Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በምዕራብ ወለጋ የሚገኙ ባንኮች ምን ያህል ገንዘብ እንደተዘረፉ እስካሁን አልታወቀም

ተዛማጅ ፅሁፎች

በምዕራብ ወለጋ በሦስት ዞኖች ውስጥ የግልና የመንግሥት የባንኮች ላይ ዝርፊያ መፈጸሙንና ቅርንጫፎቹም አገልግሎት እንዳቋረጡ ከየአቅጣጫዎች ሲነገርና ሲዘገብ ሰንብቷል፡፡

በምዕራብ ወለጋ በተደራጁና በታጠቁ አካላት የተዘረፉት ባንኮች ብዛት ምን ያህል ነው? የሚለው ጉዳይ ብዥታ ቢፈጥርም፣ በአገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በቀናት ልዩነት ውስጥ ባንኮች ላይ የተፈጸመው የዘረፋ ተግባር ከዚህ ቀደም ያልታየ ነበር፡፡

 በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የግል ባንኮች ኃላፊዎች እንደጠቆሙት፣ በዚህ ደረጃ ባንኮችን ለመዝረፍ የተደረገ ሙከራ ከዚህ ቀደም አልታየም፡፡ በእርግጥ በቀደሙት ጊዜያት የፖለቲካ ቡድኖች በተደራጀ ሁኔታ ባንኮች ላይ ዘረፋ ፈጽመዋል፡፡ ለአብነትም የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ታጋዮችን ጨምሮ ሌሎችም በቀደሙት ጊዜያት የተደራጀ ዘረፋ መፈጸማቸው በታሪክ የሚጠቀስ ነው፡፡ ነገር ግን በዚያን ጊዜ በባንኮች ይቀመጥ የነበረው ገንዘብ ከአሁኑ አንፃር አነስተኛ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በርካታ መጠን ያለው ገንዘብ በየባንኮቹ ቅርንጫፎች ሊገኝ ስለሚችል እንዲህ ያለው ወንጀል አሳሳቢ እንደሆነ የባንክ ባለሟሎች ይናገራሉ፡፡

በምዕራብ ወለጋ በሚገኙ ባንኮች ላይ የተፈጸመው ዘረፋ የተደራጀና በትጥቅ የታገዘ በመሆኑ፣ በቅርብ ጊዜ ከተፈጸሙት ሁሉ መጠነ ሰፊ እንደሆነም ይጠቀሳል፡፡ በአካባቢው አንፃራዊ ሰላም ቢሰፍንም አንዳንድ ባንኮችና ሠራተኞቻቸው ከሥጋት ተላቀው ሥራቸውን ለማከናወን እንደተቸገሩ እየገለጹ ነው፡፡ በባንኮቹ ላይ የተፈጸመውን ዘረፋ በማስመልከት የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን እንዳስታወቀው፣ ዘረፋው የ18 ባንኮችን ቅርንጫፎች ያዳረሰ ነበር፡፡

ሪፖርተር ባደረገው ማጣራት፣ ባለፈው ሳምንት በአካባቢው በሚገኙ የባንኮች ቅርንጫፎች ላይ ያልተሳኩ የዝርፊያ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ ቅርንጫፎቻቸው በተጣቂዎች ከተዘረፉባቸው ባንኮች መካከል የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክና አዋሽ ባንክ እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡ ዝርፊያውንም ሆነ ሙከራውን ለየት የሚያደርገው በአንድ ጊዜ ከስድስት በላይ ቅርንጫፎችን ያዳረሰ መሆኑ ላይ ነው፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የፀጥታ ችግር ባጋጠመበት ወቅት ባንኮች ቅርንጫፎቻቸውን በተደጋጋሚ ይዘጉ እንደነበር ሪፖርተር ያነጋገራቸው የባንኮች ኃላፊዎች ገልጸው፣ ገንዘብ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማጓጓዝም ከፍተኛ ሥጋት ሆኖባቸው እንደቆየም ያስታውሳሉ፡፡ ይህም ሆኖ የቀድሞው የኮንስትራክሽንና የቢዝነስ ባንክ እንዲቃጠል መደረጉና መዘረፉም የሚታወስ ነው፡፡ ነገር ግን ከሰሞኑ በምዕራብ ወለጋ የተፈጸመውን ዓይነት ጉዳት እንዳላጋጠመ በመጥቀስ፣ ባንኮች የተለየ ጥበቃ እንደሚያስፈልጋቸው አመላካች ድርጊት ሆኖ እንደተገኘ እየተነገረ ነው፡፡

ዘረፋ ከተፈጸመባቸው ባንኮች አንዱ ከሆነው ከኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ያገኘነው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ እስካሁን ሦስት ቅርንጫፎቹ በታጣቂዎች ተዘርፈውበታል፡፡ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ አንደኛው ቅርንጫፉ መዘረፉን ገልጿል፡፡ የአዋሽና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስንት ቅርንጫፎቻቸው እንደተዘረፉ እስካሁን ይፋ አላደረጉም፡፡

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ፣ በምዕራብ ወለጋ 15 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፣ ዘረፋ የተፈጸመበት በሦስቱ ቅርንጫፎቹ ላይ እንደሆነ የገለጹት የባንኩ አንድ ኃላፊ፣ በሦስቱም ቅርንጫፎቹ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ሳይዘረፍ እንዳልቀረ ይገመታል፡፡

በትክክል ምን ያህል ገንዘብ እንደተዘረፈ ለማወቅ ግን በዝርዝር ማጣራት ይጠይቃል ያሉት እኚሁ ኃላፊ፣ አሁን ባለው ሁኔታ የተዘረፈውን የገንዘብ መጠን ለማወቅ ባንኩ አስቸጋሪ እንደሆነበት ገልጸዋል፡፡ በተለይም የቅርንጫፎቹ ኃላፊዎች በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ሥጋት ከአካባቢው በመውጣታቸው የተጣራ መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡

የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቢ ሳኖ በበኩላቸው፣ በአካባቢው የባንኩን ቅርንጫፎች ሰብሮ ለመዝረፍ የተደረገ ሙከራ እንደነበር ተናግረው፣ ጉሊሲ ተብሎ በተሰየመው የባንኩ ቅርንጫፍ ላይ ግን ታጣቂዎች አስገድደው ዘረፋ መፈጸማቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት በተለይም ቅዳሜና እሑድ በባንኮች ላይ በዘመቻ መልክ ዘረፋና የዘረፋ ሙከራ እንደተቃጣ ተነግሯል፡፡ አቶ አቢ እንደገለጹት፣ በምዕራብ ወለጋ ከሚገኙት የባንኩ ቅርንጫፎች መካከል ዝርፊያ የተፈጸመበት የጉሊሲ ቅርንጫፍ ወደ 2.1 ሚሊዮን ብር የሚገመት ዝርፊያ ደርሶበታል፡፡

ከፀጥታው ችግር ባሻገር በአካባቢው የሚገኙ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክም ሆነ የሌሎች ባንኮች ቅርንጫፎች ዘረፋ እንደተፈጸመባቸው መታወቁን ተከትሎ ለቀናት አገልግሎት ለማቋረጥ ተገደዋል፡፡ ዝርፊያ የተፈጸመባቸው ቅርንጫፎችም እስካሁን አልተከፈቱም፡፡

በኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በኩል የወጣው መግለጫ፣ ባለፉት አምስት ቀናት ውስጥ በምዕራብ ወለጋ፣ ቄሌም ወለጋና ሆሮ ጉዱሩ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ 18 ባንኮች ላይ ዘረፋው ተፈጽሟል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ እንዲሁም በኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም ላይም ዝርፊያ መፈጸሙን የክልሉ መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡

በተፈጸመው ዘረፋ ሳቢያ በአካባቢው የሚገኙ ቅርንጫፎች ተረጋግተው ለመሥራት የተቸገሩ በመሆኑ፣ የፀጥታ ኃይሎች በሌሉባቸው አካባቢዎች አሁንም ድረስ ባንኮቹ ቅርንጫፎቻቸውን መክፈትና ሥራ መጀመር አልቻሉም፡፡ ይህም የባንክ አገልግሎት የሚፈልጉ ደንበኞቻቸውን እንዳያስተናግዱ በማድረጉ በአካባቢው ያለውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ጎድቶታል፡፡ ባንኮቹ ሥራቸውን ተረጋግተው ለመሥራት የመንግሥትን ሰላም የማስከበር ተግባር እንደሚፈልጉ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

እንደ አቶ አቢ ማብራሪያ፣ ዘረፋው በገንዘብ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ባንኮች የሕዝብ ኪሶች እንደመሆናቸው መጠን ደኅንነታቸው ሊጠበቅ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ የባንኮች  አገልግሎት መስተጓጎልም ኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር ስለሚችል ሕዝቡም የባንኮችን ደኅንነት በመጠበቅ ሊሳተፍ እንደሚገባው አቶ አቢ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ሀባም ከአቶ አቢ ጋር በመስማማት፣ የዘረፋና መሰል ተግባራትን ሕዝቡም እየተከላከለ የገዛ ሀብቱን መጠበቅ እንደሚኖርበት አስታውቀዋል፡፡ በእያንዳንዱ ባንክ የሚቀመጠው ገንዘብ የሕዝቡ የራሱ ሀብት በመሆኑ፣ ባንኮች ከሚያደርጉት ጥንቃቄና ጥበቃ ባሻገር ኅብረተሰቡም በእኔነት መጠበቅ እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡ በምዕራብ ወለጋ በሚገኙ ባንኮች ላይ በተፈጸመው ዘረፋ ምን ያህል ገንዘብ እንደተወሰደ እስካሁን መረጃው ተሟልቶ አልቀረበም፡፡ ሆኖም ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው ባንኮች መረጃው ተሰባስቦ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንደሚቀርብ አቶ አዲሱ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች