Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየስፖርት አካዴሚዎቹና ፌዴሬሽኖች እምን ላይ ናቸው?

የስፖርት አካዴሚዎቹና ፌዴሬሽኖች እምን ላይ ናቸው?

ቀን:

ስፖርት ፌዴሬሽኖች በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ ዕውቅና ካገኙ ማኅበራት ውሰጥ ይካተታሉ፡፡ ዕውቅና ከተሰጣቸው ወይም የኦሊምፒክ ስፖርቶች የሚባሉት ወደፊት ከሚጨመሩት አምስት ስፖርቶች ጋር 28 መድረሳቸው ይነገራል፡፡ በተለይ ኦሊምፒክ ላይ የሚካፈሉ አገሮች የሚሳተፉበት የስፖርት ዓይነቶችን በመጨመር ሲጠቀሙ ይስተዋላል፡፡ በኢትዮጵያም በስፖርት ኮሚሽን ሥር የተዋቀሩና ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው የጨመረ 27 ፌዴሬሽኖች እንዳሉ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

ፌዴሬሽኖቹ ከመንግሥት ካዝና በሚቆጠርላቸው ዓመታዊ በጀት እየተዳደሩ ይገኛሉ፡፡ ከኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ውጪ ቀሪዎቹ እምብዛም በራሳቸው ሲንቀሳቀሱ አይስተዋልም፡፡

ከጥር 7 እስከ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. በስፖርት ኮሚሽን የስፖርት ትምህርት ሥልጠናና ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት በአዳማ ከተማ በተዘጋጀው መድረክ ላይ የስፖርት ተቋማት ቁመናን አስመልክቶ ውይይት ተደርጓል፡፡ በዚሁ መድረክ የማሠልጠኛ ማዕከላት፣ አካዴሚዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡ በውይይት መድረኩ የአካዴሚዎችና የማሠልጠኛ ማዕከላት የሦስት ዓመት ሪፖርት ከመቅረቡም በተጨማሪ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ያሉበት ወቅታዊ ሁኔታ ተዳሷል፡፡ በውይይቱ ፌዴሬሽኖች አሉ ቢባልም አንዱም ፌዴሬሽን በራሱ አቅም ቆሞ ለመንቀሳቀስ ሲታትር አይስተዋልም ተብሏል፡፡

‹‹ቀደም ሲል በስፖርቱ ከመጣላት ይልቅ የቀን አበል ጉዳይና ስለ ትጥቅ የተጣሉ የጽሕፈት ቤት ኃላፊዎችን በማስታረቅ ሥራ ተጠምደናል፤›› በማለት የተናገሩት የስፖርት ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጌታቸው ባልቻ ናቸው፡፡ እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ አስተያየት ከሆነ ፌዴሬሽኖቹ ውድድር ከማሰናዳት በስተቀር ክለቦችን መሥርተውና ስፖርተኞችን ለብሔራዊ ቡደን የማፍራት፣ ባለሙያዎችን አብቅቶ ግባቸውን መወጣት ላይ ምንም እየሠሩ አይደለም፡፡

‹‹በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በመጠኑም ቢሆን የመሳተፍ ዕድል ያላቸው እግር ኳስና አትሌቲክስ፣ ከመንግሥት ዕርዳታ መላቅቅ አልቻሉም፡፡ በዚያው ልከ ውጤታቸው ተመጣጣኝ አይደልም፤›› የሚሉ አስተያየቶችም ተሰንዝረዋል፡፡

ፌዴሬሽኖች የገንዘብ አቅማቸውን አፈርጥመው፣ ዓመታዊ ዕቅዳቸውን ነድፈውና ውድድር አዘጋጅተው፣ ሥልጠና ማከናወን ይኖርባቸዋል እንጂ ከመንግሥት የማዘውተሪያ ስፍራ ግንባታንና የገንዘብ ድጋፍ ጥበቃ መላቀቅ እንደሚጠበቅባቸው የሚናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ‹‹ኮሚሽኑ ማስተባበርና ከፌዴሬሽኖች የሚነሱ የድጋፍ ጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠት ውጪ በሁሉም እንቅስቃሴ ውስጥ ጣልቃ መግባት አይኖርበትም፤›› ብለዋል፡፡

ኦሊምፒክ ኮሚቴ አራት ዓመት ጠብቆ የብሔራዊ ቡድንን ልዑካን ከመሸኘት ባሻገር ታች ወርዶ ስፖርቱ የቱ ጋ ነው ያለው ብሎ መጠየቅና መሥራት እንዳለበት ከውይይቱ የተደመጡ አስተያየቶች ያሳያሉ፡፡

መድረኩ ለስፖርቱ እንቅስቃሴ ማነቆ የሆኑትን ችግሮች በግልጽ አንስቶ ከተወያየበት በኋላ፣ ከመሠረቱ ችግሩን ለመፍታት ከፌዴሬሽን አወቃቀር ጀምሮ ጥናትን መሠረት ባደረገ መልኩ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ ጭምር ተገልጿል፡፡ ለዚህም ፌዴሬሽን ሲዋቀርና አመራሮች ሲመረጡ አግባብነት ባለው መልኩና በሙያ ብቁ የሆኑ መሆን እንዳለባቸው ተነስቷል፡፡

‹‹ምርጫ ሲደርስ በዚህም በዚያ ብሎ ለማሸነፍ ከመሯሯጥ ውጪ፣ ወደ ኃላፊነቱ ከመጡ በኋላ ቃል የገቡትን ነገር ሲተገብሩ አለመመልከት ባህል እየሆነ ከመጣ ሰነባብቷል፤›› በማለትም የችግሩን አሳሳቢነት ምክትል ኮሚሽነሩ ያስረዳሉ፡፡ በምርጫ ወቅት ተወካዮቻቸውን የመላክ ሥልጣን ያላቸው ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ቢሆኑም፣ ለስፖርቱ ይመጥናል የሚሉትን ግለሰብ ከማቅረብ ይልቅ ‹‹እከክልኝ ልከክልክ›› በሚል የቲፎዞ ሹመት ላይ መጠመዳችው ችግሩን አባብሶታል ተብሏል፡፡ ስፖርቱ የራሱን አቅም አካብቶ እንዲንቀሳቀስ ዕውቀትና ሀብት ያለው እንዲሁም የሀብት አቅም የመፍጠር ብቃት ያለው አካል እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ በተለይ በእግር ኳስ መድረኮች እየተስተዋሉ ያሉት ሁከቶችና አለመግባባቶች ከሥር መሠረቱ ለመፍታት የቤት ሥራው ከራስ መጀመር እንዳለበትና ሁሉም ስፖርት ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖረው፣ የፌዴሬሽኖች ድርሻ ጉልህ ሚና መጫወት እንዳለበት ተብራርቷል፡፡

በሌላ በኩል ኮሚሽኑ፣ ፌዴሬሽኖች፣ የክልልና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ክለቦች ወጥ የሆነ ትስስር ሊኖራቸው እንደሚገባም ተጠቅሷል፡፡

የስፖርት አካዴሚዎች ወቅታዊ አቋም

አካዴሚዎች የሁሉም ስፖርቶች መሠረት ለመሆናቸው ዓለም አቀፍ ልምዶችን መመልከት በቂ ነው፡፡ በተለያዩ ስፖርቶች አንቱታን ያተረፉ አገሮች ከዋክብትን ከአካዴሚዎች በማፍራት የራሳቸውን አሻራ ማኖር ችለዋል፡፡ ቀደም ብሎ በኢትዮጵያም ትምህርት ቤቶች፣ የሠፈር ማዘውተሪያ ሥፍራዎች እንዲሁም የዞን ውድድሮች የታዳጊ መፍለቂያዎች የነበሩ ቢሆንም፣ በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ገሽሽ መደረጋቸው አካዴሚዎችን መገንባት ብቸኛ አማራጭ ሆኗል፡፡

የወጣቶች ስፖርት አካዴሚ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ማይጨው አትሌቲክሰ ማሠልጠኛ፣ ሀገረ ሰላም፣ በቆጂ ደብረ ብርሃንና አምቦ ጎል ፕሮጀክት ጨምሮ በመንግሥት ወጪ የተገነቡ አካዴሚዎች ከዓመታት በፊት ግልጋሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡

በንድፈ ሐሳብና በተግባር ሥልጠና የሚሰጥባቸው አካዴሚዎቹ የተለያዩ ቁሳቁሶችና ባለሙያዎች ተማልቶላቸው ሥልጠናቸውን እያከናወኑ ነው፡፡ ምንም እንኳ በቂ ድጋፍና ክትትል ተደርጎላቸዋል ባይባልም፣ እንደየአቅማቸው በተለያዩ ስፖርቶች  ለብሔራዊ ቡድንና ለክለቦች አትሌቶችን ማቅረብ መጀመራቸው ይታወቃል፡፡ አትሌቶቹ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ተሳትፈውም ወርቅ፣ ብርና ነሐስ ሜዳሊያ ማምጣት ችለዋል፡፡

በ2002 ዓ.ም. የተቋቋመው የጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማዕከል በሩጫ፣ በውርወራና ዝላይ ከ250 በላይ ታዳጊዎችን በማሠልጠን ላይ ይገኛል፡፡ 200 ስፖርተኞችን  ለብሔራዊ ቡድን ማስመረጡን የሦስት ዓመት ሪፖርቱን በቀረበበት መድረክ ላይ አስረድቷል፡፡ ማይጨው 117 ስፖርተኞችን ለክለብ፣ ሀገረ ሰላም 176 አትሌቶችን ለክለብና ለብሔራዊ ቡድን፣ አምቦ ጎል ፕሮጄክት 50 እግር ኳስ ተጫዋቾችን በሁለቱም ጾታ ለክለቦች ማቅረባቸውን ሪፖርታቸው ያሳያል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዴሚም ለቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ሰባት፣ ለአዲስ አበባ ሦስት እንዲሁም ለዓለም አቀፉ ቅርጫት ኳስ ማኅበር ኤንቢኤ ዕድል ያገኙ ሠልጣኞቹን ጠቅሷል፡፡ ከዚህ ቀደም ካስመረቃቸው ሠልጣኞች በተጨማሪ በ2011 ዓ.ም. 66 ስፖርተኞችን እንደሚያስመርቅ አስታውቋል፡፡

አካዴሚዎቹ የመም (ትራክ)፣ የበጀት እጥረት፣ ከዓለም አቀፍ ስፖርት ማኅበራት ጋር ትስስር አለመፍጠር፣ የበቂ ባለሙያና የትጥቅ እጥረት ዋንኛ ችግሮች ተደርገው ተነስተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር እምቅ አቅም ያላቸውን ሥፍራዎችን የመለየት ችግር ሕገወጥ የአትሌቶች ፍልሰት፣ ተደጋጋሚ ልምምድና የውድድር ጫናን የመቋቋም አቅም ያላቸው ታዳጊዎችን ያለማግኘት ችግርን ጠቅሰዋል፡፡

ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች በጥልቀት ከተገመገሙት ጉዳዮች መካከል ዕምቅ ችሎታ ያላቸውን አካባቢዎችን ያለማገናዘብና ያለመጠቀም ችግር በስፋት እንደሚስተዋል አንስተዋል፡፡ በተለይ የአትሌቶች መፍለቂያ የሆነው የበቆጂ ስፖርት  አካዴሚ፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሥፍራዎችን በአግባቡ ያለ መጠቀም ክፍተት እንዳለ በባለሙያዎቹ ተጠቅሷል፡፡

እንደ ባለሙያዎቹ አስተያየት ከሆነ የስፖርተኞቹ የሥልጠና ቆይታ ከሁለት የኦሊምፒክ ጊዜ ማነስ እንደሌለበት፣ ዕድሜ ትኩረት እንዲሰጥበትና በሥልጠና ቆይታቸውም አካዴሚዎቹ የራሳቸውን ውድድር ማሰናዳት አንዳለባቸው ተገልጿል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ በአገሪቱ የፕሮጀክት ሥልጠና አለ ቢባልም ውድድር ሲደርስ ‹‹ሠርገኛ መጣ. . .›› ዓይነት ዝግጅት እንጂ በአግባቡ ክትትል ተደርጎበት ሲተገበር አለመስተዋሉ ፕሮጀክት አለ ለማለት አዳጋች እንደሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ በአዲሱ የመንግሥት ተቋማት ሽግሽግ ስፖርቱ ገሸሽ መደረጉ ቅሬታ ቢያስነሳም ስፖርት ኮሚሽኑ የተነሱትን ችግሮች መኖራቸውን አምኖ አዲስ የስፖርት መዋቅር ዘርግቶ መፍትሔ እንደሚያበጅ አስቀምጧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...