Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በግማሽ ዓመቱ የባንኮች የብድር ክምችት 217 ቢሊዮን ብር ደረሰ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የግል ባንኮች እስከ 2011 ግማሽ ዓመት መካተቻ ድረስ ያስመዘገቡት የብድር ክምችት ከ216.83 ቢሊዮን ብር በላይ ደረሰ፡፡ ለቦንድ ግዥ ያዋሉት የገንዘብ መጠንም ከ76 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑ ታወቋል፡፡

የባንኮቹን 2011 ዓ.ም. የስድስት ወራት አፈጻጸም የሚያመለክተው ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርት 16ቱ የግል ባንኮች ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ብልጫ ያለው ብድር ለደንበኞቻቸው አሠራጭተዋል፡፡ ባንኮቹ የፈቀዱትና የሰጡት የብድር ክምችት ዓምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረበት መጠን በ55 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው፡፡ ባንኮቹ የፈቀዱትና ያሠራጩት የብድር ክምችት 161.8 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡

ከመረጃው መረዳት እንደሚቻለው፣ የባንኮቹ አፈጻጸም ለብድር የሚያውሉት ገንዘብ መጠን በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ነው፡፡ ባንኮቹ በጥልቅ ከሰጡት ብድር ውስጥ ከፍተኛውን ብድር በመልቀቅ የሚጠቀሱት ስድስት ባንኮች ናቸው፡፡ አዋሽ፣ ዳሸን፣ ኅብረት፣ አቢሲኒያ፣ ኦሮሚያ ኅብረት ሥራና ወጋገን ባንኮች በቀዳሚነት የሚጠቀሱት ናቸው፡፡

ስድስቱ ባንኮች በ2011 ግማሽ ዓመት በጥቅል የደረሱበት የብድር ክምችት መጠን፣ 16ቱ ባንኮች በጠቅላላው ከደረሱበት አኳያ ከ30 በመቶ ያላነሰ ድርሻ እንዲይዙ አስችሏቸዋል፡፡ ስድስቱ ባንኮች በአጠቃላይ ከ154.6 ቢሊዮን ብር በላይ የብድር ክምችት አስመዝግበዋል፡፡

ከባንኮቹ ያልተጠቃለለ ሒሳብ ሪፖርት መረዳት እንደሚቻለው እስከ ታኅሳስ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ አዋሽ ባንክ ያስመዘገበው የብድር ክምችት 37.15 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ዳሸን ባንክ 28.2 ቢሊዮን ብር፣ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ 19.1 ቢሊዮን ብር፣ አቢሲኒያ ባንክ 21.2 ቢሊዮን ብር፣ ኅብረት ባንክ 17.5 ቢሊዮን ብር፣ ንብ ባንክ 16.7፣ ወጋገን ባንክ 15.5 ቢሊዮን ብር አስመዝግበዋል፡፡

የባንኮቹ የብድር መጠን ዕድገት ከተቀማጭ ገንዘብ ዕድገታቸው ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ በ2011 አጋማሽ ዓመት 16ቱም ባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ ረገድ የደረሱበት ውጤትም ይህንኑ ያሳያል፡፡ የባንኮቹ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን በጠቅላላው 311.2 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም በ2010 የመጀመርያው ግማሽ ዓመት ወቅት ከነበራቸው ተቀማጭ መጠን ጋር ሲነፃፀር ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው ያሳያል፡፡ በ2010 ግማሽ  ዓመት የባንኮቹ ተቀማጭ ገንዘብ 231.1 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ 

በአንፃሩ የባንኮቹ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ዕድገትና በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የብድር መጠን በአስገዳጅነት ለቦንድ ግዥ የሚያውሉትን የገንዘብ መጠን እየጨመረ እንዲመጣ ማድረጉንም ያመላክታል፡፡ ከሰባት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመርያ መሠረት፣ የግል ባንኮች ከእያንዳንዱ ብድር ላይ 27 በመቶ በመቀነስ ለቦንድ ግዥ የሚያውሉበት አሠራር እየተተገበረ ይገኛል፡፡

በዚህ ዓመት አጋማሽ 16ቱም ባንኮች ለቦንድ ግዥ ያዋሉት የገንዘብ መጠን 76 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በዓምናው በግማሽ ዓመት ባንኮቹ የ59 ቢሊዮን ብር ግዥ ፈጽመው ነበር፡፡ የዘንድሮው ግማሽ ዓመት ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ለቦንድ ግዥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት ከፍተኛውን ብድር እያቀረቡ ያሉት ባንኮች ሲሆኑ፣ ከባንኮች መካከል እስከ ታኅሳስ መጨረሻ ከፍተኛውን የቦንድ ግዥ በመፈጸም ዳሸን ባንክ ዋናውን ድርሻ ይዟል፡፡ ዳሸን ለቦንድ ግዥ ያዋለው ገንዘብ 11.1 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ከዳሸን ባሻገር አስገዳጁን ቦንድ በመግዛት የሚጠቀሰው አዋሽ ባንክ ነው፡፡ አዋሽ ባንክ እስካሁን የ8.77 ቢሊዮን ብር ግዥ ፈጽሟል፡፡

ከሁለቱ ባንኮች ባሻገር ከስድስት ቢሊዮን እስከ 6.5 ቢሊዮን ብር ለቦንድ ግዥ ያዋሉት ሌሎች ስድስት ባንኮች ሲሆኑ፣ እነዚህም አቢሲኒያ፣ ወጋገን፣ ኅብረት፣ ንብና የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንኮች ናቸው፡፡ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ 5.3 ቢሊዮን ብር ለቦንድ ግዥ ማዋሉ ተመልክቷል፡፡ የተቀሩት ዘጠኝ ባንኮች ከ775 ሚሊዮን ብር እስከ 2.9 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለቦንድ ግዥ አውለዋል፡፡

አስገዳጁ የቦንድ ግዥ መመርያ ባንኮችን በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳ ነው እየተባለ በተለያዩ መድረኮች አቤቱታ ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡ የባንኮቹ ኃላፊዎችና የኢትዮጵያ ባንኮችን ማኅበርም በተደጋጋሚ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ከርመዋል፡፡ አስገዳጁ መመርያ ከሳምንት በፊት የግል ባንኮች ኃላፊዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር በተነጋገሩበት ወቅት መነሳቱ ይታወሳል፡፡ መንግሥት የግል ባንኮችን በየጊዜው እንደተጫናቸውና በፈለጉት መጠን እንዲያድጉም የቦንድ ግዥ መመርያው ተፅዕኖ መፍጠሩን በማውሳት መንግሥት መመርያውን እንዲያነሳው መጠየቃቸው አይዘነጋም፡፡

የጥያቄያቸው መነሻ እስካሁን ድረስ ለቦንድ ግዥው ያዋሉት የገንዘብ መጠን ለተለያዩ የኢኮኖሚ ክፍሎች ቢያበድሩት ኖሮ ባንኮቹ ከሚያኙት ጥቅም አንፃር አቅማቸውንም ለማጎልበት ይረዳቸው እንደነበር በማስረዳት ጭምር ነበር፡፡ የፋይናንስ ባለሙያዎችም የመመርያው አተገባበር ላይ ትችት ይሰነዝራሉ፡፡ መመርያው የወጣው በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል ብድር ለሚፈልጉ የልማት ሥራዎች እንዲደገፉበት ቢሆንም፣ በአብዛኛው ለመንግሥት ብድርና ለበጀት ጉድለት ማሟያው ሲጠቀምበት መቆየቱን በማንሳት ባለሙያዎቹ ይተቻሉ፡፡ ለልማት የዋለው ብድርም በአብዛኛው የውኃ ሽታ ሲሆን መታየቱ የመመርያውን አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ ከቶታል፡፡ 

ይሁንና በአሁኑ ወቅት መመርያውን ለማንሳት መንግሥት ዝግጁ እንዳልሆነ ለባንኮቹ ተነግሯቸዋል፡፡ ለቦንድ ግዥ የሚከፈለው የወለድ መጠን ዝቅተኛ መሆኑም ለባንኮቹ ምሬት ሌላው ምክንያት ነው፡፡ ባንኮች ለገንዘብ አስቀማጭ ደንበኞቻቸው የሚከፍሉት ሰባት በመቶ ሲሆን፣ ቦንድ በመግዛታቸው የሚያገኙት ሦስት በመቶ ወለድ ነው፡፡ ይህም ጉዳታችንን አባብሶታል በማለት ይሞግታሉ፡፡ ይህም ቢባል ግን ባንኮቹ መቼም ቢሆን ከፍተኛ ትርፍ ከማስመዝገብ አላቦዘናቸውም፡፡ ከፍተኛ የገንዘብ ክምችት አላቸው፡፡  ባለፈው ዓመት 16ቱም ባንኮች ከታክስ በፊት ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፋቸው ይታወሳል፡፡

ከባንኮቹ የገንዘብ አፈጻጸም በተጨማሪ መረጃዎች፣ ቅርንጫፎቻቸውን በማስፋፋት ረገድም ብዙ እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ እስከ ታኅሳስ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ 16ቱም ባንኮች የቅርንጫፎቻቸውን ቁጥር ወደ 3,472 አድርሰዋል፡፡

በብሔራዊ ባንክ መረጃ መሠረት እስከ 2010 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ የባንኮቹ የቅርንጫፎች ብዛት 3,275 ነበር፡፡ በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ 197 አዳዲስ ቅርንጫፎች መክፈታቸውን መረጃው ይጠቁማል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች