Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  ‹‹አንድ ባንክ ሲዘረፍ ማንም ቆሞ ማየት የለበትም››

  አቶ አዲሱ ሀባ፣ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ፕሬዚዳንት

  ባለፈው ሳምንት በምዕራብ ወለጋ አካባቢ በተለያዩ ባንኮች ቅርንጫፎች ላይ ዘረፋ መካሄዱ ተሰምቷል፡፡ በአንዳንድ ቅርንጫፎች ላይም ያልተሳካ የዘረፋ ሙከራ እንደነበርም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በተደራጀና በታጠቀ ኃይል በተፈጸመው ዘረፋ ምክንያት በአካባቢው ያሉ የባንክ ቅርንጫፎች ሥራ ተስተጓጉሏል፡፡ እስካሁን ድረስ የተዘረፈው የገንዘብ መጠን ባይታወቅም፣ መጠኑን ለማወቅ መረጃ የማሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ ይሁን እንጂ አለ ከሚባለው የፀጥታ ችግር አንፃር በቂ መረጃ አልተገኘም፡፡ በአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ ዘረፋ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል እንዳልሆነ ይነገራል፡፡ የባንኮች ቅርንጫፎች እየተስፋፉ ከመምጣታቸው አንፃር፣ በዚያው ልክ ደኅንነታቸው ሊጠበቅ እንደሚገባ አመላካች መሆኑን፣ ወደፊትም ከዘመናዊ ባንክ አገልግሎት አንፃር ከሥጋት የነፃ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖር ለማድረግ ከወዲሁ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ በዘርፉ ባለሙያዎች ይገለጻል፡፡ ከዚህ አንፃር ባንኮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ምን ማድረግ አለባቸው? በሚለው ጥያቄ ላይ ዳዊት ታዬ ከኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ሀባ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡  

  ሪፖርተር፡- በቅርቡ በምዕራብ ወለጋ አካባቢ በሚገኙ የተለያዩ ባንኮች ቅርንጫፎች ላይ የታጠቁ ኃይሎች ዘረፋ መፈጸማቸው ተሰምቷል፡፡ ምን ያህል ገንዘብ እንደተዘረፈ ማወቅ ተችሏል?

  አቶ አዲሱ፡- በአካባቢው የተፈጸመውን ዘረፋ ሰምተናል፡፡ ሆኖም የትኛው ባንክ ምን ያህል ቅርጫፎቹ እንደ ተዘረፉና የገንዘቡን መጠን የሚጠቅስ መረጃ የለንም፡፡ ዘረፋው የተፈጸመባቸው ባንኮች መረጃውን በቀጥታ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንደሚያቀርቡ ነው የተነጋገርነው፡፡

  ሪፖርተር፡- በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተደጋጋሚ ዘረፋዎችና ሙከራዎች እየተደረጉ መሆኑ ይሰማል፡፡ እንዲህ ያለውን ያልተለመደ ነገር ለመከላከል ምንድነው መደረግ ያለበት? ባንኮች እንዴት መጠበቅ አለባቸው?

  አቶ አዲሱ፡- የጥበቃ ሠራተኞች አሉ፡፡ በዲጂታል መንገድ ጥበቃ የሚደረግበት አሠራር አለ፡፡ በአካል በጠንካራ ሰዎች በመሣሪያ የማስጠበቅ አሠራር አለ፡፡ ሌላው በጥሬ ገንዘብ መያዝ የሚገባህን መጠን መወሰን ነው፡፡ ይህ ደግሞ በኢንሹራንስም ይታገዛል፡፡ ትልቁ ነገር ቅርንጫፎች እንደ ደረጃቸውና እንደሚያንቀሳቅሱት የገንዘብ መጠንን የሚወሰን የተቀመጠላቸው ገደብ አላቸው፡፡ አንድ ቅርንጫፍ በጥሬ ገንዘብ መያዝ ያለበት መጠን ምን ያህል መሆን እንዳለበት የተቀመጠላቸው ገደብ አለ፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ቅርንጫፍ ለሥራው የሚያስፈልገውን ወይም በተቀመጠለት ገደብ መሠረት ነው ገንዘብ መያዝ የሚገባው፡፡ ከዚህ ውጪ ለወደፊቱ በረዥሙ መሠራት ያለበት ጥሬ ገንዘብ የምንጠቀምበትን አሠራር እየቀነሱ መሄድ ነው፡፡ ወደ ካርድ ክፍያ ሥርዓት ገብቶ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ የገንዘብ እንቅስቃሴውን በሞባይልና በመሰል ኤሌክትሮኒክ አሠራሮች እየተገበሩ መሄድ የግድ ነው፡፡ ይህ ሲሆን በየቅርንጫፎቹ የምትይዘው ገንዘብ ብዙ ስለማይሆን አደጋውን ለመቀነስ ያስችላል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ብዙ ጊዜ ጥሬ ገንዘብ  ይያዛል፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ ቢዘረፍ አደጋ ነው፡፡ ቢዘረፍ እንኳን ገንዘቡን ለማስመለስም ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ ጥንቃቄዎቹ እንዲህ ካሉት ጉዳዮች አንፃር መታየት አለባቸው፡፡ ለዚህም ደግሞ ሁሉም ባንኮች ዝግጅት ሊያደርጉ ይገባል፡፡  

  ሪፖርተር፡- ባልተለመደ ሁኔታ ባንክ ተዘረፈ የሚሉ መረጃዎች በተደጋጋሚ እየተሰሙ ነው፡፡ ሰሞኑን በምዕራብ ወለጋ አካባቢ ባሉ ቅርንጫፎች ላይ ያጋጠመው ዘረፋ የተደራጀና በርከት ያለ ቁጥር ያላቸውን ቅርንጫፎች ያካተተ ቢሆንም፣ መሣሪያ በመታጠቅ የባንክ ዘረፋ ተፈጸመ የሚለው ዜና የዋዛ አይደለም እየተባለ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር ለመከላከል የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ምን ለማድረግ አስቧል? የባንኮችን ደኅንነት ለማስጠበቅ ምን እያደረገ ነው?

  አቶ አዲሱ፡- በእኛ በኩል ደኅንነቱን እንዴት ነው ማጠናከር የሚቻለው? ለዘለቄታ እንዴት ነው መሠራት ያለበት? የሚለውን የባንኮች ማኅበር እንደ አንድ ጉዳይ ይዞ እየሠራበት ነው፡፡ ለምሳሌ በዚህ ረገድ ያለውን ሥጋት ለመቀነስ በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አንድ ጥናት እንዲጠና አድርገናል፡፡ ይህ ጥናትም አልቋል፡፡ ያሉትን የባንክ ቅርንጫፎች ዞረው ጥሩ ጥናት አቅርበዋል፡፡ ጥናቱ መወሰድ የሚገባውን ጥንቃቄም የሚያሳይ ነው፡፡ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም እንዴት መተባበር እንዳለባቸው የሚያመለክት ጥናት ነው፡፡ ይህንን ጥናት በመያዝ በቅርብ ጊዜ አንድ ዓውደ ጥናት አዘጋጅተን ወደ ተግባር እንገባለን ብለን ነው የምናስበው፡፡ ሌላው ሐሳብ ደግሞ በጥሬ የሚያዘውን የገንዘብ መጠን መወሰን ነው፡፡ ጥሬ ገንዘብ በጆንያ ጭምር በመያዝ የማዘዋወር አሠራር በጣም አሥጊ ነው፡፡ ይህ የሚዘዋወረው ጥሬ ገንዘብ መጠን ምን ያህል ነው? ትራንዛክት በምናደርግበት ጊዜ ዝም ብሎ አሥርና ሃያ ሚሊዮን ብር በጆንያ ተሸክሞ ማንቀሳቀስ መቅረት አለበት የሚለውን ነገር በመያዝ፣ እንዴት መተግበር እንደሚቻል አመላካች የሆነ አንድ ጥናት እያስጠናን ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- ከባንክ ጥበቃና ደኅንነት ጋር በተያያዘ ከሚስተዋሉ አንዳንድ ክፍተቶች አንደኛው፣ በቂ የሆነ የጦር መሣሪያዎች ያለመኖር ችግር ይነሳል፡፡

  አቶ አዲሱ፡- እንዲህ ያለውን ክፍተት ቀደም ብዬ በገለጽኩልህ ጥናት ውስጥ ተካቷል፡፡ በሰው ኃይል የሚደረገውን ጥበቃ እንዴት ማጠናከር እንደሚችል አካቷል፡፡ ይኼ ጉዳይ በተደጋጋሚ የተነሳ ጉዳይ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በምንወያይበት ጊዜ ይህንን እንደ አንድ ጉዳይ አንስተናል፡፡ የሠለጠነ ባለሙያ መኖር ይኖርበታል፡፡ እነዚህ ባሙያዎችም የታጠቁ መሆን አለባቸው፡፡ ሌላው ቢቀር የከበደ ነገር ቢመጣ እንኳን ለመከላከል በሚያስችል ደረጃ መታጠቅ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም የቅርንጫፎቻችን ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው፡፡ የሠራተኞችም ቁጥር እያደገ ነው፡፡ ስለዚህ የሚያስፈልገው የመሣሪያ ፍላጎት እያደገ የሚመጣ ስለሆነ፣ እኛም ይህ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራበት ግፊት እያደረግን ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- እርስዎ ከ40 ዓመታት በላይ በኢንዱስትሪው ውስጥ እያገለገሉ ነው፡፡ በዚህን ያህል ደረጃ ባንኮች ተዘረፉ የተባለበትን ጊዜ ያስታውሳሉ? እንዴትስ መከላከል ይቻላል?

  አቶ አዲሱ፡- በቅርቡ አዲስ አበባ ጎሮ አካባቢ በሚገኝ አንድ የግል ባንክ ላይ የተደረገ የባንክ ዘረፋ ሙከራን ያስጣለው የአካባቢው ሕዝብ ነው፡፡ ተሯሩጦና ተጯጩሆ ዘረፋውን ተከላክሏል፡፡ ኅብረተሰቡም ቢሆን በየትኛውም ባንክ ውስጥ ያለው ገንዘብ የራሱ መሆኑን ማወቅ አለበት፡፡ ስለዚህ ባንኮች የምናደርገው ጥንቃቄ እንደተጠበቀ ሆኖ ሕዝቡ ገንዘቡ የራሴ ነው፣ የራሴ ሀብት ነው ብሎ መከላከል አለበት፡፡ የመንግሥት አካላትም በተመሳሳይ መሥራት አለባቸው፡፡ መከላከያም፣ ፌዴራል ፖሊስም ሆነ የአካባቢ ሚሊሻዎች በየባንኩ ያለው ገንዘብ የሕዝብና የራሳቸው ሀብት መሆኑን በማወቅ ጥበቃ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ የሕዝብ ሀብትና ገንዘብ ነው የምንለው በትክክልም የሕዝብ ስለሆነ ነው፡፡ ምክንያቱም የግል ባንኮችን ያቋቋሙት ባለአክሲዮኖች ገንዘብ የተወሰነ ነው፡፡

        ሌላው በየባንኩ ያለው ተቀማጭ ገንዘብ ከሕዝቡ ተሰባስቦ የተቀመጠ ነው፡፡ ስለዚህ በየትኛውም ባንክ ያለ ገንዘብ በሙሉ የሕዝቡ ነው፡፡ አንድ ባንክ ሲዘረፍ ማንም ቆሞ ማየት የለበትም፡፡ ይህ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ በተደራጀ መንገድ ዝርፊያ ከዚህ ቀደም ነበር ወይ? ለሚለው ጉዳይ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ኢሕአፓም ሆነ በህዕቡ የሚንቀሳቀሱ ድርጀቶች፣ ከዚያ በኋላ ሌሎችም ጫካ የገቡ ድርጅቶች ባንኮችን ዘርፈዋል፡፡ ግን ያኔ ይያዝ የነበረው ገንዘብ አነስተኛ ነበር፡፡ አሁን ግን የሚያዘው ገንዘብ ከፍተኛ ስለሆነ በዚያው ልክ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል፡፡ በቅርንጫፎች በሚቀመጥ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ በገንዘብ ዝውውርና እንቅስቃሴ ላይም የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ አንድ ባንክ 80 ሚሊዮን ብር የሚሆን ገንዘብ መንገድ ላይ ተዘርፏል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ባለው ደረጃ ዝርፊያ ካለ ሕዝቡ በመከላከሉ ሥራ ላይ መኖር አለበት፡፡ እኛ የምናደርገው ጥንቃቄ እንደተጠበቀ ሆኖ ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይከሰቱ ሕዝቡ ሊኖረው የሚገባው ሚና ትልቅ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ተግባራዊ መሆንና እየተጠናከረ መሄድ እንዲህ ላሉ የዘረፋ ሙከራዎችና ስርቆቶች መፍትሔ እንደሚሆን ይነገራል፡፡ ከዚህ አንፃር የባንኮች እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

  አቶ አዲሱ፡- ይህ ጉዳይ ወሳኝ ነው፡፡ ዘመናዊ አገልግሎቱን ወደ ሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ ብዙ ኢንቨስትመንት ይጠይቃል፡፡ ባንኮች በዘመናዊ የባንክ ቴክኖሎጂ ለመሥራት ጥረት እያደረጉ ናቸው፡፡ ሕዝቡም ይህንን መረዳት አለበት፡፡ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማሳደግ ግን አቅም ይጠይቃል፡፡ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶችን የተፈለገው ደረጃ ለማድረስ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በአንዴ ግን እንዲህ ያለውን ችግር ለመከላከል የሚያስችል ደረጃ ላይ ግን አይደረስም፡፡

  ሪፖርተር፡- የእከሌ ባንክ ቅርንጫፍ ተዘረፈ፣ በእከሌም ላይ ተሞክሮ ነበር የሚባለው ጉዳቱ እንዴት ይገለጻል? በባንኮችና በተጠቃሚዎች ላይ የሚደርሰው ተፅዕኖ ምን ያህል ነው?

  አቶ አዲሱ፡- ገንዘብ ጠፋ ማለት ትልቅ ጉዳት ነው፡፡ ነገር ግን ባንኮች በቅርንጫፎች የሚያኖሩት ገንዘብ የኢንሹራንስ ሽፋን አለው፡፡ በአንፃሩ ግን በምንም ሁኔታ ቢሆን ከባንኮች የሚዘረፍ ገንዘብ እንዲመለስ ጥረት መደረግ አለበት፡፡ ሰዎችን አሳደህ ይዘህ እንዲመልሱ ማድረግ የግድ ነው፡፡ ሌላው አደጋውን ለመከላከል የምትይዘውን የጥሬ ገንዘብ መጠን ማሳነስ አንድ መፍትሔ ነው፡፡ ሌላው ነገር ደግሞ ባንኮች እርስ በርስ ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር ይኖርባቸዋል፡፡  

  ሪፖርተር፡- እንዴት?

  አቶ አዲሱ፡- ለምሳሌ አዳማ ያለ አንድ ባንክ ገንዘብ ቢያጥረው የሚፈልገውን ገንዘብ ለመሙላት አዲስ አበባ መጥቶ ነው የሚወስደው፡፡ ይህንን ማድረግ የገንዘብ እንቅስቃሴው ላይ ሊያጋጥም የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ ይረዳል፡፡ እዚያው አዳማ ላይ ካለ ከሌላ ባንክ ቅርንጫፍ የሚቀበልበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም እዚያው በቀላሉ ተደጋግፈህ መፈጸም እየቻልክ ለአደጋ መጋለጥ የለብህም፡፡ አንዱ ከሌላው እየተቀባበለ ጊዜያዊ ችግሩን መሸፈን ይችላል፡፡

  ሪፖርተር፡- በእያንዳንዱ ባንክ ያለ ተቀማጭ ገንዘብ የኢንሹራንስ ሽፋን አለው ብለዋል፡፡ ይህ ማለት በባንኮች ውስጥ ያለ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ የመድን ዋስትና አለው ማለት ነው? ወይስ ቅርንጫፎች ብቻ በተለየ ዋስትና የሚያገኙበት አሠራር ነው?

  አቶ አዲሱ፡- ለሁሉም ተቀማጭ ገንዘብ ሳይሆን በአንድ ቅርንጫፍ ማስቀመጥ በሚገባህ የገንዘብ መጠን ልክ የሚሰጥ ዋስትና ነው፡፡ የኢንሹራንስ ሽፋኑም የሚሰጠው በዚያ ቅርንጫፍ እንድታስቀምጥ የሚፈቀድልህ ገንዘብ መጠን ስላለ፣ ኢንሹራንስም በዚያ መልክ ሽፋን ይሰጥሃል፡፡  

  ሪፖርተር፡- በአንድ ቅርንጫፍ እስከ ምን ያህል ድረስ ገንዘብ እንዲቀመጥ ይፈቀዳል?

  አቶ አዲሱ፡- ከቅርንጫፍ ቅርንጫፍ ይለያያል፡፡ እንደ እንቅስቃሴው መጠን የሚወሰን ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ለማስፋፋት የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ ይህም ቢሆን ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆን አለበት፡፡ ከባንክ ሥራ ጋር በተያያዘ ሊከሰቱ ከሚችሉ ሥጋቶች ውስጥ አንዱ የሳይበር ጥቃት ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር ለመከላከል ምን እየተሠራ ነው?

  አቶ አዲሱ፡- ለሳይበር ጥቃት የራሱ መከላከያ አለው፡፡ የሳይበር ደኅንነት ወሳኝ ነው፡፡ ቴክኖሎጂው ውስብስብ በሚሆንበት ጊዜ መከላከያውም በዚያው ልክ መደራጀት አለበት፡፡ የሳይበር ደኅንነት በአገር ደረጃ የሚታይ ነው፡፡ ኢንሳ የሚሠራው አለ፡፡ ባንኮች በራሳቸው መንገድ የሚሠሩት አለ፡፡ ራሳቸውን ለመከላከል የሚችሉበትን መንገድ ይቀይሳሉ፡፡ ሞባይል ባንኪንግ፣ ኢንተርኔት ባንኪንግ፣ ኤጀንት ባንኪንግና የመሳሰሉትን እሠራለሁ በሚሉበት ጊዜ ጠቅላላ የዲጂታል ደኅንነቱም የዚያኑ ያህል ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ሁሉም ባለበት ደረጃ ከሚሰጠው አገልግሎት ጋር የሚሆን መከላከያ እያደራጀ ይሄዳል፡፡

  ሪፖርተር፡- ጠንካራ የሳይበር ጥቃት የመከላከያ ሥልት እንዲኖራችሁ ለማድረግ እየተሠራ ያለው ሥራ ምን ያህል ተራምዷል?

  አቶ አዲሱ፡- ቀደም ብዬ እንደገለጽኩልህ ለዚህ የሚያስፈልጉ ጥንቃቄዎችን ተግባራዊ እያደረጉ መሄድ ነው፡፡ ይህንንም እያደረግን ነው፡፡ የኢንተርኔት ባንክ አገልግሎትን ተግባራዊ ያደረጉ ባንኮች አሉ፡፡ እነሱ ሌላው ሰርጎ እንዳይገባ በሚያደርግ ሁኔታ ደንበኞቻቸው አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረጉ ነው፡፡ ከሳይበር ጥቃት እንዲጠበቁ ይሠራሉ፡፡ እንዲህ ካላደረግክ በዚህም መንገድ ዝርፊያ ሊኖር ይችላል፡፡ አሁን ባለበት ደረጃ ግን አስፈላጊው ጥንቃቄ ተደርጎ እየተሠራበት ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ዘርፊያዎች ካሉ በኢንተርፖልም በኩል እየተገለጸልን ነው፡፡ ለምሳሌ የኤቲኤም ማሽን ስትጠቀም የሚፈጠሩ ማጭበርበሮች ይኖራሉ፡፡ ካርዶችን ኮፒ አድርገው ወይም ፈጥረው አድርገው የሚጠቀሙ ሌቦች አሉ፡፡ እንዲህ ያለው ነገር ስለሚታወቅ ቀድሞ የጥንቃቄ ሥራ ይሠራል፡፡

  ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ጥንቃቄ?

  አቶ አዲሱ፡- ለምሳሌ በኤቲኤም ማሽኑ ላይ ካሜራዎች አሉ፡፡ ማን በዚያ ካርድ ተጠቀመ የሚለውን ታያለህ፡፡ በካሜራ የሚደረገውን ክትትል ለማጠናከር በየቦታው መትከል አለብህ፡፡ ስለዚህ አገልግሎቱን ብቻ መስጠት ሳይሆን፣ አገልግሎቱን ለሥጋት እንዳይጋለጥ ያልተቋረጠ ክትትል መደረግ አለበት፡፡ ሰው በይለፍ ቃልና በተለያዩ መንገዶች እንዳይጠቃ መጠበቅ አለበት፡፡

  ሪፖርተር፡- እየተነጋገርንበት ካለው ጉዳይ ጋር ባይያያዝም አንድ ጥያቄ ላንሳ፡፡ ባለፈው ሳምንት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር ተገናኝታችሁ በምትመክሩበት ወቅት በማኅበራችሁ አማካይነት ሥጋት ናቸው ብላችሁ ካቀረባችኋቸው ጥያቄዎች አንዱ፣ አሁን የውጭ ባንኮች ቢገቡ እንጎዳለን የሚለው ይገኝበታል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት እንዲጠናከሩ የመንግሥት ጫና ይነሳልን ብላችኋል፡፡ ይህ ጥያቄያችሁ ከምን አንፃር የተነሳ ነው?

  አቶ አዲሱ፡- እኛ እንደ ሥጋት ያነሳነው መጠንከር አለብን በማለት ነው፡፡ በየትኛውም ጊዜ የውጭ ባንኮች ሊገቡ ይችላሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ሊፈቅድ ይችላል፡፡ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ስትሆን ይህ አይቀርም፡፡ ስለዚህ እስከዚያው ድረስ የአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት መጠንከር አለባቸው፡፡ ካፒታላችን ማደግ አለበት፡፡ ዕውቀት ማጎልበት አለብን፡፡ ቴክኖሎጂ መጠቀም አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ አቅም ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን አቅማችን በሚፈለገው ደረጃ እንዳይደርስ መንግሥት ተፅዕኖ እያደረገብን ነው የሚለውን ሐሳብ አንፀባርቀናል፡፡ ይህን ያልንበት ምክንያት አንዳንድ መመርያዎች የፋይናንስ ተቋማትን እንዳይጠናከሩ የሚያደርጉ በመሆናቸው ነው፡፡ ለምሳሌ የ27 በመቶው የቦንድ ግዥ ላይ በአነስተኛ ወለድ እንድንፈጽመው ይፈለጋል፡፡ 27 በመቶ ለቦንድ ግዥ የምናውለውን ገንዘብ ብንጠቀምበት የበለጠ አቅማችን ይጠነክር ነበር፡፡ የፋይናንስ ተቋማት እንዳይጠናከሩ የመንግሥት ተፅዕኖ አለበት ያልነው ሌላው ጉዳይ ደግሞ፣ ከምንሰበስበው የውጭ ምንዛሪ ውስጥ 30 በመቶ በገዛንበት ዋጋ ለብሔራዊ ባንክ ሽጡ መባላችን ነው፡፡ ይህንንም የውጭ ምንዛሪ ብንጠቀም ኖሮ የተሻለ ትርፍ አግኝተን አቅማችንን ባጎለበትን ነበር፡፡ ትርፋችን ባደገ ቁጥር አቅማችንን ማሳደግ፣ ካፒታላችንን መጨመርና ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት ያስችለን ነበር፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉት የመንግሥት ተፅዕኖዎች ተነስተው አቅም እንድንፈጥር ይደረግ በማለት ነበር ያቀረብነው፡፡ እነዚህ መመርያዎች ተነስተው ራሳችንን እናሳድግ ነው ያልነው፡፡ ለኢኮኖሚው ዕድገት የሚመጥን ዕድገት እንዲኖረን መመርያዎቹ ይነሱልን ብለናል፡፡

  ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምን ምላሽ ሰጡ?

  አቶ አዲሱ፡- እሳቸው አሁን ባለው ደረጃ ይህ መሆኑ አስፈላጊ መሆኑን ነው የጠቀሱልን፡፡ መመርያዎቹ አሁን ሊነሱ አይችሉም፡፡ እናንተ ግን በርትታችሁ እንድትሠሩ እንፈልጋለን፣ እንደግፋቸዋለን ብለዋል፡፡ የውጭ ባንኮች መግባትን በተመለከተው ምላሻቸው አሁን ባለው ሁኔታ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ አይደረግም፣ ለጊዜው ይህ አቅጣጫ የለንም ብለዋል፡፡

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት