በገነት ዓለሙ
የአገራችን ገበሬ ዛሬም ‹‹አሁን ማን ያውቀዋል የማረሻን ለዛ!›› እያለ ማንጎራጎርና ማድነቁ ባይቀርም እህል ለመቅመስ፣ ከንፈርን ለማውዛት (አሁን ማን ያውቀዋል የማረሻን፣ የሞፈሩን ለዛ፣ እህል ካልቀመሱ ከንፈርም አይወዛ አይደል የሚባለው?) ማረሻና ሞፈርን ማገናኘት ትርጉም እንዲኖረው ለማድረግ፣ ነዳጅ ያን ያህል የሚዘፈንለትና የሚዘመርለት ሸቀጥ ሆኗል፡፡ ከእሑድ ጥር 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ዓይናችን በቀጥታ ገጠመኝ በሚያየው መጠን በየነዳጅ ማደያው ተሠልፎና ተኮልኩሎ የምናየው ጭንቅ፣ የችግሩም ሆነ የነዳጅ ፋይዳ ስብርባሪ/እንክትካች ገጽታና ዕይታው ብቻ ነው፡፡
ዓለም አቀፋዊው ዕለታዊ የነዳጅ ፍጆታ እውነቱን ለመናገር ለአዕምሮዬ በማይገባ ሁኔታ 0.1 (ዜሮ ነጥብ አንድ) ቢሊዮን በርሜል ወይም 16,000,000m3 ሲባል እሰማለሁ፣ አነባለሁ፡፡ ከዚህ ‹‹ውቅያኖስ›› ውስጥ የኢትዮጵያ የፍጆታ ድርሻ (ሪፖርተር በኅዳር 2011 እንደዘገበው) አንድ ሚሊዮን ሊትር ቤንዚን፣ 6.5 ሚሊዮን ሊትር ዲዝል (ነጭ ናፍጣ)፣ ሁለት ሚሊዮን ሊትር የጄት ነዳጅ ነው፡፡ የኬሮሲን (ላምባ) የዓመት ፍጆታችን ደግሞ 260,000 ሜትሪክ ቶን ነው፡፡
ከፍጆታው መጠን በላይ የነዳጅን ‹‹ለዛ›› እና ፋይዳ ለእኔ ይበልጥ ያመላከተኝ በሁለት ዘርፎች ወይም መስኮች ሕግ ለነዳጅ የሰጠው ትኩረት ነው፡፡ ትኩረቱ የልብ ነው? ምን ያህልስ የአደባባይ ሠልፍ ማሳመሪያ ነው? ምን ያህልስ የቢሻኝ ውሳኔ ነው? ምን ያህልስ ዘላቂ ሆኖ ቀጠለ? የሚል ጥያቄ የሚነሳበት ቢሆንም፣ ነዳጅ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ቦታ ግን ከማንኛውም ሌላ ነገር በላይ ያመላክታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ‹‹የነዳጅ ምርቶች ከማንኛውም ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ጋር ያላቸውን ከፍተኛ ትስስርና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በመገንዘብ›› የተቋቋመው የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ አንደኛው ‹‹ትኩረት››፣ አንደኛው ማመላከቻ ነው፡፡ ከሰኔ 26 ቀን 1993 ዓ.ም. ጀምሮ በፀና በዚህ ሕግ መሠረት የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንዱ ተቋቋመ፡፡ ፈንዱ የገንዘብ ሚኒስቴር በሚከፍተው ልዩ የባንክ ሒሳብ ውስጥ ተቀማጭ የሚሆን የገንዘብ አቅም ይኖረዋል፡፡ የገንዘብ ምንጮቹም አንደኛው በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ በመቀነሱ ምክንያት የሚገኘው ተራፊ ሒሳብ ነው፡፡ ሌላውና ሁለተኛው ደግሞ ለነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ እንዲውል ከሚገኝ የውጭ ዕርዳታ ነው፡፡
በዚህ መሠረት ባለጉዳዩ የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት የአገር ውስጥ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ በሚወስንበት ጊዜ፣ ለነዳጅ መግዣና ለሌሎችም ጉዳዮች ታሳቢ ተደርገው በነበሩ ወጪዎችና በትክክል በተደረገው ወጪ መካከል የሚኖረውን ልዩነት (በየሦስት ወሩ የሚደረገው የነዳጅ ምርቶች ዋጋ ማስተካከያ ተግባራዊ ከተደረገበት ወር እ.ኤ.አ. አምስት የሥራ ቀናት ውስጥ) ለፈንዱ ሒሳብ ገቢ ያደርጋል፡፡ እንዲህ ሆኖ የተሰበሰበው ገንዘብ ማለትም ፈንዱ በዓለም ገበያ በሚከሰተው የነዳጅ ዋጋ ማደግ ምክንያት የሚያስፈልገውን ተጨማሪ ወጪ በመደጎም የነዳጁን ዋጋ ያረጋጋል፡፡ ፈንዱ በሕጉ የተገለጸውን ይህንን ዓላማ የሚያሳካ ሥራ ሠርቷል ወይ? ፈንዱን ያቋቋመው ሕግ ግዴታ በሚያደርገው መሠረት የፈንዱ የሒሳብ መዛግብትና የእነዚህም የዋናው ኦዶተር ምርመራ ይህንን ያሳያል ወይ? ብሎ መጠየቅ የአባት ቢሆንም ‹‹የመንግሥት የአሠራር ግልጽነት›› ግን ይህንን መከላከል ምናባህ አገባህ የሚል መላና ዘዴ አለው፡፡ ከዚያም በላይ ፈንዱ በአዋጅ ከተቋቋመ በሁለት ዓመት ውስጥ ከግንቦት 19 ቀን 1995 ዓ.ም. ጀምሮ በፀና ማሻሻያ አዋጅ የፈንዱ ዓላማ ‹‹ትንሽ›› ተሸሻለ፡፡ በአዋጅ ቁጥር 342/1995 እንደተሸሻለው፣ ‹‹በዓለም ገበያ በሚከሰተው የነዳጅ ዋጋ ማደግ ምክንያት የሚያስፈልገውን ተጨማሪ ወጪ በመደጎም የነዳጅን ዋጋ የማረጋጋት›› የፈንዱ ዓላማ ተጨማሪ ‹‹ግዳጅ›› ታከለበት፡፡ ‹‹የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ ዓላማን ሳያደናቅፍ መንግሥት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ሥራዎች ወጪ መሸፈን›› የሚል ሌላ ሽፍንፍንና ድፍንፍን ያለ ‹‹ዓላማ›› ተጨመረ፡፡
የሕጉ ፍጥርጥርና አፈጻጸም ይህን ያህል (የመንግሥት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዜና የዓለም የነዳጅ ዋጋን እርግፍ አድርጎ እንደተወው) መዘንጋትና መረሳት ቢደረስበትም፣ የሕጉ አስፈላጊነት መሞከሩ በራሱ የነዳጁን ቦታና ‹‹ለዛ›› አመላካች ነው፡፡ ባይተገበርም፣ አተገባበሩ ቢልከሰከስም፣ ‹‹የነዳጁ ምርቶች ከማንኛውም ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ጋር ያላቸውን ከፍተኛ ትስስርና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ›› መገንዘብ በራሱ ትልቅ ምስክርነት ነው፡፡
ዋጋ ማረጋጋትን ከመሰለ ዓላማ ላቅ ያለ፣ እሱንም ሊያግዝ የሚችል ሌላም በሕግ የተደነገገ ጉዳይ አለ፡ ይህም አገራዊ ብሔራዊ የመጠባበቂያ ነዳጅ የሚባል ግዳጅ ነው፡፡ ልክ እንደ የአስቸኳይ ጊዜ የክፉ ቀን የምግብ ክምችት ማለት ነው፡፡ ብዙ ተጓዳኝ አስተዳደርና ተቋማት ይኖሩታል፣ አሉት፡፡ የመጠባቂያ ክምችት አስተዳደር፣ የዕለት ደራሸ የዕርዳታ ትራንስፖርት፣ ወዘተ የሚባሉ ተቋማት ያጅቡታል፣ ያግዙታል፡፡
አገራችንም መጀመርያ ራሱን የቻለ ብሔራዊ የመጠባበቂያ ነዳጅ ዴፖዎች አስተዳደር የሚባል የመንግሥት መሥሪያ ቤት በአዋጅ ያቋቋመችው፣ የነዳጅ አቅርቦት ቢቋረጥ ወይም እጥረት ቢያጋጥም ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችል ብሔራዊ የመጠባበቂያ ነዳጅ ማከማቸት አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ብሔራዊ የነዳጅ ዴፖዎች አስተዳደር የሚባል የሕግ ሰውነት ያለው ራሱን የቻለ የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት ተቋቋመ፡፡ የአስተዳደሩ ዓላማ ብሔራዊ የመጠባቂያ ነዳጅ ክምችት መያዝና ማስተዳደር ነው፡፡ ነዳጅ ሲባል ቤንዚን፣ ነጭ ናፍጣ፣ ጥቁር ናፍጣ፣ የጄት ነዳጅ፣ ላምባ፣ ቡታ ጋዝና ሌሎች የኃይድሮ ካርቦን ውጤቶች ማለት መሆኑን፣ አስቸኳይ የነዳጅ እጥረትም በተፈጥሮ ወይም በሰው ሠራሽ አደጋ ወይም በሌላ ምክንያት የሚፈጠር የመደበኛ የነዳጅ አቅርቦት ማነስ ወይም መቋረጥ መሆኑን ሕጉ ደነገገ፡፡ የነዳጅ እጥረት በሚከሰትበት ጊዜ እጥረቱን ለመሸፈን የሚያስችል የነዳጅ ክምችት የሚይዘውና እሱንም የሚያስተዳድረው ተቋም ተጠሪነት አግብብ ላለው ለኢነርጂ ሚኒስትር ሆኖ፣ ከሌሎች መካከል ሊከማች የሚገባው ብሔራዊ መጠባበቂያ ነዳጅ መጠን የሚያቅደው፣ ሲፈቀድም ነዳጅ ገዝቶ የሚያከማቸው፣ ክምችቱም በአግባቡ መያዙን የሚቆጣጠረው፣ አስቸኳይ የነዳጅ እጥረት ሲከሰት ከሚኒስትሩ በሚሰጠው መመርያ መሠረት ከክምችት ወጥቶ እንዲከፋፈል የሚያደርገው ይኼው የመንግሥት ተቋም ነው፡፡ ይህ የቆየው ግን ከ1989 ዓ.ም. መጨረሻ እስከ 2004 ዓ.ም. መጨረሻ ነው፡፡
በ2004 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 265/2004 የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት ይባል በነበረው የመንግሥት የልማት ድርጅት ምትክ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የሚባል ሌላ የመንግሥት የልማት ድርጅት ሲቋቋም፣ ብሔራዊ የመጠባበቂያ ነዳጅ ዴፖዎች አስተዳደር እየተባለ ይጠራ የነበረው የሕግ ሰውነት ያለው ሆኖ ራሱን የቻለ የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት ሆኖ ተቋቁሞ የነበረው መሥሪያ ቤት በዚያው ደንብ ፈረሰ፡፡ የፈረሰው የመንግሥት የአስተዳደር መሥሪያ ቤት የመጠባበቂያ ነዳጅ ክምችት የመያዝና የማስተዳደር ሥራ ለልማት ድርጅቱ ተላለፈ፡፡ በዚህ መሠረት ‹‹አገሪቱ የሚያስፈልጋትን ብሔራዊ የመጠባበቂያ ነዳጅ መጠን ማቀድ፣ ማከማቸት፣ ከምችቱን ማስተዳደርና ከመንግሥት በሚሰጥ መመርያ መሠረት ከክምችት ወጥቶ እንዲከፋፈል ማድረግ›› ለልማት ድርጅቱ ተላለፈ፡፡
በተለይም በአሁኑ ጊዜ ‹‹አስቸኳይ የነዳጅ›› እጥረት በሚያሠጋ ልክና መልክ በተፈጠረበት ወቅት፣ ብሔራዊ የመጠባበቂያ ነዳጅ አስተዳደርን ከመንግሥት የአስተዳደር መሥሪያ ቤት ወስዶ ለመንግሥት የልማት ድርጅት መስጠት ተገቢ ነው ብሎ መጠየቅ አጉል መሞላቀቅ ሊሆን ይችላል፡፡ ጉዳዩን ማንሳት የሚከለክለው ደግሞ በሳምንቱ ውስጥ የተመለከትነው የነዳጅ እጥረት የተለመደው ዓይነት አለመሆኑ ነው፡፡ የተለመደው ዓይነት የምንለው ከዚህ በፊት የምንሰማው ዓይነት የመንገድ ሥራ፣ የመንገድ ላይ አደጋ ዓይነቱን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ 20 በመቶውም ሆነ 80 በመቶው የሚገባባቸው ቀጣናዎች የአሁኑ የፀጥታ ሁኔታ ከሌላው ጊዜ የተለየ ነው፡፡
በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያን ብሔራዊ የመጠባበቂያ ነዳጅ የሚያስተዳድረው ማንም ሆነ ማን፣ ዛሬ ጥያቄው ይኼ ተቋም ከክምችቱ ወጪ አድርጎ ነዳጅ የሚያድለው ምን እስኪሆን ነው የሚጠብቀው? የሚል አይደለም፡፡ በመኪናዎች ሠልፍ ማዘንና መብሰልሰልም ‹‹እጥረት በፈጠሩ የነዳጅ አቅራቢ ተቋማትና ዴፖዎች ላይ ዕርምጃ›› የመውሰድ ነገርም፣ ‹‹በሞተር ሳይክል ሆነው ነዳጅ እየቀዱ ዞር ብለው ዋጋ ጨምረው የሚቸበችቡ ሰዎችን›› ወዮላችሁ ማለትም ዋናው ሕመማችን አይደለም፡፡ የሕግ ማስከበር መልክ ያላቸው ማስጠንቀቂያዎችና ዕርምጃዎችም በአብዛኛው ‹‹አህያውን ፈርተው ዳውላውን›› ናቸው፡፡ ዛሬ በከተሞችና በአገራችን በጠቅላላው የሚታየው ‹‹አስቸኳይ የነዳጅ እጥረት››ም ብሔራዊ የመጠባበቂያ ነዳጅና አስተዳደሩን የምንፈትንበት ‹‹አጋጣሚ››ም አይደለም፡፡
በዚህ ረገድ በእርግጥ ብዙ የሚጠየቁ፣ መመለስ ያለባቸውም ጉዳዮች አሉ፡፡ ብዙዎቹ በግብር ይውጣ ተድበስብሰው የሚያልፉ፣ እንደ አገር ሚስጥርም የሚሸፋፈኑ ናቸው፡፡ ለመሆኑ ሊከማች የሚገባውን ብሔራዊ መጠባበቂያ ነዳጅ መጠን መንዕስ (ሚኒመም) ልኩ ተወስኗል? በሕግ መወሰን የለበትም? አስቸኳይ የነዳጅ እጥረት ማለትስ ምን ማለት ነው? ምን ማለትስ አይደለም፡፡ የዛሬ ችግራችን ግን ለጊዜው ማንም ሆነ ማን ብሔራዊ የነዳጅ ክምችት የመያዝና የማስተዳደር የአገር ግዳጅ ከተሰጠው፣ ወይም ‹‹ወድቆ ከመሬት ካነሳው›› መሥሪያ ቤት በላይ ያለ የአገርና የለውጡ ጉዳይ ነው፡፡ ለውጡን የማገዝና የማራመድ አገርን የማዳን ተግባር ነው፡፡
ትናንት ከዓብይ በፊት ለለውጥ የተካሄደውን ትግል ማውደምና ማጥቃት፣ እንዲሁም ጥላቻ አለበት ብለን ብዙዎቻችን ድምፃችንን አሰምተናል፡፡ ከጥፋትና ከውድመት ከጥላቻም ጋር የተዛመደ ትግል ወደ ፍጅት ያንሸራትታል ብለን ተናግረናል፡፡ አመፅና ውድመት ከመብት ፈላጊነት ጋር ይጋጫል፡፡ ዛሬ በዶ/ር ዓብይ የሚመራው መንግሥት ጥላቻና በቀልን ተፀይፎ ዕርቅና ይቅርታን ከፍ በማድረጉ፣ እንዲሁም የዚህ አካባቢ ባለቤት እኔ ነኝ እያሉ ማብረር ያጠፋናል እንጂ ‹‹አያሻግረንም››፣ የሚያሻግረን በአገርም በቀጣና ደረጃም ‹‹መደመር›› ነው በሚል አቋም በመታወቁና በዚህም አቅጣጫ ከጎረቤቶች ጋር ያለንን ግንኙነት የበለጠ የማሻሻል ስኬት ገና ከጅምሩ በማሳየቱ በአገር ውስጥም በውጭም፣ በኢትዮጵያውያንም፣ በትውልደ ኢትዮጵያውያንም፣ በውጭ አገር ሰዎችም ትልቅ ድጋፍ አግኝቷል፡፡ የመንግሥት ተቃዋሚዎችም አገር ቤት ገብተዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን የውስጥ ፈተናችን ገና በጭራሽ አልቀለለም፡፡ ለውጡ ድልን የመቀዳጀቱን ነገር በአጣብቂኝ ውስጥ የከተቱት በርካታ ችግሮች አሉብን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ምላሽ አጥተው የቆዩ፣ ሰሚ አጥተው ያደሩ፣ ተወዝፈው የኖሩ፣ ሕዝብን ከሕዝብ፣ ሕዝብንና መንግሥትን የሚያነካኩ ውዝግቦችና ጥያቄዎች አሉ፡፡ እነዚህ ደጅ እየወጡ እያፈተለኩ እየተቅበጠበጡም በቀላሉ ወደ ሁከት የተንሸራተቱበት ሁኔታም ዓይተናል፡፡ ቁጣና ውድመት (ያላግባብ) የለውጥ አዋላጅና የመንግሥትን ጆሮ ማግኛ ሆኖ እንዳገለገለ ሁሉ፣ ያ ልምድ ለብሶተኛው ፈጣን ምላሽ ማግኛ ሆኖ ለውጡን እየጎዳው ነው፡፡ ለውጡን በትርምስ ማጎሳቆል ለሚፈልጉም እነዚህ ጥያቄዎች ሽፋን ሆነው ማገልገላቸው አልቀረም፡፡
‹‹ብሔራዊ ክልልን ለማስፋት ወይም ባለበት ለማርጋት፣ የወሰን ጉዳይን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማረጋገጥ ወይም ሌላ ክልል የ‹‹ያዘው››ን መሬት ለማግኘት፣ ወይም ‹‹ባለቤቶቹ›› ያልፈቀዷቸውን ባዕዳን ለማፅዳት የሚወሰድ ዕርምጃና የሚካሄድ ግጭት ለውጡን ከማስገደል በስተቀር፣ ለለውጡ እንደማይጠቅም ለለውጡ ደጋፊዎች ጭምር ገና ያልተጤና ጉዳይ ሆኗል፡፡ መንግሥትን አስደንግጦ ክልል ወይም ልዩ አስተዳደር ልሁን የሚል ወይም ሌላ ጥያቄን ለማሳካት ወይም ሥጋቴ ያለውን ማኅበረሰብ ለመመንጠር፣ ይህ የሽግግርና የለውጥ ጊዜ ጥሩ አጋጣሚ ነው ብሎ ለመጠቀም እየሞከረ ያለ በየቦታው አለ፡፡ በተለይም ለውጡ ተዝረክርኮ፣ የመነጠል ፖለቲካ አዲስ አበባን ቀለበት ውስጥ አስገብቶ ከሌላው የአገሪቱ ክፍል የመቁረጥ የትግል አባዜ ጋር ከተገናኘ በጣም አደገኛ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በ2010 ሰኔ ማለቂያ ላይ ግምቢና ነቀምቴ መካከል ተከሰተ የተባለው በከባድ መኪና መንገድ የመዝጋት ድርጊትም ከባድ ማስጠንቀቂያ ነበር፡፡ በተለይም ኦሮሞን በተለመደው ብሔርተኝነት ካርታ ውስጥ አጥሮ ሥልጣን ላይ ለመውጣት፣ ዓብይና የለውጥ ቡድናቸው ስህተት ሠርተውላቸው ከኦሮሞ ጋር ለማቆራረጥ ከማድባትና ነገር ከመሥራት የማይመለሱ መኖራቸውም ዛሬ የማያደናግር እውነት ነው፡፡ የሥርዓቱን የጎሰኛነት ገመና ሽፋን አድርጎ ቀውስ በማራባት በመንግሥትና በሕዝብ ላይ መወነባበድ ፈጥሮ ለውጡን የማክሸፍ ሥውር ሥራም እንደሚኖር አንድና ሁለት የለውም፡፡ የአማራንና የኦሮሞን አንድ ላይ መግጠም የአናሳ ብሔረሰቦች መታፈኛ አድርጎ መተርጎምም ሆነ ለምሳሌ ‹‹የኢሕአዴግ ባንዲራ›› ተብሎ የሚፈረጅ ኪሳራ የደረሰበትን ሰንደቅ ዓላማ መቃወሚያ ሆኖ፣ በውስጥም በውጭም ከፍ የተደረገውን ልሙጥ ባንዲራ የቅልበሳ ማረገጋገጫ አድርጎ ውዥንብር መንዛት የዚሁ ለውጡን የማምከን ጥረት መገለጫዎች ናቸው፡ ልሙጡን ሰንደቅ ዓላማ የመመለስ ምኞት ያላቸውም ወደ ጽንፍ እንዳይሄዱና አፀፋዊ የስሜት መጎሽ እንዳያስከትሉ መቻቻል የሚባል ነገር የትም አይታይም፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ በለውጥ ኃይሎችና ፈላጊዎች ውስጥ ጭምር ቅደም ተከተል አናውቅም ማለታቸው ትልቁ ችግር ነው፡፡ ተቀዳሚ የዴሞክራሲ ግንባታ ተግባሮች አለመለየታቸው ነው፡፡ ለውጥና ማሻሻያዎችን መጠየቅና ማካሄድ ማለት በጥያቄ ማዋከብ፣ ከየአቅጣጫው ለሚመጡ ጥያቄዎች እየተዋከቡ መገበር ማለት አይደለም፡፡ ትንሽም ትልቅም ጥያቄዎች እያግተለተሉ አዙሪት መፍጠር ተቀዳሚ የለውጥ ተግባርን ከዕይታ እስከ ማጥፋት መንገድ ሊያስት ይችላል፡፡
ተቀዳሚዋቹ የዴሞክራሲ ግንባታ ተግባራት ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው አይጥና ድመት የነበሩ ቡድኖች ሳይቀሩ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አገር መገንባትን ጉዳያችን ብለው የተሰባሰቡበት፣ እንዲሁም ነፃ የብዙኃን ማኅበራትና ነፃ የሕዝብ ዴሞክራሲዊ ተሳትፎዎች የሚፍለቀለቁበት መልካም የፖለቲካ አየር መፍጠር፣ በዚህ አየር ውስጥ የፖለቲካ ወገንተኝነት የሌላቸው የዴሞክራሲ ተቋማትንና አውታራትን ማሰነዳዳት፣ እንዲሁም ከቡድኖች የፖለቲካና የድምፅ ትርፍ ይልቅ ለጤናማ የምርጫ ዘመቻና ላልተጭበረበረ የድምፅ አሳጣጥ ሥር መያዝ መጨነቅን ያገዘፈ የኅብረተሰብ ንቃተ ህሊናን የማጎልበት ሥራ ነው፡፡
ሁለተኛው መፍትሔ አሁኑኑ ውለዱ እያሉ ማዋከብ በሌለበት አኳኋን በጥናት ላይ የተመሠረቱና የሰከኑ ውይይቶችን እያካሄዱ፣ ለፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መዋጣትና ለሁሉን አቀፍ የማኅበረ ኢኮኖሚ ልማታችን የሚበጁ ሁነኛ ጉዳዮችን መመርመርና ማብላላት ነው፡፡ የሁሉም የለውጥ ኃይሎች የመጀመርያው ደረጃ አብሮ የመሥራት ተልዕኮ አስቀድሞ የታወቀ ማለትም ዴሞክራሲ የሚፈልጋቸውን ሁኔታዎች የማመቻት ነው፡፡ መሆንም ያአለበት ይኼ ነው፡፡
በዚህም ገና በጠላትነት የመወጋገዝ ፖለቲካን አቋርጠው ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎቹ፣ እንዲሁም ኢሕአዴጎች እርስ በርሳቸው አብሮ ወደ መሥራት ሲያመሩና ሁለቱም ወገኖች ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰላምና ግስጋሴ አስፈላጊነታቸው በግልጽ ሲወጣ፣ ኅብረተሰቡ ውስጥ ተሸጋግሮ የነበረውም የጠላትና የወዳጅ ፍረጃ መበተን ይጀምራል፡፡ የዴሞክራሲ መብቶች ይበልጥ ተግባራዊ ተጨባጭነት ያገኛሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ የቅማንትና የወልቃይት ዓይነት ጥያቄዎች ሌላ ጠንቅ በማይተክሉበት፣ የሚመለከታቸው ሕዝቦች ሳያሸካከሩ ተቀባይነት በሚያገኙበት መንገድ ለመፍታት ይስማማል፡፡ የብዙኃን ማኅበራት ነፃና ንቁ ሕይወት ያገኛሉ፡፡ የእነዚህ ሁኔታዎች መፍካት፣ ከፖለቲካ ወገናዊነት ገለልተኛ መሆን በሚገባቸው የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ያለ ወገንተኝነትን ትዝብት ውስጥ ይከታል፣ ለማረም ይበረታታል፡፡
የፍትሕ አካላት ያለ አድልኦ ለመሥራት የሚመች ነፃ ደመና ያገኛሉ፡፡ በፖለቲካ ታማኝነት የመንግሥት ሠራተኛን የማንሳትና የመጣል ዘልማድ ይጋለጣል፡፡ የፀጥታ ኃይሎች ሊይዙት የሚገባቸውን ባህርይና በሚዲያም ሆነ በሌላ መድረክ ሊያራምዱ የሚችሉትን አቋም አንድ ሁለት ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ እነዚህን በመሳሰሉት አደፋፋሪ ሁኔታዎች በመታገዝ ባለው የተወካዮች ምክር ቤት በኩል የማያፈናፍኑ ሕጎች እንዲቃኑ ማድረግ ይከተላል፡፡ ለተከታዩ ምርጫም ከእስካሁኑ በእጅጉ በኢወገንተኝነት የተሻለ የምርጫ አስፈጻሚ መዋቅር ማደራጀት ይቻላል፡፡
እዚህ ሒደት ውስጥ መግባት ከቻልን የነዳጅ እጥረት ጉዳይ ተራ እጥረት፣ የሠለጠነ የብሔራዊ የመጠባበቂያ ነዳጅ አስተዳደር መሥሪያ ቤት ሥራ ይሆናል፡፡ የዴሞክራሲ ጅምራችን በጥያቄ፣ በጫጫታና ጋጋታ ከመቀጨት ዕድል ይድናል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡