Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምርት ገበያው ኑግና ባቄላን ወደ ግብይቱ ለማምጣት መዘጋጀቱን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ኑግና ባቄላን በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ በማካታት የሚያገበያያቸውን ምርቶች ብዛት ለማሳደግ እየሠራ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡ የሽንብራና የአኩሪ አተር ምርቶች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በምርት ገበያው መስተናገድ ጀምረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድምአገኝ ነገራ እንዳስታወቁት፣ ኑግና ባቄላ በጥቂት ወራት ውስጥ ግብይታቸው እንደሚጀመር አስታውቀዋል፡፡

 ባለፈው ሳምንት ምርት ገበያውን ስለተቀላቀሉት የሽምብራና የአኩሪ አተር ምርቶች እንደተገለጸው፣ በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ መሠረት ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ በአማካይ 439 ሺሕ ቶን ሽምብራና 76 ሺሕ ቶን አኩሪ አተር በኢትዮጵያ ሲመረት ቆይቷል፡፡ ይህንን ያጣቀሱት አቶ ወንድምአገኝ፣ ከዚህ ምርት ውስጥ በየዓመቱ በአማካይ 54 ሺሕ ቶን ሽምብራና 58 ሺሕ ቶን አኩሪ አተር ለውጭ ገበያ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡ ለአብነት ያህል ዓምና 110 ሺሕ ቶን አኩሪ አተርና 49 ሺሕ ቶን ሽምብራ ለውጭ ገበያ ቀርቦ፣ በጠቅላላው ከ91 ሚሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱንም አስታውሰዋል፡፡

ምርት ገበያው በውጭ ገበያ ተፈላጊነት ያላቸውን ሁለቱን ምርቶች ወደ ግብይት ሥርዓቱ ያስገባው አርሶ አደሩ፣ አቅራቢዎችና ላኪዎች ብሎም ኢትዮጵያ ተጠቃሚ የምትሆንበትን አሠራር ለማስፋት እንደሆነ አቶ ወንድማገኝ ይገልጻሉ፡፡ በዚህ መሠረት ምርቶቹን ከታኅሳስ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በዘጠኙም ቅርንጫፎቹ መቀበል መጀመሩንና አቅራቢዎችም ከፍተኛ ፍላጎት በማሳየታቸው በሁለት ሳምንታት ውስጥ 29,787 ኩንታል ቶን አኩሪ አተር ለገበያ አቅረቦ እንደነበር፣ በአራት የግብይት ቀናት ውስጥ ብቻ 2,550 ኩንታል ምርት መገበያየቱን አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከጠቅላላው የአኩሪ አተር ምርት ውስጥ 99.6 በመቶ የሚመረተው በኦሮሚያ፣ በአማራና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች እንደሆነ የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ሽምብራም 90 በመቶው በአማራና በኦሮሚያ እንደሚመረት ተጠቅሷል፡፡ እነዚህን ምርቶች በከፍተኛ መጠን ከሚገዙ አገሮች መካከል የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ፓኪስታንና ህንድ ሽምብራን፣ ቻይና፣ ህንድ፣ ሲንጋፖርና ቬትናም አኩሪ አተርን በመግዛት ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ ሁሉም ምርቶች በዓለም ገበያ ያላቸው ተፈላጊነት ከፍተኛ በመሆኑ በምርት ገበያው በኩል ግብይታቸው ሲፈጸም ለወጪ ንግዱ አስተማማኝ አቅርቦት እንዲኖርና ጥራቱን የጠበቀ ምርትም እንዲላክ ያስችላል ተብሏል፡፡ አቅራቢዎችም ግብይት በተፈጸመ ማግሥት የምርታቸውን ዋጋ እንዲያገኙ ስለሚረዳቸው፣ ምርትና ምርታማነትም በዚህ አግባብ እንዲያድግ ስለሚያግዝ በምርት ገበያው በኩል ምርቶች የመስተናገዳቸው ፋይዳ ወሳኝ እንደሆነ ይታመናል፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአኩሪ አተርና የአረንጓዴ ማሾ ግብይት አስገዳጅ ሆኖ በምርት ገበያው በኩል ብቻ እንዲከናወን በመወሰኑ፣ ግብይቱ ውጤታማ ሆኖ እንዲጓዝ አስተዋኦ እንደሚያደርግ አቶ ወንድምአገኝ ተናግረዋል፡፡ ሽምብራ በአማራጭ ምርትነት ግብይት እንዲፈጸምበት ቢወሰንም በአርሶ አደሩና በአቅራቢዎች ዘንድ በምርት ገበያ በኩል ግብይቱ እንዲከናወን ያለው ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ፣ ምርቱ በብዛት ይቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡

‹‹በሽምብራና በአኩሪ አተር ግብይት ውስጥ ተሳታፊ የሆናችሁ ተዋንያን እንኳን ወደ ዘመናዊ የግብት ሥርዓቱ ተቀላቀላችሁ፣ ‹‹ሽምብራ ገበያው ደራ፣ አኩሪ አተር ኮራ ብለን አዲሱን ግብይት የምናስተዋውቀው የምርቶቹ ወደ ዘመናዊ ግብይት ሥርዓቱ  መምጣታቸው ወደፊት የሚኖረውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማስገንዘብ ነው፤›› በማለት አቶ ወንድምአገኝ ምርቶቹን ማገበያየት ባስጀመሩበት ወቅት ተናግዋል፡፡

የሁለቱን ምርቶች ግብይት ያስጀመሩት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ሲሆኑ፣ በፕሮግራሙ ላይ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦሊሮ ኦፒዬና በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር አቶ ፍፁም አረጋ ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የአገልግሎቱን ተደራሽነት ለማሳደግ ከሚያከናውናቸው ተጨማሪ ተግባራት መካከል ክልላዊ የኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከላትን ማቋቋም የሚገኝበት ሲሆን፣ በዚህ መሠረት የመጀመሪያውን ማዕከል በሐዋሳ መመረቁን አስታውሰዋል፡፡ በቅርቡ የግንባታው 90 በመቶ የተጠናቀቀው የሁመራ የኤሌክትሮኒክስ የግብይት ማዕከል አገልግሎት መስጠት ይጀምራል፡፡ በቀጣይም ሦስተኛው ማዕከል በነቀምት ይከፈታል፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ በጂማ፣ በጎንደር፣ በኮምቦልቻና በአዳማ ማዕከላት ለመክፈት እሠራን ይገኛልም ብለዋል፡፡

የምርት መቀበያ ተደራሽነታችንንም ለማሳደግ በመቱና በቴፒ አዳዲስ ቅርንጫፎችን ለመክፈት ዝግጅት እያደረግን ነው ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፣ የመቱ ቅርንጫፍ በቅርቡ ሥራ ይጀምራል ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የመጋዘን አገልግሎታችንን በቴክኖሎጂ በተደገፈ አሠራር ለማሻሻል፣ የመጋዘን ደረሰኞች ለባንክ ዋስትና ሆነው ገበሬው ብድር የሚያገኝበትን አሠራር ለመዘርጋትና የመሳሰሉትን ተጨማሪ አገልግሎት ለመስጠት የዝግጅት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡ ይህም ዘመናዊ የግብይት ሥርዓቱ የበለጠና የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ሰፋፊ ሥራዎችን እየሠራ ስለመሆኑ ወቅታዊ ክንውኑ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች