የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ለብሔራዊ መግባባትና ዕርቅ ቅድሚያ እንዲሰጡ ጥሪ ቀረበላቸው፡፡ ጥሪውን ያቀረበው ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በብሔራዊ መግባባትና አጀንዳ ላይ በጋራ እንዲወያዩ እየሠራ መሆኑን ያስታወቀው፣ የኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ መግባባትና ዕርቀ ሰላም ዓለም አቀፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ነው፡፡ በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የተደራጁ ልሂቃን የሚያስተላልፉት የአንድነት መልዕክት ወሳኝ ነው ሲልም አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያውያን ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ መግባባትና ዕርቀ ሰላም ዓለም አቀፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ከአንድ ዓመት በፊት በአሜሪካ ሲያትል ከተማ ለሦስት ቀናት በተደረገ ጉባዔ፣ በ26 የሲቪክ ማኅበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎች አማካይነት የተቋቋመ ነው፡፡
ኮሚቴው በብሔራዊ መግባባትና ዕርቅ ላይ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የሚሳተፉበት መድረክ እንዲመቻች እየሠራ እንደሆነ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበርና የኮሚቴው አባል አቶ ስለሺ ጥላሁን አስታውቀዋል፡፡
ኮሚቴው ለሚያቅደው የብሔራዊ መግባባትና ዕርቅ አጠቃላይ ጉባዔ ግብዓት ለመሰብሰብ ያመቸው ዘንድ፣ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎችን በመጋበዝ ማክሰኞ ጥር 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ጽሕፈት ቤት ውስጥ የምክክር መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡
‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎችን አንድ ላይ የማምጣት ወይም ያለማምጣት ጉዳይ አይደለም፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሞች ቢኖሩም በአገራዊ ጉዳይ ላይ ስምምነት ከሌለ፣ የፓርቲዎችን ፍልስፍና በሕዝቡ ውስጥ ማስረፅ አይቻልም፡፡ ስለዚህ መሠረታዊውና መቅደም ያለበት ጉዳይ ብሔራዊ መግባባትና ዕርቅ ነው፤›› ያሉት አቶ ስለሺ ፓርቲዎች የርዕዮተ ዓለም ልዩነቶች ሳይገድቧቸው፣ ለብሔራዊ መግባባትና ዕርቅ ቅድሚያ ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በሲያትሉ ጉባዔ የተሳተፉት 26 የሲቪል ማኅበራትና የፖለቲካ ድርጅቶች የፖለቲካ ልዩነቶች እንዳሉ ሆነው፣ በአገሪቱ የሚስተዋለውን አደጋ ለማክሰም የየራሳቸውን አቅጣጫ አንጥረው በማውጣት ብሔራዊ መግባባትና ዕርቅን መሠረት ያደረገ ሁሉን አቀፍ ጉባዔ መደረግ አለበት በሚለው መስማማታቸውን አቶ ስለሺ አስታውሰዋል፡፡ ይህ የምክክር መድረክም ዓላማው ሁሉንም ኃይሎች አንድ ላይ አምጥቶ በጉዳዩ ላይ ለመምከርና መፍትሔ ለመምጣት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ኮሚቴው ከዚህ ቀደም ሁለት ተመሳሳይ መድረኮች በአዲስ አበባ ራስ ሆቴል ማካሄዱ የሚታወስ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ ሰማያዊ ፓርቲ (ሰማያዊ)፣ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) እንዲሁም የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረት (ኦሕዴህ) የኮሚቴው አባል የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው፡፡