Thursday, May 30, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

በሕግ አምላክየሰብዓዊ መብትን ባህል የማድረግ አስፈላጊነትም ፈተናም

የሰብዓዊ መብትን ባህል የማድረግ አስፈላጊነትም ፈተናም

ቀን:

በውብሸት ሙላት

ሕገ መንግሥት ብዙና የተለያዩ ግብና ዓላማ አለው፡፡ ሕገ መንግሥት የቅንጦት ሰነድ አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥት የአንድን አገር ሁሉ ነገር እንዴት መከናወን እንዳለበት በጥቅልና በጥቂት ገጾች ላይ የሚያስቀምጥ የጉዞ ካርታ ዓይነት ባህርይ አለው፡፡ ግን በጥብቅ ሊከተሉት የሚገባ፣ ባጣ ቆየኝ ያልሆነ፡፡

ከሕገ መንግሥት ቁልፍ ሚና አንዱ መንግሥት (መስተዳድሩ) ተግባርና ኃላፊነቱን የሚወጣበት፣ ዜጎችም መብታቸውን የሚያስከብሩበትም ግዴታቸውን የሚወጡበትም ተቋም መፍጠር ነው፡፡ ሥልጣን እንዴትና ለምን እንደሚያዝና ወሰኑንም ያሳውቃል፡፡

- Advertisement -

ከዚህ በተጨማሪም ሕገ መንግሥት ሁሉን አቀፍ የሆኑ ዕሴቶችንም በአገር ውስጥ ሥር እንዲሰዱ ማድረግ ተቀዳሚ ፋይዳው ነው፡፡ እነዚህ ሁሉን አቀፍ የሚባሉት ወይም የሰው ልጅ መላው የሰው ልጅ ይጋራቸዋል ተብሎ የሚታሰቡት የሰብዓዊ መብት፣ የሕግ የበላይነት፣ ነፃነት፣ ፍትሕ፣ ግልጽና ተጠያቂ መንግሥታዊ አሠራር ይገኙበታል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የዚህ ጽሑፍ ጭብጥ የሆነው የሰብዓዊ መብት ነው፡፡ ከዚያም የሰብዓዊ መብትን ባህል የማድረግ ጉዳይ፡፡ የሰብዓዊ መብትን ባህል የማድረግ ምንነቱን፣ ፋይዳውን እንዲሁም እንዴት ባህል ማድረግ እንደሚቻልም መፍትሔዎችን ይጠቋቁማል፡፡

የሰብዓዊ መብት ባህል ምንነትና ፋይዳ

የሰብዓዊ መብት ባህልን (Human Rights Culture) በተሻለ ለመገንዘብ የሰብዓዊ መብትን እንደ ተፈጥሯዊ ሕግና በተፈጥሮ እንደሚገኙ መብቶች መውሰድ ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት ሰው በመሆን ብቻ የሚገኙ እንጂ በሕግ ወይም በሌላ አኳኋን የሚፈጠሩ አይደሉም፡፡ ሰው በመሆን ብቻ በተፈጥሮ የሚገኙ መብቶች ስለሆኑ ይህንን ግንዛቤ በማስፋትና ተግባራዊ ማድረግን ይመለከታል፡፡ ስለሆነም አንድ የተለየ ባህልን ማስፈን ወይም መገንባት ሳይሆን እነዚህን በተፈጥሮ የሚገኙ መብቶችን እንደ ዝቅተኛና የየትኛውም አገር መንግሥትም ሕዝብም የሚጋራቸው፣ የሚጨነቅላቸው፣ የሚያከብራቸው፣ የሚያስከብራቸው፣ የሚንከባከባቸው ማድረግን ነው የሰብዓዊ መብት ባህል የሚያመለክተው፡፡

ማይክል ጋልቺንስኪይ የተባሉ ፕሮፌሰር “The Problem with Human Rights Culture” በሚለው የምርምር ጽሑፋቸው ላይ ስለ ሰብዓዊ መብት ባህል የሚከተሉትን ቁልፍ ነጥቦች ዘርዝረዋል፡፡ ከብዙ በጥቂቱና ሳይረዝም በማሳጠር “የሰብዓዊ መብት ባህል እንደ አንድ ፕሮጀክት ብንወስደው ብዙ የሚከናውናቸው ድርጊቶች አሉት፡፡ ምሳሌ እንጥቀስ ቢባልም ኪነ ጥበቡ፣ ሥነ ጥበቡ፣ ግላዊ ዘወትራዊ ተግባራት አንኳር የሆኑ ሰብዓዊ ክብርን እኩልነትንና ነፃነትን ማንፀባረቅና በዚህ የተቃኙ ማድረግን ይይዛል፡፡

“የሰብዓዊ መብት ባህል ጥንተ ኅልውናዋን ከአሜሪካ የነፃነት አዋጅና የፈረንሳይ አብዮት በመቅዳት የሁለተኛው ዓለም ጦርነት እንዳከተመ የተባበሩት መንግሥታት ቻርተርና ሁሉን ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት መግለጫ ላይ ቅርጽ ይይዛል፡፡ ከእዚያም ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ነገር ግን ሁሉ አቀፋዊነትን ያስፋፉ ስምምነቶች በማፍራት ሒደት ላይ ነው፡፡ የሃይማኖትና የጎሳ/የብሔር ልዩነት ሳይገድበው ለሁሉ ሰው መዳረስን ቀጥሏል፡፡ የሲቪክና የሥነ ምግባር ፋይዳዎችንም በማስፋት እንደ ሌላው ሕግ ከመንግሥት ወደ ሕዝብ መምጣትን ሳይጠብቅ በማንኛውም ሰው የሚተገበር ሆኖ የአግድሞሽ ዕድገቱን ተያይዞታል፡፡ በመሆኑም የማንኛውም የሲቪክ ማኅበር፣ የሚዲያ፣ የኪነ ጥበብና ሥነ ጥበብ ባለሙያ ወዘተ የሚከውነው ነው፡፡

“እንዲህ ዓይነቱ ሥራ የአደባባይ ብሎም የማንም ሰው አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም የሥነ ማኅበረሰብ ባለሙያዎች እንደሚሉት የዘወትር ልማድ፣ ማሰብና ማሰላሰል የማይፈልግ ዓመል (habits of heart) የመሆን ጉዞ ነው፡፡”

ሰብዓዊ መብትን ባህል ለማድረግ በቅድሚያ ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅናና ጥበቃ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በዚህም በየመንግሥትን ኃይል/ጉልበት መገደብን፣ ለዴሞክራሲ መደላድል መሆን ወደ ባህልነት ለማሳደግ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ ባህል ማድረጉም የሕገ መንግሥትን ቅቡልነት መጨመርም ነው፡፡ በመሆኑም ግለሰባዊና ቡድናዊ መብቶችን ዕውን ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶችን፣ ግለሰቦችም መብቶቻቸውን ለማስከበር የመንግሥት ባለሥልጣናትና ተቋማት ላይ አቤቱታ ማቅረብን ማሳለጥ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ተግባራት አማናዊ ለማድረግ ከሕገ መንግሥቱ ያለፈ ግን ያላነሰ አካሄዶችንም ይከተላል፡፡ በመሆኑም የሰብዓዊ መብት ባህል ሕግ ከማውጣት፣ ስምምነት ከመፈረም ወዘተ የዘለለ ነው፡፡ 

እንደሚታወቀው የሰብዓዊ መብት ሁሉን አቀፍ የሆነ ሰብዓዊነትን መሠረት ያደርጋል፡፡ በሕግ ዕውቅና መስጠት ብቻ ሳይሆን ሕግን ጠምዝዞ ለግል ፍላጎት ማሳኪያ አለማድረግንም ይጠይቃል፡፡ መብቶቹም እርስ በራሳቸው የተሰናሰሉና፣ የተዛመዱ፣ አንዱ በሌላው ላይ የተንጠላጠሉ መሆናቸውም ሌላው ባህርያት ስለሆኑ፣ እንዲህ ዓይነቶቹን ባህርይና መርሖችንም ልማድ ማድረግ ነው የሰብዓዊ መብት ባህል የሚባለው፡፡

ፋይዳውም የሰብዓዊ መብት መጠበቅ ብሎም ማኅበራዊ ዳራቸው የቱንም ያህል ልዩነት ቢኖራቸውም በሰላም አብሮ መኖርን ያሳድጋል፡፡ ስለሆነም ሰላምን በማስፈን አብሮ ለመኖር ዋስትናም ይሆናል ማለት ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተንሰራፋበት አገር ሰላም ስለሚጠፋ አብሮ በአንድነት ተከባብሮ ወይም ተቻችሎ መኖርም የመራቁ ነገር ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡  ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብት መግለጫ በመግቢያው ሁለተኛው አንቀጽ ላይ የሰብዓዊ መብትን ዕውቅና በመስጠት የማስከበርን ፋይዳ ሲናገር ማንኛውም ሰው ተፈጥሯዊ የሆነውን ሰብዓዊ ክብርንና እኩልነትን ከሰውየው ሳይነጥሉ ዕውቅና መስጠት ዓለም ላይ ነፃነት፣ ፍትሕና ሰላም ይሰፍን ዘንድ ካስማ እንደሆኑ አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

ሰብዓዊ መብትን የማክበር ባህል በሌለበት፣ ሕገ መንግሥት ላይ የሰብዓዊ መብቶችን ዕውቅና የሚሰጥ ጥበቃ አደርጋለሁ ብሎ የሚምል የሚገዘት አንቀጽ ቢደረደር ፋይዳቢስ ሰነድ ከመሆን የዘለለ እርባና አይኖረውም፡፡ የባለሥልጣናት ውሳኔዎች ቅኝታቸው መብትን ማጣበብና ማኮስመን ሳይሆን ማስፋፋትና ማፋፋት፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ጉልህ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ሰዎችም መብትን የማክበር፣ የመብት ጥሰትን የመከላከልና ተጎጅዎችን የማገዝ ልማዳቸው ዘወትር የሚተገብሩት ባህላቸው ማድረግ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ መብትን አስቀዳሚ አካሄድ ተመልሶም የባህልነት ሒደቱን ያጠናክረዋል፡፡

ባህል ለማድረግ ከተግዳሮቶቹ በጥቂቱ

የሰብዓዊ መብትን ባህል ማድረግ ከብዙ ፈተናና ተግዳሮቶች የፀዳ አይደለም፡፡ በተለያየ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መሥፈርትና መሠረት በሌሎች ቡድኖች ውሳኔ ሰጭነት መብታቸውን ለማስከበር የሚያዳግታቸው አናሳ ቡድኖች በልዩነትና በድጋፍ መልክ መብታቸው እንዲከበር መፈላጋቸው ከእኩልነት ጋር በተቃርኖ ይቆማል፡፡ ሁለቱን ማጣጣም ራሱን የቻለ ተግዳሮት ይሆናል፡፡

የሴቶች በቤተሰብ ውስጥ የእኩልነት ጥያቄ በብዙ ማኅበረሰብ ዘንድ አሁንም ራስ ምታት እንደሆነ ነው፡፡ በእኛ አገርም ይኼው የቤተሰብ ሕግ ማውጣት ያቃታቸው ክልሎች አሉ፡፡ ጋምቤላ፣ ሶማሊያ፣ ሐረርና አፋር እስካሁን አላወጡም፡፡ በጋብቻ ውስጥ የባልና ሚስት እኩልነትን የማረጋገጥ ፈተና መሆኑ ነው፡፡

ያለፉ የሰብዓዊ ጥሰቶችን ለማስተካከል ጥረት ሲደረግም እንዲሁ ሌላ ተግዳሮት አለው፡፡ ብዙ ብሔረሰቦች በሚገኙበት ደግሞ የሥልጣን ክፍፍል ከእኩልነትም ከውክልናም ጋር ስለሚያያዝ  እንዲሁም ብቃትና ችሎታም አስፈላጊ በመሆኑ ሌላ ተግዳሮት ነው፡፡

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ግዴታዎችን ከአገር ቤት ሕግጋት ጋር ለማጣጣም በሚደረግ ጥረትም በማኅበረሰቡ ዘንድ ጸንቶ ከኖረው ልማዳዊና ሃይማኖታዊ ድርጊቶች ጋር የሚላተምበት ሁኔታ ሲኖር የማስታረቁ ነገር ፈተና ነው፡፡ ለምሳሌ ጋብቻን ብንወስድ እስከ ሰባት ሚስት ማግባት የሚፈቅድ ባህል ያለው ብሔር የሰብዓዊ መብትን ባህሉ ማደረግ ያዳግተዋል፡፡ ሕግ ተምሮ፣ ዳኛ ወይም ዓቃቤ ሕግ ሆኖ ከአንድ በላይ ሚስት ያገባ፣ ከሕጉ ይልቅ የብሔረሰቡን (የጎሳውን)፣ የሃይማኖቱን ደንብና ልማድ በሰበብነት የሚጠቀሙ ሰዎች በአገራችንም ጭምር አሉ፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣንም ሆነው እንዲሁ አሉ፡፡ (ጸሐፊው በግል የሚያውቃቸውም ጭምር!)

እንዴት ባህል ማድረግ ይቻላል?

ሰብዓዊ መብትን ማክበርና ማስከበር የማንኛውም ሰው የዘወትር ልማዱ እንዲሆኑ ከመንግሥትም ከግለሰቦችም የሚጠበቁ ቁልፍ ጉዳዮች አሉ፡፡ በተለይ ከመንግሥት በኩል መንግሥታዊ ጉልበትና ሥልጣኑን የሚገሩ ሕግጋትን ሥራ ላይ ማዋል፡፡ በኢትዮጵያ በቅድሚያ ያለፉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጉዳይ መዝጋት ያስፈልጋል፡፡ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት፣ በተለይም ደግሞ ቀረብ ባሉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ የተፈጸሙት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ያደረውን ዕዳ በመዝጋት ሀ ብሎ ከእንደገና የሰብዓዊ መብትን ጉዳይ መጀመር ያስፈልጋል፡፡ በዕርቀ ሰላም የሚቋጨውን በዕርቀ ሰላም፣ በፍርድ ቤት ዕልባት የሚሰጣቸውንም እንዲሁ በመለየት አዲስ ምዕራፍ መጀመር ነው፡፡

ሌላው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችን በመፈረም መቀበልና ተግባራዊ ለመድረግም መጣር ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ አይደለም ሰብዓዊ መብት የመከበር ጉዳይ ወደ ባህልነት ለማደግ ጉዞ መጀመር ቀርቶበት ሕግና መብትን እንዲያስከብር የተፈጠረው መንግሥት ራሱ ሕግና መብትን በመጣስ ከመሰማራት እንዲቆጠብ የሚያስገድደው ነገር ጠፍቶ ነበር፡፡ የመንግሥትን ባህርይ ለመግራት የሚያስችሉ አሠራሮችን መከተል የባለሥልጣናትን ማናለብኝነት ለማስቀረት ይረዳል፡፡

ከእነዚህ ውስጥም የሰብዓዊ መብትን ለማስከበር የሚረዱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና ሌሎች አማራጭ ፕሮቶኮሎችን ማፅደቅንም ያካትታል፡፡ ለምሳሌ ያህል ማሰቃየትን የሚከለክለውን እ.ኤ.አ. የ1984ቱን ዓለም አቀፍ ስምምነት (Convention Against Torture,  and Other Cruel, Inhuman and Degrading Treatment and Punishment/CAT)፣ ግለሰቦች መብታቸው በተጣሰና በአገር ውስጥ ፍትሕ የማግኘት መብታቸው በሚጣስበትና ዕድሉን በሚነፈጉበት ጊዜ ወደ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ፍርድ ቤቶች መሄድን የሚፈቅዱ አማራጭ ፕሮቶኮሎችን (Optional Protocols) መፈረም አንዱ ነው፡፡

የ1984ቱን ማሰቃየትን ለማስቆም የወጣውን ዓለም አቀፍ ስምምነት የፈረሙ አገሮች በርካታ ግዴታዎች አሉባቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ዋነኛው እስረኞችን ስቃይ እንዳይደርስባቸው ለማድረግ የሚያግዝና አሰቃዮችን የሚቀጣ ብሔራዊ ሕግ ማውጣት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ራሱን የቻለ የፀረ ማሰቃየት ሕግ የላትም፡፡ በሕገ መንግሥቱም ላይ በግልጽ ማሰቃየትን የሚከለክል አንቀጽ የለም፡፡ ማንኛውም የማሠቃየት ተግባር ኢሰብዓዊ፣ ጭካኔ የተሞላበትና ክብርን የሚያዋርድ በመሆኑ፣ በአንቀጽ 18 ንዑስ ቁጥር 1 ላይ ዕውቅና ተሰጥቶታል ማለት ቢቻልም፣ ማሰቃየትን ልዩ የሚደርጉት ነጥቦች ስላሉ እንዲሁም የተጠያቂዎቹን ኃላፊነት በግለሰብ ደረጃ ብቻ ስለሚያስቀረው ተጨማሪ ሕግ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም ይህ አንቀጽ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡

በአገር ደረጃ ማሰቃየት እንዳይኖር የሚከታተል ኮሚቴ የማቋቋም እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ሥር የሚገኝ የፀረ የማሰቃየት ኮሜቴ እስር ቤቶችን በመጎብኘት ማሰቃየት መኖር ወይም አለመኖሩን እንዲመረምር ሥልጣን የሚያሰጠውን አማራጭ የፀረ ማሠቃየት ፕሮቶኮልም ለመፈረም አልፈለገችም፡፡

በሽግግር መንግሥቱ ዘመን (በ1984 ዓ.ም.) የተቀበልነውን የፀረ ማሰቃየት ስምምነት በመከተል በአገር ደረጃ ሕግ ማውጣት ይጠበቅ ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነት ሕግ መኖሩ መንግሥት በተለያዩ ተቋማቱ አማካይነት ዜጎች ላይ የሚያደርሳቸውን ጥቃቶች እንዲቀንስ በማድረግ ረገድ አጋዥ ነው፡፡ ዜጎችና ድርጅቶች በሽብር ድርጊት መንግሥት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ፣ ካደረሱም ለመቅጣት ሲባል የፀረ ሽብር ሕግ እንዳለውና እንደሚኖረው ሁሉ በተቃራኒው ለሚደርሱት ደግሞ የፀረ ማሰቃየት ሕግ ይኖር ዘንድ ግድ ነው፡፡

ማሰቃየትን በፍጹም የሚቃወም፣ እንዳይፈጸም የሚተጋና ባህሉ ያደረገ መንግሥት መሆን ይቅርና ከማሰቃየት ልማዱ ቢወጣ በራሱ ትልቅ ውጤት ነው፡፡ ነገሩ “ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነኝ” የሚለውን ብሂል ይመስላል፡፡ የሆነ ሆኖ የማያሰቃይ (ቶርቸር የማያደርግ) ብሎም የፀረ ማሰቃየት ልማድ ማሳደግ ተገቢ ነው፡፡ 

ከማሰቃየት ባለፈ የኢትዮጵያ መንግሥት በከፋ ሁኔታ ከሚተችባቸው ድርጊቶቹ መካከል አስገድዶ ስወራ አንዱ ነው፡፡ ዜጋን አስገድዶ ከሚሰውር መንግሥት ለመዳን አንዱ ዕርምጃ ሁሉንም ሰው ከአስገድዶ ስወራ ለመጠበቅ የወጣው ዓለም አቀፍ ስምምነትንም (International Convention for the Protection of All Persons from Enforced Disappearance)  መፈረምና ማፅደቅ ነው፡፡  ይህ ስምምነት እ.ኤ.አ. ከታኅሳስ 2010 ላይ ሥራ ላይ ውሏል አስገዳጅም ሆኗል፡፡ አሁን ላይ 58 አገሮችም አፅድቀውታል፡፡ 97 አገሮች ደግሞ ፈርመዋል፡፡ ኢትዮጵያ ተቀብላ አላፀደቀችውም፤ ፈራሚም አይደለች፡፡

ስምምነቱ አስገድዶ መሰወርን በሰብዕና ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች (Crimes against humanity) አንዱ እንደሆነ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ የተሰወረው ሰው ቤተሰቦች ከመንግሥት ካሳ የመጠየቅ መብት እንዳለቸው አረጋግጧል፡፡ ከገንዝብ ካሳ በተጨማሪ የተሰወረው ሰው ቤተሰቦችን እንዲያገግሙና የሞራልና የመንፈስ ተሃድሶ እንዲያደርጉ ማመቻቸት፣ ክብራቸው እንዲመለስ ማድረግ፣ ተጨማሪ ስወራ በቤተሰባቸው ላይ እንዳይከሰት ዋስትና መስጠትን ይዟል፡፡  

አስገድዶ የመሰወር ወንጀል በሰብዕና ላይ ከሚፈጸሙ ምሕረትም ይቅርታም ከማያሰጡ አሰቃቂ ወንጀሎች አንዱ መሆኑን ሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ ከዚህ ሌላም ኢትዮጵያ ተቀብላ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችም ላይ በሰብዕና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ምሕረትና ይቅርታ እንደሌላቸው ብሎም በይርጋ እንደማይታገዱ ይገልጻሉ፣ እነዚህን አፅድቃለች፡፡

ኢትዮጵያ በሰብዕና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመዳኘት፣ ወንጀለኞችን ለፍትሕ ለማቅረብ የተቋቋመውን ዓለም አቀፉን የወንጀል ፍርድ ቤት (International Criminal Court) ማቋቋሚያ አልተቀበለችም፣ አልፈረመችምም፡፡ እንደውም ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ፈራሚ እንዳይሆኑም ስትሠራ የነበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ፍርድ ቤቱ አፍሪካን ለመጉዳትና ዘረኛም ነው የሚል ነው፡፡ በሰብዕና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን እንደማይፈጽም የሚተማመን መንግሥት የፍርድ ቤቱ ዘረኝነት አያሳስበውም፡፡ ወንጀሉን ካልፈጸመ ቀድሞውን ስለማይከሰስ፡፡

ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት መመሥረቻንም ሆነ አስገድዶ መሰወርን ለመከላከል ሲባል የወጣውን ዓለም አቀፍ ስምምነት አልተቀበለችም፡፡ ሰዎችን ከአስገድዶ መሰወር ሊታደግ የሚችል፣ ከተፈጸመም ሰዋሪዎቹን ለፍትሕ ለማቀርብ የሚያስችል፣ የተጎጂ ቤተሰቦችንም ካሳና ሌሎች መሰል መፍትሔዎችን የሚሰጥ የሕግ ማዕቀፍም የላትም፡፡  አሁን በሥራ ላይ ያለውን የወንጀል ሕግ በምንፈትሽበት ጊዜ ራሱን ችሎ አስገድዶ መሰወርን ወንጀል የሚያደርግ አንቀጽ አናገኝም፡፡ አስገድዶ የመሰወር ወንጀል ተፈጽሟል ለማለት የመንግሥት ትብብር መኖር አንዱ መሥፈርት ነው፡፡  ስለሆነም የመሰወር ፍላጎት የሌለው መንግሥት ሰውን ከአስገድዶ መሰወር ለመጠበቅ ዝርዝር ሕግ ያወጣ ነበር፡፡ ዓለም አቀፍ ስምምነቶቹንም ለመቀበል ሰበብ አስባብ አይደረድርም ነበር፡፡

ከላይ ከቀረቡት ባለፈም ኢትዮጵያ መፈረም የማትፈልጋቸው የሰብዓዊ መብት ሰነዶች አሉ፡፡ ከዋናው የሰብዓዊ መብት ስምምነት በተቀጽላነት የሚወጡ አማራጭ ፕሮቶኮሎች አልፎ አልፎ አለ፡፡ ለምሳሌ የዓለም አቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነትን ሁለት አማራጭ ፕሮቶኮሎች ያሉት ሲሆን፣ የመጀመሪያው ግለሰቦች (ዜጎች) የሰብዓዊ መብታቸው ተጥሶ በአገር ውስጥ መፍትሔ ለማገኘት አማራጮች ሁሉ ከጠፉ ለዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት አቤቱታቸውን የሚያቀርቡበትን አሠራር አገሮች እንዲቀበሉ የሚጠይቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነቱን ፕሮቶኮል ለመፈረም አዝማሚያ አሳይታ አታውቅም፡፡ ይህ ደግሞ “መብቶቹን ብጥስም እኔው ዳኝነት የመስጠት ብቃትና አቅም አለኝ” የሚል የተዓብዮ ምላሽ ነው መንግሥታዊ ምክንያቷ፡፡ ምክንያቱ ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ላለመጋለጥ ይመስላል፡፡

ከዓለም አቀፍ ስምምነቶቹ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በርካታ ሕግጋትን (አንዳንዶቹ የተወሰኑ አንቀጾችን ብቻ) ማሻሻልና አዳዲስ ሕጎችንም ማውጣት ይጠበቅባታል፡፡ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ለማክበርም፣ ለማስከበርም እንዲሁም ለማሟላት አስፈላጊ የሆኑ አሉ፡፡ የተወሰኑ ክልሎች የቤተሰብ ሕጋቸው በ1952 ዓ.ም. የወጣው የፍትሐ ብሔር ሕግ ነው፡፡ የመንግሥታዊ አስተዳደራዊ ሥርዓትን የሚገልጽ ሕግ የለም፡፡ የማስረጃ ሕጉ ጎዶሎ ነው፡፡ ብዙ ምሳሌ መዘርዘር ይቻላል፡፡ መሻሻል ያለባቸውንም ጭምር፡፡

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት በነፃነትና በገለልተኝነትን የመቋቋማቸው መነሻ የሆኑትን ምክንያቶች ማሳካት አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 210/1992 አንቀጽ 5 ላይ እንደተገለጸው ሦስት ዋና ዓላማዎችን እንዲያሳካ የተመሠረተ ተቋም ነው፡፡ እነዚህም ስለሰብዓዊ መብቶች ግንዛቤ እንዲጨምር ማስተማር፣ መብቶቹ እንዳይጣሱ መጠበቅና ሳይሸራረፉ እንዲተገበሩ ማድረግ፣ እንዲሁም ተጥሰው ሲገኙ አስፈላጊውን የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ናቸው፡፡ እነዚህን ዓላማዎች ለማሳከት የሚደረገው ጥረት ሰብዓዊ መብትን ባህል የማድረግ ጉዞ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በኦፊሴልና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያስተዋወቀችው የሰብዓዊ መብትን ለማስከበር ድርጊት መርሃ ግብር ነድፋ ነበር፡፡ አንደኛው መርሃ ግብር ዘመኑ ተቋጭቶ ሁለተኛውም እየተገባደደ ነው፡፡ እንደ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሆኑ ነው፡፡ የአንደኛው መጠናቀቅም የሁለተኛውም መኖር በኅብረተሰቡ ዘንድ የመታወቁ ነገር አጠራጣሪ ነው፡፡ እንደውም እነዚህ የድርጊት መርሃ ግብሮች ከፀደቁ በኋላ የነበረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የባሳ ነበር፡፡ አይደለም በተሻለ መልኩ ሰብዓዊ መብት ተክብሮ ወደ ባህልነት ጉዞ ሊጀምር ቀርቶ፡፡

መንግሥት ዋነኛ ስቃይ (ቶርቸር) ፈጻሚነቱን ገፋበት፡፡ ሕግና ሥርዓትን ማስጠበቅ ተስኖትም በአገሪቱ ተዘዋውሮ የመሥራት፣ መብት ባለፉት ሁለት ዓመታትን ያህል እክል ገጥሞት አያውቅም፡፡ በተፈናቃይ ብዛት ከቀዳሚዎቹ አገሮች ተርታ ተሰለፈች በሁለተኛው የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር ዘመን፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹንና ሌሎቹንም የሰብዓዊ መብቶችን በነፃነትና በገለልተኝነት የሚያስጠብቁም የሚቆጣጠሩም ተቋማት መኖር አስፈላጊ ነው፡፡ ስለሆነም የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት ገና እንደ አዲስ የመወለድ ያህል ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የፍርድ ቤቶችና የሌሎች የፍትሕና የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲሁ! ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ የሲቪክና የበጎ አድራጎት ማኅበራት ሰብዓዊ መብት ላይ እንዳይሠሩ መከልከል በሁሉ አስቀድሞ የሰብዓዊ መብትን ዓለም አቀፋዊነት መካድ ነው፡፡ አይደለም ባህል ማድረግ ይቀርና መብት ከመጣስ ልማድ ለማቆም አለመፈልግን ያሳያል፡፡

አንድን ነገር ልማድ ማድረግ ከባድ ቢሆንም ልማድነት ደረጃ ላይ ከደረሰ ልማዱ በጎም ይሁን መጥፎ ማስወገድ ከባድ ነው፡፡ የሰብዓዊ መብትን ባህል ማድረግ ለኢትዮጵያ ፈታኝና አስቸጋሪ ቢሆንም ወደ ባህልነት ወይም ልማድነት ያደገ ነገርን ለማስቀረት (ለመመለስ) የሚኖረውን ፈተና ከከበደ ሚካኤል የቅጣት ማዕበል ተውኔት ላይ ከልሌና በላይ የተባሉ ገጸ ባህርያት የሚያደርጉትን ቃለ ተውኔታዊ ምልልስ ጥቂት በመጥቀስ ይህን ጽሁፍ እንቋጭ፡፡

ከልሌ፡    የተማረ ሲሆን የሰው ልጅ ኅሊና፣

የሚሻሻል መስሎህ አትውደቅ ከስህተት፣

      መማር አለመማር ዋጋቢስ ነው ዕውቀት፣

በላይ፡    ልዩ ነው ማለት ነው የትምህርት ፈንታው፣

ከልሌ፡   ልማድ ያሰረውን ዕውቀትም አይፈታው፣

በላይ፡    ምን ያህል ብርቱ ነው ኃይለኛ ጠንካራ፣

ከልሌ፡    ልማድ የሁሉ ምንጭ ያሳር የመከራ፡፡

በላይ፡    ታዲያ ሰው መቼ ነው ከልማድ የሚድን?

ከልሌ፡    በልማድ ወፍሮ ሰብቶ ሲደነድን፣

   ሥር እየሰደደ የያዘው በሽታ፣

   ተገዥ ይሆናል በመታገል ፈንታ፡፡

   ቂሙ አይነቀል መርዙ የማይጠፋ፣

   ምን ነገር ይገኛል ከልማድ የከፋ፡፡

ከምልልሱ ማሠሪያ እንደምንረዳው ልማድ ክፉ ነው፡፡ አይለቅም፡፡ በጎ ነገርም ልማድ ከሆነ እንዲሁ ነው፡፡ የመንግሥት የሰብዓዊ መብት የመጣስ ልማድ አስቀርቶ ማክበርና ማስከበርን ልማድ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...