Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመቀሌ ነጋዴዎች ይጠይቃሉ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የውጭ ባለሀብቶች ‹‹ከልብስ ሰፊነት የዘለለ ሚና›› አልተወጡም

በክልል ደረጃ የሚካሄዱ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የጋራ የምክክር መድረኮች በቋሚነት የሚካሄዱት የየክልሎቹ መስተዳድሮች የክልሉ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ጋር ባደረጉት ስምምነት መሠረት ነው፡፡

በዚሁ መሠረት ባለፈው ሳምንት የትግራይ ክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ ከዓመታት በፊት ከክልሉ አስተዳደር ጋር ባደረው ስምምነት መሠረት በየስድስት ወሩ ከሚያካሂደው የምክክር የጋራ መድረክ የ2011 ዓ.ም. የመጀመርያ ፕሮግራም ባለፈው ሳምንት በመቀሌ ማካሄዱ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትና የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ ገብረ ሥላሴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዚህ የምክክር መድረክ ላይ በክልሉ የሚገኙ የንግዱ ኅብረተሰብ ያሉበት ችግሮች ቀርበውበታል፡፡

የምክክር መድረኩ ከመካሄዱ በፊት ንግድ ምክር ቤቱና የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ በጋራ የመወያያ አጀንዳዎችን ቀርፀው ነበር፡፡ ከ42 ወረዳዎች የተሰባሰቡ የነጋዴው ችግሮች ለውይይት ቀርበው ነበር፡፡ እንደ አቶ አሰፋ ገለጻ፣ ከ42 ወረዳዎች የተሰባሰቡት አንኳር ችግሮች በ87 ዋና ዋና ጉዳዮች ተከፍለው የቀረቡ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በንግድና በኢንቨስትመንት ዙሪያ አሉ የተባሉ ችግሮች በዝርዝር ቀርበውበታል፡፡

በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የንግድ፣ የኢንዱስትሪና የከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊው አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) እና በክልሉ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በተመራው በዚህ ውይይት ወቅት ከተነሱ ጥያቄዎች ውስጥ አንዳንዶቹን አቶ አሰፋ ከሰጡት ማብራሪያ ጋር በማዋዛት እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

ወርቅና ኮንትሮባንድ

በባህላዊ መንገድ ወርቅ ከሚመረትባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች አንዱ ትግራይ ነው፡፡ በክልሉ የሚመረተው ወርቅ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይቀርባል ያሉት አቶ አሰፋ፣ አቅርቦቱ ግን በየጊዜው እየቀነሰ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ ባጣራው መሠረትም ከክልሉ ለብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው ወርቅ አሽቆልቁሏል፡፡

ባህላዊ ወርቅ አምራቾች ምርቱ የቀነሰበትን ምክንያትና አሉብን ያሏቸው ችግሮች በውይይቱ ወቅት ማቅረባቸው ታውቋል፡፡ ለውይይት የቀረበው የጥናት ሰነድ ውስጥ ከአራት ዓመታት በፊት ከትግራይ ክልል ብቻ በዓመት 20 ኩንታል ወርቅ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይቀርብ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ከክልሉ የሚቀርበው መጠን ወደ ሁለት ኩንታል አዘቅዝቋል፡፡ ይህም የሆነው ከባህላዊ ወርቅ ግብይትና አሠራር ጋር በተያያዘ ከጉምሩክ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሳቢያ ወደ ማዕከል ገበያ የሚቀርበው ወርቅ እንዲቀንስ ስላስገደደ ነው፡፡ በመሆኑም የወርቅ የኮንትሮባንድ ንግድ እንዲስፋፋ፣ በሕጋዊ መንገድ ይደረግ የነበረውን ግብይትም እንዲቀዛቀዝ አድርጎታል፡፡

ስለዚህ ማብራሪያ የሰጡት አቶ አሰፋ፣ የወርቅ ግብይቱ በዚህ ደረጃ ማሽቆልቆሉ አምራቾች እንዲከፍሉ የሚጠየቁት ግብር ጋር ያልተጣጣመና ከሚሸጡት በላይ ግብር ክፈሉ በመባላቸው ሳቢያ፣ መደበኛውን የግብይት ሥርዓት ጎድቶታል ይላሉ፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ይረዳ ዘንድ ከጉምሩክ ኃላፊዎች በመነጋገር ጉዳዩ ታይቶ መፍትሔ ይሰጠዋል ማለታቸውም ተሰምቷል፡፡ ይህም ይባል እንጂ ሕጋዊ የወርቅ ግብይት እየተጎዳና የኮንትሮባንድ ንግዱም እየተስፋፋ መምጣቱ እንደሚያሳስብ አቶ አሰፋ ገልጸዋል፡፡

የኃይል አቅርቦት

በየስብሰባዎቹ በነጋዴው ከሚቀርቡ ጥያቄዎች፣ ምሬቶችና ትችቶች መካከል  በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ላይ የሚነሳው አንደኛውና ዋነኛው ነው፡፡ በመቀሌው ውይይትም ይኸው ችግር ቀርቧል፡፡

የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ፣ ግንባታቸው ለተጠናቀቁ ማምረቻዎችና ኢንዱስትሪዎች ኃይል አለመልቀቅ ሲነሱ ከነበሩት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ ትራንስፎርመር ለማግኘት ሁለት ዓመት ለመጠበቅ መገደድም ከችግሮቹ መካከል ሲደመጥ የነበረው ነው፡፡

‹‹ባለሀብት መሬት ይወስዳል፡፡ ከባንክ ይበደራል፡፡ ትራንስፎርመር ሲጠብቅ ሁለት ዓመታት ሳይሠራ ይቀመጣል፡፡ ስለዚህ ሳያመርት ዕዳ መክፈል ይጀምራል፤›› ለሚለው ጥያቄ፣ በዕለቱ የተገኙት የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ተወካይ የተሰጠው ማሻሻያ እንደሚደረግና የተንዛዙ ጉዳዮች በቶሎ እንዲቋጩ ቃል ተገብቶ ነበር፡፡

ደረቅ ወደብ

በትግራይ ክልል ደረቅ ወደብ ለምን እንዳልተገነባ ጥያቄ ቀርቧል፡፡ የክልሉ መንግሥት ለደረቅ ወደብ መገንቢያ 42 ሔክታር መሬት ቢያዘጋጅም፣ ግንባታው እስካሁን አልተካሄደም፡፡ ወደ ክልሉ የሚገባው ዕቃ የሚስተናገደው ለደረቅ ወደብ በተዘጋጀው ቦታ ላይ ነው፡፡ ምንም መሠረተ ልማት በሌለበት ማለት ነው፡፡

አቶ አሰፋ እንደገለጹት ለደረቅ ወደብ አገልግሎት የተከለለ ቦታ ላይ አገልግሎት እየሰጠ ያለው አሮጌ ክሬን ብቻ በመሆኑም፣ በሌሎች አካባቢዎች እንደተገነቡት ደረቅ ወደቦች በመቀሌም እንዲገነባ ቢደረግና መሣሪያዎች ተሟልተውለት እንዲሠራ ቢደረግ የሚታየውን የሎጂስቲክስ ችግር ለመቅረፍ በመጠኑ ያግዝ ነበር፡፡

እንደ አቶ አሰፋ ገለጻ፣ የደረቅ ወደብ ግንባታው አለመጠናቀቁ የወጪና ገቢ ዕቃዎች ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው፡፡ ግንባታው እንዲካሄድ በተደጋጋሚ ለቀረበው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ እንዳልተገኘም ጠቅሰዋል፡፡ ለደረቅ ወደብ ግንባታ በተዘጋጀው ቦታ ላይ በወር እስከ ሁለት መቶ ያህል የወጪና ገቢ ንግድ ምርቶችን ያጨቁ ኮንቴይነሮች ይስተናገዳሉ፡፡

የኢትዮ ኤርትራ ድንበር መዘጋት

ኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላም ስምምነት ከፈረሙና ግንኙነት ከጀመሩ በኋላ የዛላምበሳ ድንበር ተከፍቶ የሰዎች፣ የተሽከርካሪዎችና የሸቀጦች እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር፡፡ ካለፈው ወር ጀምሮ ግን ድንበሩ ዳግም ተዘግቷል፡፡ ነጋዴዎች ይህንን ጉዳይ አንስተው እንደሆነ አቶ አሰፋ ተጠይቀው በመድረኩ መወያያ ጉዳይ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ የዛላምበሳ ድንበር ለምን ተዘጋ? የሚለውን ጥያቄና ምላሹን በተመለከተ አቶ አሰፋ ሲናገሩ ድንበሩ በቅርቡ እንደሚከፈት ገልጸዋል፡፡

የዛላምበሳና የራማ ድንበር የተዘጋው በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥና እንቅስቃሴ ሕጋዊ መስመር ለማስያዝ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ ድንበሩን በመክፈት ሕጋዊ እንቅስቃሴ እንዲፈጠር በሁሉም መንግሥታት ተመክሮበት ወደ መጨረሻው ምዕራፍ በመቃረቡ በቅርቡ ድንበሮቹ ይከፈታሉ ተብሏል፡፡

የኢንቨስትመንት መሬት

ለኢንቨስትመንት ከተሰጡ ቦታዎች አንዳንዶቹ ምንም ሳይሠራባቸው ታጥረው የመቀመጣቸው ጉዳይም በስብሰባው የተነሳ ጉዳይ እንደነበር ከአቶ አሰፋ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

 መሬት አጥረው ባስቀመጡት ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸውም ሐሳብ ቀርቧል፡፡ ከዚህም በኋላም ለትክክለኛው ዓላማ መሬቱ መሰጠት እንዳለበት ማሳሰቢያ ቀርቧል፡፡ ‹‹የመሬት ፍላጎት በጣም እየሰፋ መጥቷል፡፡ በተለይ ለኢንዱስትሪ የሚጠየቀው እየጨመረ ነው፤›› ያሉት አቶ አሰፋ፣ መሬት ወስደው ያለሙ በርካቶች ቢኖሩም አጥረው ያስቀመጡት ላይ ግን ዕርምጃ መውሰድ እንደሚጀመር ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል፡፡  

የውጭ ኢንቨስትመንት

  ከነጋዴው ጋር ከተካሄደው ውይይት ባሻገር በክልሉ ኢንዱስትሪዎችን የሚያንቀሳቅሱ ባለሀብቶች የተሳተፉበት ሌላ መድረክ መካሄዱን ያስታወሱት አቶ አሰፋ፣ ትልልቅ ከሚባሉ የኢንዱስትሪ አንቀሳቃሾች ጋር የተደረገው ውይይት በዋነኛነት ከአገር በቀል ተቋማት ጋር ያላቸውን የገበያ ትስስር የዳሰሰ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

 የከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ዋነኛ ዓላማ ለወጪ ንግድ የሚሆኑ ምርቶችን ማምረት ነው፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችም መተካት መቻል ነው፡፡ አብዛኞቹ ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች በቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት መስህብ ቢሆንም የታሰበውን ያህል የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማስገኘት እንዳልቻሉ ይታወቃል፡፡ ለአብነትም ጨርቃ ጨርቅ አምራቾች ግብዓቶችን ከውጭ በማስመጣት ይጠቀማሉ፡፡ ምርቶቻቸውን ልከው የውጭ ምንዛሪ ቢያስገኙም፣ ለግብዓት መግዣ ያገኙትን የውጭ ምንዛሪ መልሰው ማስወጣታቸው ጥያቄ የሚያጭር ሆኗል፡፡

አብዛኛው የውጭ ምንዛሪ ተመልሶ ለጥሬ ዕቃ ግዥ ይወጣል ያሉት አቶ አሰፋ፣ እነዚህ ኩባንያዎች ከውጭ የሚገባውን ምርት በመተካቱ ላይ የፈየዱት ነገር አለ ለማለት ይከብዳል ይላሉ፡፡ ይህም የሚያሳየው ኢንዱስትሪዎች ከአገር ውስጥ ተቋማት ጋር ተመጋጋቢ ሥራ እንደማይሠሩ ወይም ከአገር ውስጥ አምራቾች ተገቢውን ግዥ እንደማይፈጽሙ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ለአልባሳቱ የሚሆን ዚፕ፣ ቁልፍ፣ ባጅና ማሸጊያ ካርቶን በሙሉ ከውጭ እየገባ ነው፡፡ በአገር ውስጥ እርግጥ የጥሬ አምራቾች ችግር ቢኖርም፣ እዚህ በቀላሉ ሊመረቱ የሚችሉትን ግብዓቶች መጠቀም እንዳለባቸው የሚያሳስብ ውይይት መካሄዱን ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ኢንዱስትሪዎች በተፈለገው መጠን የቴክኖሎጂ ሽግግር እያደረጉ እንዳላካሄዱም በአጽንኦት ተመክሮበታል ተብሏል፡፡ ‹‹ከዚህ አንፃር ሲታዩ በተለይ በውጭ ኢንቨስትመንት ስም የገቡ የውጭ ኩባንያዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠርና ሼድ ከመከራየት ውጭ ልብስ ሰፊ ሆነዋል፤›› ብለዋቸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሌሎች ኢንዱስትሪዎችን ሳይጨምር በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ብቻ ከውጭ የገቡ 11 የጨርቃ ጨርቅ ኩባንያዎች ማምረቻ ተከራይተው እንደገቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በመድረኮቹ ለተነሱ ጥያቄዎች በኃላፊዎች ምላሽ ቢሰጥም፣ በአስተዳደሩ ዕርማት ይደረግባቸዋል፣ ይስተካከሉ የተባሉ ጉዳዮች በእርግጥም ስለመፈጸማቸው ማረጋገጥ ተገቢ በመሆኑ ከስድስት ወራት በኋላ በሚካሄደው የምክክር መድረክ ስለክንውናቸው መረጃ እንዲያቀርቡ ስምምነት ላይ ተደርሷል ተብሏል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ‹‹ግዳጄን እየተወጣሁ መብቴን እጠይቃለሁ፤›› በሚል በገቢዎች ሚኒስቴር የተጀመረውን አገራዊ ንቅናቄ በመደገፍ የክልሉ ንግድ ምክር ቤት ከክልሉ አስተዳደር ጋር በመሆን ሰባት የታክስ አምባሳደሮችን ሾመዋል፡፡ አምባሳደሮቹ ከምሁራን፣ ከአርቲቪስቶች፣ ከሃይማኖት መሪዎችና ከባለሀብቶች የተወጣጡ ናቸው፡፡ በታክስ ማነቆዎች ላይም ውይይት እንደተካሄደ አቶ አሰፋ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች