Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበአሰላው የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና አራት ክልሎች አይሳተፉም

በአሰላው የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና አራት ክልሎች አይሳተፉም

ቀን:

በኢትዮጵያ ታላላቅ አትሌቶችን በማፍራት ከሚጠቀሱ ከተሞች በተለይም አሰላ በቀዳሚነት ትጠቀሳለች፡፡ ከአዲስ አበባ 175 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው አሰላ ከተማ ከዛሬ ጥር 15 እስከ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ የሚቆይ ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና እንደምታስተናግድ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡ በውድድሩ ልቀው የሚወጡ ወጣቶች በመጪው ሚያዝያ በናይጀሪያ አቡጃ በሚከናወነው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ይሳተፋሉ፡፡

አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞችን ጨምሮ ከአምስት ክልሎች ማለትም ከኦሮሚያ፣ ከአማራ፣ ከደቡብና ከሐረሪ የተውጣጡ 385 ሴቶችና 513 ወንዶች በድምሩ 898 አትሌቶች እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡ በሻምፒዮናው የትግራይ፣ አፋር፣ ጋምቤላና ሶማሌ ክልሎች የማይሳተፉት በበጀትና ተያያዥ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡ 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሚተችባቸው መካከል የአትሌቶች የዕድሜ ተገቢነት ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የሪፖርተር ዝግጅት ክፍል ቀደም ባሉት ዓመታት በተደረጉ ተመሳሳይ ሻምፒዮናዎች በተለይም ከዕድሜ ጋር በተያያዘ ያነጋገራቸው አንዳንድ ክልሎች፣ ‹‹ላለፉት ዓመታት ታዳጊዎችንና ወጣቶችን ስናወዳድር ቆይተናል፡፡ ይሁንና የውድድሩ ዓላማና ግብ ለአንዳንዶቻችን ሜዳሊያ በመሰብሰብ አንዱ ክልል ከሌላው ለመብለጥ እንጅ በወረቀት ላይ እንደሰፈረው ብቻ ሳይሆን ፌዴሬሽኑም እንደሚለው የነገዎቹን ተተኪዎች ለማፍራት አይደለም፡፡ ይህ እየሆነ በሚገኝበት በዚህ ወቅት በወጣት ስም የሕዝብ ሀብት ማባከን ተገቢ አይደለም፤›› በማለት መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

የዕድሜ ተገቢነትን ጉዳይ በተመለከተ በተለይ የትግራይ አትሌቲክስ ባለሙያተኞች፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የውድድሩን ስያሜ የሚመጥን ሕግና ሥርዓት ሊኖረው እንደሚገባ በመደበኛ ጠቅላላ ጉባዔዎችና በሌሎችም መድረኮች ሲያስተጋቡ ተደምጠዋል፡፡ ዘንድሮ የሚካሄደውን የወጣቶች ሻምፒዮና አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው፣ ነገር ግን ማንነታቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የፌዴሬሽን ሙያተኞች እንደሚናገሩት ከሆነ፣ ‹‹ችግሩ መቸም ቢሆን መፍትሔ አይኖረውም፣ ምክንያቱም አሁን ባለው ሥርዓት በውድድር መሸነፍና ማሸነፍ የሚሰጠው ትርጉም የሚያያዘው ከማንነት ጋር ነው፡፡ በዚህ ተቃኝቶ ለውድድር የሚመጣ ማንኛውም የክልል ተወካይ አንዱ ከሌላው የተሻለ መሆኑን የሚያረጋግጠው ደግሞ ሜዳሊያ በመውሰድ ስለሆነና ሜዳሊያውን ለማግኘት ሲባል ለሻምፒዮናው ተገቢ ያልሆኑ አትሌቶችን ከማሰለፍ የተሻለ አማራጭ አይኖራቸውም፤›› በማለት የችግሩን አሳሳቢነት ያስረዳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ