእያንዳንዱ ፕሮጀክት ላይ ለገንዘብ የተከፈለውን ጥቅም የማረጋገጥና በፕሮጀክት ባለድርሻነት የሚሳተፍባቸው እንደሚሆኑ ሚኒስትር ዴኤታ ተሾመ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ መንግሥት እንደ ፍላጎቱ ገንዘብ በማዋጣት የሚሳተፍባቸው ፕሮጀክቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያብራሩት ኃላፊው፣ በአብዛኛው የግሉ ዘርፍ ብዙም የመሳተፍ ፍላጎት ባላሳየባቸው በእንዲህ ያሉት ትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ መንግሥት ለፕሮጀክቶቹ የሥጋት ተጋሪ በመሆንና ዋስትና በመግባት እንደሚሳተፍ ተብራርቷል፡፡

ሥጋታቸውን በመጋራት ዋስትና ተሰጥቷቸው እንዲሳተፉ የሚጋበዙት ኩባንያዎች ለ20 ዓመታት የሚቆይ ስምምነት በመፈረም፣ በመንግሥት የታመነበትና ቁጥጥር የሚደረግበት ታሪፍ በማውጣት አገልግሎት የሚሰጡበት የጋራ ኩባንያ እንደሚመሠርቱም ይጠበቃል፡፡ መንግሥት በሚያወጣላቸው ታሪፍ መሠረት ኩባያዎች አገልግሎቶችን እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል፡፡ ለአብነት የተነሳው የፍጥነት መንገድ ሲሆን፣ በዚህ መስክ በግንባታ የተሳተፉት ኩባንያዎች፣ በመንግሥት ታሪፍ መሠረት አገልግሎቱን እንዲያቀርቡና ክፍያውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ዕድሉ እንደሚፈጠር ተብራርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች