Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየድሬዳዋ አለመረጋጋት በፖለቲካ ኃይሎች የተቀናበረ እንደሆነ ከንቲባው አስታወቁ

የድሬዳዋ አለመረጋጋት በፖለቲካ ኃይሎች የተቀናበረ እንደሆነ ከንቲባው አስታወቁ

ቀን:

ጥር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. የጥምቀት በዓል ማግሥት በድሬዳዋ ከተማ የተፈጠረው አለመረጋጋትና ግጭት ሃይማኖታዊ ሳይሆን የፖለቲካ አጀንዳ ባላቸው ኃይሎች አማካይነት የተቀነባበረ፣ ድሬዳዋን የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ የታቀደና አስቀድሞ የተሠራ መሆኑን፣ የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ኢብራሂም ኡስማን ለሪፖርተር አስታወቁ፡፡

በድሬዳዋ ከተማ ችግር መፈጠር የጀመረው ጥር 12 ቀን 2011 ዓ.ም. የሚካኤል ታቦት ካደረበት ሥፍራ ሲመለስ ባልታወቁ ሰዎች ድንጋይ ከተወረወረ በኋላ መሆኑን፣ ከከተማው ነዋሪዎች ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ ክስተት በነጋታው በድሬዳዋ ከተፈጠረው ችግር ጋር ቀጥታ ግንኙነት የለውም ሲሉ ግን ከንቲባው ያስረዳሉ፡፡

‹‹የችግሩ መነሻ ታቦት ሲገባ የተፈጠረው ክስተት አይደለም፡፡ አስቀድሞ ከአምስት ቀናት በፊት ይህንኑ ፀብ ለማጫርና ድሬዳዋን የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ የተደረገ የዝግጅት ሥራ እንደነበረ ደርሰንበታል፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

ችግሩን የሃይማኖትና የብሔር ግጭት ለማስመሰል መሠራቱን የገለጹት ከንቲባው፣ በዚህም ምክንያት በበርካታ የንግድ ተቋማት ላይ ዘረፋ መፈጸሙን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የተወሰኑ ዘራፊዎች ግርግሩን በመጠቀም ለዘረፋ እንዲያመቻቸው ችግሩን እያባባሱት ይገኛሉ፤›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡

አመራር ይቀየርልን የሚል ጥያቄ እየተነሳ መሆኑን በመጥቀስ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹የሆነ አካል አመራሩ ይውረድ እያለ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሕጋዊ ሒደቱን ጠብቆ አመራሩ መውረድ ካለበት ይወርዳል፣ ለሕግ መቅረብ ካለበትም ይቀርባል፡፡ ነገር ግን በጉልበትና በኃይል ይህን ማድረግ አይቻልም፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ከብጥብጡ ጀርባ ያሉ ኃይሎች ማን እንደሆኑ በተመለከተ ደግሞ ሁለት አካላት መለየታቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የመጀመርያው የፖለቲካ ዓላማ ኖሮት ከዚህ ቀደም የነበረው አስተዳደር አግላይ ነው የሚል አስተሳሰብ ይዞ ለረዥም ጊዜ ሲሠራ የነበረና ውጭ አገር ድረስ ትስስር የነበሩት የመሩት እንደሆነ ዓይተናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቅርቡ ወደ አገር ውስጥ የገቡ የፖለቲካ ድርጅቶችም ይኖሩበታል ብለን እናምናለን፤›› ብለዋል፡፡

‹‹አሁን በክልሉ ከተፈጠረው ችግር ጀርባ ያለው ሁለተኛ ኃይል ደግሞ ከሶማሌ ክልል የቀድሞ አመራሮች ጋር ቀጥተኛ ትስስር ያላቸው አካላት፣ ፀብ የማጫር ድርጊት ላይ ሊሳተፉ እንደሚችሉ ገምግመናል፤›› በማለት አሁን ከተፈጠረው ብጥብጥ ጀርባ አሉ ያሉዋቸውን አካላት ገልጸዋል፡፡

በድሬዳዋ ከተማ ላለፉት ቀናት በተከሰተው አለመረጋጋት የአንድ ሕፃን ልጅ ሕይወት በተባራሪ ጥይት ማለፉን፣ 15 ሰዎች ደግሞ ቀላል የሚባል ጉዳት ደርሶባቸው ሕክምና አግኝተው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ከንቲባው ገልጸዋል፡፡

ከንብረት ጋር በተያያዘ ግን ከፍተኛ የሆነ ዘረፋ መፈጸሙን አስታውቀዋል፡፡ ዓርብ ጥር 17 ቀን 2011 ዓ.ም. የተወሰኑ ባንኮችንና የገበያ ማዕከላትን የመክበብ አዝማሚያ እንደነበርም አክለው ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ሱቆችና የግለሰብ መኖርያ ቤቶችም የዝርፊያ ሰለባ መሆናቸውን ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡

ሐሙስ ጥር 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የመከላከያ ሠራዊት ድሬዳዋ ቢገባም፣ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ መንገዶች ተዘግተው ነበር፡፡ በተፈጠረው ሁከት ምክንያት የተጠረጠሩ 84 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፖሊስ አስታውቋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ጥረት እያረጉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...