Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ከፖለቲካው ባልተናነሰ የኢኮኖሚው ጉዳይ ያሳስባል!

  በአሁኑ ጊዜ ከአነስተኛ የንግድ ሥራዎች እስከ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች ድረስ ከፍተኛ የሆነ መቀዛቀዝ ይታይባቸዋል፡፡ አገር ጤና ሆኖ ውሎ ማደር ሲያቅተው እንኳን የተትረፈረፈ ምርት ይዞ ገበያ መውጣትም ሆነ መሸመት፣ በሰላም ወጥቶ መግባትም ያዳግታል፡፡ ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውሉና የኤክስፖርት ምርቶች  እንደ ልብ ገበያ ውስጥ ሳይቀርቡ፣ ከውጭ የሚገቡ መሠረታዊ አቅርቦቶችም እክል ሲገጥማቸው ሠርቶ አዳሪውንም ሆነ ሥራ ፈላጊውን ያስደነግጣል፡፡ በየቦታው ባጋጠሙ ግጭቶችና ትርምሶች ምክንያት በተፈጠሩ ሥጋቶች አምራቾች፣ አከፋፋዮች፣ ቸርቻሪዎች፣ ትራንስፖርተሮች፣ እንዲሁም አስመጪዎችና ላኪዎች ሥራዎቻቸው ተደነቃቅፈዋል፡፡ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ችግር ያጋጠመው በፀጥታ ችግር መንገዶች እየተዘጋጉ መንቀሳቀስ ባለመቻሉ ነው፡፡ ሥጋት ባለበት ሥፍራ ደግሞ ቱሪስት ድርሽ አይልም፡፡ አገልግሎት ሰጪዎችም መሥራት አይችሉም፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ከዓመት ወደ ዓመት እያሽቆለቆለ የመጣው ቀደም ሲል ቢሆንም፣ ሰላማዊ ድባብ በሌለበት ደግሞ የበለጠ እየደረቀ ነው፡፡ ለዓመታት የታፈነ ማኅበረሰብ እግረ ሙቁ ሲወልቅለት ከተለያዩ አቅጣጫዎች በርካታ ጥያቄዎችን ይዞ በመነሳቱ፣ ይህንን አጋጣሚ ለራሳቸው አጀንዳ ያደረጉት ደግሞ ለግጭት መቀስቀሻ ስለተጠቀሙበት፣ የአገር ኢኮኖሚ ከበርካታ ችግሮች ጋር ተፋጧል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ሐሳብ መለዋወጥ ይገባል፡፡

  ኢትዮጵያ አሁንም በዓለም በፍጥነት እያደጉ ካሉ አገሮች ረድፍ ስሟ ቢነሳም፣ ከዓለም ደሃ አገሮች መሀል አንዷ እንደሆነች የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት ከአሥር ሚሊዮን በላይ ወገኖች የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ይፈልጋሉ፡፡ ከእነዚህ ወገኖች መካከል ሁለት ሚሊዮን ያህሉ በተለያዩ ሥፍራዎች በተከሰቱ ግጭቶች የተፈናቀሉ ናቸው፡፡ በድህነት ምክንያት በሴፍቲኔት በምግብ ለሥራ ፕሮግራም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖች ታቅፈዋል፡፡ በገጠርና በከተማ በዓለም አቀፍና በአገር በቀል ረድኤት ድርጀቶች የምገባ ፕሮግራም ሥር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ይገኛሉ፡፡ የደሃ ደሃ ተብለው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አነስተኛ ተቆራጭ የሚደረግላቸው ሚሊዮኖችም አሉ፡፡ ሃያ አምስት ሚሊዮን ያህል ወገኖች ከድህነት ወለል በታች ይገኛሉ፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት መጠኑ በጣም ጨምሯል፡፡ በየዓመቱ ከ600 ሺሕ በላይ ወጣቶች በከተማ ሥራ ፈላጊውን ኃይል ይቀላቀላሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ግጭት ሲጨመርበት መከራው ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ለማወቅ ነብይ መሆን አያስፈልግም፡፡ ፖለቲካው ተስተካከሎ በፍጥነት ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መመለስ ካልተቻለ፣ መጪው ጊዜ ከመቼም ጊዜ በላይ ከባድ ይሆናል፡፡

  መሰንበቻውን እየተሰማ እንዳለው በኦሮሚያም ሆነ በተለያዩ አካባቢዎች ያጋጥሙ የነበሩ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ከተቻለ እርሻዎችን፣ ፋብሪካዎችን፣ ማከፋፈያዎችንና የመሳሰሉትን በሙሉ አቅም ለማንቀሳቀስ አይከብድም፡፡ ለውጭ ምንዛሪ አስተዋጽኦ ያላቸውን የእርሻና የኢንዱስትሪ ምርቶች በብዛትና በጥራት ማቅረብ ይቻላል፡፡ የተዘጋጉ መንገዶች ተከፍተው ሰዎች በነፃነት ከሥፍራ ወደ ሥፍራ ሲንቀሳቀሱ ንግድና ኢንቨስትመንት፣ እንዲሁም ቱሪዝም ይቀላጠፋሉ፡፡ ከዚህ በፊት የፖሊሲና የስትራቴጂ ችግር የነበረባቸው አሠራሮች ሲስተካከሉ፣ ብቃት ያላቸው አመራሮችና ባለሙያዎች ሲመደቡና የሠራተኞች ትጋት ሲጨምር ውጤታማነት ይገኛል፡፡ አገሪቱን ትንፋሽ ያሳጣውን ሥራ አጥነት በተጠና መንገድ ለመቅረፍ የሚያስችሉ የመፍትሔ ሐሳቦች እየመነጩ ወደ ሥራ ሲገባ፣ እንደ ተራራ የገዘፉ ችግሮች ቀስ በቀስ ይቃለላሉ፡፡ በተለይ በንግድና በኢንቨስትመንት አካባቢ የሚታዩ ችግሮች እየተፈቱ ሲሄዱ፣ የአገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ኢንቨስተሮች መተማመኛ እያገኙ በብዛት ሥራ ይጀምራሉ፡፡ የሥራ ፈጠራው ስኬት የሁሉንም ወገኖች ርብርብ ስለሚሻ፣ እግረ መንገድ የቢሮክራሲውን አፋኝ መረብ መበጣጠስ የግድ ይላል፡፡

  ለኢትዮጵያ አሁን የሚያስፈልጋት ዘመኑን የመረዳት ብቃት ነው፡፡ ዓለም በቴክኖሎጂ እየገሠገሠ በሀብት ላይ ሀብት በሚያገኝበት በዚህ ጊዜ አስተዋይነት አስፈላጊ ነው፡፡ አገር የምትከበረውና ተፈላጊነቷ የሚጨምረው ሰላም፣ ነፃነት፣ ፍትሕና እኩልነት ሲረጋገጥባት ነው፡፡ የፈለገውን ያህል ነዳጅ፣ አልማዝ፣ ዩራኒየም፣ ብርቅዬ ማዕድናትና የመሳሰሉት ቢኖሯት ሰላም ከሌላት ማንም አይፈልጋትም፡፡ የሚፈልጓት ካሉም ከጦር አበጋዞች ጋር የሚደራደሩ ኮንትሮባንዲስቶችና ወንበዴዎች ናቸው፡፡ አገር የማደግና የመመንደግ ፀጋን ማግኘት የምትችለው በዓለም ታዋቂ ከሆኑ ኢንቨስተሮች ጋር ጭምር መሥራት ሲቻል ነው፡፡ በዓለም ታዋቂ የሆኑ ኢንቨስተሮችንና የተቋማት መሪዎችን ለማግኘት ደግሞ ከፍተኛ ብልኃትና ጥረት ያስፈልጋል፡፡ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በዳቮስ የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ላይ ያገኙዋቸው ኢንቨስተሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች፣ ለኢትዮጵያ የሰጡት ተስፋ የተገኘው በቀላሉ አይደለም፡፡ ይህንን ተስፋ ወደ ተግባር ለመለወጥ ከፍተኛ ትጋት ስለሚያስፈልግ፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ መረባረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ተስፋ የተጣለበት የአገር ጉዳይ ተልከስክሶ እንዳይቀር አስፈላጊውን መስዋዕትነት መክፈል የግድ ይሆናል፡፡

  ፖለቲካውን በአግባቡ ባለማስኬድ ምክንያት በተፈጠሩ ችግሮች የደረሱ ጉዳቶች ይታወቃሉ፡፡ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል፣ በደቡብ፣ ወዘተ. ክልሎች በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት በርካቶች ተገድለዋል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል፡፡ የአገር አንጡራ ሀብት ወድሟል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ የተገኘው ትርፍ ሳይሆን ጥፋት ነው፡፡ ግጭት ባለበት እንኳን ሀብት ማፍራት በሕይወት የመኖር ጉዳይ አጠራጣሪ ነው፡፡ ከግጭት ውስጥ በፍጥነት በመውጣት ወደ መደበኛ ሕይወት መመለስ ይገባል፡፡ ለአገር የሚጠቅሙ የፖሊሲና የስትራቴጂ ጉዳዮች ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ ጥላቻና ቂም በቀል እየዘሩ አገር ማተራመስ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ቀልድና ስላቅ ላይ ተጥዶ መዋልና ማደር፣ የብሽሽቅ ፖለቲካን ሙጥኝ ብሎ መነታረክ፣ ግላዊ ጉዳይን የብሔር ታርጋ እየለጠፉ መጋጨትና ለሐሳብ ልዕልና ሥፍራ አለመስጠት ኋላ ቀርነት ነው፡፡ ሥልጣን በአቋራጭ ለማግኘት ሲባል ብቻ የንፁኃንን ሕይወት እየቀጠፉ አገር ማመሳቀል ነውርም ወንጀልም ነው፡፡ አገሩ ከሠለጠኑትና ከበለፀጉ አገሮች ተርታ እንድትሠለፍ የሚፈልግ ማንም ቅን ዜጋ፣ ከፖለቲካው ባልተናነሰ ለኢኮኖሚው ትኩረት እንዲደረግ መወትወት አለበት!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የንብረት ታክስ ጉዳይ በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ጉባዔ ቀዳሚ አጀንዳ ይሆናል ተባለ

  መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚጀምረው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን...

  በዕድሳት ምክንያት የተዘጋው የአዲስ አበባ ስታዲየም በቅርቡ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል

  የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታ በሚፈለገው ልክ እየተከናወነ እንዳልሆነ ተገልጿል ከስፖርታዊ...

  መንግሥት ለሶማሊያ የፀጥታ ኃይሎችና የመንግሥት ሠራተኞች ሥልጠና ለመስጠት ቃል ገባ

  የኢትዮጵያ መንግሥት ለጎረቤት አገር ሶማሊያ የመንግሥት ሠራተኞችና የፀጥታ አካላት...

  የኢትዮጵያ ባንኮችን የማዋሃድ አስፈላጊነት ፍንትው ያደረገው ዓመታዊው የአፍሪካ ባንኮች የደረጃ ምዘና ሪፖርት

  የአፍሪካ ባንኮችን በየዓመቱ በመመዘንና ደረጃ በመስጠት የሚታወቀው አፍሪካ ቢዝነስ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች