Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተርየአገራችን ‹‹ለውጥ›› ትርፍና ኪሳራው

የአገራችን ‹‹ለውጥ›› ትርፍና ኪሳራው

ቀን:

ለውጥ የሚለውን ቃል፣ የአንድ ኅብረተሰብ የፖለቲካ ሥርዓት ወይም የመንግሥት መዋቅር በሌላ መተካት እንደሆነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ የተዘጋጀው መዝገበ ቃላት (2000) በከፊል ይተረጉመዋል፡፡

በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፉ መዝገበ ቃላትም ቃሉ በተመሳሳይ መልኩ የመንግሥት ለውጥን በምሳሌነት በማስቀመጥ አንድን ነገር በሌላ አዲስ ወይም በተለየ ነገር የመቀየር ሒደት እንደሆነ ይገልጸውታል፡፡ ከአጠቃላይ የቃሉ አተረጓጎም አንፃር እንደምንረዳው፣ በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ ምክንያቶች የሚከሰቱ፣ በሰው ልጅ ቁጥጥር ሥር ያሉና የሌሉ ሁኔታዎች አማካይነት የሚፈጠሩ ለውጦች በሙሉ ዘርፈ ብዙ እንደሆነ ነው፡፡

ከታሪክ እንደምንገነዘበው፣ የምንኖርባት ዓለም በተለያዩ አጋጣሚዎች የተለያዩ አዎንታዊና አሉታዊ ክስተቶችን እያስተናገደች አሁን የደረሰችበት ደረጃ ደርሳለች፡፡ በመጥፎ ትዝታ ከሚታወሱት መካከል አንደኛውና ሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች በሰው ልጅ ላይ ያስከተሉት ጠባሳ ከቅርብ ጊዜው የሰው ልጅ ታሪክ ገዝፈው የሚታዩ ነው፡፡ እነዚህ ጦርነቶች ለውጥን አስከትለው አልፈዋል፡፡ ለሚሊዮኖች ዕልቂት ምክንያት ሆነዋል፡፡

- Advertisement -

የጦርነቶቹን ማብቃት ተከትሎ ቀዝቃዛው ጦርነት የተሰኘውና ዓለም በሁለት ጎራ የተከፈለችበት፣ የርዕዮተ ዓለምና የፖለቲካ ልዩነት ተፈጠረ፡፡ በአገራችን ሕዝቦች ዘንድም ቀዝቃዛው ጦርነት የፈጠረው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ተፅዕኖ እንደዚሁ ከለውጥ ክስተቶች ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡ በእርግጥ በአዎንታዊ መልኩ ስናየው፣ ዓለም የተለያዩ የሥልጣኔ ዓብዮቶችን አስተናግዳለች፡፡ ከኢንዱስትሪ ዓብዮት ጀምሮ አሁን እስካለበት የኢንፎርሜሽን ዘመን በለውጥ እየተጓዘች ነው፡፡

አገራችን ረጅም የሰው ልጅ ታሪክና ሥልጣኔ ካላቸው አገሮች አንዷ ነች፡፡ ሕዝቦቿ ያለፉባቸው የታሪክ ምዕራፎችና ያመጧቸው ለውጦች ከሌላው ዓለም ሕዝቦች ጋር የሚጋሩት በርካታ ጉዳይ መኖሩ ጥርጥር የለውም፡፡ የተጠቀሱት የዓለም ክስተቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በአገራችንም መጥፎም በጎም ለውጦች አስከትለው አልፈዋል፡፡ በፖለቲካው አቅጣጫ ስንመለከተው ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ ባላባታዊ የፊውዳል ሥርዓት፣ የደርግ፣ የኢሕአዴግ መንግሥት ላይ እስከ ሚገኘው የሪፎርሚስት አስተዳደር ድረስ ከአንዱ ከሌላው ጋር የተደረጉ ሽግግሮች ብዙ ዋጋ ያስከፈሉ የለውጥ ክስተቶች ነበሩ፡፡

ከጂኦፖለቲካው አንፃር እንደዚሁ ከተበታተነችው ኢትዮጵያ ጀምሮ ኤርትራን ጨምሮ እንደገና አንዷ ኢትዮጵያ እስከሆነችበት ያለው ሒደት ተቀይሮ ኤርትራ ያልተካተተችበት ኢትዮጵያ መመሥረቷን ስንመለከት፣ ያለፈችበት አስከፊ ገጽታ በርካታ እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን፡፡ ለውጥ የማይገታ፣ ለተከታዩም ቦታውን የሚለቅ ነው፡፡

በአሁኗ ኢትዮጵያ የመደመር፣ የፍቅርና የይቅርታ እሳቤ ወደ ተግባር ለመቀየር ከቃላት ያለፈ የፖለቲካ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለማስተናገድ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና አስተዳደራቸው የጀመሩት አዎንታዊ የለውጥ መንገድ የሚደገፍ ነው፡፡ ይህን ለማስፈጸም በአዲሱ አስተዳደር ከተወሰዱ ዕርምጃዎች መካከል በሕግ ጥላ ሥር የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ታራሚዎች እንዲፈቱ ማድረጋቸውና በተለያየ ምክንያት ከአገር የወጡና በተፃራሪው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ሊሂቃንና ድርጅቶቻቸው ያለ ቅድመ ሁኔታ አገር ቤት ገብተው በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ሲባል እንዲህ ያለውን ከባድ ውሳኔ ማሳለፋቸው፣ በተለያዩ ወገኖች ቅሬታ መፍጠሩ እንደማይቀር ሳይገነዘቡት የሚቀሩ አይመስለኝም፡፡ ለኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የተሻለ ነገር መፍጠር ያስችል ይሆናል በሚል እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡

በፖለቲካው መስክ እንደዚሁ አዲሱ አስተዳደር የአገሪቱን የፀጥታ ሁኔታ፣ የሕዝቦቿን ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር፣ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን፣ በለውጡ ዙሪያ የጋራ መግባባት ለማምጣት ጥረት እያደረገ ስለመሆኑ በፌዴራል መንግሥት ደረጃ በየጊዜው ከሚወጡ መግለጫዎች መረዳት ቢደመጥም፣ በተግባር የሚታዩ የፀጥታ መደፍረሶች፣ በደቦ ፖለቲካ ብሔር ተኮር ጥቃቶች እዚህም እዚያም እየተደጋገሙ መከሰታቸው፣ የሚፈናቀልና የሚሞት ዜጋና የሚወድም ንብረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ በመሄዱ፤ ሕዝቡ ለውጡን በጥርጣሬ ቢመለከተው ላያስገርም ይችላል፡፡ እርግጥ ነው ለውጡ በአዎንታዊ መልኩ ለማስቀጠል የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሚዲያ ተቋማት፣ በመንበረ ሥልጣን ላይ ያለው የኢሕአዴግ ድርጅት መሪዎችና አባላቶቻቸው እንደዚሁም በመንግሥት መዋቅር ያሉ ሠራተኞች፣ ከዚያም አልፎ በቅንነትና ኃላፊነት የተሞላበት የሁሉም ዜጋ የጋራ ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ዕሙን ነው፡፡

ይህም ሆኖ የፌዴራል መንግሥት በክልል መንግሥታት መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ግጭቶችን ለማስተካከልና ወደ ነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ መቸገሩን የሚያሳብቁ ሁኔታዎች የሚታዩ ይመስላሉ፡፡ እውነት እንነጋገር ከተባለ ከአሁን በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከተለያዩ ክልሎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀዬያቸው፣ አገሬ ብለው ሀብት ንብረታቸውን አፍሰው ከሚኖሩበት አካባቢ ተፈናቅለው አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ መሆናቸው በአንዳንድ አካባቢም በደቦ ፍርድ ልጇዋን ያጣች እናት፣ ወንድሟን ያጣች እህት፣ አባትም እናት ያጡ ሕፃናት፣ ያልተገባ ነገር የተፈጸመባቸው ዜጎች ሁሉ ለውጡ ምናቸው ነው፡፡

በሌላ በኩል በሕዝቦች መካከል ያለው ማኅበራዊ ትስስርስ አሁን በምን ደረጃ ላይ ነው? ወቅታዊ ጥናት የሚያስፈልገው አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፡፡ እንደሚዲያ ተቋማት የመሳሰሉት በቀላሉ ለሕዝብ ተደራሽ የሆኑ አካላት በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸው አስተዋጽኦ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መልኩ እንዴት ይገለጻል፡፡ በተለይ የሚዲያ ተቋማት ከሞራል ባሻገር ከሙያዊ ግዴታቸው አንዱና ዋናው በሕዝቦች መካከል ጥላቻንና ጥላቻ የሚወልዳቸውን ጥቃትና ዕልቂቶች ለመከላከል በእውነት በመሠራት ማኅበራዊ ትስስሩ እንዳይላላና እንዳይበጠስ መትጋት መሆን አለበት፡፡ በየዕለቱ ልዩነትን በማራገብ፣ ጥላቻን በመዝራት የሚሠሩ ከሆነ ግን፣ በሩዋንዳ፣ በምሥራቅ አውሮፓና አሁንም በመካከለኛ ምሥራቅ ሕዝቦች መካከል የተፈጠሩ ግጭቶችና እልቂቶችን አልተማርንባቸውም እንደማለት ነው፡፡ በአገራችን ‹‹ሰው ከራሱ ብልህ ከሰው ይማራል›› ይባላል፡፡ ብልኅ ሰው ከሌሎች ስህተት፣ ሞኙ ግን ከራሱ ስህተት የሚማር ነው ለማለት ነው፡፡ ለዚህ የሚበጀንን ዓይነት ምልከታ ሊኖረን ይገባል፡፡

መገናኛ ብዙኃን እንደስሙ ለብዙኃን መሆን ሲገባው ራሱን በራሱ ሳንሱር እያደረገ ማንን ያስደስታል፣ ማንን ያስከፋል በሚል እየተመረጠ ዘገባዎችን ዜናዎችን፣ ትርክቶችን የሚሠራ ከሆነ፣ ጋዜጠኛውም እንደተቋም ሳይሆን፣ እንደግለሰብ የግሉን አመለካከት የሚያንፀባርቅበት ከሆነ አሁንም ሚዲያው ከነበረበት አዙሪት አልወጣም ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማወቅ አለበት ከተባለ፣ በሻሸመኔ የተፈጸመው ሰውን ያህል ክቡር ፍጡር በጅምላ ደብድቦና ዘቅዝቆ መስቀል መግደልን የመሰለ ዘግናኝ ተግባር ፈጻሚዎች ማንነትና የፍርድ ሒደቱ መገለጽ አልነበረበትም? በአንዳንድ አካባቢዎች ወጣቶች በድንጋይ ተወግረው የተገደሉበት ኋላቀር አረመኔያዊ ተግባር ፈጻሚዎች ማንነትና የፍርድ ሒደቱ መገለጽ አልነበረበትም? በአማራ ክልል በጎንደርና በመተማ አካባቢ የተፈጸመው ሕዝቡን ያፈናቀለ የግድያ ጥቃት ዜጎች አገር ለቀው እንዲሰደዱ ያደረገና ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቀውን ‘ከኢትዮጵያዊነት ሥነ ምግባር ውጭ’ የሆነውን ተግባር ፈጻሚዎችና አስፈጻሚዎች ማንነትና የፍርድ ሒደቱስ ለሕዝብ መገለጽ አልነበረበትም? ሌሎችም ሊጠቀሱ የሚችሉ አስነዋሪ ተግባራት ፈጻሚዎች ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ በሚዲያው ሽፋን ያላገኙ ወይም በቂ ሽፋን ያላገኙ አሉ፡፡ ‹ቅኝት› መቀየር እኮ መለወጥ ሳይሆን፣ መምሰል ነው፡፡ እርግጥ ነው ከመገናኛ ብዙኃን ሚዲያዎች ፍፁምነት መጠበቅ አይቻል ይሆናል፡፡ እንኳንና እንደኛ ባላደጉ አገሮች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በጀታቸው ከመንግሥት ካዝና ወይም ከሌላ አካል የሚሰነዘርላቸው ይቅርና በዴሞክራሲ ልዕልና አላት የምትባለው አሜሪካ ሲኤንኤን በተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያዋ ጋዜጠኞች ላይ በመንግሥት እየደረሰ ያለው ጫና በዓይናችን የተመለከትነው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ሪፖርተሮች ይዋከባሉ፡፡ የሥራ ፈቃዳቸውን ይነጠቃሉ ምናልባትም ጣቢያውን በኃላፊነት በሚመሩ ላይም የበረታ ተፅዕኖ ሊኖር እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡

በኢኮኖሚያችን መስክ ዙሪያ ያለው እንደዚሁ ሲቃኝ ኢኮኖሚያችን በዕውን በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለማሳየት በአኃዝ ተደግፎ ሲነገር እንደሚደመጠው አገሪቱ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ጥቂት ምርቶች የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ከውጭ ለምታስገባው ነዳጅ ብቻ ከምታወጣው ብዙ የማይራራቅ መሆኑ፣ የዋጋ ግሽበት ወይም የገንዘብ የመግዛት አቅም ከወር ወር እያሽቆለቆለ መሄዱ ኢኮኖሚው ምን ያህል በአስከፊ ሁኔታ ላይ እንዳለ ማሳያ ነው፡፡ የነብስ አድን መድኃኒት፣ ማዳበሪያ፣ የትምህርት መሣሪያ፣ አንቡላንስ በምን ይገዛል? ግራ ያጋባል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአገሪቱ ለረዥም ጊዜ የተከማቸ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በተለይ የሥራ አጥነት ጉዳይ በቀዳሚነት የሚያሳስብ የተጠመደ ፈንጅ ነው፡፡ ስለዚህ ወጣቱ ክፍል በጠራ መልኩ የለውጥ አካል በማድረግ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ማድረግ ለነገ የማይባል መሆኑን በግልጽ የሚያሳየን እውነታ ነው፡፡ ውጤት የሚያመጡ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ብቻ የሚውሉ ተስፋዎች መመገብ ምንም ውጤት እንደማያመጣ እየታየ ነው፡፡ ስለሆነም ለአርሶ አደሩ፣ ለአርብቶ አደሩ፣ ለከተሜው፣ ለወጣቱ፣ ለሊኂቃኑ፣ ለፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን፣ የሁሉም ተሳትፎ ታክሎበት ተጠቃሚነቱን የጋራ ባደረግን ቁጥር እንደ ዜጋ ያሉንን እሴቶች ጠብቀን ልዩነታችንን ደምረን፣ ኢትዮጵያውያን ሆነን በተሠማራንበት የሥራ መስክ ሁሉ በየጊዜው ሊያጋጥሙን ለሚችሉ ችግሮች አፋጣኝ መልስ እየሰጠን፣ እየፈታን የተከፋፈለች አገር ሳትሆን አንድነትዋን የጠበቀች፣ የተዋረደችና መዘባበቻ የሆነች ሳትሆን፣ የተከበረች አገር ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ሁሉም መትጋት እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ ሰላም ለአገራችን፡፡

(ሰው አለ በእውነቱ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...