[ክቡር ሚኒስትሩ ከባለሀብት ጋር እያወሩ ነው]
- እንኳን ደስ አለዎት፡፡
- ምን ተገኘ?
- አልሰማሁም እንዳይሉኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ምኑን?
- ዕግዱ ተነሳ፡፡
- ከአገር እንዳትወጣ የተባልከው?
- እሱን እንኳን ማረጋገጥ አልቻልኩም፡፡
- እንዴት?
- የሦስት ሺሕ ሰዎች የጉዞ ዕግድ መነሳቱን ሰምቻለሁ፡፡
- ዋናው የአንተ ተነስቷል ወይ?
- አላወቅኩም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ ምኑ ነው ደስ ያለህ?
- እኔ ስለሌላ ዕገዳ ነው የማወራው፡፡
- የምን ዕገዳ?
- የሪል ስቴት፡፡
- አትለኝም?
- ይኸው ከስብሰባ ወጥቼ ነው የማናግርዎት፡፡
- እንዴት ተነሳ?
- በቃ ተነሳ፡፡
- ስማ እኔ እኮ እንቅልፍ ካጣሁ ሰነባበትኩ፡፡
- ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር እኔ ራሴ መቼ ተኝቼ አውቃለሁ?
- ይጣራል ከተባለ ጀምሮ ጤናዬ ጥሩ አይደለም፡፡
- የስንት ሰው ጤና መታወኩን እኔም አውቃለሁ፡፡
- ታዲያ ዕግዱ እንዴት ተነሳ?
- እኔም ግራ ገብቶኛል፡፡
- ሊያዘናጉን እንዳይሆን?
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ማለቴ ነፃ ነን ብለን ስንዘናጋ ጎል እንዳይከቱን፡፡
- መጠርጠሩ አይከፋም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ አገልግሎት መስጠት ጀመሩ?
- የምን አገልግሎት?
- ለሪል ስቴቶቹ የስም ማዘዋወር ምናምኑን ነዋ፡፡
- ይጀመራል ተብሏል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ስለዚህ እኔ በአፋጣኝ በስሜ ያሉትን ቤቶች ማስተላለፍ አለብኝ፡፡
- ለማን ነው የሚያስተላልፉት?
- ለወዳጅ ዘመዶቼ ነዋ፡፡
- እሱን አሁን ማድረግ አደጋ አለው፡፡
- የምን አደጋ?
- ዕግዱ የመጣው እኮ ከፍተኛ የሆነ የቤትና የንብረት ዝውውር ስለነበረ ነው፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- በስምዎ ያሉትን ንብረቶች ለሌሎች ቢያስተላልፉ በድጋሚ መንግሥትን ሊያነቁት ይችላሉ፡፡
- እንዴት?
- ብቻዎን እኮ ያሉዎት ቤቶች ክፍለ ከተማ ያስመሠርቱዎታል፡፡
- እ. . .
- ሐሳባችንንማ አክሽፎብናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ማን ነው ያከሸፈው?
- ለውጡ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እስኪ ተወው፡፡
- የእኔ እኮ ሐሳብ በስምዎ ከተማ መመሥረት ነበር፡፡
- ምን ታደርገዋለህ?
- ሥርዓቱ ባይቀየር እኮ እርስዎ ብቻዎን መሆን ይችሉ ነበር፡፡
- ምን?
- ክልል!
[ክቡር ሚኒስትሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ያለ ኃላፊ ዘንድ ይደውላሉ]
- ዛሬ ከየት ተገኙ ክቡር ሚኒስትር?
- እንዲያው እንዳትረሱኝ ለማለት ነው፡፡
- ምነው አምባሳደር መሆን ፈለጉ?
- ምነው? ምን አደረግኩህ?
- እንዴት በፊት አምባሳደር መሆን እንደሚፈልጉ ነግረውኝ ነበር እኮ?
- ድሮ ነዋ፡፡
- አሁን ምን ተገኘ?
- ስማ ድሮ እኮ አምባሳደርነት መጦሪያ፣ ከዚያም በላይ የሽምግልና ቢዝነስ መሥሪያ ነበር፡፡
- አሁንማ እሱ ቀርቷል፡፡
- ስለዚህ ምን በወጣኝ ብዬ ነው በስተርጅና የምሰቃየው?
- ለነገሩ አሁን የሚሠራ ብቻ ነው አምባሳደር መሆን የሚቻለው፡፡
- ሁሉን ነገር መዘጋጋት ግን ያዋጣል?
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ቢያንስ አምባሳደርነት ዕድሜያችንን ሙሉ ያገለገልን ሰዎች መጦሪያ ነበራ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ማንን ነው ያገለገሉት?
- ሕዝቡን ነዋ፡፡
- ራስዎን እንደ ሕዝብ ነው እንዴ የሚቆጥሩት?
- አልገባኝም?
- ዕድሜዎን ሙሉ ራስዎን ሲያገለግሉ ነበራ፡፡
- አሁንማ የማንም መጫወቻ መሆኔን አውቃለሁ፡፡
- ምን ያደርጉታል?
- ለማንኛውም ሊስት ውስጥ አለሁበት?
- የምን ሊስት?
- ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እጓዛለሁ ወይ ብዬ ነው፡፡
- ለምንድነው የሚጓዙት?
- መደመሬን ለማሳየት ነዋ፡፡
- ለማን ነው የሚያሳዩት?
- ለዓለም ሕዝብ ነዋ፡፡
- ሞራልዎ እኮ ደስ ይላል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት?
- የዓለም ሕዝብ ያውቀኛል ብለው ነው የሚያስቡት?
- በሚገባ እንጂ፡፡
- ኧረ እንደዚህ መወጣጠር አያስፈልግም ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ማለት ነው?
- እንኳን በዓለም እዚህም በቅጡ የሚያውቅዎ የለም፡፡
- ምን ነካህ ታዋቂማ ነኝ፡፡
- ከታወቁም የሚታወቁት በአንድ ነገር ነው፡፡
- በምን?
- በሌብነት፡፡
- እንከባበራ?
- ለመከበር መጀመርያ የሚያስከብር ሥራ መሥራት አለብዎ፡፡
- ከዚህ በላይ ምን ልሥራ?
- የሠሩት ለራስዎ እንጂ ለአገር አይደለም፡፡
- ተረቱም እኮ ከራስ በላይ ንፋስ ነው የሚለው፡፡
- ስለዚህ እርስዎ ተደምረዋል ለማለት ይከብዳል፡፡
- እኔ ሙሉ ለሙሉ ነው የተደመርኩት፡፡
- እንዳይነቀሱ ይፍሩ፡፡
- ለማንኛውም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መሄድ እፈልጋለሁ፡፡
- እ. . .
- በርካታ ማግኘት የምፈልጋቸው ባለሀብቶች እዚያ አሉ፡፡
- የት?
- ዳቮስ፡፡
- እና ዳቮስ ነው መሄድ የፈለጉት?
- አዎን፡፡
- እርስዎ መሄድ ያለብዎ ዳቮስ ሳይሆን ሌላ ቦታ ነው፡፡
- የት?
- እንጦሮጦስ!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ዳያስፖራ ደውሎላቸው እያወሩ ነው]
- እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
- አገሪቷን እየለመድካት ነው?
- ክቡር ሚኒስትር ኧረ በፍፁም ልለምዳት አልቻልኩም፡፡
- እናንተ ዳያስፖራዎች ደግሞ ማካበድ ታውቁበታላችሁ፡፡
- እያካበድኩ አይደለም ክቡር ሚኒስትር?
- ታዲያ ምን እያደረግህ ነው?
- አገሪቱ እኮ በየጊዜው ከድጡ ወደ ማጡ እየሄደች ነው፡፡
- ምን ጠብቀህ ነበር?
- እኔማ ለውጡን ተማምኜ ነበር አገር ቤት የገባሁት?
- ወይ ለውጥ?
- ለነገሩ እርስዎ የቀድሞው ሥርዓት ናፋቂ እንደሆኑ አውቃለሁ፡፡
- እንዴት ማለት?
- በቃ ብዙ ነገር ቀርቶብዎታል፡፡
- ምን ቀረብኝ?
- አሁን ፈላጭ ቆራጭ አይደሉማ፡፡
- ውጤቱን እኮ እያየነው ነው፡፡
- የምን ውጤት?
- ይኸው አገሪቱ ያለችበትን ችግር አታየውም እንዴ?
- እሱ እንኳን አሳሳቢ ነው፡፡
- አሳሳቢ ብቻ ሳይሆን አሥጊ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በየቀኑ የምሰማው ወሬ እያሳመመኝ ነው፡፡
- ለምን?
- አገሪቱ እኮ ልትፈራርስ ነው የምትመስለው?
- መፍረስ እንኳን አትፈርስም፣ ግን ያው ቤት ሲታደስ የሚፈርስ ነገር አለው፡፡
- ለማንኛውም ከሰሞኑ ስብሰባችሁ እኮ ብዙ ነበር የሚጠበቀው፡፡
- የትኛውም ስብሰባ?
- የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ነዋ፡፡
- ምን ጠብቀህ ነበር?
- ማለቴ አገሪቱ እንዲህ በምጥ ላይ እያለች ሕዝቡ ወሳኝ መግለጫ ነበር የሚጠብቀው፡፡
- መግለጫው ምን ሆነ?
- የተለመደና በቃላት የተደረተ ብቻ ነው፡፡
- አየህ እሱ የኢሕአዴግ ባህል ነው፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ውስጥ እርስ በርሳችን እንፋለማለን፣ ስንወጣ ግን ሁሉንም ነገር ሰላም እንደሆነ እናስመስለዋለን፡፡
- ክቡር ሚኒስትር የሚሻለው ግን ፊት ለፊት ሁሉን ነገር በግልጽ ማውጣት ነው፡፡
- እሱማ የኒዮሊበራሎች አካሄድ ነው፡፡
- አሁንም ኒዮሊበራሎችን ይቃወማሉ እንዴ?
- ሁሌም ጠላቶቼ ናቸው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር መንግሥት እየሄደበት ያለው አቅጣጫ እኮ በእሱ መስሎኝ?
- ቢሆንም እኔ በእሱ አልስማማም፡፡
- ውስጣችሁማ ክፍፍል እንዳለ ያስታውቃል፡፡
- የምን ክፍፍል?
- የብዙ ነገር ክፍፍል፡፡
- ይኼ የጠላት ወሬ ነው፡፡
- እኔ እንዲያውም የሥራ አስፈጻሚው አባላት ሁሉም ሥራ አስፈጻሚ አይመስሉኝም፡፡
- ምን ማለት ነው?
- አንዳንዶቹ የሚያስፈጽሙት ሥራ አይደለም፡፡
- ምንድነው የሚያስፈጽሙት?
- ሕገወጥነት!
[ክቡር ሚኒስትሩ ለደላላ ወዳጃቸው ስልክ ይደውላሉ]
- አንተ ሰውዬ ምን ሆነሃል?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- በተከታታይ ስልክ ስደውልልህ ለምንድነው የማታነሳው?
- ስልኩ ጥሩ አይደለም ብዬ እኮ ብዙ ጊዜ ቢሮ ብመጣ አጣሁዎት፡፡
- ምን ሆነህ ነው የጠፋኸው?
- ክቡር ሚኒስትር ድምፄን ላጥፋ ብዬ እኮ ነው፡፡
- ለምን?
- ከነገ ዛሬ ቢያስገቡኝስ?
- ስማ እስከ መጨረሻው ጠብታ ነው መታገል ያለብህ፡፡
- ምን ተገኘ ታዲያ?
- ቢዝነሱን ተውከው እንዴ?
- ምን ያው ሁሉ ነገር ስለተቀያየረ አስቸጋሪ ሆኗል እኮ?
- አንተ ደግሞ ለዚህ መቼ ትታማለህ? ለ20 ዓመታት ጥርስህን የነቀልክበት አይደል እንዴ?
- እንዲያው እንዲህ ሞራል የሚሰጠኝ ካገኘሁማ አሁኑኑ ነው የምጀምረው፡፡
- ለመሆኑ ሰሞኑን ሚዲያ እየተከታተልክ ነው?
- ምን አዲስ ነገር አለ ክቡር ሚኒስትር?
- በየቦታው እኮ ባንኮች እየተዘረፉ ነው፡፡
- እሱን ሰምቻለሁ፡፡
- ታዲያ ቶሎ ብለህ ሥራውን አትጀምርም እንዴ?
- የቱን?
- የእጥበቱን ነዋ፡፡
- እ. . .
- በአዲስ መልክ ጀምረናል ብለህ ማስታወቂያ ማስነገር እኮ ነው፡፡
- በሚዲያ?
- ኧረ በኔትወርክህ፡፡
- የምን እጥበት ነው ግን?
- የገንዘብ!