Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊኢትዮጵያ ያልተጠቀመችበት የዱር ስጦታ

ኢትዮጵያ ያልተጠቀመችበት የዱር ስጦታ

ቀን:

ኢትዮጵያ ባላት መልክዓ ምድራዊና የመሬት አቀማመጥ እንዲሁም የሥነ ምድርና የአየር ንብረት ብዙኃነት የተነሳ የበርካታ ብርቅዬ የዱር እንስሳት ዝርያዎች ባለቤት እንድትሆን ተፈጥሮ አድሏታል፡፡ የቀደምት ሥልጣኔ፣ በአያሌ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ባህላዊ ቅርሶቿ ተለይታ የምትታወቅ እንደመሆኗ መጠን በዓለም ላይ ለቱሪዝም ሀብት አለኝታነታቸው በቀዳሚነት ደረጃ ከሚፈረጁ አገሮች ተርታ የመመደብ ብቃት አላት፡፡

ይህንን በተፈጥሮና ከ3,000 ዓመታት በላይ በዘለቀ የታሪክ ሒደት የታደለችበት የዱር እንስሳት ሀብትና ተያያዥ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች በአግባቡና በተቀናጀ መልኩ ጠብቆ መጠቀም ከተቻለ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ ምኅዳራዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

የኢትዮጵያን የዱር እንስሳት ሀብት ልማትና ጥበቃን አስመልክቶ ጥር 16 ቀን 2011 ዓ.ም. በተካሄደው አገራዊ ውይይት ላይ የወጣው መረጃ እንዳመለከተው፣ ይህንን ዕድል ከግምት ውስጥ በማስገባት ካለፉት 50 ዓመታት ወዲህ የዱር ሕይወት ሀብቷን በአግባቡና ዓለም አቀፍ ደረጃን በተከተለ መልኩ ጠብቆ ከመጠቀም አንፃር ቀላል የማይባል ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡  

- Advertisement -

በተጠቀሱት የጥረት ዓመታት ከተወሰዱት ዕርምጃዎች መካከልም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የአገሪቱን የቆዳ ሽፋን 14 በመቶ የያዘ ከ70 በላይ የተለያዩ የጥበቃ ክልሎች ማለትም ብሔራዊ ፓርኮች፣ የዱር እንስሳት መጠለያዎችን፣ የዱር እንስሳት የጥበቃ ክልሎችን፣ የቁጥጥር አደን ቀበሌዎችንና የባዮሰፊር ሪዘርቭ ማቋቋም፣ የጥበቃና የቁጥጥር ሥራዎች የማካሄድ ተግባራት ይገኙበታል፡፡

መረጃው የቅርብ ጊዜ ጥናቶችን ዋቢ አድርጎ እንዳብራራው፣ የኢትዮጵያ የጥበቃ ቦታዎች በተለይም ከቱሪዝም፣ ከሕጋዊ አደን፣ ከግጦሽ፣ ከካርቦን አምቆ መያዝ፣ ከብዝኃ ሕይወት መዳቀልና መራባት፣ ከተባይ መቆጣጠር፣ ከአፈር መሸርሸር መከላከል፣ ከሥነ ምኅዳር መስተጋብር፣ ከውኃና ከመድኃኒት ምንጭነትና መሰል አገልግሎቶች በዓመት 6.5 ቢሊዮን ዶላር ጥቅም ያስገኛል፡፡

ይሁን እንጂ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የዱር እንስሳት ሀብቱ በአግባቡ ለምቶና ተጠብቆ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም፡፡ ከዚህም አንፃር በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ለዱር እንስሳት ሀብት ጥበቃና ልማት ዓላማ ተሰይመው የሚገኙ የጥበቃ ቦታዎች ሕልውናቸው በወረቀት ላይ ብቻ ተወስኖ ቀርቷል ከሚባልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

በተለይም በአሁኑ ጊዜ የበርካታ የጥብቅ ቦታዎች የቆዳ ሽፋን እጅግ እየተጣበበ ነው፡፡ በርካታ የዱር እንስሳት ዝርያዎችም በመጥፋት ላይ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ከማጎ ብሔራዊ ፓርክ ቀጭኔ፣ የሜዳ አህያ፣ ሳላ፣ የሜዳ ፍየልና ሰጎን ዝርያቸው ሙሉ በሙሉ ሲጠፉ የፓርኩ የቆዳ ስፋትም እጅግ ቀንሷል፡፡ የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክም የሜዳ አህያ፣ ሰጎንና አቦ ሸማኔ ከፓርኩ ሲጠፉ፣ ሌሎች ደግሞ ቁጥራቸው እጅግ በመመናመን ላይ ይገኛል፡፡

 በተለይም የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ መጠሪያ የሆነው የሳላ ቁጥር 7,000 አካባቢ የነበረው በአሁኑ ጊዜ ከ200 እንደማይበልጥ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ጫፍ በባቢሌ የዝሆኖች መጠለያም የሚገኙ ዝሆኖች በአሁኑ ጊዜ ዝርያቸው ለመጥፋት እንደተቃረበ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ በሌሎች ፓርኮችና ዱር እንስሳት ጥበቃ ሥፍራዎች ተመሳሳይ ጥፋት በመከሰት ላይ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

የችግሮቹም ሥረ መሠረቶች፣ መንግሥት ለዘርፉ እያደረገ ያለው ክትትልና ቁጥጥር እጅግ አነስተኛ መሆን፣ ዘርፉን የሚወክለው ተቋም ደካማ መሆኑና የቅንጅት ማነስ፣ በጥበቃ ቦታዎች አካባቢ የሚኖረውን ማኅበረሰብ በተጠቃሚነትና በጥበቃው ዙሪያ በበቂ አለማሳተፍ፣ በጥበቃ ቦታዎች አካባቢ የሚታየው በመሣሪያ የተደገፈ ሥርዓት አልበኝነት መሆኑን መረጃው ጠቁሞ፣ ይህ ምትክ የለሽ የተፈጥሮ ፀጋ በአግባቡ ተጠብቆ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ቢቻል ኖሮ ለሕዝባችን ማኅበረ ኢኮኖሚ፣ ልማትና ዕድገት የሚያበረክተው ድርሻ ከየትኛውም ተጓዳኝ ዘርፍ የማይተናነስ እንደሆነ በእርግጠኝነት መመስከር እንደሚቻል አመልክቷል፡፡

በዚህ ዘርፍ ላይ ሥር ነቀል የሆነ አሉታዊ ለውጥ ለማምጣት እጅግ ተጠናክሮ መሥራት ይጠበቃል፡፡ በተለይም መንግሥት የሰየመው የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን በባለሙያ የተደገፈ ሥልት በማዘጋጀት፣ በጋራ መንፈስ ውስጣዊ ጥንካሬን በመፍጠር፣ የሥራ አንድነትንና ተነሳሽነትን በማሳደግ፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት በዘርፉ ላይ የተጋረጠውን ችግር በማቃለል አገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ይጠበቃል፡፡ የሚመለከታቸው ከፍተኛ የመንግሥት አመራርም የዘርፉን ውጤታማነት በቅርበት በመገምገምና ወቅታዊ የዕርምት ዕርምጃ በመውሰድ አመርቂ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም ከመረጃው ለማወቅ ተችሏል፡፡  

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ ከኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ቲንክ ታንክ ጋር በመተባበር ባካሄደው በዚሁ የውይይት መድረክ ላይ የዱር እንስሳት ሀብትና ይህን ሀብት በማልማትና በመጠበቁ ሒደት ላይ በአጋጠሙ ተግዳሮቶች እንዲሁም ለተግዳሮቶቹ መፍትሔ ሊሆኑ በሚችሉ ሐሳቦች ላይ ትኩረት ያደረጉ ሁለት የመነሻ ጽሑፎች ቀርበው በታዳሚ አስተያየት ተሰጥቶበታል፡፡

አስተያየታቸውን ከሰነዘሩት ታዳሚዎች መካከል አሶሴሽንስ ፎር ሰስተነብል ዴቨሎፕመንት ኦልተርኔቲቭ የተባለ አገር በቀል ድርጅት መሥራችና ዳይሬክተር ታከለ ተሾመ (ዶ/ር) ይገኙበታል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ አስተያየት፣ በተፈጥሮ ሀብትና በብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ላይ ተጨባጭ ውጤት ሊመጣ ያልቻለው ብዙዎቹ ነገሮች እላይ ተንጠልጥለው በመቅረታቸውና በሀብቱ ተጠቃሚዎች ዘንድ የወረደ ሥራ አለመሠራቱ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኰንን አገላለጽ፣ የዱር እንስሳቱ አሁን ያሉበት ደረጃ በመኖርና ባለመኖር መካከል ነው፡፡ ብሔራዊ ፓርኮችም በሰው ሠራሽ ችግሮች ለበርካታ ጉዳቶች ተዳርገዋል፡፡ ከጉዳቶቹም መካከል ልቅ ግጦሽ፣ ሕገወጥ እርሻ፣ ደን ጭፍጨፋ፣ ከሰል ማክሰልና ሕገወጥ አደን ተጠቃሾች ናቸው፡፡ እነዚህ ችግሮች ከኅብረተሰቡ ጋር ለመፍታት ጋምቤላ፣ ባቢሌ አዋሽ ላይ የንቅናቄ መድረኮች ተጀምረዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ከመዋቅር ጀምሮ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት፣ ከዚህም በመነሳት መዋቅራዊ አደረጃጀት በአዲስ መልክ ተዘጋጅቶ ለሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እንደተላከ፣ በተረፈ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጀምሮ በየደረጃው ባሉት የፖለቲካ አመራሮች ዘንድ የተፈጥሮ ጉዳይ የእኛ ጉዳይ ነው፣ ስለዚህ ተፈጥሮን መንከባከብ መቻል አለብን የሚል ነገር አለመኖሩ ሌላው ቁልፍ ችግር እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

የኅብረተሰቡ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እስካልተረጋገጠ ድረስ ብሔራዊ ፓርኮች ዘለቄታ እንደማይኖራቸው ምክትል ዳይሬክተሩ ገልጸው፣ በአሁኑ ጊዜ እየተሠራ ያለው ብሔራዊ ፓርኮችና ጥበቃ ቦታዎች አሁን ባሉበት ሁኔታ ብቻ እንዲቀጥሉ ማድረግ ወይም የእሳት ማጥፋት ሥራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ አኳያ በአንድ ፓርክና ጥበቃ ቦታ ላይ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሙከራ መሥራትና ይኼንንም ምርጥ ተሞክሮ ወደ ሌሎች ፓርኮችና ጥብቅ ቦታዎች የሚስፋፉበትን አካሄድ መፍጠር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል በበኩላቸው፣ ቀቀቦ ክልል ተሻጋሪ በሆኑ ፓርኮችና ጥብቅ ቦታዎች ላይ የሁለቱ ክልሎችና አጎራባች መንግሥታት እኩል ቁርጠኝነት የሚያሳዩበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ፓርኩን ጠብቁት፣ አትንኩት ከማለት በስተቀር ከፓርኩ ከተገኘው ገንዘብ ለኅብረተሰቡ ጠብ ከማድረግ አኳያ ዘርፉን ከሚመሩት ሰዎች ትልቅ ትኩረት አልተደረገም ብለዋል፡፡

ኅብረተሰቡ በዱር እንስሳት በሚጠቃበት ጊዜ ካሳ የሚያገኝበት አሠራር በሥርዓቱ ውስጥ መካተት እንዳለበት፣ ይህም ሁኔታ ኅብረተሰቡ በደረሰበት ጉዳት የተነሳ በዱር እንስሳቱ ላይ ብቀላ እንዳያካሂድ ያደርጋል የሚል እምነት እንዳላቸው ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ለባለሥልጣኑ የተሰጠው ሥልጣን ከፓርኩ ውጪ ያሉትን የዱር እንስሳትን ማስተዳደር ሲሆን፣ ፓርኩ ውስጥ ያሉትን የዱር እንስሳት ደግሞ ከሦስት ዓመት በፊት የወጣው አዋጅ ባህልና ቱሪዝም እንዲያስተዳደር ሥልጣን እንደሰጠው፣ ዘንድሮ በወጣው አዋጅ ደግሞ የዱር እንስሳት ጉዳይ ሙሉ ለሙሉ ከአዋጁ ውስጥ እንዳወጣ፣ በዚህም የተነሳ የዱር እንስሳት ጉዳይ ሙሉ ለሙሉ ተጠቃሎ ለአካባቢ የአየር ንብረት፣ ደንና የአየር ፀባይ ለውጥ ባለሥልጣን እንዲካተት የሚያስችል የደንብ ረቂቅ ተዘጋጅቶ በሕግ አካላት እየታየ መሆኑ ታውቋል፡፡  

የአማራ ክልል የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር፣ የክልሉ 2.8 በመቶ የሚሆነውን ቦታ በጥበቃ ሥፍራ መያዝ አለበት ተብሎ፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ የተያዘውን ዕቅድ ሁለት ብሔራዊ ፓርኮችና አራት ጥብቅ ቦታዎችን በማቋቋም ተሳክቷል ብለዋል፡፡

የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፈቃዱ በየነ (ፕሮፌሰር)፣ በአገሪቱ እየተከናወነ ያለው የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ምንም እንኳን በዘመቻ ቢከናወንም ጥሩ ውጤትና ለውጥ እየታየባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህም የተገኙት ውጤቶች ገላጣ ቦታዎች ከመራቆት እንደዳኑ፣ የውኃ አካላት የማገገም ሁኔታ እንደታየባቸው፣ ይህ ዓይነቱን ኅብረተሰብ አቀፍ እንቅስቃሴ ወደ ፊት በተደራጀና በተቀናጀ አኳኋን ለማስቀጠል እንደታቀደ ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ እየሠራ መሆኑንና በቅርብ ጊዜ ተጠናቅቆ ተግባር ላይ ሲውል የተሻለ ሥራ ለመሥራት እንደሚረዳ ከኮሚሽኑ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...