Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ከአዲስ አበባ ወደ ባህር ዳር የሚሄደውን አውሮፕላን ለመሳፈር ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመጨረሻው ቦታ ላይ ደርሻለሁ፡፡ የአየር መንገዱ ሠራተኞች መንገደኞችን የሚያስተናግዱበት ሥፍራ ላይ ተቀምጬ ስጠባበቅ፣ ከዓመታት በፊት ዩኒቨርሲቲ አብረውኝ ከተማሩ ሁለት ሰዎች ጋር ተገናኘን፡፡ ለረዥም ጊዜ በአካል ባላገኛቸውም በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ደህና በሚባል ደረጃ የኃላፊነት ወንበር ላይ መቀመጣቸውን አውቃለሁ፡፡ እንደተለመደው የወዳጅነት ሰላምታችንን ተለዋውጠን ስለሥራ፣ ቤተሰብና ሌሎች ጉዳዮች መወያየት ጀመርን፡፡

እኔ ባህር ዳር የምሄደው የምሠራበትን የአማካሪ ድርጅት አንድ የፕሮጀክት ሥራ ለመገምገም ሲሆን፣ እነኝህ የቀድሞ ወዳጆቼ ደግሞ የድርጅታቸው የኢሕአዴግ አንደኛው አካል የሆነው ብአዴን (አሁን አዴፓ) ጉባዔ ላይ ለመገኘት ነው፡፡ በደርግ ዘመን ዩኒቨርሲቲ ሆነን በዚያች ፊሊፕስ ሬዲዮናችን የአሜሪካ ድምፅን፣ የጀርመን ሬዲዮ ጣቢያና የኢሕአዴግ የጫካ ሥርጭትን እንዴት እናዳምጥና እንወያይ እንደነበር ትዝታችንን አነሳሁባቸው፡፡ ወዳጆቼ ያ ሁሉ የጭንቀትና የዋይታ ዘመን አብቅቶ ሰላም የሰፈነበት ዘመን ላይ በመሆናችን፣ የሕዝቡ ትኩረት ልማት ላይ መሆኑን ተራ በተራ ነገሩኝ፡፡ በእርግጥም እኔም ይኼንን ሐሳብ እጋራለሁ፡፡ የደርግ አስጨናቂ አገዛዝ ካበቃ በኋላ ሰላም በመስፈኑ እኔም ደስተኛ ነኝ፡፡ ነገር ግን ያኔ የምንመኘው ነፃነት፣ የሰብዓዊ መብት ክብር፣ እኩልነትና የመልካም አስተዳደር ጉዳይ አሁንም እንደሚያሳስበኝ አነሳሁባቸው፡፡

እነዚህ ወዳጆቼ በተመሳሳይ አቋም በአገሪቱ ዴሞክራሲ ገና እየተለመደ መሆኑን፣ ከድህነት ጋር የሚደረገው ትንቅንቅ ጊዜ የማይሰጠው መሆኑን፣ በተነፃፃሪ ሁኔታ ሕዝቡ መሪዎቹን በዴሞክራሲያዊ መንገድ እየመረጠ መሆኑን፣ በሒደት መልካም አስተዳደር እንደሚሻሻል፣ ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬ ደግሞ ነገ እየተሻለ እንደሚሄድ ነገሩኝ፡፡ መንግሥት የአገሪቱን ህዳሴ ለማረጋገጥ እንቅልፍ አጥቶ እየሠራ መሆኑንና በሒደት የሚያጋጥሙ ችግሮች እየተፈቱ እንደሚሄዱ እየተቀባበሉ አስረዱኝ፡፡ እኔ ደግሞ ፍትሐዊ ልማትና ዕድገት አስፈላጊ መሆኑን፣ ጎን ለጎን የሰው ልጆች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንዳለባቸው፣ የተለያዩ አመለካከቶች በእኩልነት መስተናገድ እንደሚገባቸው፣ በየደረጃው ያሉ ሹሞች በሚገባ እየተገመገሙ ቁጥጥር ሊደረግባቸው የግድ መሆኑን፣ በሌብነትና ዘረፋ የተዘፈቁ ግለሰቦች የድርጅት አባል በመሆናቸው ብቻ በኔትወርክ እየተሳሰሩ አገር መበደል እንደሌለባቸው፣ በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩ መገናኛ ብዙኃን የተለያዩ አስተሳሰቦችን ለሕዝብ ማድረስ እንዳለባቸው፣ የሕዝብን ፍላጎት የሚፃረሩ ሕጎች እየወጡ አፈና ማስከተል እንደሌለባቸው አነሳሁላቸው፡፡

ሁለቱ ካድሬ ጓደኞቼ የእኔን ሐሳብ በከፊል እንደሚጋሩ ገልጸውልኝ፣ በአሁኑ ጊዜ ከኢሕአዴግ በተቃራኒ የቆሙ ኃይሎች ‹ኪራይ ሰብሳቢዎችና የውጭ ኃይሎች ተላላኪ ናቸው› አሉኝ፡፡ የልማታዊው መንግሥት አካሄድን በመፃረር በአፍራሽ ተግባር ላይ የተሰማሩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ፀረ ሕዝብ መሆናቸውንና ፈጽሞ አማራጭ መሆን እንደማይችሉ ተነተኑልኝ፡፡ ከኢሕአዴግ በተፃራሪ የቆሙ ኒዮሊበራሎች ሕዝብን ለማደህየት፣ መሬት ለመዝረፍ፣ ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት ለመናድ ከጠላት ጋር ሳይቀር የሚያብሩ በመሆናቸው በኢትዮጵያ ምድር ቦታ እንደሌላቸው በኩራት ነገሩኝ፡፡ ‹ያለው መንገድ አንድ ነው እሱም የኢሕአዴግ መንገድ ብቻ ነው› በማለት አቋማቸውን አፍረጥርጠው አሳወቁኝ፡፡ በዚህ መሀል ተሳፈሩ ተብለን በአየር መንገድ ሠራተኞቹ ሲነገረን መቀመጫችን የተለያየ ስለነበር እዚያው ተሰነባበትን፡፡

አውሮፕላኑ ውስጥ ገብቼ በተወሰኑ ደቂቃዎች ውስጥ የሚገባደደውን የሰማይ ጉዞ እየተጠባበቅኩ የድሮ ጓደኞቼ የአሁኖቹ ኢሕአዴጎች አነጋገር አሳሰበኝ፡፡ አውሮፕላኑ ተንደርድሮ ተነስቶ ወደ ላይ ከፍ እያለ ሲወጣና የአዲስ አበባ ከተማ ከዓይኔ ዕይታ እየጠፋች ስትሄድ ዴሞክራሲ የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ ከአዕምሮዬም ሙልጭ ብሎ ወጣ፡፡ እንደ ቀድሞ ጓደኞቼ ገለጻ ከሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለው ብቸኛው መንገድና አማራጭ ኢሕአዴግ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው አይረቤ ነው ማለት ነው፡፡ በፊት በምናውቀው የዴሞክራሲ አስተምህሮ መሠረት የተለያዩ አማራጮች ይቀርቡና ሕዝብ የፈለገውን ነፃ ሆኖ ይመርጣል፡፡ ኢሕአዴግ ይህንን አባባሉን ለምርጫ ቅስቀሳ ቢጠቀምበት አይገርመኝም፡፡ ነገር ግን ሌሎች አማራጮች የማይኖሩበት መደላድል አበጅቶ ከእኔ በስተቀር ዋ ካለ እንዴት ይደረጋል? የእነዚህ ጓደኞቼ ገለጻ በእርግጥም የድርጅታቸው መርህ መሆኑ አልጠፋኝም፡፡ የጠፋብኝ ግን ሁላችንም አንድ ዓይነት ማሊያ ለብሰን መሠለፍ አለብን የሚለው ነው፡፡ ይታያችሁ ባርሴሎና ያንን ውብ የእግር ኳስ ጨዋታ እኮ የሚያሳየን ከተቃራኒው ጋር ሲጋጠም ነው፡፡ ያለበለዚያማ የእርስ በርስ ግጥሚያ ከሆነ ከልምምድ በምን ይሻላል? ኢሕአዴግ ከተቃዋሚዎቹ ጋር ጠንካራ ፉክክር ሳይገጥመው ባዶ ሜዳ ላይ ቢጋልብ ምን ይፈይዳል? ግራ ቢገባኝ የምንኖረው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ወይስ ሰሜን ኮሪያ? ማለት ከጅሎኝ ነበር በወቅቱ፡፡

ያ ሁሉ አልፎ አንድ ቀን ማታ ቤቴ ሆኜ ቴሌቪዥን ሳይ ከሁለቱ የቀድሞ ወዳጆቼ አንዱ ያለፉትን 27 የኢሕአዴግ ዓመታት ሰቆቃ ይዘረዝራል፡፡ እንዴ ሰውዬው ምን ነክቶት ነው ለማለት አሰብኩና ወዲያው ተውኩት፡፡ እርግጥ ነው የሰው ልጅ በነበረበት እንደ ድንበር ድንጋይ ተገትሮ መቅረት የለበትም፡፡ ነገር ግን ከአንድ ወደ ሌላ ፓርቲ ወይም አስተሳሰብ ሲሸጋገር በነበረበት ሥፍራ ለደረሰ ጥፋት ኃላፊነትን መጋራት ይኖርበታል፡፡ ትናንት ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩለት የነበረውን ድርጅት ትተው ሌላ ድርጅት እንደተቀላቀሉ የሰማሁላቸው እነዚያ ሁለት ሰዎች፣ ዛሬ ደርሰው ከእኛ በላይ ላሳር የሚሉ ነውጠኞች መሆናቸውን ከሌሎች ሰዎች ካረጋገጥኩ ወዲህ አንድ የገባኝ ነገር መኖሩን ተረድቻለሁ፡፡ እሱም ሥልጣንና የሚያስገኘውን ገደብ የለሽ ጥቅም ብቻ ነው፡፡ የተቀረው ከንቱ ዲስኩር ነው፡፡ የድሮ ወዳጆቼ አንድ ነገር ልንገራችሁ፡፡ የኋላ ታሪካችሁ እንደ ቃጭል ጀርባችሁ ላይ ሆኖ ስለሚያንቃጭል ለጊዜው ነው እንጂ ማንንም እስከወዲያኛው አታታልሉም፡፡ እንደ ካርታ ጆከር እዚህም እዚያም ጥልቅ እያሉ መሰካት ለጊዜው ነው እንጂ ዘለቄታ የለውም፡፡ በሕዝብ ስም መነገድ የሚያከትምበት ጊዜው እየደረሰ ነው፡፡ የስፖንሰሮች ገንዘብ ሲቆም ነውጠኝነቱም ይቆማል፡፡ አስመሳይነት ዕድሜ ስለሌለው፡፡ ታሪክ የሚያስተምረንም ይህንን ነውና፡፡

(ወርቁ አስማማው፣ ከአዲሱ ገበያ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...