Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ10 ሺሕ በላይ ሥራ ፈጣሪ ሴቶችን ያካተተው ፕሮጀክት

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሴቶች ኢንተርፕሩነርሺፕ ልማት ፕሮጀክት በፌዴራል ከተሞች ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ሥር ከሚገኙ ፕሮግራሞች አንዱ ነው፡፡ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማስፋት ሲባል መንግሥት ከዓለም ባንክ ጋር በጋራ የሚተገብረው ፕሮጀክት ነው፡፡ ለተግባራዊነቱም ዓለም ባንክ 50 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ለመንግሥት አበድሯል፡፡ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ለሥራ ማስኬጃና ለተያያዥ ጉዳዮች በስጦታ የቀረበ ነው፡፡

ከዓለም ባንክ የተገኘው 50 ሚሊዮን ዶላር በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ለሚሆኑ ነጋዴ ሴቶች በብድርነት የተዘጋጀ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ የመጀመርያ ክፍል ይተገበር የነበረውም በአዲስ አበባ፣ መቀሌ፣ ባህር ዳር፣ አዳማ፣ ሐዋሳ፣ ድሬዳዋ ከተሞችና በዙሪያቸው በሚገኙ ሌሎች ከተሞች ከአምስት ዓመታት በፊት ነው፡፡ ቢያንስ  ለስድስት ወራት  የሠሩበት ሕጋዊ የንግድ ፈቃድ ያላቸው፣ ሀብታምም ደሃም የማይባሉ ነጋዴ ሴቶች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው ይህ ፕሮጀክት በተመረጡት ከተሞች ለሚገኙ ሴቶች ብድር እንዲያገኙ ያደርጋል፣ አስፈላጊውን ሥልጠናም ይሰጣል፡፡ ለሴቶች ብቻ የተዘጋጀው ይህ የብድር ገንዘብ በየከተሞቹ በሚገኙ 12 ዋና ዋና ማይክሮ ፋይናንሶች በኩል ይሠራጫል፡፡ እነዚህ አበዳሪ ተቋማት በሚያበድሩት ገንዘብ ላይ ከ13 እስከ 21 በመቶ የወለድ ምጣኔ በመያዝ ነው ብድሩን የሚሰጡት፡፡

በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የተሠራጨው 50 ሚሊዮን ዶላር የብድር ገንዘብ ከ10,000 በላይ የሚሆኑ ሴቶችን ተደራሽ አድርጓል፡፡ ለአምስት ዓመት ተብሎ የተዘጋጀው ገንዘብ ግን የተጠናቀቀው አራተኛ ዓመቱ አካባቢ ነበር፡፡ ነገር ግን የተባለው ገንዘብ ስላለቀ የብድር አገልግሎቱ አልተቋረጠም ነበር፡፡ እነዚህ ተቋማት ከ10,000 በላይ ለሚሆኑ ሴቶች 2.6 ቢሊዮን ብር ሊያበደሩ 32 በመቶ የሚሆነውን ወይም 837 ሚሊዮን ብር ያበደሩት የዓለም ባንክ ካቀረበው ገንዘብ በተጨማሪ ከራሳቸው በጀት ነበር፡፡

የፕሮጀክቱ ኮሙዩኒኬሽን ስፔሻሊስት አቶ ብርሃኑ ሲሳይ፣ ሴቶች ላይ ያተኮረው ፕሮጀክቱ ተበድረው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዕድል ሰፊ ያደረገ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከተለመዱት መያዣዎች በተጨማሪ ዕቁብ፣ ደረቅ ቼክ የመሳሰሉት በመያዣነት እንዲካተቱም አድርጓል፡፡ የመያዣ አማራጮችን ከማስፋት ባሻገርም የመክፈያ ጊዜው እስከ አምስት ዓመታት ድረስ ተራዝሟል፡፡ ‹‹ነገር ግን በቀራቸው ብር ላይ ወለድ ስለሚታሰብ ቀድመው ነው ብድራቸውን የሚከፍሉት፡፡ የብድር አከፋፈል ሁኔታውም 98.7 በመቶ ነው፤›› የሚሉት አቶ ብርሃኑ፣ የተከፈለው ገንዘብ እየተገላበጠ ዳግመኛ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማቱ ከመንግሥት ባገኙት ፈቃድ እያበደሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ አዋጭ ስለሆነ ነው ከተዘጋጀው የብድር ገንዘብ በተጨማሪ 837 ሚሊዮን ብር ከራሳቸው በጀት ያበደሩትም ብለዋል፡፡

ላለፉት አምስት ዓመታት ሲተገበር የቆየው ይህ ፕሮጀክት የተጠናቀቀው ዓምና 2010 ዓ.ም. ላይ ነው፡፡ በወቅቱ በዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ የነበሩ ሴቶች ከሚያገኙት የገንዘብ ብድር ባሻገር ተገቢውን ሥልጠናም ያገኙ ነበር፡፡ በአጠቃላይ 26,000 ሴቶችን በብድርና በሥልጠና ተደራሽ ማድረግም ተችሏል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ 20,000 ሴቶችን በመሠረታዊ ንግድ ክህሎት፣ የሥራ ተነሳሽነትና ሙያ ሥልጠና መስጠት ታቅዶ ነበር፡፡ ነገር ግን መድረስ የተቻለው 16,299 ሴቶችን ብቻ ነበር፡፡

ሥልጠናውን ሲሰጡ የነበሩ 20 የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት በሰው ከ840 እስከ 1,365 ብር ድረስ እየተከፈላቸው ነው፡፡ የመሠረታዊ የንግድ ክህሎትና የራስ ተነሳሽነት ሥልጠና ከአምስት እስከ አሥር ቀናት ውስጥ የሚያልቅ ሲሆን፣ በሰው 840 ብር ይከፈልበታል፡፡ ከአንድ ወር እስከ ሦስት ወራት ሊቆይ በሚችለው የሙያ ሥልጠና ደግሞ በሰው 1,365 ብር ይከፈል እንደነበር አቶ ብርሃኑ ያስረዳሉ፡፡ ሥልጠናው ከብድር አቅርቦት ጋር ተደምሮ የሴቶቹን ትርፋማነት ወደ 44.7 በመቶ፣ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅማቸውን ደግሞ በ55.7 በመቶ ከፍ አድርጎታልም ብለዋል፡፡

ያስገኘውን ውጤት ተከትሎም የጣልያን መንግሥት 15 ሚሊዮን ዩሮ፣ የጃፓን መንግሥት 500 ሚሊዮን ዶላር፣ በቅርቡ ደግሞ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ 30 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ በዓለም ባንክ በኩል ሰጥቷል፡፡ ይህም የፕሮጀክቱ ሁለተኛ ክፍል ታኅሳስ 2010 ዓ.ም. እንዲጀመር ምክንያት ሆነ፡፡

ክፍል ሁለት ተጨማሪ አራት ከተሞችን አካቶ ብቅ ብሏል፡፡ አዲስ አበባ፣ መቀሌ፣ አክሱም፣ ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ አሰላ፣ አዳማ፣ ዲላ፣ ሐዋሳና ድሬዳዋ ተደራሽ የተደረጉ ሲሆን፣ በእነዚህ ከተሞች በ50 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች 89 ከተሞችም ተጠቃለዋል፡፡ በጥቅሉ 99 ከተሞች በክፍል ሁለት የሴቶች ኢንተርፕሩነርሽፕ ልማት ፕሮጀክት አካል ሆነዋል፡፡

ሁለተኛው ዙር ለሁለት ዓመታት የሚቆይ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ብርሃኑ፣ የተገኘው የገንዘብ ድጋፍ ሦስተኛውን የፕሮጀክቱን ክፍል ማስቀጠል የሚያስችል በመሆኑ በቀጣይ ክፍል ሦስት ተግባራዊ የሚደረግበትን አካሄድ እያስተካከሉ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ በሦስተኛው ዙር አራት ትልልቅ ከተሞች እንደሚጨመሩ አቶ ብርሃኑ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በተደገባቸው ጊዜያት ፍሬያማ ውጤቶችን ቢያስመዘግብም የተለያዩ ችግሮች ታይተዋል፡፡ የመጀመርያው የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ብድር ከማስመለስ ጋር ተያይዞ የታየው የአቅም ውስንነት ነው፡፡ ያበደሩትን ገንዘብ ማስመለስ ካልቻሉ ከብሔራዊ ባንክ ብድር ማግኘት አይችሉም፡፡ እንዲህ ያሉ ማይክሮ ፋይናንሶች የመጨረሻ ዕድል ሥራ ማቆም ነው፡፡

መሰል ችግር የተስተዋለባቸው የመቀሌው ደደቢትና የሐዋሳው ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ናቸው፡፡ ደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ የነበረበት ችግር በመጀመርያዎቹ አምስት ዓመታት የተፈታ ቢሆንም፣ ሐዋሳና አካባቢውን የሚያገለግለው ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ግን ችግር ውስጥ እንደተዘፈቀ ይገኛል፡፡ ይህም ሐዋሳ ላይ የሚገኙ የብድር አገልግሎት የሚያገኙ ሴቶች ቁጥር ዝቅተኛ እንዲሆን ምክንያት ነው፡፡ ሐዋሳ ላይ እየሠሩ የሚገኙት አጋርና ቪዥን የተባሉ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ሲሆኑ እስካሁን ማበደር የቻሉት ለ368 ሴቶች፣ 97 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ከፍተኛ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ቁጥር ባላት አዲስ አበባ የተበዳሪዎች ቁጥር ብዙ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከስምንት ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ጋር ሲሠሩ 5,649 ሴቶች 1.5 ቢሊዮን ብር መበደር እንደቻሉ አብራርተዋል፡፡

ሌላው ከማስያዣ ጋር በተያያዘ የሚስተዋለው ክፍተት ነው፡፡ አበዳሪ ተቋማቱ በመያዣነት የሚወሰዷቸው ንብረቶችና ሀብቶችን ዓይነት ቢያሰፉም፣ ከመያዣው ግምት በላይ እስከ 175 በመቶ የሚሆን የገንዘብ ብድር ይሰጣሉ፡፡ ለመያዣዎች የሚሰጡት የዋጋ ግምት ነባራዊውን የገበያ ሁኔታ ያላገናዘበ በመሆኑ፣ ሴቶቹ ካስያዙት ንብረት ያነሰ ገንዘብ እንዲበደሩ ሆኗል፡፡ ለምሳሌ ገበያ ላይ አንድ ሚሊዮን ብር ያወጣል ተብሎ የተገመተን ቤት በ200 ሺሕ ይገምታሉ፡፡ የሚሰጡት የብድር መጠንም በግምታቸው ልክ የተወሰነ ነው፡፡

ከዚህ ባሻገር ደግሞ ለማስያዣነት የሚውል ሀብት ማፍራት ያልቻሉ ሴቶች ብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህም የሚያሲዙትን ንብረት በማጣት ብቻ ብድር ለማግኘት ፍላጎቱ ቢኖራቸውም የዕድሉ ተጠቃሚ አይደሉም፡፡ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ዓለም ባንክ ከወሳሳ ማይክሮ ፋይናንስ ጋር በመሆን የጀመረው አንድ አሠራር አለ፡፡ አሠራሩ ለሚጠይቁት ብድር ማስያዣ መስጠት የማይችሉ ሴቶች ንብረት ስለሌላቸው ብቻ ብድር እንዳይከለከሉ የሚያደርግ አሠራር ነው፡፡ ይኸውም የተበዳሪዋን ፍላጎትና አቅም በመገምገም አስተማማኝ ሆና ከተገኘች ያለማስያዣ ብድር እንድታገኝ ማድረግ ነው፡፡ አሠራሩ በተያዘው ዓመት የተጀመረ ሲሆን፣ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘውም በአዳማ ከተማ ነው፡፡ በዚህ ዕድል እስካሁን 15 ሴቶች ተጠቃሚ እንደሆኑ ለሪፖርተር የገለጹት አቶ ብርሃኑ፣ አሠራሩ ውጤታማ ከሆነ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ተግባራዊ እንደሚሆንም  ታውቋል፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ከዚህ ቀደም ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማቱ ለአንድ ሰው የማበደር አቅማቸው ከ50 ሺሕ አይበልጥም፡፡ ከፕሮጀክቱ ጋር አብረው መሥራት ከጀመሩ በኋላ ግን ለአንድ ሰው በአማካይ ሁለት ሚሊዮን ድረስ እያበደሩ ይገኛሉ፡፡ አንዳንዶችም እስከ 30 ሚሊዮን ብር እያበደሩ ይገኛሉ፡፡ ተደራሽነቱን ለማስፋት እየሠራ የሚገኘው ፕሮጀክቱ ፍላጎት ያላቸውን ዜጎች በሙሉ ተጠቃሚ ለማድረግ አቅም አይወስነውም ብለዋል፡፡ አገልግሎቱን በማሳለጥ ረገድ ዓይነተኛ ሚና የሚጫወቱት በአሥሩ ከተሞች በሚገኙ ወረዳዎች የሚሠሩ 49 የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች