Thursday, February 22, 2024

ራሱን እያስታመመ የሚገኘው ኢሕአዴግ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹እንደሚታወቀው ኢሕአዴግ በየትግል ምዕራፉ ራሱን ከሁኔታዎች ጋር እያጣጠመ፣ እያስተካከለና እያጠራ የመሄድ ተሞክሮዎች ያሉት ድርጅት ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ራሱን ከሕዝቡ ፍላጎቶችና ከአዳጊ ሁኔታዎች ጋር በማጣጣም፣ ከሚፈለገው የአመራር ብቃትና ቁመና ላይ ከመድረስ አኳያ ከፍተኛ ድክመቶች አሉበት። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራችን ያጋጠመው የፖለቲካ ቀውስም ከዚሁ ድክመት የሚመነጭ ነው።››

ከላይ የተገለጸው ሐሳብ ከመስከረም 23 ቀን 2011 ጀምሮ ለሦስት ቀናት በሐዋሳ ከተማ በተካሄደው የኢሕአዴግ 11ኛ ጉባዔ ላይ የቀረበ የመወያያ ሰነድ፣ የአገሪቱን ወቅታዊ የፖለቲካ ቀውስ የገለጸበትና አገር የሚመራው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ለዚህ ቀውስ ያበረከተውን ቀዳሚ ድርሻ ያመለከተበት ነበር።

ከላይ በተገለጸው ሐሳብ ውስጥ ሁለት ግዙፍ ነጥቦች ጉልህ ሆነው ይታያሉ። አንድም ኢሕአዴግ ራሱን እያስተካከለና እያነጠረ የመሄድ ተሞክሮ ያለው ድርጅት መሆኑን፣ ሌላው ደግሞ ኢሕአዴግ አለኝ የሚለው ይህ ተሞክሮ አሁን ከውስጡ ጠፍቶ አገሪቱ ለምትገኝበት የፖለቲካ ቀውስ ዋነኛ ምንጭ እንዲሆን መዳረጉን ያመለክታሉ።

ኢሕአዴግ ወደዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዴት ገባ የሚለው ጥያቄም በዚሁ ሰነድ ጥርት ብሎ ተብራርቷል። ይኸውም የድርጅቱ ውስጣዊ ዴሞክራሲ መሞትና በኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች መካከል፣ እንዲሁም በእያንዳንዱ ፓርቲ ውስጥ እርስ በእርስ መጠራጠር መጎልበቱ በመሠረታዊነት የተጠቀሰ ነው።

ነገሩ ጥያቄ እንዲያጭር የሚያደርገው ከሦስት ዓመታት በፊት በተካሄደው የኢሕአዴግ 10ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ፣ ይኸው ተመሳሳይ ጉዳይ በስፋት ውይይት ተደርጎበት የመፍትሔ ውሳኔ ተላልፎ የነበረ መሆኑ ነው።

ራሱን እያስታመመ የሚገኘው ኢሕአዴግ

 

በወቅቱ በተደረገው በዚህ ጉባዔ ይኸው ተመሳሳይ የኢሕአዴግ ሕመም ላይ በመምከር፣ ‹‹ኢሕአዴግ የፖለቲካ ሁኔታው የሚጠይቀውን ጥንካሬ ይዞ የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ፣ የአመራሩንና የአባላቱን ፖለቲካዊና ርዕዮተ ዓለማዊ ብቃታ በማጎልበት ብቁ ማድረግ ይገባል፤›› በማለት ውሳኔ አሳልፎ ነበር።

ይሁን እንጂ አፈጻጻሙ በተቃራኒው ሆኖ፣ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታም በዚሁ ምክንያት ከዓመት ዓመት ተባብሶ የመበተን አደጋ በተጋረጠበት ሁኔታ ውስጥ 11ኛው ጉባዔው ላይ ደርሷል።

በሐዋሳው ጉባዔ ላይ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ድርጅታዊ የፖለቲካ ሥራዎች በመገምገም ለውይይት የቀረበ ሰነድ፣ ‹‹አመራሩ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ አመራር እንዲሰጥ ሲጠበቅ፣ መሠረታዊ የሚባሉ የመስመር ጉዳዮች ላይ ጭምር ዝንፈቶች የሚታዩበት ሆኖ ቆይቷል፤›› በማለት ተመልክቶታል።

በሌላ በኩል የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲያዊ ትግል የተዳከመበት ወቅት እንደነበር፣ የአመራር ነፃና ግልጽ ተሳትፎና የተሟሟቀ የሐሳብ ውይይት የጠፋበት፣ የሐሳብ ልዩነት ያለማስተናገድ፣ ሐሳቦችን ማፈን፣ ቂም መቋጠር፣ ሐሜትና አሉባልታ የተበራከተበት እንደነበር ሰነዱ ይገመግማል፡፡ በመርህ ላይ ያልተመሠረተ ትግል ማካሄድ፣ ይኼንን ተከትሎም የአመራሩ ጓዳዊ ግንኙነት በርካታ ችግሮች ያሉበት መሆኑ፣ ከተግባር የተነጠሉ ግምገማዎች እየሰፉ በመምጣታቸው ምክንያት የግል ሐሳብን የማይደግፉ አመራሮችን ማጥቃትና በመርህ አልባ ግንኙነት መጠቃቀም የተስተዋለባቸው ዓመታት እንደነበሩ ይጠቁማል፡፡

የድርጅቱ ግምገማዎች፣ እንዲሁም ሒስና ግለ ሒስ ለግንባታ መሆናቸው ቀርቶ የማስፈራሪያና ማጥቂያ እየሆኑ መምጣታቸውንም ይገልጻል፡፡

‹‹ስለሆነም ድርጅቱ በውስጡ ጠንካራ ዴሞክራሲ ሳይሰፍን ጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት ሊገነባ አይችልም፤›› ሲል የችግሩን ጥልቀት አመላክቷል፡፡

የድርጅቱ አመራርና አባላት ለሚታገሉለት ዓላማ ስኬታማነት ለየትግል ምዕራፉ የሚመጥን የፖለቲካዊና ርዕዮተ ዓለማዊ ብቃትና ሥነ ምግባር ሊኖራቸው የግድ ቢሆንም፣ የአመራሩና የአባላቱ ፖለቲካዊና ርዕዮተ ዓለማዊ ብቃት ችግሮችን በመሠረታዊነት የሚፈታ አለመሆኑን፣ በዚህም ረገድ የግንባታ ሥራ አለመከናወኑን ያትታል፡፡

በየደረጃው የሚገኙ የድርጅት አመራር አባላትና አደረጃጀቶች ተልዕኳቸውን በብቃት ለመፈጸም ከሚችሉበት ቁመና ላይ አለመድረሳቸውን፣ በተለይም የህዋስና የመሠረታዊ ድርጅቶች በእጅጉ የተዳከሙ መሆናቸውን ሪፖርቱ ይዘረዝራል፡፡

የአባላት ምልመላ ሥራው ጥራት የሌለው፣ ከድርጅቱ ጥቅም ፈልጎ የሚመጣውን ሁሉ አሠራሩን ሳይከተሉ የመቀበል፣ በተጨማሪም ከምልመላው የጥራት ችግር ባሻገር አባላት ድርጅቱን በብዛት የሚለቁበት ሁኔታ መፈጠሩን ያብራራል፡፡

የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባርን፣ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ከምንጫቸው በማድረቅ መልካም አስተዳደርን ማስፈን እጅግ ወሳኝ መሆኑ በ10ኛው ጉባዔ በግልጽ የተቀመጠ አቅጣጫ የነበረ ቢሆንም፣ በቁርጠኝነት ባለመፈጸሙ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ሙስናን ከምንጩ በማድረቅ መልካም አስተዳደርን በማስፈን ረገድ ይህ ነው የሚባል ለውጥ አለመምጣቱን የሐዋሳ ጉባዔ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

በዚህም ምክንያት ለኢሕአዴግ ህልውና ፈተና መሆኑን አስረግጦ ይገልጻል፡፡ ችግሩ ሰፊና ጥልቅ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በየደረጃው የሚገኝ አመራር ከተለመደው አሠራርና አካሄድ ያልተላቀቀ በመሆኑ ጭምር የተፈጠረ እንደሆነም ሰነዱ ያስነገዝባል፡፡

‹‹የሪፎርም ሥራዎች ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ መሠረታዊ ለውጥ አላመጡም፡፡ የልማታዊ መንግሥት ተልዕኮን የሚመጥን የሲቪል ሰርቪስ አልተገነባም፡፡ የዕውቀት፣ የአመለካከትና የክህሎት ጉድለቶች በስፋት የሚታዩበት ነው፡፡ የፍትሕ ሥርዓት ሪፎርም ሥራ ተወስዶ ሲታይ ተመሳሳይ ችግር ሆኖ የሚታይበት ሆኖ፣ በራሱ ባህርይ ሲመዘን የሕግ የበላይነትን ማስከበር የተሳነው፣ አስከፊ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ድርጊቶችን ማስቀረት ያልቻለ፣ ወንጀል የመከላከል ሥራውም ደካማና ግጭቶችን በአግባቡ የመያዝ አቅሙ ዝቅተኛ መሆኑ ታይቷል፤›› በማለት ችግሮቹን ይተነትናል፡፡

 ባለፉት ሦስት ዓመታት በላይ የነበረውን አገራዊ የፖለቲካ ሁኔታ በጥቅሉ በዚህ ሁኔታ የገመገመው የድርጅቱ 11ኛ ጉባዔ የአመራር ለውጥ ካደረገበት መጋቢት ወር 2010 ዓ.ም. ወዲህ፣ በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተስፋ ያሳደሩ ለውጦች መመዝገባቸውን በግምገማው አመልክቷል።

በአመራር ለውጡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡት የኢሕአዴግ ሊቀመንበር የድርጅቱን አመራር እንደገና በማደራጀት፣ አገሪቱ የገባችበትን አጣብቂኝ በጥሞና በመገምገም የወሰዱት ዕርምጃ ተጨባጭ ለውጦችን በማምጣት፣ አገሪቱ ከአስከፊ ውድቀትና ሕዝቦችን ከመከፋፈል አደጋ በማውጣት ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገር መጀመሩን በጉባዔው በበጎነት ተነስቶ ነበር።

ይኼንን በጎ ሁኔታ አጠናክሮ ለማስቀጠልም የኢሕአዴግ 11ኛ ጉባዔ፣ ድርጅቱ በቀጣይ ትኩረት ሊያደርግባቸው የሚገቡ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ውሳኔዎችን ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡

 ከእነዚህም መካከል ኢሕአዴግና አባል ድርጅቶቹ ለቆሙለት ዓላማ ታማኝና ዙሪያ መለስ መስዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ የሆኑ አባላትን ብቻ በማስቀረት አድርባይ አባላትን የማጥራት፣ አባላትን የመመልመልና የመገንባት ሥራ እንዲከናወን አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

‹‹የመጨረሻውን ዘመን ኢሕአዴግ ለመፍጠር የአባላት የእርስ በርስ ቅንጅት በመፍጠር፣ በማነሳሳትና በማዋሀድ የላቀ ድምር ውጤት የሚያስመዘግብ ብቃት ያለው የአመራር ስብስብ ለማምጣት ይሠራል፤›› በማለት የጉባዔው ቀጣይ አቅጣጫ ሰነድ ያስረዳል፡፡

ውጤት አልባነት፣ ውጤት የማያስመዘግብ አመራር፣ ውጤት የማያስመዘግብ ፓርቲ ወይም የፓርቲ መዋቅር ከዚህ በኋላ በኢሕአዴግ ውስጥ መቀጠል እንደማይችል ሌላው በጉባዔው የተላለፈ ውሳኔ ነው፡፡

ቀጣይ አቅጣጫዎችን የሚዘረዝረው ሰነድ እንደሚያመለክተው፣ በፓርቲና በመንግሥት መካከል እየተፈጠሩ ያሉ ትክክለኛም ሆነ የተሳሳቱ ውዥንብሮችን በማጥራት አንድነታቸውንና ልዩነታቸውን በሕግና በአሠራር ጠብቀው እንዲቀጥሉ ለማድረግ፣ የአሠራር ግልጽነቶችን መፍጠርና መተግበር እንደሚገባ ውሳኔ መተላለፉን ያመለክታል፡፡

ከኢሕአዴግ ጉባዔ ጀምሮ ያሉ የግንባሩ ተቋማትና መዋቅሮች ከግለሰብ ተፅዕኖ ተላቀው ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ እንዲገቡ፣ ጠንካራ ሆነው ተልዕኳቸውን እንዲወጡም በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫነት ተካቷል፡፡

የእርስ በርስ ትግል፣ መወያየት፣ መከራከር፣ መተቻቸትና ግልጽ ድርጅታዊ መዋቅርና ምደባ የሚፈጥር የዳበረ የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ እንዲሰፍንም ውሳኔ ተላልፏል፡፡

የፌዴራል ሥርዓቱ ዴሞክራሲያዊና ከግጭት የፀዳ ወይም ግጭት ቢፈጠር የሚፈታበት ሕጋዊ አካሄድን የተላበሰ እንዲሆን፣ ሁሉንም የኅብረተሰብ አካላት አካታችና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የሪፎርም ሥራዎች በጥናት ላይ በመመሥረት እንዲከናወኑ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡ በፍትሕ ሥርዓቱ እውነተኛ ዳኝነት የሚገኝበት፣ የሕግ የበላይነት የሚረጋገጥበት፣ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነትና ከጉቦ የፀዳ የፍትሕ አገልግሎት የሚሰጥበት እንዲሆን አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ በመልካም አስተዳደር ረገድ ከአጭር ጊዜ አኳያ ሕዝቡን በየደረጃው ያስመረሩ ጉዳዮች ብዙ ካፒታልና የተለየ ቴክኖሎጂ የማይጠይቁ፣ ቅንነት ብቻ የሚጠይቁና በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉት ተለይተው እንዲተገበሩ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

በተጨማሪም በአባል ድርጅቶች ውስጥና መሀል ያሉ ልዩነቶች የሚስተናገዱበትና ዴሞክራሲያዊ አንድነትን መፍጠር፣ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም ያመለክታል፡፡

ከአራት ወራት በኋላ

በሐዋሳ የተካሄደው የኢሕአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ የድርጅቱን ሊቀመንበር በመሉ ድምፅ መርጦ ካጠናቀቀ በኋላ ባወጣው መግለጫ ጉባዔው የአመለካከት አንድነት በሰፈነበት መንገድ መካሄዱን፣ ይህም የድርጅቱን አንድነት መልሶ የሚያፀና እንደሆነ አስታውቋል። ከድርጅቱ ጉባዔ መጠናቀቅ በኋላ በነበሩት ወራት የተስተዋሉት ሁነቶች ግን የተገላቢጦሽ ሆነው አገሪቱን መልሶ ወደ ባሰ ሥጋት ውስጥ እንደከተቱ፣ በድርጅቱ አባል ፓርቲዎች መካከል የተፈጠረው መቃቃር ወደሚመሩዋቸው አልፎ እያጋጨ፣ በዚህም በኢሕአዴግ ድርጅቶች መካከል የእርስ በእርስ አንድነት ጠፍቶ፣ ወደ መፍትሔ ከመመልከት ይልቅ እርስ በእርስ መወቃቀስ፣ አንዱ ለአንዱ ህልውና መጥፋት ወይም መጠላለፍ ውስጥ እስከ መግባት ደርሰው ይገኛሉ።

ይህ ሁኔታ ያሠጋቸው የአገሪቱ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች በጋራ በመሆን ሰላምን ከመስበክ አልፈው፣ በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ዕርቅ እንዲወርድ ቅራኔ የፈጠሩትን እስከ ማግባባት ሥራ ውስጥ ገብተው ይገኛሉ።

ይህም ኢሕአዴግ ራሱን ከሁኔታዎች ጋር አጣጥሞና ራሱን አስተካክሎ የመሄድ ተሞክሮ እንዳለው በተምሳሌትነት ለሚጠቅሰው ድርጅት፣ የተገላቢጦሽ እውነት ነገር ግን አማራጭ የሌለው መፍትሔ ሆኖ በታሪኩ ውስጥ እንዲመዘገብበት ተገዷል።

በዚህ ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ነው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባውን ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ጥር 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ማካሄድ የጀመረው።

 ለውይይቱ መሠረታዊ አጀንዳነት እርስ በእርስ መጠላለፍን መዝጋትና የድርጅቱ አንድነትን መልሶ መፍጠር፣ ከዚህ ለሚመነጩ አለመረጋጋቶች እልባት መስጠት የሚለው ዳግም የውይይቱ ርዕስ ሆኗል።

ውይይቱን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምግባሩ ከበደ፣ በአገሪቱ ፈታኝ እየሆነ የመጣውን ሕግ የማስከበርና የሰላም ጉዳዮችን እንዴት መፍታትና ማለፍ እንደሚቻል ጭምር ውይይት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ኢሕአዴግ አገር የሚመራ መንግሥት በመሆኑ የሚመራውን ሕዝብ ደኅንነት የመጠበቅ ተፈጥሯዊ ግዴታ እንዳለበት፣ በኢሕአዴግ ውስጥ የሚፈጠር መፈረካከስ እንደማይኖር፣ እንዲያውም የበለጠ ተጠናክሮ የሚወጣበት ግምገማ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ፈቃዱ ተሰማ በበኩላቸው፣ የሰሞኑ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ኢሕአዴግ ተጠናክሮ ወደ አንድነቱ ተመልሶ አመራር የሚሰጥበትን ሁኔታ ለመፍጠር የተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡  ከዚህም ከዚያም የሚነሱ ግጭቶችንና ውጥረቶችን ከሥር መሠረታቸው ለማድረቅ የጋራ አመራር መስጠት የሚያስችል ውይይት መካሄዱን አስታውቀዋል፡፡

የሕወሓትና የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አሁን በአገሪቱ ያሉትን ፈተናዎች ግምት ውስጥ በማስገባት ውይይት የተካሄደበት፣ አመራሩም አንድነቱን ጠብቆ ሥራውን ካልሠራ ከአገር ህልውና ጋር የተያያዘ ችግር ሊገጥም የሚችል መሆኑን አፅንኦት መስጠቱን አስረድተዋል፡፡ የሚደረገው ግልጽ ውይይትም ከስምምነት እንደሚያደርስ ተስፋቸውን አስረድተዋል፡፡

የደኢሕዴንና የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፣ ኢሕአዴግ በኅብረተሰቡ የተቀሰቀሰውን የለውጥ ፍላጎት ማርካት የሚያስችል አመራር መስጠት እንዳለበት በጉባዔው አቅጣጫ መቀመጡን አስታውሰዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ሐሳቦች በነፃነት ተነስተው ያሉት ችግሮች ላይ ውይይት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ኢሕአዴግ እንዲህ ዓይነት ውይይት ሲያካሄድ የመጀመርያው አይደለም፡፡ ጥያቄው ኢሕአዴግ በዚህ ውይይት ታክሞ ይድናል ወይ የሚለው ነው፡፡ የሐሳብና የተግባር አንድነቱ ይቀጥል ወይም አይቀጥል እንደሆነ ግን ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -