Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹የሰዎችን መፈናቀልና ሞት ልናቆም ይገባል›› ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት...

‹‹የሰዎችን መፈናቀልና ሞት ልናቆም ይገባል›› ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ

ቀን:

‹‹ወንዝና ተራራ ሰው ሊጠቀምባቸው እንጂ ሊለያይባቸው አልተፈጠሩም. . . በኃጢአት ምክንያት በተፈጠረው የነገድ፤ የጎሳ እና የብሔር ልዩነት ምክንያት በመለያየት እንዳንጎዳ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። አንተ የዚህ አገር ነህ አንተ የዚያ ተባብለን ውጣ አንተ ግባ የምንባባልበት ሁኔታ ከየት መጣ? የነበረው የመከባበር ባህላችንስ ከየት ጠፋ? የቆየ የመተሳሰብ ባህላችን የተወደደ ነውና ልናከብረው ይገባል፡፡››

ይህ ዐረፍተ ሐሳብ የተስተጋባው ጥር 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ዓመታዊ የጥምቀት ክብረ በዓል በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በጃንሜዳ በነበረው ሥነ ሥርዓት ላይ ነው፡፡ ከወቅታዊው የኢትዮጵያ ገጽታ በመነሳት ቃለ ምዕዳን (ምክር) ያሰሙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ናቸው፡፡

በመላው ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት በሚገኙባቸው የዓለም ክፍሎች የተከበረው የጥምቀት ክብረ በዓል እህት ቤተ ክርስቲያኖች የኤትራና የግብፅ እንዲሁም የጁሊያን ካላንደርን የሚከተሉ እነ ሩሲያን የመሳሰሉ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በዓሉን እንደየ ባህላቸውና ትውፊታቸው አክብረዋል፡፡

የህንድ ኦርቶዶክስ (የማላንካ) ፓትርያርክ ተወካይ ሊቀጳጳስ በተገኙበት በአዲስ አበባ በዓሉ ሲከበር ቃለ መዕዳን ያሰሙት የቅዱስ ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በቅርብ ወራት ከተፈጸሙት ክስተቶ አኳያ ጠንከር ያለ መልዕክታቸው እንዲህ ሲሉ አስተላልፈዋል፡፡

‹‹የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት ተከትለን ከሄድን ሰውን በሰውነቱ ብቻ ማክበርና መቀበል ይገባል። አንድነት እንጂ ተለያይቶ ውበትም፤ ድምቀትም የለም። በኃይለ ቃላት ውርወራ መጎናተል ትቶ በአንድነት በመተሳሰር ችግሮችን መፍታት ያስፈልጋል። የሰዎች መፈናቀልና መሞት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ልናቆመው ይገባል። ወጣቶችም የአባቶችን ምክር በመስማት ጥሩ ሥነ ምግባራቸውን ማስቀጠል አለባቸው።››

የማንነት መገለጫ ሰውነት ብቻ መሆኑን በመገንዘብ ሰውን በሰውነቱ ብቻ መቀበልና ማክበር ይገባል ያሉት አቡነ ማትያስ፣ ‹‹ሰው በመሆናችን ብቻ ተስማምተን፣ ተጋግዘን፣ ተዋደን፣ በአንድነትና በእኩልነት በመኖር ፋንታ በዘር፣ በጎሳ፣ በቋንቋና በመልክዓ ምድር እየተከፋፈልን እርስ በርሳችን እንዳንጎዳዳ መጠንቀቅ ይገባናል፤›› ሲሉም በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

ከአርባ ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸመው ስህተት ዳግም እንዳይመጣ ወጣቶች መጠንቀቅ እንደሚገባቸው ያሳሰቡት ፓትርያርኩ፣ አክቲቪስቶችም ሰከን እንዲሉ የልሂቆቻቸውንም ሐሳብ እንዲያጤኑም ሳይመክሩም አላለፉም፡፡

የዘንድሮው የጥምቀት ክብረ በዓል በአዲስ አበባ በተለያየ ቦታ ሲከበር  ካጀቡ ባህላዊ መሣሪያዎች ነጋሪት፣ መለከት፣ እምቢልታ፣ በገና ማሲንቆ ይገኙባቸዋል፡፡ የወጣቶቹም ሃርሞኒካም አልጠፋችም፡፡

‹‹አታሞውን ምታው

አርገው ደምቧ ደምቧ

እንደወለደች ላም

አታሰኘው እምቧ፤›› ይባላል ለበዓል ክብር፣ ለክተት ስሪት ነጋሪት ሲመታ:: መቺውን ለማትጋት የሚወረወር ቃል ነው፡፡ ከየባሕረ ጥምቀት ወደየአጥቢያቸው የሚያልፉትን የየአብያተ ክርስቲያናቱ ታቦተ ሕግ በታላቅ አጀብ ከዘለቁት ምዕመናን ጋር ከተሠለፉት ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች እምቢልታ፣ ጥሩምባ ወዘተም በዐውደ ጉዞው ታይተዋል፡፡

ዋዜማውን ከተራ (ጥር 10) እና ማግሥቱን (ጥር 12) ቃና ዘገሊላን ይዞ በዓለ ጥምቀት በተለይ በምንጃር ሸንኮራ፣ በዝዋይ ደሴት፣ በጎንደር፣ በማይጨውና በአክሱም እንዲሁም በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች መንፈሳዊና ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ተከብሯል፡፡ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንም በዓሉን አክብራለች፡፡

የጥምቀት ክብረ በዓል የእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በተከበረ 12ኛው ቀን በምሥራቅም በምዕራብም ያሉ የኦርቶዶክስና ካቶሊክ ክርስቲያኖች ያከብሩታል፡፡ የተወሰኑ ኦርቶዶክሳዊ አገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ ጥር 11 ቀን (በጁሊያን ቀመር ጃንዋሪ 6) ሲያከብሩ ግሪጎሪያን ካላንደርን የሚከተሉት ‹‹ጃንዋሪ 6›› ብለው ያከበሩት 13 ቀናት በፊት ነበር፡፡

በኦርቶዶክሳዊቷ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሚከበረው የጥምቀት በዓል፣ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ በ30 ዓመት ከሞላው በኋላ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ጥር 11 ቀን 31 .. (5531 ዓመተ ዓለም) በአጥማቂው ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ባሕር የተጠመቀበትን ዕለት የሚያስታውስ ነው፡፡ ‹‹ኤጲፋንያ››፣ ‹‹ቴዎፋንያ›› በመባልም ይታወቃል፡፡

የየአጥቢያው ታቦተ ሕግ በየዓውደ ምሕረቱ ሲደርስ ምዕመናኑ በደስታ ያዜሙት እንዲህ በማለት ነበር፡፡-

‹‹በሕይወት ግባ በዕልልታ

የዚህ ሁሉ አለኝታ

በሕይወት ግቢ እምዬ

እንድበላ ፈትዬ››

በብሔራዊ ደረጃ ጥር 14 ቀን 2009 .. የተመዘገበው የጥምቀት ክብረ በዓልን በዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት) በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት ለማስመዝገብ (Representative List of Intangible Cultural Heritage of Humanity)  የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ከአራት ዓመት በፊት ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን በተለያዩ አካባቢዎች  ያደረገውን ጥናት አጠናቆ  የ‹‹ይመዝገብልኝ›› ማመልከቻውን መጋቢት 21 ቀን 2010 .. ለዩኔስኮ መላኩ ይታወሳል፡፡ የዩኔስኮ ኮሚቴ ከኅዳር 29 እስከ ታኅሣሥ 4 ቀን 2012 .. በኮሎምቢያ ዋና ከተማ ቦጎታ በሚደርገው ልዩ ስብሰባው ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኮሎምቢያ ከላቲን አሜሪካና ካሬቢያን አገሮች ይህን የዩኔስኮ ልዩ ስብሰባ በማዘጋጀት የመጀመርያዋ ነች፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰባት ዓበይት በዓላት አንዱ የሆነው የጥምቀት ክብረ በዓል፣ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓተ አምልኮ መሠረት መከበር የጀመረው በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመንነገሥታቱና በቅዱሳኑ አብርሃአጽብሐ መሆኑና በዚያው ዘመን የክርስትና ሃይማኖትን ብሔራዊ ሃይማኖት አድርገው በዓሉ በብሔራዊ ደረጃ እንዲከበር ማድረጋቸው በታሪክ ድርሳናት ተመዝግቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...