Monday, May 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የተቀዛቀው ኢኮኖሚ በአፍሪካ ልማት ባንክ ቅኝት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ይፋ የተደረገው የአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርት፣ የየአገራቱን ኢኮኖሚያዊ ክራሞት አስፍሯል፡፡ በሪፖርቱ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የተመለከተው ክፍል እንዳሰፈረው ከሆነ፣ ኢትዮጵያ በገጠማት የእርስ በርስ ግጭትና በፖለቲካዊ ችግሮች ሳቢያ እንዲሁም መንግሥት በጀመራቸው የፖሊሲ ማስተካከያዎች ኢኮኖሚው በተሸኘው ዓመት (በአውሮፓውያን አቆጣጠር) መቀዘቀዙን አስፍሯል፡፡

በማክሮ ኢኮኖሚው መስክ ኢትዮጵያ ያለባትን ከፍተኛ የዕዳ ጫና ለማቃለል የፊስካል ዕርምጃዎችን መውሰዷን ያተተው፣ ‹‹አፍሪካን ኢኮኖሚክ አውት ሉክ›› የተሰኘው የአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርት፣ የኢትዮጵያ የዕዳ ጫና ከኢኮኖሚው አንፃር (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) ወደ 62 በመቶ መድረሱን አስታውሷል፡፡ ከዚህ የዕዳ ጫና ውስጥ አብዛኛው መንግሥት ከአገር ውስጥ የፋይናንስ ምንጮች የተበደረው ከፍተኛውን መጠን ሲይዝ፣ በአንፃሩ ከውጭ ምንጮች የኢኮኖሚውን እስከ 20 በመቶ የሚሸፍን የብድር ዕዳ ክምችት ተመዝግቧል፡፡

ከአፍሪካ ልማት ባንክ ባሻገር ሌሎች ሪፖርቶችም የዕዳ ጫናን ለማቃለል የሚውሉ ክፍያዎች በአፍሪካ የኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ስለሚያሳድሩት ጫና እያሳሰቡ ነው፡፡ በተያዘው ዓመት የዚህ ተጎጅ ከሚሆኑት ውስጥ ኢትዮጵያ ትካተታለች፡፡ ባለፈው ዓመት እስከ 20 ቢሊዮን ብር የሚገመት የብድር ዕዳ ክፍያ ሲፈጸም፣ በዚህ ዓመትም እስከ 25 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ክፍያ ሊፈጸም እንደሚችል የገንዘብ ሚኒስቴር አኃዞች አመላክተዋል፡፡ ይሁንና የዕዳ ማቃለያ ክፍያው እስከ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ወይም እስከ 42 ቢሊዮን ብር ሊያድግ እንደሚችል የሚጠቁሙ መረጃዎችም ይታያሉ፡፡

የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ከባለ ሁለት አኃዝ ዕድገት ከተራራቀ ከሦስት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ... 2017/18 ዕድገቱ ወደ 7.7 በመቶ ዝቅ ማለቱም ይታወሳል፡፡ በተያዘው ዓመት ምናልባት ወደ 8.2 በመቶ እንደሚያንሰራራ የዓለም የገንዘብ ድርጅትን የመሰሉ ተቋማት በቅርቡ ያወጡትን ትንበያ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክም ተጋርቷል፡፡ የተጠቀሰውም ዕድገት ቢሆን የተመዘገበው የአገልግሎት ዘርፉ 8.8 በመቶ፣ ኢንዱስትሪው 12.2 በመቶ ዕድገት በማሳየታቸው የመጣ ነው፡፡ በኢንዱስትሪ መስክ በተለይም በኢነርጂ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እንዲሁም በትራንስፖርት መሠረተ ልማት መስክ የታየው እንቅስቃሴ ለዘርፉም ለጠቅላላው ኢኮኖሚም ድርሻ አበርክቷል፡፡ የግል ፍጆታና ኢንቨስትመንትም ለኢኮኖሚው ማደግ ሚና እንደነበራቸው ሲጠቀስ መንግሥት በመሠረተ ልማት ዘርፍ የሚያደርገው ኢንቨስትመንት ብሎም እያሽቆለቆለም ቢሆን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱ ታክሎበት፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ 7.7 በመቶ ዕድገት ነበረው፡፡ በአንፃሩ 80 በመቶ በላይ የገጠሩ ሕዝብ የሚተዳደርበት የግብርናው ዘርፍ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ምሰሶ ቢሆንም፣ ዓመታዊ ዕድገቱ በየጊዜው እያሽቆለቆለ መጥቷል፡፡ በተለይም ካቻምና ወደ 2.3 በመቶ ወርዶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ባለፈው ዓመት ወደ 6.7 በመቶ ዕድገት አንሰራርቷል፡፡ ለግብርናው ዘርፍ ዕድገት ማገገም ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ያሳየው የዋጋ መሻሻል ምክንያት እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ ሆኖም በዚህ ዓመት ለግብርናው ዘርፍ ይበልጥ ማገገም ሚና እንደሚኖራቸው በአፍሪካ ልማት ባንክ ከተጠቀሱት መካከል፣ ኢትዮጵያ በማዳበሪያ ላይ የምታካሂደው ኢንቨስትመንት (ሊገነባ የታቀደውን የማዳበሪያ ፋብሪካ እንደሚያካትት አልተጠቀሰም) በመስኖ እርሻ ልማት እንዲሁም በምርጥ ዘር አቅርቦት በኩል የሚጠበቁ ውጤቶች ለግብርናው ተስፋ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት ከሚጎትቱ ደካማ አፈጻጸሞች መካከል የወጪና የገቢ ንግድ መዛባት ዋናው ተጠቃሽ ነው፡፡ ምንም እንኳ እየተስፋፋ ዘመናትን ባስቆጠረው በንግድ ሚዛን ጉድለት ምክንያትና የክፍያ ሚዛን መዛባት ሳቢያ የአገሪቱ ጠቅላላ አገሪቱ ኦፊሴላዊ የመጠባበቂያ ክምችት 2.1 ወራት ብቻ የሚበቃ ሆኗል፡፡ ካቻምና እርግጥ 2.5 ወራት የሚያዘልቅ ክምችት ተመዝግቦ እንደነበር ሪፖርቱ አጣቅሷል፡፡ አገሪቱ ምንም ዓይነት የውጭ ምንዛሪ ገቢ ወይም የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ሳይኖራት ከውጭ ዕቃ ለማስገባት የሚያስችላት ክምችት መጠን በወራት የሚገለጽ ሲሆን፣ ጤነኛ የሚባለው እስከ ሰባት ወራት ድረስ ሊያዘልቅ የሚችል ክምችት ሲኖር ነው፡፡ 

የአገሪቱ የዕዳ መጠን (ከውጭም ከአገር ውስጥም የተመዘገበው እስከ 60 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል) እያደገ መምጣቱ መንግሥት እንደቀድሞው የሚያካሂደውን መጠነ ሰፊ የልማት ኢንቨስትመንት ከከፍተኛ ወደ መካከለኛ ደረጃ እንደሚያወርደውም ይታመናል ሲል ባንኩ በሪፖርቱ አስፍሯል፡፡ ይኸውም የተመዘገበውን የዕዳ ጫና ለማቃለል እንዲያግዝ ነው፡፡ ለልማት ይፈለግ የነበረው ገንዘብ ለብድር ክፍያ ስለሚቀነስለት ነው፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ መንግሥት ለልማት ሥራዎች የሚያወጣውን ወጪዎች ለመቀነስ ሆኖም ልማቱ እንዳይቋረጥ ያግዛሉ ከተባሉት ውስጥ ሙሉ በሙሉና በከፊል ወደ ግል ይዛወራሉ የተባሉት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ናቸው፡፡ ሪፖርቱ የባቡር ኮርፖሬሽን፣ የማሪታይምና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ዘርፉ፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና የቴሌኮም ኢንዱስትሪው ለግል ባለሀብቶች ተሳትፎ ክፍት እንደሚደረጉ መወሰኑ፣ በመንግሥት ላይ የነበረውን የልማት ወጪዎችን ጫና እንደሚቀንስለት ያትታል፡፡ ከዚህም ባሻገር በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገትም ሆነ መስፋፋት ዕድል የሚሰጡ መልካም ጎኖችም ተጠቅሰዋል፡፡ እያደገ የመጣው የሕዝቡ የገቢ መጠን፣ የፍጆታ ዕቃዎች ገበያ እያደገ መምጣት፣ የከተሜነት መስፋፋት ለኢኮኖሚው ተስፋ ናቸው፡፡

እስከ ካቻምና ድረስ 21 ዓመታት ያህል በተጓዘው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ውስጥ በከፍተኛ የድህነት አረንቋ ውስጥ ይኖር የነበረው 46 በመቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ 24 በመቶ ገደማ ዝቅ እንዲል ያስቻለ ኢኮኖሚያዊ ግስጋሴ ቢታይም፣ በኢትዮጵያ  24 ሚሊዮን ያላነሰ ሕዝብ ያውም በዝቅተኛው የድህነት መመዘኛ ሥሌት መሠረት አሁንም በድህነት ይማቅቃል፡፡ የኢትዮጵያን የድህነት ቅነሳ ፈታኝ ከሚያደርጉት ችግሮች መካከል ፖለቲካዊ ችግሮችን ጨምሮ፣ የሕዝብ ብዛትና የዕድገት ግፊቱ፣ እንዲሁም የልማት ጉዞ መነሾ ከታች ወይም ከምንም መሠረት የሚነሳ መሆኑ የአፍሪካ ልማት ባንክና ሌሎችም የሚስማሙበት አመክንዮ ነው፡፡ ምንም እንኳ ሪፖርቱ አንዳንዶቹን አኃዞች ሳያሻሽል ቢያቀርብም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ የአሌክትሪክ ኃይል የማያገኘው 40 በመቶ እንደሆነ፣ 34 በመቶውም የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ማግኘት እንዳልቻለ አስታውሷል፡፡ በመንገድ ልማት መስክም በርካታ ውጤቶች ቢመዘገቡም፣ ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች አኳያ ዝቅተኛው የጥሪጊያ መንገድ ሥርጭት የሚገኝት አገር መሆኗም ታይቷል፡፡

ይህም ይባል እንጂ መጪው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት በዓለም ላይ ከፍተኛ እንደሚሆኑ ከሚጠበቁት ውስጥ ቁንጮው ነው፡፡ በስዊዘርላንዷ የኢኮኖሚስቶች ክበብ ዳቮስ ከተማ የሚካሄደው የዘንድሮው ውይይት ወቅት መነጋጋሪያ ከሚሆኑ ጉዳዮች መካከል፣ ቻይናን የመሰሉ ግዙፍ አገሮች ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ያዝመገባሉ፣ ይህም ለዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት መዳከም ትልቅ ሰበብ እንደሚሆን ተገምቷል፡፡ በአንፃሩ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ እንደ ሩዋንዳና ጂቡቲ ያሉት አገሮች ለዓመታት ያሳዩት ዕድገት በተወሰነ ደረጃ ቅናሽ ቢታይበትም፣ አሁንም ቀጣናው በአፍሪካ ትልቁ ዕድገት የሚመዘገብበት እንዲሆን ድርሻው ጉልህ ስለመሆኑ የአፍሪካ ልማት ባንክ አስነብቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች