Sunday, February 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በዚህ ዓመት የሦስት መስኖ ግድቦች ግንባታ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመስኖ ውኃ ታሪፍ እየተዘጋጀለት ነው

የጊዳቦ ግድብ ምርቃት ለሁለተኛ ጊዜ ተራዝሟል

ለበርካታ ዓመታት ሲጓተቱ ከቆዩት የመስኖ ግድብ ግንባታዎች ውስጥ በሰሜኑ ክፍል ግንባታቸው የሚገኙ ሦስት የመስኖ ግድቦች በዚህ ዓመት ሊጠናቀቁ እንደሚችሉ ተገለጸ፡፡

የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ለሪፖርተር እንዳስታወቀው፣ በዚህ ዓመት ግንባታቸው እንደሚጠናቀቁ የሚጠበቁት የርብ፣ የመገጭና የዛሬማ መስኖ ግድቦች ናቸው፡፡ የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ እንደጠቀሱት፣ በዚህ ዓመት እንዲጠናቀቁ ከሚጠበቁት መካከል የመገጭ ሳርባ፣ የርብ መስኖ አውታርና የዛሬማ ማዕዴን የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በዚህ ዓመት እንደሚጠናቀቁ ተስፋ የሚደረጉት ናቸው፡፡ መገጭ ሳርባ 4,000 ሔክታር የአርሶ አደር ማሳ የሚያለማ ሲሆን፣ የርብ ግድብም 3,000 ሔክታር የአርሶ አደሮች መሬትን የማልማት አቅም ያለው የመስኖ አውታር ነው፡፡

በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን፣ ፋርጣ ወረዳ 2000 .. የተጀመረው የርብ መስኖ ልማት ግድብ፣ ከአሥር ዓመታት በኋላ ግንባታው ተጠናቆ ጥቅምት 18 ቀን 2011 .. በይፋ መመረቁ ይታወሳል፡፡ ይህ ፕሮጀክት 2000 .. በአራት ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ቢባልም፣ ግንባታው በተለያዩ ችግሮች ለስድስት ዓመታት ዘግይቷል፡፡

ፕሮጀክቱ 1.6 ቢሊዮን ብር በጀት የተጀመረ ቢሆንም ግንባታው በተያዘለት ጊዜ ገደብ ባለመጠናቀቁ፣ በጀቱ እስካለፈው ዓመት ጥቅምት 2010 .. ድረስ 3.7 ቢሊዮን ብር መድረሱ ታውቋል፡፡ የግድቡንዲዛይንና የቁጥጥር ሥራውን ያካሄደው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን ሲሆን፣ ግንባታውን ደግሞ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን አከናውኖታል፡፡

የርብ መስኖ ልማት ግድብ የዘገየው በዲዛይን ለውጥ፣ በተቋራጩና በአማካሪ ድርጅቱ አቅም ውስንነትና ልምድ ማነስ፣ በውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አስተዳደር ችግርና በግንባታ ዕቃዎች አቅርቦት እጥረት ምክንያት እንደነበር ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ የግድቡ ሥራ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆና የውኃ ማስተላለፊያ ቦዮቹ ግንባታ አልቆ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት የሚጀመረው በዚህ ዓመት መጨረሻ ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በየጊዜው ቢጀመሩም በተያዘላቸው የጊዜ ገደብና በጀት ስለማይጠናቀቁ ከፍተኛ ክስረት እያስከተሉ ይገኛሉ፡፡ ይህ በመሆኑም ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ትልልቅ ፕሮጀክቶች ከመጀመራቸው በፊት ሰፊ ጥናትና ዝግጅት እንዲረግባቸው ኃላፊነት እንደተሰጠው የሚታወስ ነው፡፡

የጊዳቦ ግድብ በታኅሳስ ወር ሥራው ተጠናቆ እንደሚመረቅ መርሐ ግብር ቢያዝለትም ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡ ለጥር 14 ቀን 2011 ዓ.ም. የተያዘው መርሐ ግብርም ጥር 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በድንገት በተላለፈ መረጃ መሠረት እንዲራዘም ተደርጓል፡፡ ይሁን መቼ እንደሚካሄድ አልታወቀም፡፡ መገኘት ያለባቸው ኃላፊዎችና ወቅታዊ ሁኔታዎች ተደማምረው ለምርቃቱ መራዘም ሰበብ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በሁለት ዓመታት ውስጥ ግንባታው እንደሚጠናቀቅ ታቅዶና 258 ሚሊዮን ብር በጀት የተጀመረው የጊዳቦ መስኖ ልማትና ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት፣ ከስምንት ዓመታት መጓተት በኋላ 1.66 ቢሊዮን ብር መጠናቀቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 2002 .. ግንባታው የተጀመረው የጊዳቦ ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት፣ እንዲጓተት ካስገደዱት ምክንያቶች መካከል መሠረታዊ የዲዛይን ለውጦች መደረጋቸው ሲሆን፣ የፕሮጀክቱ ግንባታ ከተፈረመ በኋላ ለሁለት ዓመታት ግንባታው ሳይጀመር መጓተቱም ለዋጋ ንረት እንደፈጠረ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ይፋ አድርጓል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ሦስት ተቋማትን በመጠቅለል ከተቋቋመ ከሦስት ዓመታት ወዲህ ከተረከባቸው ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው የጊዳቦ መስኖ ልማትና ግድብ ሥራ ፕሮጀክት፣ በግንባታ ጥሬ ዕቃዎች እጥረት፣ በተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር መጓደል፣ በካሳ ክፍያዎችና በሌሎችም ምክንያቶች በሁለት ዓመታት እንዲጠናቀቅ የተቀመጠለት ጊዜ ከመጓተቱም ባሻገር ወጪውም 645 በመቶ ገደማ ጨምሮ ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡

ፕሮጀክቱ ከመነሻው ከታቀደው 16 ሜትር የግድብ ከፍታ ወደ 22.5 ሜትር ተሻሽሎ እንዲሠራ መደረጉን ኮርፖሬሽኑ አስታውቆ፣ ከሰባት ኪሎ ሜትር በላይ የሚዘረጋ የውኃ መተኛ ቦታ 315 ሜትር ርዝማኔ ኖሮት እንዲገነባ መደረጉንም የኮርፖሬሽኑ መረጃ ይጠቁማል፡፡ በግድቡ 63 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ ውኃ የመያዝ አቅም እንዲኖረው ተደርጎ በመገንባቱ 13.5 ሺሕ ሔክታር መሬት በመስኖ ለማልማት እንደሚያስችል ታውቋል፡፡

መንግሥት ለመስኖ ልማት አውታሮቹ ግንባታ ያወጣውን ወጪ ለእርሻ ማሳያዎች ከሚያቀርበው ውኃ በታሪፍ በማስከፈል ገቢ የመሰብሰብ ዕቅድ አለው፡፡ በመሆኑም የመስኖ ውኃ ታሪፍ እንዴት እንደሚወሰንና በምን አግባብ እንደሚያስከፍል የሚደነግግ ዝርዝር ረቂቅ ሕግ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ይሁንና የመስኖ ምሕንድስና ባለሙያዎች ግን እንዲህ ያለው መረጃ በአግባቡ እንዲደርሰው መደረግ እንዳለበትና ለሚቀርብለት የመስኖ ውኃ የሚከፍልበት አካሄድ ሊኖር እንደሚችል የሚገልጹ ዝግጅቶች ከወዲሁ ሊደረጉ እንደሚገባቸው ያሳስባሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች