Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጣልያኑ ጨርቃ ጨርቅ አምራች ከኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምርት መላክ ጀመረ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአውሮፓ ጉብኝታቸው ቀዳሚ ካደረጓት ጣልያን ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች ጋር በተወያዩበት ወቅት የተሳተፈውና ካርቪኮ ግሩፕ የተሰኘው የጨርቃ ጨርቅ ኩባንያ ምርቶቹን ለአውሮፓ ገበያ ማቅረብ ጀመረ፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ኃይሉ ለሪፖርተር በገለጹት መሠረት፣ ኩባንያው በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ100 ሚሊዮን ዶላር የሴንተቲክ የሲንተቲክ ጨረቃ ጨርቅ ምርቶች እያመረተ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም ኩባንያው ከ350 ሺሕ ዶላር ያላነሰ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማስገኘቱን አስታውቀዋል፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በጎንዮሽ ውይይታቸው የጣሊያን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተሳተፉበትና አሥር የጣልያን ባለሀብቶች የተካተቱበትን  ኢንቨስትመንት ተኮር ስብሰባ አካሂደዋል፡፡ ከአሥሩ ኩባንያዎች መካከል በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ100 ሚሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ የመጀመርያው የተባለውን የሴንተቲክ ጨርቃ ጨርቅ ምርት ለማምረት ኢንቨስት ያደረገው የካርቪኮ ግሩፕ ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ላውራ ይገኙበታል፡፡

የካርቪኮ ግሩፕ ከኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባሻገር በ23.5 ሔክታር መሬት ላይ ከፓርኩ ጋር የተያያዘ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ እየገነባ እንደሚገኝ ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ የግንባታ የመጀመርያው ምዕራፍም ሙሉ በሙሉ እንደተጠናቀቀና የሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታም ከ15 በመቶ በላይ ስለመከናወኑ ተገልጿል፡፡ ኩባንያው በጣሊያንና በቬትናም በተከላቸው ፋብሪካዎቹ ለ30 ኢትዮጵያውያን የሙያ ሥልጠና እንደሰጠም ታውቋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍፁም አረጋ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አበበ አበባየሁን ያካተተው የኢትዮጵያን ልዑካን  ስለኢትዮጵያ የኢንቨሰትመንት መስህቦች ለባለሀብቶቹ ማብራሪያ ተሰጥቷል። ጣሊያናውያኑ በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉም ተጋብዘዋል፡፡

መንግሥት ከዓለም ባንክ ለቦሌ ለሚ ሁለት ግንባታ ካገኘው ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ፣ በዩሮ ቦንድ ሽያጭ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ማዋሉም ሲዘገብ ቆይቷል፡፡ ይህም ሆኖ ባለፈው ዓመት በቦሌ ለሚና በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ማምረት የጀመሩ ኩባንያዎች ባለፈው ዓመት የ100 ሚሊዮን ዶላር የወጪ ንግድ ማስመዝገባቸውንና ከ55 ሺሕ በላይ የሥራ ዕድል ስለመፍጠራቸውም የቀድሞው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር በላቸው መኩሪያ (ዶ/ር) መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

2009 ዓ.ም. ሥራ የጀመሩት የመቀሌና የኮምቦልቻ ከተሞችን ጨምሮ የሐዋሳና የቦሌ ለሚ አንድ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት 650 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ መደረጉ ይታወሳል፡፡ የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በ75 ሔክታር መሬት ላይ የተገነባ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ለተገነባው ቦሌ ለሚ አንድ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከወጣው 110 ሚሊዮን ዶላር በተጨማሪ፣ ለሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ 350 ሚሊዮን ዶላር፣ ለኮምቦልቻ 90 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ለመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ 100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል፡፡ ለአራቱ ፓርኮች ግንባታ ብቻ በጠቅላላው 650 ሚሊዮን ዶላር መንግሥት ማውጣቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በጅማ ከተማ ለተገነባውና ሥራ ለጀመረው ፓርክ 60 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም፣ ለአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክም 140 ሚሊዮን ዶላር ወጪ መደረጉ ይታወቃል፡፡ ይሁንና ትልልቅ አቅም ያላቸው ባለሀብቶችን የማምጣቱ ሥራ እንዳሰበው አልሆነለትም፡፡ የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ በቅርቡ ግንባታው ተጠናቆ ሥራ መጀመሩም ይታወቃል፡፡

በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ በጠቅላላው 30 ያህል የኢንዱስትሪ ፓርኮች እስከ 2017 ዓ.ም. እንዲለሙ መታቀዱ፣ የፓርኮቹ መገንባት የአምራች ኢንዱስትሪውን ኢኮኖሚያዊ ድርሻ ለማሳደግና የሥራ ዕድሎችን ለማስፋፋት ፋይዳው ትልቅ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ በየዓመቱ 200 ሺሕ የሥራ ዕድሎችን ከመፍጠር በተጨማሪ የአምራች (ማኑፋክቸሪንግ) ኢንዱስትሪው ኢኮኖሚያዊ ድርሻ አሁን ካለው የአራት በመቶ ወደ 25 በመቶ እንዲያድግ፣ ከወጪ ንግዱ አኳያም አሁን ካለው የስምንት ከመቶ ድርሻ ወደ 20 በመቶ እንዲያድግ ለማድረግ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት ለወጪ ንግዱ የሚኖረው ፋይዳ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች