Tuesday, December 6, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሰብዓዊ መብቶችን አስመልክቶ ለተመድ ያዘጋጀውን ረቂቅ ሪፖርት ለውይይት አቀረበ

  ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሰብዓዊ መብቶችን አስመልክቶ ለተመድ ያዘጋጀውን ረቂቅ ሪፖርት ለውይይት አቀረበ

  ቀን:

  በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ውሳኔ 17/119 መሠረት የሚዘጋጀው ‹ዩኒቨርሳል ፔሪዮዲክ ሪቪው› የሰብዓዊ መብቶችን አያያዝ በተመለከተ ኢትዮጵያ የተሰጣትንና የተቀበለቻቸውን ምክረ ሐሳቦች መሠረት በማድረግ የተዘጋጀ የመጀመርያ ረቂቅ ምላሽ ሪፖርት፣ ባለድርሻ አካላትና ዜጎች አስተያየት እንዲሰጡበት ይፋ ማድረጉን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታወቀ፡፡

  ለሦስተኛ ጊዜ እ.ኤ.አ. ሜይ 2019 የሚቀርበው ሪፖርት የመጀመርያ ረቂቅ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን፣ ሪፖርቱ ተጠናቆ ለሚመለከተው አካል ከመላኩ በፊት የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት፣ እንዲሁም ማንኛውም ዜጋ ግብዓት እንዲሰጥበት በማስፈለጉ ረቂቅ ሪፖርቱ ለውይይት ይፋ መሆኑን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በድረ ገጹ አስታውቋል፡፡

  በኢትዮጵያ መንግሥት አማካይነት ሰብዓዊ መብቶችን ከማክበር፣ ከማስከበር፣ እንዲሁም በተጠናከረ መንገድ ተፈጻሚ ከማድረግ አንፃር ሊወሰዱ ይገባል በማለት ከዚህ ቀደም የተሰጡና ተቀባይነት ያገኙ ምክረ ሐሳቦችን መሠረት በማድረግ የተዘጋጀ እንደሆነ፣ በ30 ገጾች የተጠናቀረው ረቂቅ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም ረቂቅ ሪፖርቱ በአገሪቱ ሰብዓዊ መብቶችን ከማስከበር አንፃር ያጋጠሙ ፈተናዎችንና ስኬቶችን አካቶ መዘጋጀቱ፣ አገሪቱ እያካሄደች ካለችው ፖለቲካዊ ተሃድሶ አንፃር የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታን ለማሳየት ያለመ እንደሆነ በረቂቅ ሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

  ረቂቅ ሪፖርቱ አጠቃላይ ዝርዝር ጉዳዮችን፣ የሲቪልና ፖለቲካዊ መብቶችን፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና፣ ባህላዊ መብቶችን፣ እንዲሁም ለተለዩ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች የተሰጡ መብቶች በሚሉ አራት ዓበይት ክፍሎች የተዋቀረ ነው፡፡

  በዚህም መሠረት አጠቃላይና ዝርዝር የሰብዓዊ መብቶችን በሚመለከተው ክፍል በፖለቲካዊ ማዕቀፍና መልካም አስተዳደር፣ አለማግለል፣ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት፣ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ትግበራ ዕቅድ፣ የሰብዓዊ መብቶች ትምህርትና ሥልጠና፣ ተቀባይነት ያላቸው ዓለም አቀፍ ተለምዷዊ አሠራሮች አፈጻጸም፣ ከልዩ አሠራሮችና የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ጋር ያለው ትብብር፣ ከሲቪል ማኅበራት ጋር የተከናወኑ ትብብሮች፣ ሰብዓዊ መብቶችና የፀረ ሽብርተኝነት ሥራዎችን አስመልክቶ የተሰጡ፣ እንዲሁም ተቀባይነት ያገኙ ምክረ ሐሳቦችን አስመልክቶ የተሰጡ ምላሾችን አካቷል፡፡

  የሲቪልና ፖለቲካዊ መብቶችን በተመለከተ ደግሞ ግርፋት፣ ማሰቃየትና ኢሰብዓዊ አያያዝ፣ የእስረኞች ሁኔታ፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ነፃነትና ደኅንነት፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የፍትሕ ሥርዓትና ፍትሐዊ የክስ ሒደት፣ የመምረጥና በሕዝባዊ ጉዳዮች የመሳተፍ፣ እንዲሁም ከትዳርና ከቤተሰብ መብቶች ጋር ተያይዘው የተሰጡና ተቀባይነት ያገኙ ምክረ ሐሳቦችን አስመልክቶ የተዘጋጁ ምላሾች ተካተዋል፡፡

  ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ መብቶችን አስመልክቶ ደግሞ ምግብ የማግኘት፣ ማኅበራዊ ዋስትና፣ ደኅንነት፣ ንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ መልካም የሥራ ሁኔታ፣ ጤና፣ እንዲሁም የመማር መብቶችን በተመለከተ የተሰጡ ተቀባይነት ያገኙ ምክረ ሐሳቦችን በተመለከተ የተዘጋጁ ምላሾች ተካተዋል፡፡

  በመጨረሻውና ለተለዩ ግለሰቦችና ቡድኖች የተሰጡ መብቶችን አስመልቶ ደግሞ አካል ጉዳተኞች፣ ስደተኞች፣ በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች፣ ሴቶች ላይ ስለሚፈጸም አድሎዓዊነት፣ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ፣ የሴቶች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ማበረታቻዎች፣ ፆታ ተኮር ጥቃቶች፣ የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾችን አስመልክቶ የተሰጡና ተቀባይነት ያገኙ ምክረ ሐሳቦችን መሠረት አድርገው የተሰጡ ምላሾች ተካተውበታል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...