Thursday, November 30, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ተስፋ ባላት አገር በሥጋት ተከቦ መኖር ይብቃ!

የአገር ጉዳይ ሲነሳ በተስፋ የተሞሉ መልካም አጋጣሚዎች እንዳሉ ሁሉ፣ በሥጋት የተሞሉ ክፉ ነገሮችም አሉ፡፡ የአገራቸው ዕጣ ፈንታ ከሚያሳስባቸው ቅን ዜጎች ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱ የተባሉ ስመጥር ሰዎች ድረስ፣ ተስፋና ሥጋት በተለያዩ ፈርጆች ይተነተናሉ፡፡ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግሮቿን በመፍታት የአፍሪካ ቀንድን ማዋሀድ የሚያስችል አቅም እንዳላት ሲነገር፣ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ብትንትኗ ሊወጣ እንደሚችል መላምት ይቀርባል፡፡ የወቅቱን የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በቅርበት መከታተል ከተቻለ ግን፣ መስቀለኛ መንገድ ላይ እንዳለች ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ተስፋና ሥጋትን በእኩል ዓይን በማየትና ለመፍትሔው ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ፣ ኢትዮጵያን ከገጠሟት ችግሮች በማላቀቅ ታላቅ አገር የማድረግ ምኞትን ማሳካት አያቅትም፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ኢትዮጵያዊያን በቅን ልቦና ተነሳስተው ልዩነቶቻቸውን በማክበር አብረው መሥራት ከቻሉ፣ በዚህች ታሪካዊት አገር ተዓምር መፍጠር አዳጋች አይሆንም፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን በሠለጠነ መንገድ እየተነጋገሩ ልዩነትን በማጥበብ፣ ለአገር ዘለቄታዊ ህልውና የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ ልዩነትን እያከበሩና እንደ ወዳጅ እየተያዩ የጋራ አገር መገንባት ካልተቻለ፣ በመጠፋፋት ጎዳና ላይ እየጋለቡ አገርን ቀውስ መክተት በጣም ቀላል ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ የጥፋት ድርጊት ግን ለዚህ ዘመን ትውልድ አይመጥንም፡፡ በዚህ መንገድ ሕዝብን ችግር ውስጥ መክተትም ከዚህ ትውልድ አይጠበቅም፡፡ የሥጋት ኑሮ ይብቃ፡፡

አገርን ከሚጠብቃት መልካም አጋጣሚ በማደናቀፍ የግጭት አውድማ ለማድረግ የሚጥሩ ኃይሎችን ሕዝብ በቃችሁ ማለት አለበት፡፡ ማክሰኞ ጥር 14 ቀን 2011 ዓ.ም. የኦሮሞ አባ ገዳዎች ኅብረት፣ በኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ዕርቀ ሰላም ለማውረድ ውይይት አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በተለይ የክልሉ ገዥ ፓርቲ አዴፓና በቅርቡ ከውጭ የተመለሰው ኦነግ በመሀላቸው የተፈጠረውን ችግር እንዲፈቱ ነው ጥሪ የቀረበው፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶቹ እርስ በርስ መጋጨት አቁመው ችግራቸውን በውይይት እንዲፈቱ ተጠይቀዋል፡፡ ድርጅቶቹ የቀረበላቸውን ጥያቄ ካልተቀበሉ አዛውንቶቹ እንደማይቀመጡና ወደ ቤታቸው እንደማይሄዱ በማስታወቃቸውም፣ ድርጅቶቹ በአንድነት የቀረበላቸውን ጥሪ በመቀበል ውይይት መጀመራቸው ተሰምቷል፡፡ የአባ ገዳዎች ኅብረት ሰብሳቢ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹አገራችንን የምንጠብቀው እኛ ነን፣ የአገራችን ጉዳይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን የእኛም ነው፣ ሁላችንንም የአገራችን ሰላም ያገባናል፣…ሰላም ከሁሉም ነገር ቀዳሚው ነው፣ ሕዝባችን በሰላም ወጥቶ መግባት ይፈልጋል…›› ብለዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት የሕዝቡ ጭንቀት በሥጋት ተከቦ መኖር ነው፡፡ ይኼንን ሥጋት ከሥር መሠረቱ በማስወገድ ተስፋ ያላት አገር መገንባት የግድ ይላል፡፡

እንደሚታወቀው የአገሪቱ የፖለቲካ ሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት ሕዝብ ነው፡፡ ሕዝብ በአገር ጉዳይ ከእኔ በላይ የለም ብሎ ሲነሳ፣ የለም ከአንተ በላይ አውቅልሃለሁ ብሎ ዘራፍ ማለት አይቻልም፡፡ ከዚህ ቀደም የጋሞ የአገር ሽማግሌዎች የወጣቶችን ቁጣ አብርደው ሰላም እንዳሰፈኑት ሁሉ፣ አሁን ደግሞ የኦሮሚያ ክልልን የጦር ቀጣና እንዲሆን ምክንያት የሆነውን የፖለቲካ ድርጅቶች አለመግባባት መፍታት አማራጭ የለውም፡፡ በሌሎች አካባቢዎችም የአገር ሽማግሌዎችና የቤተ እምነቶች መሪዎች እንዲህ ዓይነቱን አርዓያነት በተግባር ማሳየት አለባቸው፡፡ ያጠፋውን መገሰፅ፣ የተበደለውን ልቡ ለይቅርታ ክፍት እንዲሆን ማድረግ የአንጋፎች ኃላፊነት ቢሆንም፣ ወጣቶችም በተቻላቸው መጠን ከስሜታዊነት ርቀው በምክንያታዊነት ለሰላም መሥራት አለባቸው፡፡ ያልተረጋገጡ ወሬዎችን ጫፍ ይዞ እርስ በርስ መጋጨትም ሆነ ሌላውን ወገን ማጥቃት ኋላቀርነት ነው፡፡ ዓለም እንደ መንደር እየጠበበች የሰው ልጆች ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተቀራረቡ ባሉበት በዚህ ዘመን፣ ራስ ላይ አጥር መሥራት ወይም ግንብ መገንባት ጤነኝነት አይደለም፡፡ በአቋራጭ ሥልጣን ለመያዝ በሚቅበዘበዙ ራስ ወዳዶች እየተታለሉም አገርና ሕዝብን ማመስ ለፀፀት ይዳርጋል፡፡ ህልቆ መሳፍርት ተስፋዎች በሚታዩባት አገር ውስጥ ግጭት እየቀሰቀሱ፣ ሕዝብን በሥጋት አቅል ማሳጣት ከንቱነት ነው፡፡ ከሕዝብ ጋርም እስከ ወዲያኛው ያጣላል፡፡

ኢትዮጵያ የሰከነ የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ ገብታ ፍትሕ፣ ነፃነትና እኩልነት እንዲረጋገጡ መሥራት የእያንዳንዱ ዜጋ የውዴታ ግዴታ መሆን አለበት፡፡ ለፍትሕ፣ ለነፃነትና ለእኩልነት እታገላለሁ የሚል ግለሰብም ሆነ ስብስብ የዴሞክራሲን የጨዋታ ሕግ ጠንቅቆ ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡ ይኼንን ሕግ ሳያውቁ የመጫወቻ ሜዳው ውስጥ መግባት የሕዝብ ድምፅ ያሳጣል፡፡ በዚህ ጊዜ ሕዝብን በጠመንጃ አግቶ የፈለጉትን ማድረግ አይቻልም፡፡ ከዚህ በፊት ሠርቶ ነበር በማለት ለመሞከር መንገታገትም ይዋል ይደር እንጂ በሕዝብ ያስተፋል፡፡ ሕዝብ ደግሞ ከምንም ነገር በላይ የአገሩን ሰላም ነው የሚፈልገው፡፡ ይህችን አገር ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች ለመከላከል በርካታ ትውልዶች በደማቸው መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ አገርን እንደ ቆዳ ጠቅልለው ለመያዝ የሚፈልጉም ሆነ፣ ምኞታቸው ሳይሳካ ሲቀር አተራምሰው መበታተን የሚፈልጉ ጭምር የማይሳካላቸው፣ ሕዝብ ሐሳባቸውን ስለማይፈልገው ብቻ ሳይሆን ስለሚፀየፈው ጭምር ነው፡፡ ይኼንን የተከበረና ጨዋ ሕዝብ ፍላጎቱን በሚገባ ተረድቶ ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ፉክክር መዘጋጀት ሲገባ፣ አጓጉል ድርጊቶች ውስጥ መዘፈቅ ለውርደት ይዳርጋል፡፡ ሕዝብ በነፃነት እንጂ በሥጋት መኖር ሰልችቶታል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ችግሮችን ለይቶ መፍትሔ ለማግኘት የሚያስፈልገው ቅን ልቦና ነው፡፡ ቅን ልቦና ሲባል በማንም መነዳት ወይም በጅረት መወሰድ ሳይሆን፣ ብልኃትንና አስተዋይነትን በመጎናፀፍ የመርህ ሰው መሆን ማለት ነው፡፡ ሴረኞች እናገኘዋለን ብለው ከሚያስቡት ጥቅም በታች አገርን ሲያወርዱ፣ ተላሎች ደግሞ በየዋህነት ዓላማዎቻቸውን ሲያሳኩላቸው እየታየ ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን ደካማነትና ቅን ልቦናን በፍፁም ማወዳደር አይገባም፡፡ ነገር ግን አቅሙና ዝግጅቱ ያላቸው በርካታ ኢትዮጵያዊያን ስላሉ፣ እነዚህ ወገኖች ደግሞ ልዩነትን አጣጥሞ ማስኬድ ስለሚችሉበት፣ እዚህ መሀል ልቦናን ቅን አድርጎ መነጋገር ሲቻል ሥጋት እየመነመነ ተስፋ ያብባል፡፡ ሴረኞችና መሰሪዎች እንደ እባብ እየተሹለከለኩ የአገር ተስፋን ጉም ማልበስ አይችሉም፡፡ በተለይ ወጣቶች አረጋውያን አባቶችንና እናቶችን፣ እንዲሁም ሕፃናትንና አቅመ ደካሞችን የበለጠ ተጠቂ የሚያደርጉ ጥቃቶች ውስጥ ከመሳተፍ በመቆጠብ፣ ለአገራቸው ሰላምና ህልውና ዘብ መቆም ግዴታቸው መሆኑን ጠንቅቀው ማወቅ አለባቸው፡፡ ለአገር ደንታ የሌላቸው የሚሸርቡት ሴራ ሰለባ ላለመሆንም ንቁ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ ያላት አገር ስለሆነች በሥጋት ተከቦ መኖር ማብቃት አለበት ሊባል ይገባል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...

ሀብቱንና ትርፉን እያሳደገ የቀጠለው አዋሽ ባንክ

አዋሽ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...