የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ)፣ በወርቅ ደረጃ ከሚመድባቸው የጎዳና ውድድሮች ዱባይ ማራቶን ይጠቀሳል፡፡ ለአሸናፊ አትሌቶች ዳጎስ ያለ የዶላር ሽልማት በማቅረብም ይታወቃል፡፡ የዘንድሮው ዱባይ ማራቶን ዓርብ ጥር 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ሲከናወን በሁለቱም ጾታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡበት ታሪካዊ ውድድር ሆኖም አልፏል፡፡ በወንዶቹ ኬንያዊው አራተኛ ሆኖ ከመግባቱ በቀር ከአንደኛ እስከ ዘጠነኛ ድረስ ያለውን ኢትዮጵያውያኑ ተቆጣጥረውታል፡፡ በሴቶች ኬንያዊቷ ቀዳሚ ብትሆንም ከሁለተኛ እስከ ስምንተኛ ተከታትለው ገብተዋል፡፡
የሽልማቱ ገንዘብ መጠን በግማሽ የመቀነሱ ጉዳይ ግን አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ለወትሮ ለአሸናፊዎች ለሁለቱም ጾታ 200,000 ዶላር በማቅረብ የሚታወቀው ዱባይ ማራቶን፣ ዘንድሮ በግማሽ ቀንሶ አንደኛ ለወጣው 100,000፣ ለሁለተኛው 80,000 የነበረውን ወደ 40,000፣ ለሦስተኛ ከ40,000 ወደ 20,000 ዝቅ ማድረጉ ታውቋል፡፡ የመወዳደሪያ ቦታው ያን ያህል አስቸጋሪ ውጣ ውረድ እንደማይበዛበት የሚታወቀው የዱባይ ማራቶን ከፍተኛ ገንዘብ በመክፈል እስከ ዓምና ድረስ ቁጥር አንድ ከፋይ ነበር፡፡ አሁን ቦስተን ማራቶን ተረክቦታል፡፡
ጌታነህ ሞላ በአንደኛነት ባጠናቀቀበት ውድድር እርሱን ጨምሮ ስምንት ኢትዮጵያውያን ደረጃ ውስጥ በመግባታቸው ለውድድሩ ከተዘጋጀው 192,500 ዶላር ውስጥ 180,000 ዶላሩን ተሸልመዋል፡፡ በሴቶችም 87,000 ዶላር ተገኝቷል፡፡ በሁለቱም ጾታዎች ካጠቃላይ 385,000 ዶላር ሽልማት 267,000 ዶላር የኢትዮጵያውያን ሆኗል፡፡
ዓርብ ማለዳ በተከናወነው የዱባይ ማራቶን በወንዶች ኢትዮጵያውያኑ ከዘጠኙ የደረጃ ሰንጠረዥ፣ ኬንያዊው ኢማኑኤል ኪፕኬምቦ አራተኛ ደረጃ ላይ ጣልቃ ከማስገባታቸው ውጪ እርስ በእርሳቸው ያደረጉት ፉክክር ሆኖ አልፏል፡፡ የውድድሩ አሸናፊ ጌታነህ ሞላ ርቀቱን 2፡03.34 በመግባት ሲያጠናቅቅ፣ በስድስት ማይክሮ ሰከንድ የዘገየው ሔርጳሳ ነጋሳ ደግሞ 2፡03.40 ጨርሶ ሁለተኛ ሆኗል፡፡ ሦስተኛ የሆነው አሰፋ መንግሥቱ በበኩሉ 2፡04.24 አጠናቆ መሆኑ ታውቋል፡፡ ሸረፋ ታምሩ 2፡05.18 አምስተኛ፣ ከልክል ገዛኸኝ 2፡06.09 ስድስተኛ፣ አዱኛ ታከለ 2፡06.32 ሰባተኛ፣ ብርሃነ ተሾመ 2፡08.20 ስምንተኛና ፍቃዱ ከበደ በ2፡09.49 በዘጠነኛነት አጠናቋል፡፡
በሴቶች መካከል በተደረገው ተመሳሳይ ውድድር ኬንያዊቷ ሩት ቹፒንጌቴግ 2፡17.08 በመግባት አሸናፊ ከመሆኗም በላይ ለከታታይ ዓመታት የበላይ የነበሩትን ኢትዮጵያውያን አቁማለች፡፡ ወርቅነሽ ደገፋ 2፡17.41 ሁለተኛ፣ ወርቅነሽ ኤዴሳ 2፡21.05 ሦስተኛ እና ዋጋነሽ መካሻ 2፡22.45 አራተኛ፣ ስንታየሁ ለወጠኝ፣ ራህማ ቱሳ፣ ሙሉሀብት ጸጋና ሱሌ ዑትራ እስከ ስምንተኛ በመሆን ተከታትለው መግባታቸው የአይኤኤኤፍ ዘገባ ያስረዳል፡፡
የዱባይ ማራቶን ሽልማት ለምን ተቀነሰ?
የዱባይ ማራቶን እስከ ዓምና ድረስ ለአሸናፊ 200,000 ዶላር በመሸለም ቀዳሚ ነበረ፡፡ ከዱባይ ቀጥሎ ከፍተኛ ክፍያ በመክፈል ይታወቁ የነበሩት ቦስተንና ኒዮርክ ማራቶኖች ሲሆኑ፣ በተለይ የቦስተን ማራቶን 150,000 ዶላር በመክፈል ይታወቃል፡፡ የመጨረሻውንና አነስተኛውን ክፍያ በመክፈል የሚታወቀው ለንደን ማራቶን 50,000 ዶላር ቢሆንም እንደ ዘርፉ ሙያተኞች ከሆነ ግን ለንደን ማራቶን ተያያዥ ሽልማቶችን ጨምሮ ተወዳዳሪዎቹ ቢያሸንፉም ባያሸንፉም መመዝገቢያ በሚል ዳጎስ ያለ ክፍተኛ ክፍያ ይከፍላል፡፡ በውድድሩ የሚሳተፉ አትሌቶች አዘጋጁ ባላቸው ወቅታዊ ብቃትና ውጤት የተመረጡ ብቻ እንደሚሆኑ፣ ዱባይ ማራቶን ግን የመወዳደር ፍላጎት ያላቸው ሁሉም የሚሳተፉበት ስለመሆኑ ጭምር ያስረዳሉ፡፡
የዓምናው የዱባይ ማራቶን አሸናፊ ኢትዮጵያዊው ሙስነት ገረመው ሲሆን፣ አትሌቱ በወቅቱ ያገኘው የገንዘብ ሽልማት 200,000 ዶላር እንደነበር አይዘነጋም፤ በሴቶችም እንደዚሁ፡፡ ይሁንና ለዘንድሮ አሸናፊዎች የቀረበው የሽልማት መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ለምን ሊቀንስ ቻለ? የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም፡፡
የዱባይ ማራቶን ውድድር ዳይሬክተር ፔተር ኮነርተን የገንዘቡ ሽልማት በግማሽ የተቀነሰው ኢንተርናሽናል ፌዴሬሽኑ የዱባይ ማራቶንን ከአዲሱ የፕላቲኒየም ደረጃ ባለማካተቱ እንደሆነ በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡
ይህንኑ አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአትሌቶች ማናጀር ለሽልማቱ መቀነስ ሰበቡ በየዓመቱ ውድድሩን የሚያሸንፉት ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን ብቻ መሆናቸው ነው፡፡
በተለያዩ መድረኮች እንደሚታየው ከረዥም ርቀት እስከ ማራቶን የበላይነቱን ይዘው የሚገኙት ምሥራቅ አፍሪካውያኑ ናቸው፡፡ በኦሊምፒክ መድረክ ከሆነ የ5,000 እና 10,000 ሜትር ውድድሮች ያጋጠማቸው መገለል ወደ ጎዳናው እንዳያመራ ሥጋታቸውንም የሚገልጹ አሉ፡፡