Sunday, June 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹እግር ኳስ ብሔርና ዘር የለውም›› አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ፣ የቀድሞ የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ከዘመናዊ ስፖርት ጋር መተዋወቅ የጀመረችው በ20ኛው ምዕት ዓመት የመጀመርያ ሩብ በትምህርት ቤቶችና በውጭ ማኅበረሰብ አማካይነት መሆኑ ይወሳል፡፡ በተለይ እግር ኳስ ነዋሪነታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በነበሩ የጣሊያን፣ የህንድ፣ የአርመንና የግሪክ ዜጎች አማካይነት ከ1916 ዓ.ም. ጀምሮ መዘውተር መጀመሩ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ እግር ኳስ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ስፖርቶች ዓለም አቀፋዊ ቅርፅና ይዘት ኖሯቸው ይቀጥሉ ዘንድ በተለይ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስዱ አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ያስረዳሉ፡፡

በወቅቱ የስፖርቶቹ ደንቦችና መመርያዎች በፈረንሣይኛና እንግሊዝኛ የተዘጋጁ በመሆናቸው አቶ ይድነቃቸው በተለይ የፈረንሣይኛውን ትርጉም ወደ አማርኛ በመመለስ እንዳዘጋጁት የሚናገሩት አቶ ፍቅሩ፣ የመጀመርያውን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መተዳደሪያ ደንብ ያረቀቁ ስለመሆናቸው ጭምር ያስረዳሉ፡፡ በተለይ አፍሪካውያን ባልዘመኑበት በዚያን ዘመን ብዙ ነገሩን በማበርከት የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ እግር ኳስ አሁን ላይ ምን ነክቶት የጀማሪ መጨረሻ እንዲሆን ተገደደ? የሚል ጥያቄ የሚያነሱ አሉ፡፡

አበው ‹‹ማን ይናገር የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ›› እንዲሉ በኢትዮጵያ በዚያን ወቅት የስፖርቱን ጨምሮ የነበሩ አስተዳዳሪዎችና መሪዎች ቋንቋን ጨምሮ የዕውቀት ችግር ስላልነበረባቸው፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የሆነ ተቀባይነት የነበራቸው መሆኑ የሚናገሩት አቶ ፍቅሩ፣ ለኢትዮጵያ ስፖርት ውድቀት ምክንያቱ ዘርፉን በዕውቀት መምራት አለመቻል እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ ስፖርቶችን በማንቀሳቀስ ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ከሃያ በላይ መሆናቸው ይታመናል፡፡ ይሁንና ብዙዎቹ በተለይም በአሁኑ ወቅት የሚያስተዳድሩት ስፖርት ቀርቶ፣ መኖራቸው በራሱ የሚታወቀው በዓመት አንድ ጊዜ በሚያደርጓቸው መደበኛ ጉባዔ መሆኑ ውሎ ካደረ ሰነባብቷል፡፡ እንደ አቶ ፍቅሩ የዚህ ችግር አንዱና ዋነኛው ‹‹ስፖርቱን እንመራዋለን›› ብለው ኃላፊነት የሚወስዱ አመራሮች ቦታውን ሲረከቡ ለዘርፉ የሚመጥን ዕውቀት ‹‹አላቸው የላቸውም›› የሚል መመዘኛ ባለመኖሩ ነው፡፡

ለዚህ አንዱና ዋናው ማሳያ የሚሉት አቶ ፍቅሩ፣ የፊፋም ሆነ የካፍ ኮንፈረንሶች ሲካሄዱ እንዲሁም ሌሎችም ከ30 ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያን ወክለው የሚቀርቡ፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የሆኑ ደንብና መመርያዎችን አንብበው ለኢትዮጵያም ሆነ ለስፖርቱ ‹‹ይጠቅማል አይጠቅምም›› ብሎ ተከራክሮ ውሳኔዎችን ሲያስቀይሩም ሆነ ሲያፀድቁ አይታይም፡፡ ምክንያቱም ከቋንቋ ጀምሮ አካሄዶችን የመረዳት ችግር አለ፡፡

ሌላው ችግር የሚሉት አቶ ፍቅሩ ስፖርቱ ከዘርና ከፖለቲካ እንዲሁም ከሃይማኖት የፀዳ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የዛሬ 60 ዓመት አካባቢ በተለይ ከኤርትራ ጠቅላይ ግዛት የሚመጡ ቡድኖች ሙሉ በሙሉ ማለት በሚያስችል መልኩ በዘር (በአውራጃ) ተዋቅረው የሚመጡ መሆናቸውን ተከትሎ አቶ ይድነቃቸው በወቅቱ ዓለም አቀፍ የስፖርት መርሆዎችንና ሕጎችን የሚያውቁ ስለነበሩ፣ ይህንኑ በማስረዳት ቡድኖቻቸው ሕግና ሥርዓቱን ተከትለው ስማቸውን እንዲቀይሩ አድርገው ነበረ፡፡ ለምሳሌ ሐማሴን ‹‹ኣስመራ››፣ ኣከለ ጉዛይ ‹‹እምባይሶራ››፣ ለጎጨዋ ‹‹ማይለሃም›› ሲባሉ በትግራይ እንደርታ፣ በሸዋ ሶዶ ምንጭ ‹‹አዋሽ ምንጭ›› ተብለው መቀየራቸው ይታወሳል፡፡ በወታደር ክፍሎችም ይኸው ለውጥ ተፈጽሞ ጦር ሠራዊት (መከላከያ) ‹‹መቻል››፣ አየር ኃይል ‹‹ንብ››፣ ፖሊስ ‹‹ኦሜድላ››፣ ክብር ዘበኛ ‹‹መኩሪያ››፣ ባሕር ኃይል ‹‹መልሕቅ›› ሸዋ ፖሊስ ‹‹ዳኘው›› እና ሌሎችም በዚሁ መልክ መጠሪያቸውን እንዲሰይሙ ተደርጎ ነበር፡፡

ዓለም አቀፍ የስፖርት መርህ ማንኛውም ሰው የፈለገውን ሃይማኖትም ሆነ ብሔር ሊኖረው እንደሚችል፣ ይሁንና በስፖርት ማዘውተሪያዎች ግን ያንን ማንፀባረቅም ሆነ ወደ አደባባይ ይዞ መውጣት በፍፁም እንደሚከለክል የሚናገሩት አቶ ፍቅሩ፣ ስፖርቱን ሽፋን በማድረግ በኢትዮጵያ በማቆጥቆጥ ላይ የሚገኘውን ዘረኝነት ለማስቀረት ፌዴሬሽኖችና መንግሥት ይህንን ጉዳይ ከዓለም አቀፍ የስፖርት ቻርተሮች ጋር አጣጥመው መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለው ያምናሉ፡፡

ለዚህ ደግሞ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት የግንዛቤ ሥራዎችን መሥራት፣ ሕግና ደንቦችን በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ወደ ኅብረተሰቡ በማውረድ ማስተማር እንደሚያስፈልግ የሚያምኑት አቶ ፍቅሩ፣ በዘረኝነት ላይ የተመሠረተ እግር ኳስ  ለስፖርቱ ዕድገትም ሆነ ለተመልካቹም አይጠቅምም፡፡ ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች የኦሊምፒክና የፊፋ ቻርተሮች ጽንሰ ሐሳብ ምንነትና በሥራ የሚተረጉሙበትን አካሄድ በየጊዜው እየተከታተሉ ወቅታዊ የሆኑ መመርያና ደንቦችን ማስረጽ እንደሚያስፈልግ ጭምር ይናገራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ስፖርት በተለይ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ዘረኝነት ብቻ ሳይሆን ምርጫና መሰል ምደባዎች የሚደረጉለት አትሌቲክስ የእከሌ፣ እግር ኳስ ደግሞ የዛኛው ብሔር እንደሆነ ተደርጎ የሚታይበት ደረጃ ላይ መድረሱን የሚናገሩት አቶ ፍቅሩ፣ አዲሱ የመንግሥት አወቃቀር ይህን ጉዳይ አንድ ቦታ ላይ ሊያስቆመው እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡ በምርጫም ይሁን በምደባ ወደ አመራር የሚመጡ ግለሰቦች ከየትኛውም ክልልና የከተማ አስተዳደር ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን ለተቋሙ ወይም ይመራዋል ተብሎ ለሚታመነው ስፖርት አቅሙ እንዴት ነው ተብሎ ከብሔሩ፣ ከሃይማኖቱና ከፖለቲካ አመለካከቱ በፊት መመዘኛ ተቀምጦለት ያንን መነሻ ያደረገ እንዲሆን ማድረግ ላይ ሊሠራ እንደሚገባው አበክረው ይከራከራሉ፡፡

እንደ አቶ ፍቅሩ፣ ‹‹በሁሉም ክልሎችም ሆነ ከተማ አስተዳደሮች እግር ኳሱን አልያም አትሌቲክሱን ሊሆን ይችላል ሊያስተዳድር የሚችል አቅም ያላቸው ሰዎች እጥረት የለም፡፡ በርካቶች አሉ፣ የምንከተለው አካሄድ ግን ቡድነኝነት፣ ዘር፣ ሃይማኖትና የፖለቲካ አመለካከት ላይ መሠረት ያደረገ በመሆኑ እነዚያ ሙያተኞች ይገለላሉ፣ አልያም ካልተፈለግኩኝ ምን አገባኝ ብለው ራሳቸውን መደበቅ ይመርጣሉ፡፡›› ይህ ደግሞ አገሪቱ አስፋፋዋለሁ ብላ ለምታምነው ስፖርት በገንዘብ ሊተመን የማይችል ከፍተኛ ጉዳት ያለው መሆኑን ጭምር ያስረዳሉ፡፡

በሁሉም ስፖርቶች ቀደምት የሆኑ ሙያተኞች ሲናገሩ እንደሚደመጡት ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በስፖርቱ የነበራት ተሰሚነት ከአፍሪካም አልፎ ዓለም ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ እንደነበረች፣ ይሁንና የነበረው ነገር በጊዜ ሒደት እየተሸረሸረ ዛሬ ላይ የሁሉም ነገር የመጨረሻ መሆኗን ነው፤ አቶ ፍቅሩም በዚህ አባባል ይስማማሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ስፖርት ‹‹የጠፋው›› ከመነሻው መሆኑን በመግለጽ የሚከራከሩ አሉ፡፡ እንዲያውም ‹‹አቶ ይድነቃቸው ሠርተዋል ከተባለ የሠሩት ለኢትዮጵያ ስፖርት ሳይሆን ለአፍሪካ ነው›› የሚሉ አልታጡም፡፡

ይህንን አስተሳሰብ አጥብቀው የሚቃወሙት አቶ ፍቅሩ፣ ያለዕውቀትና ያለዕውነት የሚሰጥ አስተያየት መሆኑን ያመለክታሉ፡፡

‹‹ይህን የሚናገሩ በሙሉ ምንም የማያውቁ ናቸው፤ እውነታው ሌላ ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ አቶ ይድነቃቸውም ሆኑ አቶ ፍቅሩ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ ናቸው፤ ስለሆነም የሚናገሩትና የሚያወሩት ቅዱስ ጊዮርጊስን መነሻ ያደረገ ነው ብለውም ያምናሉ፡፡ እውነቱን እንናገር ከተባለ ቅዱስ ጊየርጊስ ሁሉንም ዘርም በለው ሃይማኖት ሳይለይ የሁሉም ክለብ ነው፡፡ ይህንኑ መነሻ በማድረግ አቶ ይድነቃቸው፣ አንድ ቀን ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይቋቋሙ ቢባል መሠረቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ መሆን ነበረበት ብሎ ይናገር ነበር፡፡ ምክንያቱም በክለቡ ውስጥ ሁሉም እንደሚያውቀው ክርስቲያኑም፣ ሙስሊሙም ሁሉንም ያቀፈ በመሆኑ ነው፡፡››

 አቶ ፍቅሩ አክለውም፣ አቶ ይድነቃቸው ለኢትዮጵያ ስፖርት ምን ያልሠራው ነገር አለ? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹እንዲያም እሱ ለኢትዮጵያ ስፖርት የሰጠውን አገልግሎት ያህል የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድም ዓይነት ውለታ ያልዋሉለት መሆኑ ነው ሊታወቅ የሚገባው፤›› የሚሉት አቶ ፍቅሩ፣ እዚህ አገር መጥፋት ያለበት ቢኖር እከሌ ምን ሠራ? ብለው የሚቀርቡ ግለሰቦች እውነት ላይ ያልተመሠረተ ክርክርና አስተያየት መሆኑን ጭምር አጥብቀው ያምናሉ፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ይድነቃቸው ባገሩ የሚገባውን ያህል ክብር ባያገኝም፣ ለስፖርቱ ባበረከተው አስተዋጽኦ አፍሪካውያኑን ጨምሮ ዓለም ላይ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ተቋማት ትልቅ ቦታና ክብር የሰጡት መሆኑ ነው፡፡

‹‹እንዲህ የመሰሉ ክርክሮችና ተግዳሮቶች ሲኖሩ ማመሳከሪያ ዶክመንቶችን መመልከት ይገባል፡፡ እዚህ አገር ትልቁ ችግር በስማ በለው ካልሆነ ለማስረጃዎች የሚሰጠው ቦታ በጣም ደካማ ነው፡፡ በግለሰብ ደረጃ እኔ ጋ ይድነቃቸው በፈረንሣይኛና በእንግሊዝኛ ያዘጋጃቸው ደንቦችና መመርያዎች አሉኝ፡፡ አለፍ ሲልም ሁሉም ነገር በፊፋም ሆነ በኦሊምፒክ ቻርተር ላይ ይገኛል፡፡ ያንን እንኳን በውልና በአግባቡ ተረድቶ ሥራ ላይ ማዋል ባልተቻለበት ሁኔታ ነው እንዲህና እንዲያ የምንባባለው፣ የሚሉት አቶ ፍቅሩ፣ ለሁሉም የሚበጀውና የሚጠቅመው ለኢትዮጵያ ስፖርት ሲባል እኔም ሆንኩ ሌላው ምን ሠራሁ ብሎ ራሱን መጠየቅ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባን ምሳሌ አድርገን ብንወስድ በርካታ ኮንዶሚኒየምና ዘመናዊ ሕንፃዎች ተገንብተዋል፡፡ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ስታዲየሞችም በዚያው ልክ በመገንባት ላይ ይገኛሉ፣ ሁሉንም በበጎ ጎኑ ወስደን ለእነዚህ ዘመናዊ ስታዲየሞች የሚመጥኑ ታዳጊዎች የሚፈሩበት ድሮ እንደነበረው ጥርጊያ ሜዳዎች ግን የሉም፡፡ እንዴት ነው ይህን የመሰለውን አካሄድ የማንተቸው? ታዳጊ ወጣቶች የሚገኙት ከየት ነው? እነዚህ ነገሮች ባልተሟሉበት የምንመኘውና የምናልመው ውጤት የሚመጣው ከየት ነው? የስፖርት ተቋማት ከሚኒስትሩ ጀምሮ ለምን ብሎ የሚጠይቅ እንኳን በሌለበት ቁጭ ብለን ነው የምናወራው፤›› በማለት እዚህ አገር የተለመደው በራሱ ጥረትና ፍላጎት በኦሊምፒክም ይሁን በሌሎች መድረኮች አንድ ወይም ሁለት የወርቅ ወይም የብር ሜዳሊያ ሲገኝ ለሚዲያ ፍጆታ የሚደረገውን ወከባና ሩጫ እንደማያስኬድ አቶ ፍቅሩ ይተቻሉ፡፡

በእነዚህና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ የሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎችን አግኝተው ስፖርቱ በሚመራበት አጠቃላይ ቁመና ላይ ዕድሉን አግኝተው ለማነጋገር ጥረት አድርገው እንደሆነ ላነሳንላቸው ጥያቄ አቶ ፍቅሩ፣ ‹‹ዕድሉ ገጥሞኛል፣ እኔም ሆንኩ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ሙያተኞች በዚህ ረገድ አገልግሎት ለመስጠት ወደ ኋላ የምንልበት አንዳች አይኖርም፡፡ ጥናቶችን እያደረግን ነው፤›› ብለዋል፡፡ በተለይም በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ የኦሊምፒክ ቻርተርን መሠረት ያደረገ ሁሉን አቀፍ የሆነ ጥናት እየተደረገ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡         

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች