ዲፌንድ ዲፌንደርስ የተሰኘውና በ12 አገሮች የሚንቀሳቀሰው ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን፣ ከዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በአዲስ አበባ ስብሰባውን አደረገ፡፡ በስብሰባውም ለዓመታት ተዳክሞ የከረመውን የኢትዮጵያን ሲቪል ማኅበረሰብ እንዴት እንዲያንሰራራ ማድረግ ይቻላል በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ መክሯል፡፡
ሁለት ቀናት የፈጀው የተቋሙ ዓመታዊ ጉባዔ ‹‹ጠንካራ የሲቪል ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ በድጋሚ መገንባት›› በሚል መሪ ሐሳብ በካፒታል ሆቴል ጥር 20 እና 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ተካሂዷል፡፡ ጉባዔው፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው ፈታኝ የሆነ የፖለቲካ ምኅዳር የማይካድ ቢሆንም፣ በድጋሚ ጠንካራ የሲቪል ማኅበረሰብ ማደራጀትና መገንባት›› ተገቢ መሆኑን ተወያይቶበታል፡፡ ከዚህ ባለፈ ተቋሙ ባለፉት አሥርት ዓመታት ተዳክሞ የቆየውን የሲቪል ማኅበረሰብ እንዲያንሰራራ ማድረግ ወቅታዊ ጉዳይ መሆኑን አስምሮበታል፡፡
ዲፌንድ ዲፌንደርስ በቀጥታ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ዙርያ ተሟጋች ከመሆን ባለፈ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና ቡድኖች ድጋፍና ጥበቃ እንዲያገኙ በማድረግ ይበልጥ የሚታወቅ ተቋም ነው፡፡
በጉባዔው ከታደሙ ታዋቂ የሰብዓዊ መብት ዘርፍ አንቀሳቃሾች መካከል፣ እንደ ፌሊክስ ሆርን ያሉ በኢትዮጵያ ውስጥ በዛ ያሉ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ያጠነጠኑ ሪፖርቶችን የጻፉ ሰዎችም ይገኙበታል፡፡ ፊሊክስ ሆርን በካናዳ ኦትዋ መቀመጫውን ያደረገው ሂውማን ራይትስ ዎች ባልደረባነት በኤርትራና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ተመራማሪ በመሆን ለዓመታት የሠሩ ሲሆን፣ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ይህ ከስምንት ዓመት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ መሆኑ ታውቋል፡፡ ከዚህ ባለፈ እኚህ ተመራማሪ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ያዘጋጇቸውን ሪፖርቶች በዓለም ደረጃ በእጅጉ አወዛጋቢ የነበሩ ከመሆናቸው በላይ፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋርም ጥሩ ያልሆነ ግንኙነት የነበራቸው መሆናቸው ይነገራል፡፡
ፌሊክስ ሆርን በጉባዔው ስለአቅም ግንባታ፣ ትብብርና የአፍሪካ-ለ-አፍሪካ ስደት ላይ በስፋት ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፣ በተለይ ግን ኢትዮጵያዊ ጉዳዮችን እንዴት ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ማሳወቅ ይቻላል በሚለው ጥያቄ ላይ ሐሳቦች አንስተዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያውያን ዓለም ስለኢትዮጵያ ጉዳዮች በቅጡ የሚያውቅ አድርገው ይገምታሉ፤›› ያሉት ፊሊክስ ሆርን፣ ከአጠቃላይ ጉዳዮች ባሻገር ዓለም ብዙም ስለኢትዮጵያ ግንዛቤ እንደሌለው አስምረውበታል፡፡ ‹‹በመሆኑም እንዴት ዓለም ስለአገሪቱ ማወቅ ይችላል ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡
ዴፌንድ ዲፌንደርንስን ጨምሮ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ማኅበረሰቡ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ መንግሥት እየወሰዳቸው ያለውን የለውጥ ዕርምጃዎች ዕውቅና እየሰጡ የቆዩ ሲሆን፣ በተለይ የፖለቲካ እስረኞች የመፈታትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማንሳት ዕርምጃዎቹን በስፋት ያወሱታል፡፡ ዴፌንድ ዲፌንደርስም ቢሆን እነዚህን ለውጦች ተከትሎ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጥታ ደብዳቤ በመጻፍ፣ ‹‹መንግሥት በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብትንና ነፃነትን ለማክበርና ተጠያቂነትን ለማስፈን እየወሰደ ያለው ዕርምጃ የሚደነቅ ነው፤›› ሲሉ ድጋፋቸውን መግለጻቸው ይነገራል፡፡