Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአረቢካ ቡና ዝርያ እስከ ወዲያኛው የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

60 በመቶው የአራቢካ ቡና ዝርያዎች ሊጠፉ እንደሚችሉ ተመራማሪዎች ይፋ አድርገዋል

በየጊዜው በሚከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ፣ የደን ጭፍጨፋና የቡና በሽታዎች ሳቢያ መገኛውና መነሻው ከኢትዮጵያ የሆነው የአረቢካ ቡና ዝርያ ከዓለም ሊጠፋ የሚችልበት አጋጣሚ እየተቃረበ መምጣቱን ተመራማሪዎች ይፋ አደረጉ፡፡

በእንግሊዝ የሚገኘው ሮያል ቦታኒካል ጋርደንስ የተሰኘው የምርምር ተቋም ይፋ ባደረገው ጥናት መሠረት፣ ከኢትዮጵያ የተገኘውና አሁንም ድረስ በኢትዮጵያ በሰፊው የሚመረተው የአረቢካ ቡና ዝርያ ከምድረ ገጽ ሊጠፋ መቃረቡንና አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

በዓለም ላይ 124 ዝርያዎች የቡና ዝርያዎች ቢኖሩም የአረቢካና ሮቡስታ ቡና የተባሉት ዝርያዎች በሰፊው በመመረት ለንግድ ውለዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ባሻገር እንደ ማዳጋስካር ባሉት አገሮችም በሰፊው ይመረታል፡፡ ይሁንና ከእነዚህ ዝርያዎች ውስጥ 60 በመቶው ለጥፋት የተጋለጠ በመሆኑ፣ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የተቋሙ ተመራማሪዎች ባወጧቸው ጽሑፎች አስታውቀዋል፡፡ ከፓቶጂንና ከፈንጋይ እንዲሁም ከእንስሳት በሚመነጩ በሽታዎች ተጠቂ የሆነው ይህ ቡና፣ ነገሮች አሁን ባሉበት ሁኔታ ከቀጠሉ እ.ኤ.አ. በ2088 ማለትም ከ40 ዓመታት በኋላ 50 በመቶውን ዝርያ ለማጣት የሚያስገድድ ጥፋት እንደሚከሰት አስጠንቅቀዋል፡፡

ከአረቢካ ቡና ዝርያዎች ውስጥ የጫካ ቡናም በከፍተኛ ደረጃ የመጥፋት አደጋ ውስጥ እንደሚገኝ ያስታወቀው ሮያል ቦታኒካል ጋርደን፣ በዚህ ደረጃ በዋናነት ተጠቂ የሚሆኑት በኢትዮጵያ የሚገኙት የቡና ዝርያዎች ስለመሆናቸውም አስታውቋል፡፡

የዓለም የቡና ዘርፍ እስካሁን ባለው አኳኋን በሁለት የቡና ዝርያዎች ላይ ብቻ መመሥረቱ አደጋውን ይበልጥ እንደሚያባብሰው የጠቀሱት፣ የጥናቱ መሪ አሮን ዴቪስ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ የቡናው ዘርፍ ከሌሎች የግብርና ሥራዎች አኳያ የክብካቤና የዘላቂነት ምርምር ሥራዎች ላይ እስከ 30 ዓመታት በሚገመት የጊዜ ግምት ወደ ኋላ እንደቀረ ኮፊ ደይሊ ለተሰኘው የቡና የድረ ገጽ መጽሔት ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች የተሳተፉበት ይህ የምርምር ውጤት፣ በሌሎች የዓለም ዕፅዋት ላይ የተደቀነው የጥፋት አደጋ 22 በመቶ እንደሚገመት በመጥቀስ፣ በቡና ላይ ያጠላው የ60 በመቶ የጥፋት አደጋ ለኢንዱስትሪው ትልቅ ሥጋት ስለመሆኑ አብራርቷል፡፡

የኢትዮጵያ ቡና ለውጫዊ አደጋዎችና ተፅዕኖዎች ያለው ተጋላጭነት በየጊዜው እየተባባሰ መምጣቱ እየታየ ነው፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊትም በዚሁ በሮያል ቦታኒካል ጋርደንስ አማካይት ይፋ በተደረገ ጥናት መሠረት፣ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ሙቀት መጨመር ሳቢያ የመጥፋት ዕድሉ እየተባባሰ መምጣቱን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ የሙቀት መጨመር ብሎም የአየር ብክለት ሁኔታው አሁን ባለው ሁኔታ እየተባባሰ ከሄደ እንደ ሐረር ያሉ አካባቢዎች ከነጭራሹ ቡና አብቃይነታቸው ሊያከትም የሚችልበት አደጋ መቀደኑን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ የሐረር ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ከተሰጣቸው ሦስቱ የኢትዮጵያ ቡናዎች አንዱ በመሆን የንግድ ምልክትና የተጠቃሚነት መብት ለኢትዮጵያ ያስገኘ ነው፡፡ ሲዳማና ይርጋጨፌም ከሐረር እኩል ዕውቅና የተሰጣቸው ቡናዎች ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ እስከ 15 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ በቡና እርሻ ሥራ ኑሮውን ይገፋል፡፡ ከኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ዘርፍ ትልቁን ድርሻ የያዘው ቡና፣ ከ900 ሚሊዮን ዶላር በማገስኘትም የአገሪቱን ኢኮኖሚ ይደጉማል፡፡ በዚህ ዓመት ስድስት ወራት ውስጥም ከ330 ሚሊዮን ዶላር በላይ በማስገኘት ቀዳሚው የአገሪቱ የወጪ ንግድ  ምርትነቱን አስጠብቆ ይገኛል፡፡ መንግሥት በየጊዜው የቡናውን ዘርፍ ውጤታማነት ለማሻሻል የሚረዱ እንቅስቃሴዎች ሲያደርግ መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን፣ ከሰሞኑም ያረጁ የቡና ተክሎችን የማደስ ዘመቻ ጀምሯል፡፡

በሌላ በኩል በአሜሪካ በሚካሄደው የምግብና የመጠጥ ቅምሻ ውድድር ላይ በየጊዜው ከፍተኛ ውጤት እያስገኙ ያሉት የኢትዮጵያ ቡናዎች ዘንድሮም አብላጫውን ደረጃ በመያዝ አሸናፊ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡ ‹‹ጉድ ፉድ አዋርድስ›› በተሰኘው የልዩ ጣዕም ቡናዎች  የሽልማት መርሐ ግብር ላይ ከተወዳደሩት ውስጥ አብዛኛውን ያሸነፉት በኢትዮጵያ ቡናዎች የተወዳደሩ ቡና አዘጋጆች ናቸው፡፡ ባለፈው ዓመትም ከ15 በላይ የኢትዮጵያ ቡናዎችን በመጠቀም የተወዳደሩ ኩባንያዎች አሸናፊዎች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች