Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ብላሽ ግንባታ

ስለአገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ብዙ ሲባል ኖሯል፡፡ በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ የያዘው ይህ ዘርፍ፣ ካለው አጠቃላይ ትይዩ ባሻገር ለአገር ሀብት ብክነትም ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡

ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያሉበት የግንባታው ዘርፍ በውስጣዊና ውጫዊ ተፅዕኖችም የተከበበ ነው፡፡ ለዘርፉ ከሚፈሰው መዋዕለ ንዋይ አንፃር ተገቢው ትኩረት ተችሮታል ብሎ ማመንም አስቸጋሪ ነው፡፡ አብዛኞቹ የግንባታ ሥራዎችም ጥያቄዎች የሚነሱባቸው ናቸው፡፡ ከአነስተኛ እስከ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በሰበብ አስባቡ በተያዘላቸው የግንባታ ጊዜና በጀት የማይጠናቀቁ፣ ሕዝብን በማስለቀስ የሚታወቁም ናቸው፡፡ ከግንባታ ዲዛይን ጀምሮ በሚታዩ ክፍተቶች ሳቢያ፣ ግንባታ ከጀመሩ በኋላ ጭምር የዲዛይን ማሻሻያ ተደርጓል በሚል ሰበብ ወጪዎች እየናሩ፣ የተሠራው እየፈረሰ፣ የታቀደው እየተከለሰ ስንት የሚሠራ የአገር ሀብት ለጥቂቶች ብልጽግና እንደዋለ በገሀድ የሚታወቅ ነው፡፡

ከጨረታ ሰነድ ዝግጅት ጀምሮ ያለው ሒደትም ቢሆን ለዋልጌ አሠራር የተጋለጠ፣ በጥቅም የተጣመሩ ገንቢና አስገንቢዎች የሚጠቃቀሙባቸው፣ በሕዝብ ሀብት ቁማር እየተጫወቱ የሚደልቡባቸው ስንትና ስንት መረኔዎችን ስንታዘብ ኖረናል፡፡

እንዲህ ያለው ገመድ በጠላለፋቸው አሠራሮች አማካይነት እንዲገነቡ የሚታቀዱት ፕሮጀክቶችን በበላይነት ለመምራትም የሚሰየሙት አካላትም ከችግር አይጠዴ ናቸው፡፡ የኮንትራት አስተዳደራቸው ደካማ ነው፡፡ በብልሹ አሠራሮች የተጨማለቀና ለሌቦች የተመቻቸ ዋሻ የመንግሥት የግንባታ ግዥ ነው ማለት ይቻላል፡፡  ዘርፉን በጥብቅ ለመቆጣጠር በሚያስችል ሥልት እንዲመራ አለመደረጉም የግንባታ  ኢንዱስትሪው ላይ የተንሰራፋውን ችግር አባብሶታል፡፡

የእኔነት ስሜት በጠፋበትና ሕዝብም መንግሥትም ቢጠቀሙ ባይጠቀሙ ምን ቸገረኝ በበዛበት አገር፣ ግንባታው የተጀመረን ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ ፈተናዎቹ የትየለሌ ናቸው፡፡ በአግባቡ ባለመሠራቱ ሳቢያ የተጓተተውን የግንባታ ሥራ ለመታደግ ሲባል ለሌላ ተቋራጭ እንዲሰጥ ሲደረግም አዲሱ ተቋራጭም የባሰውን ወጪ የሚያስወጣ ሆኖ ይገኝና ግንባታዎች ከመጠናቀቂያ ጊዜያቸው በላይና ከሚያስፈልጋቸው ገንዘብ በላይ እየወሰደባቸው ከንቱ ልፋት እየፈጠሩ ነው፡፡ ይህንን ማስቀረት አልተቻለም፡፡ ኪሳቸውን በሕገወጥ መንገድ ለማሳበጥ ሆነ ብለው የግንባታ ፕሮጀክቶች ከተመደበላቸው በላይ ወጪ እንዲወጣባቸው የሚያደርጉ ተቋራጮችና አማካሪዎች ብሎም ለዚህ ዝርፊያ የሚተባበሩ የመንግሥት ኃላፊዎች ስንትና ስንት በደል አድርሰዋል፡፡

ከዝርፊያው ባሻገር የጥራት ጉዳይ ቅንጦት እስኪመስል ድረስ ከተገቢው በላይ ወጪ የወጣባቸው ግንባታዎች ፈጅተዋል የተባለውን ያህል ጥራት የሌላቸው ሆነው መገኘታቸውም ጉዳቱን ድርብርብ ያደርጉብናል፡፡ ጥራት የኢንዱስትሪው መሠረታዊ ችግር ነው፡፡ ለተፈለገው ግንባታ የማይገባውን ግብዓት መጠቀም፣ የሰው ኃይልና መሣሪያ አለማሟላት፣ ለፕሮጀክቱ የተከፈለውን ቅድመ ክፍያ ይዞ መጥፋት፣ ሲያሻውም በማናለብኝነት በጅምሩ ግንባታውን አቋርጦ ይህ ጎደለኝ፣ ይህን አንሱልኝ በሚል ሰበብ ማጓተት፣ በግንባታ ስም አካባቢን መረበሽ ወዘተ. የኢንዱስትሪው መገለጫዎች ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉትን ሕገወጥ ተግባራት ለመግራት የወጣው ሕግም ተግባር ላይ ባለመዋሉ ኢንዱስትሪው ያለ ያዥ ገናዥ ማንም የሚፈነጭበት፣ የአገር ሀብት የሚዘረፍበት እንዲሆን አድርታል፡፡ መንግሥት ከ60 በመቶ በላይ በጀቱን ለግንባታ ሥራዎች እየመደበ እንዲህ ያለ ንዝህላልነትን ማስፈኑ የመጀመሪያው ተጠያቂ ያደርገዋል፡፡

ይህም ሲባል በግንባታ ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚታየው ችግር የአንድ ወገን ብቻ ባለመሆኑ አጠቃላይ ዘርፉን መፈተሽና አሠራሩን መከለስ አስፈላጊ ነው፡፡ አጠቃላይ ሪፎርም የሚያስፈልገው ዘርፍ በመሆኑ፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኮንትራት አስተዳደሩ፣ የተቋራጩ፣ የአማካሪውና ግንባታውን በባለቤትነት የሚመራው ተቋም ሙያዊ ዲሲፕሊን፣ ጨዋነትና ሕዝባዊና ኢትዮጵያዊ ተጠያቂነት ያለበት ፈራሔነትን የሚጠይቅና የሚጠብቅ ዘርፍ ነው፡፡

ዘርፉ ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት በብዙ ሊያደክም ቢችልም ማስተካከል እንደሚቻል ግን አይጠረጠርም፡፡ ምክንያቱም አጠቃላይ የግንባታ ሒደቱን ግልጽ በሆነ የመከታተያ ሥልት በመምራት፣ ሁሉንም ወገን ተጠያቂ የሚያደርግ አሠራር በመዘርጋት ለችግሩ መላ ማበጀት ይቻላል፡፡ ከሰሞኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተደደር በዚህ መንገድ ለመጓዝ የቆረጠ ይመስላል፡፡ ከፕሮጀክት አስተዳደር ጀምሮ ተቋራጮችን በመመልመል ረገድ፣ በክትትል በኩል ብሎም ጨረታ አወጣጥ ላይ ለውጦች እንደሚደረጉ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ሲናገሩ አድምጠናል፡፡ በሕዝብ ገንዘብ የግል ሀብትን ማደለብ እንደማይቻል፣ የታክስ ከፋዩ ጉሮሮ እየታነቀ በሚሰበሰብ ገንዘብ ማንም ተቋራጭ እንዳሻው ሊበለጽግበት እንደማይፈቅዱ አስታውቀዋል፡፡ እሰየው፡፡ ግን ደግሞ እንዲህ ጆሮ የሚያሰባ ንግግር ብዙ ስለተለማመድን ተግባራዊነቱን ብንነቅፍ አይገርምም፡፡ 

አንዳንዴ እንደምንታዘበው በእጁ ያለውን ፕሮጀክት ሳይጨርስና በአግባቡ ማጠናቀቅ እንዳቃተው እየታየ ተጨማሪ ሌላ ሥራ መስጠት ምን ማለት ነው? ይህንን ጥያቄያችንን ከንቲባው ምላሽ ሲሰጡበት መስማታችንም አስደስቶናል፡፡ እያንዳንዱ ተቋራጭ ይመዘናል፡፡ ይጠናል፡፡ ጥቁር መዝገብ ይያይዝበታል፡፡ እስከወዲያኛው እንዳይሳተፍ ሊታገድና በሕግ ሊጠየቅ የሚችልበት አካሔድ መዝጋቱን ስለገለጹልን የተበላሸው እንደሚቃና ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ይህ አሠራር በአገር አቀፍ ደረጃም እንደሚያዛመት እንጠብቃለን፡፡

እንደ ህዳሴው ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ያሳደሩብንን ኢኮኖሚያዊ ጫና መመልከቱ ለተነሳንበት ጉዳይ አስረጅ ነው፡፡ በ80 ቢሊዮን ብር በጀት ያውም ተከልሶ ወደ 74 ቢሊዮን ብር ዝቅ መደረጉ ሲነገርና በአምስት ዓመታት ይጠናቀቃል ስንባል የቆየነው ይህ ግዙፍ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት፣ ግንባታው ሳያልቅ ያውም 65 በመቶው ብቻ ተገባዶ፣ ወጪው ግን 100 ቢሊዮን ብር መድረሱ ለሕዝብ ቁስል፣ ለአገርም ውልቃት ነው፡፡ ለተቀረው ሥራ የሚጠይቀው ወጪ 30 ወይም 40 ቢሊዮን ብር እንኳ ቢሆን፣ ይህ ተጨማሪ ወጪ ስንት ኃይል ማመንጫዎችን ያስገነባን እንደነበር መጥቀሱ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ ተገንብቶ አልቆ ቢሆን ኖሮ በዓመት 800 ሚሊዮን ዶላር ያስገኝ እንደነበር ሲታሰብም ምን ያህል የከፋ ችግር ውስጥ ዘቅጠን እንደከረምን ያሳያል፡፡

እንደ ህዳሴው ግድብ ሁሉ ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶችም በተመሳሳይ መንገድ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ዋጋ እያስከፈሉ ናቸው፡፡ የሕንፃና የመንገድ ፕሮጀክቶች በታቀደው አግባብ እየተሠሩ አይደለም፡፡ በአዲስ አበባ በግልም ሆነ በመንግሥት ባለቤትነት የሚገነቡ የትኛውም ዓይነት ግንባታዎች ከችግር የፀዱ አይደሉም፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ግንባታቸው ተጀምሮ በሰበብ አስባቡ ለዓመታት የቆሙ ሕንፃዎችን ዞር ዞር ካልን ብዙ ልንቆጥር እንችላለን፡፡ ለምሳሌ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታዎች ውስጥ አንዱም በተያዘላቸው ጊዜ አላለቁም፡፡

ከዛሬ 15 ዓመታት በፊት የተጀመረው የማሪታይም (አሁን የኢትዮጵያ ንግድ መርከብና የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት) ሕንፃ አሁንም ኧረ ከፍፃሜ አድርሱኝ እያለ ነው፡፡ በአንፃሩ ከዚህ ሕንፃ በላይ ትልልቅ የሆኑት ከኋላው ተጀምረው ሲጠናቀቁ መታዘባችን የአገራችንን ግንባታና አጠቃላይ የተበለሻሸ አሠራሩን የሚያስተካከል መድኃኒት ብንሻ ማን ይደንቀዋል፡፡

ይህ የማሪታይም ሕንፃ ሲጀመር ይወጣበታል የተባለውን ገንዘብና እስካሁን የወጣበትን ወጪ ስናሰላ ከዚሁ ሕንፃ ጋር የተስተካከለ ሁለትና ሦስት ሕንፃ የሚያስገነባ ነበር፡፡ የመዘግየትና ወጪን በእጥፍ ማሳደጉ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ ቢጠናቀቅ ሕንፃው ያስገኝ የነበረው ገቢ ሲሰላ ጥፋቱ እጥፍ ድርብ መሆኑን እንረዳለንና ጉዳዩ በእጅጉ ሊታሰብበት የሚገባ የለውጥም አንድ አካል ሆኖ ሪፎርም የሚያስፈልገው ነው፡፡

ምክትል ከንቲባ ታከለ የጀመሩት እንቅስቃሴና ማስጠንቀቂያቸውን በመልካም ጅምርነቱ እንውሰደው፡፡ በ300 ሚሊዮን ብር የተጀመረ የመንገድ ግንባታ አንድ ቢሊዮን ብር ሲደርስ ጠያቂና ተጠያቂ ያለመኖር የተፈጠረው ችግር መሆኑን መግለጻቸው፣ የመንገድ ሥራ በብድር የሚካሄድ በመሆኑም ጭምር መጓተትና ብንክነትን እንደማይታገሱ መግለጻቸው ተስፋ እንድንሰንቅ ያደርጋል፡፡ በእርግጥም የኢንዱስትሪው የተበላሸ ታሪክ መቀየር ይኖርበታል፡፡ ይህ የሚሆነው ግን በአንደበትና በአንድ ሰሞን ዘመቻ ብቻ እንዳልሆነ መታወቅ አለበት፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት