Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለቢራ ማስታወቂያ ሰዓት እላፊ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያዎችን የሚገድብ ረቂቅ አዋጅ ለማፅደቅ የተደረገው ውይይት አግራሞት ከፈጠረባቸው አንዱ ነኝ፡፡ ሕጉ እንዲፀድቅ የሚደረገው ሙግት  ከሌሎች አዋጆች በተለየ እንዲታይ ያደርገዋል ማለት ይቻላል፡፡

 ስንት አዋጅ በመጣበት ሲፀድቅበት በከረመው ፓርላማ፣ በቢራ ማስታወቂያ ላይ ጊዜ ተሰጥቶትና ሰፋ ያለ የሐሳብ ሙግት ማስተናገዱ አንዳች የሚከነክን ጉዳይ ሳይኖው አልቀረም፡፡ ምክንያቱም በሌሎች ብርቱ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያውም ስንት መሠረታዊ ጭብጥ ያላቸው ረቂቅ አዋጆች የከረረ ውይይት ሳይደረግባቸው በለብ ለብ ሲያልፉ በማየቴ ነው፡፡ የአልኮል፣ በተለይም የቢራ ፋብሪካዎች ማስታወቂያዎች በታዳጊዎች ላይ የሚፈጥሩትን ተፅዕኖ ለመቀነስ ቢያንስ የሚያስተዋውቁበት ጊዜ ላይ ገደብ ይደረግ  የሚሉ አንቀጾችን ያካተተ ነው፡፡

ማስታወቂያዎች ባዘቦት ቀናት ከምሽት ሦስት ሰዓት በኋላ እንዲለቀቁ የሚጠይቁ አንቀፆች ይገኙበታል፡፡ በዋናነት ግን ታዳጊዎች ያለ ዕድሜያቸው ለሱስ እንዳይደረጉ፣ መገናኛ ብዙኃንም ታዳጊዎችን ላልተገባ ተጋላጭነት ከማጋለጥ እንዲጠነቀቁ ለማድረግ የተሰናዳ ሕግ እንደሆነ እገነዘባለሁ፡፡

ከዚህ አንፃር የረቂቅ አዋጁ መነሻ ሐሳብ ትውልድን መታገድ ነው፡፡ ከቢራ ፋብሪካዎቹ ወገን ግን ሕጉ እንዳይፀድቅ የሚሞግቱበት መንገድ፣ ከራሳቸው ጥቅም አንፃር ብቻ የተቃኘ ሆኖ መገኘቱ ትዝብት ላይ ሳይጥላቸው አይቀርም፡፡ በእርግጥም ያለ ገደብ የሚያዥጎደጉዷቸው ማስታወቂያዎች ስሜትን በመሳብና በማማለል ገንዘባቸውን ዕለት ዕለት ማካበትና ትርፋቸውን ማስፋት ነው፡፡ አንዳቸው ከሌላኛው የበለጠ የገበያ ሽሚያና የበላይነት ለመያዝ የሚጠቀሙት ማስታወቂያ ልክ ይኑረው፣ ታዳጊዎች በሥነ ልቦና ጫና ውስጥ ወድቀዋልና ይህንን አስተካክሉ ማለት የመንግሥትም የአባትም ነው፡፡

መንግሥት አደብ እንዲገዙ ማድረጉ ግዴታው ነው፡፡ አግራሞትን የፈጠረብኝና አገራችን ያለችበትን ደረጃ እንድመለከት ያደረገኝ ጉዳይ በቢራ ማስታወቂያ ላይ በፓርላማው የዚህን ያህል መድከም ነበረበት ወይ? የሚለውን ጥያቄ ሳብሰለስል ነው፡፡ ኩባንያዎቹ አዋጁ እንዳይፀድቅ በፓርላማ ተገኝተው የቻሉትን ሁሉ መሞገታቸው ከመብት አኳያ ካየነው ትክክል ናቸው፡፡ አመክንዮው ይቆየንና፣ የሕዝብ እንደራሴዎቹ ግን ምነው በሌሎች አዋጆችስ ላይ እንዲህ ጠበቅ፣ ጠለቅ ያለ ሙግት አለመግጠማቸው አሰኝቶኛል፡፡ የኢንዱስትሪው ሰዎችም በዚህ ጉዳይ ላይ እንተቻቸው እንጂ እንደራሴዎቹን መሞገታቸው ለሌላውም ዘርፍ መልካም ጅምር መሆኑ ሳይወሳ አይታለፍም፡፡ ውይይቱ እስከ ሦስት ጊዜ ያህል ተደጋግሞ መካሄዱ ከየትኛውም ጉዳይ ይልቅ የቢራ ማስታወቂያ አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ ፓርላማውን ፓርላማ የሚያስመስለው ወዝ ማላበሱ ባይሞካሽም ሒደቱ ግን አጀብ ያሰኘ ነው፡፡   

አዋጁ አስፈላጊ ነው፡፡ አስፈላጊ አይደለም የሚለውን ንትርክ እናቆይና አዋጁ ለምን በዚህ ደረጃ ሙግት ተፈጠረበት የሚለው ጉዳይ ሊያነጋግረን ይገባል፡፡

በሌላ በኩል እንዲህ ላሉት ሕጎች ጊዜ ሰጥቶ፣ አድምቶና አብስሎ ከመመርመር በተጓዳኝ ባለድርሻዎችን አሳትፎና አወያይቶ መጓዙ ውጤታማ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ሕጉ የሚመለከታቸውንና ጥያቄ ያላቸውን ጊዜ ሰጥቶ ማነጋገር እንደጀመረ ማሳየቱም ለፓርላማው መልካም ገጽታ ነው ማለት ይቻላል፡፡

የቢራ ማስታወቂያው ሕግ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ ድርጊቱን ባልሆነ መንገድ በማጣመም ችግር እንዳይፈጥር መታየት ያለባቸው ነገሮችም አሉ፡፡ ዛሬ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚሽከረከርበት የቢራ ኢንዱስትሪ ባለንብረቶች በአብዛኛው የውጭ ኩባንያዎች ናቸውና በአግባቡ ሥሩ፣ ሕግ አክብሩ ሲባሉ የዚህን ያህል የመሞገታቸው አንድምታው ገበያ ብቻ ነው ወይ ብሎ ማሰብ ያሻል፡፡ ዛሬ ለማስታወቂያ ሕግ ገደብ ይውጣ መባሉ እንዲህ ካስቆጣቸው፣ ነገ ከዚህ ባስ ያሉ አስገዳጅ መስፈርቶችን ቢመጡ ምን ሊኮን ነው? በኢንቨስትመንት ተጓዳኝ አድራጎት ዜጎች መጎዳት የለባቸውም የሚለው ገዥ ምክንያት ነው አይደለም የሚለው ላይ መከራከር አንድ ጉዳይ ነው፡፡ ሙግቱም በዚሁ አግባብ ቢሆን የሰመረ ይሆናል፡፡

ኩባንያዎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ከመሆናቸው አንፃር በተለይ በባለሀብቶቹ አገሮች ውስጥ የአልኮል ማስታወቂያዎቻቸው ምን ዓይነት ይዘትና በምን አግባብ እንደሚተላለፉ ማየቱም ተገቢ ይሆናል፡፡

የቢራ ማስታወቂያዎች በስፖርትና በሌሎች መዝናኛዎች ውስጥ የሚያደርጉት ተሳትፎ ቢበረታታም፣ በሌላ አማርኛ ጠጪ ትውልድ በማብዛት ዘላቂ ገበያ የመፍጠር አባዜ ያውም፣ ሕፃን ከአዋቂ በማይለይ ሰዓትና ቀን እያስላለፉ መጓዝ የኃላፊነት ምልክት አይመስልም፡፡ ከ18 ዓመት በታች አይሸጥም የሚሉ ድርጅቶች ምነው ማስታቂያችሁን ከ18 ዓመት በታች ለሆናቸው ስታሳዩ ተጠንቀቁ መባላቸው ምንድነው ሆድ የሚያስብሳቸው?

እነዚህ ኩባንያዎች ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚያደርጉት አስተዋጽኦ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ማስታወቂያዎቻቸው በአመዛኙ የሚተላለፈው በአብዛኛው ታዳጊዎች በቴሌቪዥንና በሬዲዮ የሚተላለፉ ጉዳዮችን በንቃት በሚተላለፉበት ወቅት መሆኑ እኮ የታወቀ ነው፡፡

ስለዚህ ብዙ ማስታወቂያዎቻቸው ከ18 ዓመት በላይ የሚሉ ቢሆኑም ሕፃናትና ታዳጊዎች ነገ ጠጪዎች እንዲሆኑ የሚገፋፉ ጭምር በመሆናቸው ማስታወቂያዎቹን እንዲያስነግሩ በሚፈቀድላቸው ጊዜ ቢሆን ጨዋ መሆን እንዳለበት ማስገደድ ኢንቨስትመንቱን መቃወም አይሆንም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች