በቴሌኮምና በሌሎች ኢንቨስትመንቶች የመሰማራት ዕድል መከፈቱን ለተመረጡ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ገለጹ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የበርካታ አገሮች መሪዎችና ተፅዕኖ ፈጣሪ ባለሀብቶችና የዓለም አቀፍ ተቋማት አመራሮች በሚታደሙበት የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም (መድረክ) ተገኝተው፣ በእሳቸው አመራር በኢትዮጵያ ስለተጀመረው የለውጥ ጉዞና መፃኢ ዕድሎች ረቡዕ ጥር 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ከቀትር በኃላ ያስረዳሉ።
ከአንድ ወር በፊት አዲስ አበባ ተገኝተው የነበሩት የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ዋና ዳይሬክተር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በስዊዘርላንድ ዳቮስ ከተማ በሚካሄደው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ተገኝተው፣ በኢትዮጵያ ስለተጀመረው ፈጣን የለውጥ ጉዞ እንዲያስረዱ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
የቀረበላቸውን ጥያቄ የተቀበሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ መድረክ የሚያስገኘውን የጎንዮሽ ዕድል ለመጠቀም፣ በእሳቸው የሚመራ ልዑካን ቡድን ይዘው ሰኞ ጥር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ወደ አውሮፓ ጉዞ በመጀመር በዚሁ ዕለት የስዊዘርላንድ ጎረቤት በሆነችው ጣሊያን ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸውም ከጣሊያን አቻቸው ጁሴፔ ኮንቴ ጋር ተገናኝተው በተለያዩ የኢንቨስትመንትና የትብብር መስኮች ላይ ተወያይተው ከመግባባት ላይ መድረሳቸውን፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቃል አቀባይ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጣሊያኑ አቻቻው ጋር ተወያይተው ከደረሱባቸው ስምምነቶች መካከል አንዱ፣ ኢትዮጵያን ከኤርትራ የምፅዋ ወደብ የሚያገናኝ የባቡር መስመር ለመዘርጋት በኢትዮጵያ በኩል ለተያዘው የፕሮጀክት ውጥን የጣሊያን መንግሥት ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑ ነው። የጣሊያን መንግሥት ለዚህ የባቡር ትራንስፖርት ፕሮጀክት ጥናት የሚያስፈልገውን የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ኮንቴ አረጋግጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጣሊያን ቆይታቸው በምዕራቡ ዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆነችው የሮማ ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፍራንሲስ ጋር ተገናኝተው የተወያዩ ሲሆን፣ ከዓለም የምግብ ፕሮግራም፣ ከዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ የሥራ ኃላፊዎች ጋርም በመገናኘት የመንግሥታቸውን ፍላጎት እንዳስረዱ፣ ከቃል አቀባይ ቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማክሰኞ ጥር 14 ቀን 2011 ዓ.ም. የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ወደሚካሄድበት የስዊዘርላንድ ከተማ ዳቮስ ደርሰው በመድረኩ በታዳሚነት መሳተፍ ጀምረዋል። ከዚሁ መድረክ ጎን ለጎንም የኢኮኖሚ ፎረሙን ለመታደም ከተገኙ የተመረጡ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ሥራ አስፈጻሚዎች ጋር ተገናኝተው፣ በኢትዮጵያ ስለተፈጠሩና ስለሚፈጠሩ አዋጭ የኢኮኖሚ ዕድሎች አብራርተዋል፡፡ ኩባንያዎቹ ኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት መዳረሻቸው እንዲያደርጉ ጥሪ እንዳደረጉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት ልዑክ አባል የሆኑትና በቅርቡ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት የቀድሞው የኢንቨስመንት ኮሚሽነር አቶ ፍፁም አረጋ በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተመረጡት ግዙፍ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ሥራ አስፈጻሚዎች ጋር በነበራቸው ቆይታም ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ የቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ የኃይል ማመንጫ ዘርፍና በአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ኢንቨስትመንታቸውን ሊያፈሱ እንደሚችሉ በመግለጽ ጥሪ ማቅረባቸውን አቶ ፍጹም ገልጸዋል።
በተጨማሪም ሁለት መቶ ቢሊዮን ዶላር ከሚያንቀሳቅሰው የዱባይ ዓለም አቀፍ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጋር በዳቮስ ተገናኝተው የተወያዩ መሆኑ ታውቋል። የዱባይ ዓለም ከቀፍ ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ በሆቴል ኢንቨስትመንትና በግብርና ዘርፍ ለመሰማራት እንቅስቃሴ መጀመሩ የሚታወቅ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከዚህ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጋር በነበራቸው ውይይት ወቅት ኮርፖሬሽኑ ወደ ኢትዮጵያ ፈጥኖ መንቀሳቀስ እንዲጀምር ማሳሰባቸው ታውቋል።
ረቡዕ ጥር 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ከቀትር በኃላ በኢኮኖሚ ፎረሙ ላይ በኢትዮጵያ ስለተጀመረው ፈጣን የለውጥ ጉዞና የኢትዮጵያን ዕምቅ አቅም ወደ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎች ለመለወጥ ምን ያስፈልጋል በሚል ርዕስ ተወያይ ሆነው በመቅረብ እንደሚያስረዱ፣ ከታዳሚዎችም ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ማብራሪያ እንደሚሰጡ ታውቋል።
በዚህ የኢኮኖሚ ፎረም ላይ ተገኝተው ልዩ ንግግር እንደሚያደርጉ ፕሮግራም ከተያዘላቸው መካከል የጀርመን ቻንስለር አንገላ መርከል፣ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የቻይና ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ እንዲሁም የብራዚልና የኦስትሪያ መሪዎች ይገኙበታል።
የአፍሪካ አገሮች መሪዎች እየተፈጠረ ባለው አዲስ የዓለም የፖለቲካና የኢኮኖሚ መዋቅር ውስጥ የሚኖቸውን የአመራርነት ሚና በተመለከተ በፎረሙ በሚደረግ ውይይት ላይ አፍሪካን በመወከል የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ተሳታፊ ሲሆኑ፣ ለዓለም ጤና አማራጭ የፋይናንስ አቅርቦትን በተመለከተ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የኢትዮጵያ የቀድሞ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) በዚሁ መድረክ ንግግር ከሚያደርጉ አፍሪካውያን መካከል አንዱ ናቸው።