Tuesday, February 27, 2024

ኦዴፓ የሚመራው የኦሮሚያ መንግሥትና ኦነግ የፈጸሙት ስምምነት የፈነጠቀው ተስፋና ሥጋቶቹ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኦሮሞ ሕዝብ ለዓመታት ሲያካሂድ የነበረውን ፖለቲካዊ ትግል በመደገፍ ከሌሎች ለውጥ አራማጅ አጋሮቹ ጋር በመሆን ሌላ ፖለቲካዊ ትግል በኢሕአዴግ ውስጥ የከፈተው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ)፣ ትግሉን በድል አጠናቆ ኢሕአዴግንና የፌዴራል መንግሥትን መምራት የጀመረበትን አንደኛ ዓመት ከሁለት ወራት በኋላ ይደፍናል።

ከአገር ውጭም ሆነ በአገር ውስጥ በሰላማዊም ሆነ በትጥቅ ትግል ፖለቲካዊ ንቅናቄ ሲያደርጉ የነበሩ ፓርቲዎች ሁሉን አቀፍ ሰላማዊ የፖለቲካ ተሳትፎን በአገራቸው ውስጥ በነፃነት እንዲያካሂዱ፣ የኦዴፓና የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሹመታቸውን በተቀበሉ ማግሥት ቅድሚያ ሰጥተው ጥሪ ማስተላለፋቸው፣ ባለፉት አሥር ወራት ወስጥ ከተፈጸሙና ዝናን ካጎናፀፉ ተግባራት መካከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሆኑን በርካቶች ይስማሙበታል።

ይህ ተግባርም ለኢትዮጵያ ተስፋን የጫረ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍን እንዳበረከተ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም ዓቀፍ ተንታኞች፣ እንዲሁም በራሳቸው በተፎካካሪ ፓርቲዎች ጭምር የሚታመንበት ነው። ይሁን እንጂ የዚህ ፖለቲካዊ ምዕራፍ ጅማሮ አልጋ በአልጋ አልሆነም።

በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ ተሳትፎ ለማድረግ ከመንግሥት ጋር ስምምነት አድርጎ ከኤርትራ ወደ አገር ቤት የተመለሰው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ ውስጥ አገር በገባ ጥቂት ወራት ውስጥ ከመንግሥት በተለይም ኦሮሚያን ከሚያስተዳድረው ኦዴፓ ጋር የፈጠረው አለመግባባት ወደ ግጭት አምርቷል።

ኦነግ የትጥቅ ትግል ለማቆም ተስማምቶ ወደ ከተመለሰ በኋላ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የትጥቅ ትግል ላይ የነበረውን ሠራዊቱን ትጥቅ አለማስፈታቱ፣ እንዲሁም ይህ ሠራዊት በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተለይም በምዕራብ ወለጋ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመሩ በኦነግና በኦዴፓ፣ እንዲሁም ኦዴፓ ከሚመራው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።

ኦዴፓና ኦነግ አንዱ በመንግሥት አመራርነት፣ አንዱ ደግሞ በተፎካካሪነት መስመር የተሠለፉ ይሁኑ እንጂ በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ናቸው፡፡ ለአንድ ማኅበረሰብ ፖለቲካዊ ፍላጎት የሚንቀሳቀሱ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅቶች እንደ  መሆናቸው፣ አገራዊ የፖለቲካ ለውጡ መሬት ባልያዘበት ዓውድ ውስጥ በመሀላቸው አለመግባባት መከሰቱ የፖለቲካ ውጥረቱ እንዲያይል ምክንያት መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ይስማሙበታል።

በአንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በአገሪቱ የተፈጠረው የፖለቲካ ለውጥ ረግቶ በእግሩ ባልቆመበት ከባቢ ውስጥ ውጥረቱ እርስ በርስ ወደ መጣጣል ቢሸጋገር፣ በሁለቱም ላይ ፖለቲካዊ ኪሳራ ከማምጣት አልፎ በአገር ደረጃም አሉታዊ ተፅዕኖው የከፋ ይሆን እንደነበር ተንታኞች ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ ስምምነት ላይ ለመድረስ ሳይቻልና ግጭቱ ሳይፈታ በተራዘመ ቁጥር የክልሉ መንግሥት በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነቱን መወጣት የማይችልበት ደረጃ ላይ ሲደርስ፣ ይህም የሚመራው ማኅበረሰብ እምነት እንዲሸረሸር በማድረግ ፖለቲካዊ ኪሳራ የመፍጠር ብሎም በአገር ደረጃ የተጀመረው ፖለቲካዊ ለውጥ እንዲጓተት፣ አልያም መስመሩን እንዲስት አደጋ የሚደቅን መሆኑን ይገልጻሉ።

የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የኦሮሚያ ክልል ወይም የኦዴፓ አመራሮች በተገለጹት አጣብቂኞች ውስጥ መውደቃቸውንና በጥንቃቄ ለመውጣት እልህ አስጨራሽ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ።

ይሁን እንጂ በኅዳር ወር 2011 ዓ.ም. በምዕራብ ወለጋ ነዋሪዎችና የፀጥታ አስከባሪዎች ላይ በጅምላ ተፈጸመ የተባለው ዕልቂት፣ በኦዴፓ ለሚመራው የክልሉ መንግሥትም ሆነ ለፌዴራል መንግሥት የማይታገሱት ሆኖባቸዋል።

‹‹ጠላቶች ለሸረቡት ሴራ በቂ ዕውቀት የሌለው ‹የእኛው ሰው› በሰላማዊ የኦሮሞ ሕዝብን ጭካኔ በተሞላበት የሽብር ጥቃት በፈንጂ ሕይወቱን መቅጠፉን፣ ሴቶች መደፈራቸውን፣ ንብረት እየወደመና የሕዝቡ የመንቀሳቀስ መብት እየተገደበ ነው። ሰላም ይቅደም በማለት ሲሠሩ የነበሩ የኦዴፓ አመራሮችና የሕዝብ ጋሻ የሆነው የኦሮሚያ ፖሊስ አባላትም በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፤›› ሲል፣ ኦዴፓ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ገልጾታል።

ስለሆነም በተቀናጀ መንገድ የሚሸርቡትን ሴራ አክሽፎ የሕዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ ማንኛውንም ዓይነት ዕርምጃ ለመውሰድ መወሰኑን ኦዴፓ በወቅቱ በይፋ የገለጸ ሲሆን፣ ይኼንንም ተከትሎ የአገር መከላከያ ሠራዊት በአካባቢው እንዲሰማራ በፌዴራል መንግሥት መወሰኑ ይታወሳል።

በኦዴፓና በኦነግ መካከል የነበረው ግጭት ከዚህ በኋላ የጦርነት ባህሪን የተላበሰ ሲሆን፣ የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ጦራቸው ነፃ ባወጣው መሬት ላይ ራሱን እንዲከላከል ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን በይፋ መግለጻቸው ሥጋቱ እንዲያይል ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል።

የመከላከያ ሠራዊቱ በምዕራብ ወለጋ ከተሰማራ በኋላ የአካባቢው ነዋሪዎች መለስተኛ የመንቀሳቀስ ዕድል ቢገጥማቸውም፣ ችግሩን ሙሉ በሙሉ መፍታት አልተቻለም። የመከላከያ ሠራዊቱ የዘመቻ መምሪያ ኃላፊና የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ታኅሳስ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ስለሁኔታው ሲያስረዱ፣ ‹‹የመከላከያ ሠራዊቱ ወደ ወለጋ ሲገባ ያገኘነው ጉድ ዘግናኝ ነው። ለረጅም ዓመታት በውትድርና አገልግያለሁ እንደዚህ ዓይነት ጭካኔ በወለጋ ከተፈጸመው በስተቀር ዓይቼ አላውቅም፤›› ብለዋል።

ባል ታስሮ ሚስት የምትደፈርበት፣ ሕዝብ ተጨንቆ በጉድጓድ የተደበቀበት፣ በርካታ ሰዎች ታግተው የተገኙበት፣ የመንግሥት ተሽከርካሪና የጦር መሣሪያ በሙሉ የተዘረፈበት እንደነበር ገልጸዋል።

በወለጋ የተከሰተውን የማስተካከል ሥራ የክልሉ ፀጥታ ኃይል እንጂ የመከላከያ ሠራዊቱ መሆን እንዳልነበረበት፣ ነገር ግን ችግሩን የፈጠሩት በአካባቢው የተሰማሩ ተጣቂዎች በሰላማዊ መንገድ ሊታገሉ የመጡ ናቸው እንዳትነኳቸው በመባሉ የክልሉ የፀጥታ ኃይል መንቀሳቀስ እንደተሳነው ተናግረዋል።

ጄኔራል ብርሃኑ የመከላከያ ሠራዊቱ በወለጋ ከተሰማራ በኋላ ችግሩ እየተፈታ እንደሆነ፣ የአካባቢው ነዋሪዎችም ከተደበቁበት እየወጡ ሠራዊቱን ‹‹አድኑን›› በማለት መናገር መጀመራቸውን በወቅቱ ገልጸው የነበረ ቢሆንም፣ ከዚያ በኋላ በነበሩት ቀናት 18 ባንኮች መዘረፋቸው ተገልጿል።

የታጠቀው የኦነግ ኃይልም ወደ ጫካ በመግባት ለአፀፋ ጥቃት የመደራጀት እንቅስቃሴ ውስጥ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

 በኦዴፓ በሚመራው መንግሥትና በኦነግ መካከል የተፈጠረውና እዚህ ደረጃ የደረሰውን ግጭት በወታደራዊ አማራጭ ብቻ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ፣ ሌሎች የምክክር አማራጮችን መጠቀሙን የቀጠለው የኦሮሚያ መንግሥት በስተመጨረሻ ተስፋን የፈነጠቀ ዕርቅ ከኦነግ ጋር ለማውረድ ችሏል።

የአባ ገዳዎች አማራጭ የፈጠረው ተስፋ

በኦዴፓ በሚመራው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትና በኦነግ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ከወታደራዊ አማራጭ በመለስ ለመፍታት በርካታ ውይይቶች በሁለቱ ወገኖች መካከል፣ እንዲሁም ፌዴራል መንግሥትም የተሳተፈባቸው ውይይቶች ተካሂደው የነበረ ቢሆንም ውጤት ማምጣት አልተቻለም።

በመጨረሻ ጥንታዊውን የኦሮሞ የገዳ ሥርዓት በመጠቀም የተደረገው ጥረት ግን፣ ከየትኞቹም ጥረቶች በተለየ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተስፋን የፈነጠቀ የስምምነት ዕድል አበርክቷል።

በገዳ ሥርዓትና ባህል ግጭቱን ለመፍታት የተንቀሳቀሰው የኦሮሞ አባ ገዳዎች ኅብረት፣ ጥር 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ሁለቱን ወገኖች ለማስማማት በአዲስ አበባ የዕርቀ ሰላም መድረክ አካሂዷል።

በዚህ የዕርቅ መድረክ ላይም ሁለቱም ወገኖች ለግጭት የዳረጋቸውን ምክንያት እንዲያብራሩ፣ እንዲሁም በአባ ገዳዎች እንዲሁም መድረኩን በታደሙ የኦሮሞ ልሂቃንና የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች እንዲዳኙ ተደርጓል።

የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ለመድረኩ በሰጡት አስተያየት፣ ኦነግ በኤርትራ የተደረሰውን ስምምነት ጠብቆ እንዲንቀሳቀስ የሚጠበቅበት ቢሆንም፣ ይኼንን አለማድረጉ የግጭቱ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል።

ኦዴፓ እስካሁን ሰላም እንዲወርድ ወደ ኋላ አለማለቱን፣ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ከአባ ገዳዎችና ከሌሎች የሚመለከታቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ነገር ግን ይኼ እየተሠራ እያለ በኦነግ ኃይል ጥቃት የሰዎች ሕይወት እያለፈ እንደሆነ፣ ባንኮች እየተዘረፉ እንደሚገኝና የነዋሪዎች እንቅስቃሴ መገታቱን ገልጸዋል። ይህ በመሆኑ የክልሉ መንግሥት ሕግ ለማስከበር እንደተገደደ መሆኑን አስታውቀዋል።

‹‹የአንድ አገርና የአንድ አባት ልጆች ሆነን ሳለ በፖለቲካ ምክንያት መገዳደልና አንዱ አንዱን ከአገር ማባረር መቅረት አለበት፤›› ሲሉም አሳስበዋል።

 የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳም በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር፣ ፓርቲያቸውና መንግሥት በኤርትራ ያደረጉት ስምምነት በመንግሥት ባለመከበሩ የተፈጠረ ግጭት መሆኑን አስረድተዋል።

የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከፓርቲ ተላቀው የመንግሥት መሆናቸው በሕግ እንዲረጋገጥ፣ የኦነግ ታጣቂ ኃይሎች በመንግሥት የፀጥታ መዋቅር ውስጥ የሚቀላቀሉበት ሁኔታ እንዲመቻች ስምምነት ተደርሶ ኦነግ ወደ አገር ቢገባም፣ ከኤርትራ ወደ አገር የገባው የኦነግ ጦር ካምፕ ከገባ በኃላ የኦነግ አመራሮች በካምፑ ያሉ የጦር አባላቱን መጎብኘት ባለመቻላቸው ምክንያት አለመግባባት መፈጠሩን አስረድተዋል።

 ‹‹የገዳ ሥርዓት በቀልን ሳይሆን መዋደድን፣ አንድነትንና መቀራረብን ነው ያስተማረን፡፡ እኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች የገባነውን ቃል መጠበቅ አለብን፤›› በማለት፣ በኦነግ የተሰጠውን ምክንያት የኦዴፓው ተወካይ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) አስተባብለዋል።

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በአርዳይታ ካምፕ ከገባው 1,300 የኦነግ ጦር መካከል 700 ያህሉ ወደ ኦሮሚያ ፖሊስ እንዲቀላቀል ተደርጎ ሥልጠና እየወሰደ መሆኑን፣ ይኼንንም ማንኛውም ሰው ያለበትን ሥፍራና ሁኔታ ሄዶ መጎብኘት እንደሚችልም ገልጸዋል።

ዕርቅ የሚመጣው በእውነት ላይ ሲመሠረት እንደሆነ፣ በኦዴፓ ላይ የቀረበውን ወቀሳ በተመለከተም ያለውን ሀቅ በማንኛውም ሰዓት ማጣራት እንደሚቻል ዓለሙ (ዶ/ር) በወቅቱ ተናግረዋል።

 ሁለቱ ወገኖች የግጭት ምክንያት በማለት ያነሷቸውን ቅሬታዎች ያዳመጡት የአባ ገዳዎች ኅብረትና የዕርቅ መድረኩ ታዳሚዎች፣ በኦነግ በኩል የቀረበው ምክንያት በበርካታ ሺዎች የሚቆጠረው የኦነግ የታጠቀ ሠራዊት ካምፕ እንዳይገባ የሚከለክል አለመሆኑን በመጥቀስ፣ አቶ ዳውድ ዛሬውኑ ጫካ ያለው ጦራቸው ውጊያ አቁሞ ወደ ካምፕ እንዲገባ ትእዛዝ እንዲያስተላለፍባቸው በጠየቀው መሠረት ውሳኔው ተላልፎባቸዋል።

አባ ገዳዎቹ ሁለቱንም ወገኖች በመገሰፅና በኦሮሞ መካከል እርስ በእርስ ደም መፋሰስ እንዲቆም ገዝተዋቸዋል።

የኦነግ ሊቀመንበርም በመድረኩ የተላለፈውን በመቀበል ከዚህ በኋላ የኦነግ ጦርን በተመለከተ፣ ለኦሮሞ ሕዝብና ለአባ ገዳዎች እንዲወስኑበት መስማማታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት አባ ገዳዎች በሚያስቀምጡት አቅጣጫ መሠረት የኦነግ ጦር ትጥቁን ለአባ ገዳዎችና ለአገር ሽማግሌዎች እያስረከበ ወደ ካምፕ እንዲገባ ስምምነት ተደርሷል።

ውሳኔውን ለማስፈጸምም ከአባ ገዳዎችና ሀደ ሲቄዎች (የኦሮሞ እናቶች) ጥምረት፣ ከኦሮሞ ልሂቃንና ከሁለቱ የፖለቲካ ድርጅቶች የተውጣጣ 71 አባላት የሚኖሩት የቴክኒክ ኮሚቴ ተመሥርቶ ኃላፊነቱን ወስዷል።

 ይህ ኮሚቴም በሁለት ቀናት ጊዜ ውስጥ ስምምነቱ የሚተገበርበትን መንገድ ነድፎ፣ የገዳ ሥርዓትን በተከተለ የዕርቅ ሥነ ሥርዓት ሐሙስ ጥር 16 ቀን 2011 ዓ.ም. በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ይፋ አድርጓል። ኮሚቴው ስምምነቱን ለመተግበር ይፋ ካደረገው የማስፈጸሚያ ውሳኔዎች መካከልም ከጥር 16 ቀን ጀምሮ በመንግሥትና በኦሮሞ ነፃነት ግንባር መካከል ተኩስ መቆሙን፣ ወደ ግጭት የሚያስገቡ ትንኮሳዎች ሙሉ በሙሉ መከልከላቸውን፣ እንዲሁም አንዱ በሌላው ላይ ከዚህ በኋላ መግለጫ ማውጣት ሙሉ በሙሉ መከልከሉ ይገኝበታል።

የኦነግ ሠራዊት ባለበት ቦታ በሙሉ ትጥቅ ፈትቶ ወደ ካምፕ እንዲገባ መወሱን፣ ይህም ከበቂ ጥበቃ ጋር በክብር አቀባበል ወደ ካምፕ እንዲገባ እንዲደረግ መወሰኑንም ገልጸዋል።

ሠራዊቱን ወደ ካምፕ የማስገባት ሥራም በ20 ቀናት ውስጥ መጠናቀቅ እንዳለበት የተወሰነ ሲሆን፣ ከእዚህም ውስጥ አሥር ቀናት ዝግጅት የሚደረግባቸው፣ ቀሪዎቹ አሥር ቀናት ደግሞ ሠራዊቱ ወደ ካምፕ የሚገባባቸው እንደሚሆኑ ተመልክቷል።

 ወደ ካምፕ የማስገባት ሒደቱም በሦስት ደረጃዎች ተከፋፍሎ እንደሚካሄድ፣ በዚህም የሠራዊቱ አባላት መጀመርያ ወደ ወረዳ ከተሞች እንዲሰባሰቡ፣ በመቀጠል ወደ ተዘጋጀላቸው ካምፕ እንዲገቡ ማድረግ፣ በመጨረሻም የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት አቀባበል ማድረግ መሆኑ በውሳኔው ተገልጿል፡፡

በዚህ ወቅት ትጥቅ ይዞ መንቀሳቀስ ፈፅሞ የተከለከለ መሆኑን፣ ይኼንን ተላልፎ በተገኘ ማንኛውም አካል ላይ መንግሥት ሕግ የማስከበር ሥራ እንዲያከናውን የተፈቀደ መሆኑም ተገልጿል።

የኦነግ ሠራዊት ካምፕ ከገባ በኋላም አጠቃላይ ሥልጠና እንዲወስድ ተደርጎ የመንግሥት የፀጥታ አካላት መቀላቀል ለሚፈልጉ እንደሚያሟሉት መሥፈርት እንዲቀላቀሉ፣ ከዚህ ውጪ ያሉት ደግሞ እንደ ፍላጎታቸው በሚመርጡት ዘርፍ ሥልጠና ወስደው እንዲሰማሩ ድጋፍ እንደሚደረግም ይፋ ተደርጓል።

የኦነግ ሠራዊት አባላት እስካሁን ላጠፉት ጥፋት ይቅርታ መደረጉን፣ ከላይ የተዘረዘሩትን ስምምነቶች ጥሶ የተገኘ ማንኛውም አካል ላጠፋው ጥፋት ተጠያቂ እንደሚደረግም ይፋ ተደርጓል።

ሁለቱም ወገኖች ይፋ የተደረገውን የማስፈጻሚያ መንገድ ሙሉ በሙሉ በይፋ ተቀብለውታል።

የኦሮሞ አባ ገዳዎችና እናቶች ከማኅበረሰቡ ልሂቃን ጋር በመተባበር በተለያዩ መንገዶች ተሞክሮ ያልተሳካውን ዕርቅና ሰላም ለማውረድ የሚያስችል ትልቅ ተግባር በጥቂት ቀናት ውስጥ መፈጸማቸው፣ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ አድናቆትን አግኝቷል።

የገዳ ሥርዓትም ሆነ መሰል የአገር ሽማግሌዎች አዎንታዊ ሚና ወደ ተፈጥሯዊ ቦታው መመለስና ከመንግሥታዊ ሥርዓት ጎን ለጎን ሊቀጥል እንደሚገባው ያመላከተ መሆኑን በርካቶች እየገለጹ ነው።

በሁለቱ ወገኖች መካከል ስምምነት ቢወርድም የግጭት አፈታቱን ተፈጻሚ ለማድረግ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሊፈጠር ይችላል የሚል ሥጋት በተወሰነ ደረጃ ይነሳል።

ሪፖርተር ያነጋገራቸው በቀድሞው የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የግጭት አፈታት ባለሙያ ሆነው ለረጅም ዓመታት ያገለገሉና በአሁኑ ወቅት የአንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት አማካሪ የሆኑ ተንታኝ እንደሚሉት ከሆነ፣ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ሊገጥሙ ከሚችሉ አስቸጋሪ ጉዳዮች መካከል ወደ ካምፕ እንዲገባ የሚፈለገው የታጠቀው የኦነግ ሠራዊት ትዕዛዝ የሚቀልበት ሰንሰለት በግልጽ የማይታወቅ መሆኑ ነው ይላሉ።

በሥፍራው የተሰማራ የመከላከያ ሠራዊት የአካባቢውን የአገር ሽማግሌዎች በመጠቀም ትጥቅ ለማስፈታት ጥረት ሲያደርግ እንደነበር የገለጹት እኚሁ ባለሙያ፣ ጥረቱ ያልተሳካበት ምክንያት የታጠቀ ነው የሚባለው ሠራዊት ከማኅበረሰቡ ጋር የተቀላቀለ በመሆኑ ለመለየት አስቸጋሪ እንዳደረገው ይገልጻሉ።

በተጨማሪም የአካባቢው ማኅበረሰብ ታጣቂዎችን ለይቶ ቢጠቁም ጥቃት ይደርስብኛል የሚል ፍርኃት ውስጥ የወደቀ በመሆኑ፣ እንዲሁም የአካባቢው የመንግሥት መዋቅር በአንድ በኩል የፈረሰ አልያም በኦነግ ቁጥጥር ሥር የወደቀ ስለሆነ፣ አስቸጋሪ እንዳደረገውና አሁንም ተመሳሳይ እክል ይገጥማል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ያስረዳሉ።

በሌላ በኩል በተደረሰው ስምምነት መሠረት የታጠቀው ኃይል የማይገዛ ከሆነ፣ በአማራጭነት የተቀመጠው መፍትሔ መንግሥት ሕግ የማስከበር ዕርምጃ እንዲወስድ የሚፈቅድ መሆኑ ሌላው የሥጋት ምንጭ እንደሆነ ይጠቁማሉ።

ወደ ሕግ ማስከበር ከተገባ ከፍተኛ ጥንቃቄን ተከትሎ መፈጸም ያለበት እንደሆነ፣ ካልሆነ ግን የአባ ገዳዎቹን ጥረት በዜሮ የሚያባዛ እንደሚሆን የታጠቀው ኃይልም ይኼንን አስልቶ ሊንቀሳቀስ እንደሚችል አሳስበዋል።

የተገለጹት ሥጋቶችን በተመለከተ አስተያየት እንዲሰጡ የአባ ገዳዎች ኅብረት ሰብሳቢ አባ ገዳ ሰንበቶ በየነ፣ እንዲሁም የቴክኒክ ኮሚቴው አባል አቶ ጃዋር መሐመድን ሪፖርተር የጠየቀ ቢሆንም፣ ለጊዜው አስተያየት ለመስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -