Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርየቀን ሕልም የሆነው የ40/60 ፕሮጀክት

የቀን ሕልም የሆነው የ40/60 ፕሮጀክት

ቀን:

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መሪነት እየተተገበረ የሚገኘው ለውጥ አድናቂ ነኝ፡፡ አገራችን ወዳስከፊ ጎዳና እየተጓዘች የነበረችበትን መንገድ የእነ  ዓብይ (ዶ/ር) መምጣት ነገሮችን በሚያስደንቅ አኳኋን ወደ መልካም አቅጣጫ በመቀየር ላይ ይገኛል፡፡

የተስፋፋውን ዘረኝነት፣ ዘረፋ፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ለመለወጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ አስገራሚ ለውጦችን እያየን ቢሆንም፣ ያላለቁ በርካታ ማስተዋልና ጥረትን የሚጠይቁ ጉዳዮች እንዳሉም ዕሙን ነው፡፡ አዲስ አበባ ከተማ የኢትዮጵያም የአፍሪካም መዲና ነች፡፡ ሆኖም በበርካታ ችግሮች የተተበተበች ከተማም ነች፡፡ ከእነዚህ ችግሮች ውስጥ አንዱና ዋናው የመኖሪያ የቤት ችግር ነው፡፡ ይኼንን ችግር ለማስወገድ ባለፉት ዓመታት መልካም ጥረቶችና ጅምሮች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡

በጅምሮቹ የታየው የግንባታ መጓተትና የጥራት ጉድለት ከነበሩት ከፍተኛ ችግሮች ባሻገር፣ በቤቶች ማስተላለፍ ላይ የነበረው የአፈጻጸም ችግር ከሁሉ በላይ የከፋ ነበር፡፡ እኔ ልጽፍ የፈለኩት በ2005 ዓ.ም. በተደረገው የምዝገባና የአፈጻጸም ሒደት ላይ ስላለው ችግር ነው፡፡ አመዘጋገቡ በሦስት የተከፈለ ሆኖ የሚከተለውን ይመስል ነበር፡፡ አንደኛው የ10/90 የተሰኘው ፕሮግራም ሲሆን፣ አነስተኛ ገቢ ያላቸውና አሥር በመቶ ያዋጡ ዜጎች በዕጣ ቤት የሚያገኙበት ነው፡፡ ሁለተኛው የ20/80 ቤቶች ፕሮግራም ነው፡፡ መካከለኛ ገቢ ያላቸው 20 በመቶ የቤቱን ዋጋ ሲያሟሉ በዕጣ የሚያገኙበትና ቀድሞ ከነበረው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ፕሮግራም የቀጠለ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡

 ሦስተኛ የ40/60 ፕሮግራም ሲሆን፣ ከላይ ከተጠቀሱት የተሻለ ገቢ ላላቸውና ቢያንስ ከሁለቱ በተለየ አኳኋን ሙሉ ክፍያውን በቅድሚያ የከፈሉ፣ ወይም ከ40 በመቶ በላይ ለከፈሉት የገንዘብ መጠንና የከፈሉበት ጊዜ ተገናዝቦ ቤት በቅድሚያ ያገኛሉ የሚል ሕግ ወጥቶ ምዝገባው ተካሂዷል፡፡ የቤቶችም ስፋት በሦስት ደረጃ የተከፈለ ነበር፡፡ አንደኛው ባለ ሦስት መኝታ ቤት ሆኖ የ100 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣  386‚000 ብር ይከፈልበታል፡፡ ባለ ሁለት መኝታ ቤቱ 75 ካሬ ሜትር 250‚000 ብር እንዲሁም ባለ አንድ መኝታ ለሆነው የ55 ካሬ ሜትር ቤት 156‚000 ብር ተደልድሎ ነበር፡፡ ለእነዚህ ቤቶች ሙሉ ክፍያ የፈጸሙ፣ ተመዝጋቢዎች መንግሥትን በፋይናንስ ስለደገፉ ወይም ቤቱ በራሳቸው ገንዘብ ስለተሠራላቸው በ18 ወራት ውስጥ ይሰጣቸዋል የሚል ቃል ተገብቶም ነበር፡፡

እንግዲህ ለቤት ችግረኛ ኅብረተሰብ ከዚህ የተሻለ መልካም አጋጣሚ አይገኝምና አቅሙ እንደፈቀደ ሁሉም ሰው የቻለውን በባንክ ለመቆጠብና ክፍያውን ለመፈጸም ሲረባረብ ቆይቷል፡፡ በቅርቡ በዜና እንደተገለጸው ከ20 ሺሕ በላይ ተመዝጋቢዎች ሙሉ ክፍያ ፈጽመዋል፡፡ ከቤቶቹ ግንባታ ውስጥ ቀዳሚ የሆኑት የሠንጋ ተራውና የክራውን ሆቴል ሳይት የሚባሉት ፕሮጀክቶች ነበሩ፡፡ ተመዝጋቢዎች አዝጋሚውን ግንባታ ዓይን ዓይኑን እያየን ከአሁን አሁን ደረሰን ስንል ቆይተናል፡፡ አስገራሚ ሁኔታ ተፈጽመዋል፡፡ አንደኛው ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት በከፈሉበት ቅደም ተከተል መሠረት ቤቱ ሊሰጣቸው ሲገባ፣ ከ18 ወራት በፊት ከፍለው ለጨረሱ 11,080 ተመዝጋቢዎች ዕጣ ወጣላቸው ተባለ፡፡ በሚዲያ እንደሰማሁት ላልተመዘገቡም ቤት ተሰጧቸዋል ተብሏል፡፡

ሁለተኛው የቤቱ ስፋት ከላይ እንደተጠቀሰው ሳይሆን፣ ዝቅተኛው 124 ካሬ ሜትርና ባለ ሁለት መኝታ ቤት፣ ከፍተኛው 174 ካሬ ሜትርና ባለ አራት መኝታ ቤት እንደሆነ በይፋ መነገሩ ነው፡፡ የቤቱ ብዛትም 972 ነው ተብሎ ዕጣ ወጣ ተባለ፡፡ በወቅቱ የነበሩት ምክትል ከንቲባ ‹‹ዕጣ ውስጥ ከገባችሁት ውስጥ ቤት ሳይወጣላችሁ የቀራችሁ በሚቀጥለው ጊዜ ዕጣ የምታወጡት ቤታችሁ የት አካባቢ እንደሚገኝ ለማወቅ ብቻ ይሆናል›› ተባልን፡፡ እንደ ዔሊ የሚያዘግመውን ግንባታ አሁንም ዓይን ዓይኑን ማየታችንን ቀጠልን፡፡ ዕጣው የሚወጣበት ቀን ግን እየተቀያየረ እስካሁን ቆይቷል፡፡ በመካከሉ የእነ ዓብይ (ዶ/ር) ለውጥ ሲመጣ ተስፋችን ለመለመ፡፡ የወጡት ሕጎች በተገቢው መንገድ ይፈጸማሉ መባሉም ተስፋችንን ቢጨምረውም፣ ከሰሞኑ ግን እኛ የቤት ተስፈኞች፣ በተለይም ሙሉውን ከፍለን ያጠናቀቅነው ተመዝጋቢዎች በጉጉት የምንጠብቀው ተስፋችን ላይ አዲሶቹ ሹሞች ውኃ ቸልሰውበታል፡፡ ሕጉን በምን አግባብ ሽረው፣ በምን ዓይነት ፍትሐዊ አሠራር ሊተገብሩት ፈልገው እንደሆነ ባናውቅም፣ በሸገር ሬዲዮ ቀርበው ዕጣው እስከወጣበት ቀን ድረስ 40 በመቶ ያሟሉ ወደ ዕጣው ይገባሉ በማለት አረዱን::

መቼም ትክክለኛ ፍትሕ እሰጣለሁ የሚሉት የእነ ዓብይ (ዶ/ር)ና የእነ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ለውጥ አራማጆች ይኼንን ችግር መገንዘብ ይሳናቸዋል የሚል ግምት የለኝም፡፡ ይልቁንም በለውጡ የሚያዝን ሕዝብ እንዲፈጠር ካልተፈለገ በቀር እንዲህ ያለውን ስህተት መንግሥት አያጣውም፡፡ እዚህ ላይ ማስገንዘብ የምፈልገው ጉዳይ ቢኖር፤ አንደኛ ሕግ በወጣለት ጉዳይ ላይ አፈጻጸሙን ከሕጉ ውጭ በማድረግ መለወጥ ይቻላልን? የሚለውን ጥያቄ በማንሳት ነው፡፡ አንድ ሕግ ትዝ ይለኛል፡፡ በቀደም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጊዜ በሙስና ሳቢያ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች ታስረው ነበር፡፡ በሙስና መከሰስ ዋስትና ያስጠብቅ ስለነበር በ24 ሰዓታት ውስጥ በሙስና የተከሰሰ ሰው ዋስትና አይሰጠውም የሚል ሕግ ወጥቶ ለረጅም ጊዜ የጭቅጭቅ ዓብይ ርዕስ ሆኖ ቆይቶ ነበር፡፡ ለቤቶች የወጣውን ሕግ መሻር ለምን አስፈለገ ብዬ መጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የዛሬ አምስት ዓመት ተኩል በ386‚000 ብር ይገዛ የነበረው ቤት ዛሬ ይገዛዋልን? የሚል ምክንያታዊ ጥያቄ ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡

መቼም ሕዝብ ከአምላኩ ቀጥሎ ዕምነት የሚጥለው መንግሥት ላይ ነው፡፡  በ386‚000 ብር፣ በ250‚000 ብር ወይም በ156‚000 ብር ቤት ለመግዛት ገንዘቡን ለመንግሥት ሰጥቶ ሲጠብቅ የቆየው ሁሉ ዛሬ ላይ 40 በመቶ ካሟላው ተመዝጋቢ እኩል ዕጣ ታወጣለህ ማለታቸው በምን አግባብ ነው? ይህስ እንዴት ነው መልካም አስተዳዳር እንደሚሆን የታሰበው? ይኼን ካሰቡ የ20/80 እና የ40/60 ልዩነቱ ምንድን ነው ሊሉን ይሆን? ይኼንን ችግር አይረዱም ብዬ አላስብም፡፡ አሁንም ይህ ከፍተኛ የፍትሕ መዛባት ከመፈጸሙ በፊት የሚመለከታቸው አካላት ቆም ብለው እንዲያዩት ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ ይልቁንም ቤት እያላቸው ሌላ ተጨማሪ ለማግኘት የተመዘገቡ ስላሉ የሚጣራበት መንገድ ቢፈለግ መልካም አስተዳደር ለማስፈን ይረዳል፡፡

(መምህር መኰንን፣ ከአዲስ አበባ)

***

በትልቅ ትንሹ መንገድ እየዘጉ ማስቸገር ምን ይባላል?

ባሳለፍነው ሳምንት ‹የእገሌ ክልል ነዋሪዎች ቅሬታቸውን መንገድ በመዝጋት አድማ ገለጹ› የሚለውን ዜና ሰምተን ነበር፡፡

 እሑድ ጥር 5 ቀን 2011 ዓ.ም. እዚሁ በአዲስ አበባችን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3፣ ከመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በሰንሻይን ቤቶች አቅጣጫ ወደ ሚሊኒየም አዳራሽ የሚወስደው መንገድ ላይ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ድርጅቶችና ትልልቅ ሆቴሎችን ሥራና እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ በገደበ አኳኋን በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና በፌዴራል ፖሊሶች ትዕዛዝ መንገዱ ከጠዋት እስከ ምሽት ድረስ ለእግረኞችና ለተሽከርካሪዎች ዝግ ሆኖ ነበር፡፡

ነዋሪውና የውጭ እንግዶች ቱሪስቶችን ጨምሮ ለመግባትም ሆነ ለመውጣት ተከልክለው ስለነበር ከባድ መጉላላት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ለምን ሲባልም የኦነግ ስብሰባ በሚሊኒየም አዳራሽ እየተካሔደ ነው የሚል አሳፋሪ ምክንያት ተሰጠቶበታል፡፡ ከሕዝቡና ከድርጅቶች በሚሰበሰብ ታክስና ግብር ደመወዝ የሚከፈላቸው ፖሊሶች ያለማንም ከልካይ የውጭ ዜጎችን በተለይም ቱሪስቶችን ሲያጉላሉና ድርጅቶችን ሲያዘጉ ማየት በጣም ያሳፍራል፡፡

ድሮ ድሮ ባለሥልጣኖች ሲያልፉ ለአጭር ጊዜ ይዘጋ የነበረው መንገድ አሁን ጭራሽ ለአክቲቪስቶች አቀባበል፣ ለሙዚቃ ኮንሰርት፣ ለኤግዚቢሽን፣ ለከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ምርቃት ወዘተ. እየተባሉ መንገድ መዝጋቱ በየጊዜው እየተበራከተ የመጣ ተግባር ሆኗል፡፡ በሌለ መንገድ እንዲህ ያለውን አሳሳቢ ጉዳይ የሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት በተለይም የአዲስ አበባ አስተዳደር አስቸኳይ መፍትሔ ቢሰጡት መልካም ነው፡፡

(እሱባለው መኰንን፣ የአካባቢው ነዋሪ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...